በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው?

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው?

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው?

“ጌታ ሆይ፤ የእስራኤልን መንግሥት መልሰህ የምታቋቁምበት ጊዜው አሁን ነውን?” (የሐዋርያት ሥራ 1:6) ሐዋርያት፣ ኢየሱስ መንግሥቱን መቼ እንደሚያቋቁም ለማወቅ ጓጉተው ነበር። ይህ ከሆነ ከ2,000 ዓመታት በኋላ ዛሬም ሰዎች የአምላክ መንግሥት መቼ እንደሚመጣ ለማወቅ ይጓጓሉ።

የኢየሱስ ስብከት ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ስለነበር ከላይ ስለተነሳው ጥያቄ ተናግሮ እንደሚሆን ልትጠብቅ ትችላለህ። ደግሞም ተናግሯል! “መምጣት” ወይም መገኘት ብሎ ስለጠራው አንድ የተለየ ጊዜ በሰፊው ገልጿል። (ማቴዎስ 24:37) መገኘት የሚለው ቃል ከመሲሐዊው መንግሥት መቋቋም ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው። ይህ መገኘት ምን ያመለክታል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክርስቶስ መገኘት የሚናገራቸውን አራት ነጥቦች እንመልከት።

1. የክርስቶስ መገኘት የሚጀምረው እሱ ከሞተ ከረጅም ጊዜ በኋላ ነው። ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ “የንጉሥነትን ማዕረግ” ወይም “መንግሥትን፣ [የ1954 ትርጉም]” “ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር [ከሄደ]” ሰው ጋር ራሱን አመሳስሏል። (ሉቃስ 19:12) ይህ ትንቢታዊ ምሳሌ የተፈጸመው እንዴት ነበር? ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ “ወደ ሩቅ አገር” ማለትም ወደ ሰማይ ተጉዟል። ኢየሱስ በዚሁ ምሳሌ ላይ አስቀድሞ እንደገለጸው የንጉሥነትን ማዕረግ ለመቀበል የሚመለሰው “ከብዙ ጊዜ በኋላ” ነው።—ማቴዎስ 25:19

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህኛው ካህን [ኢየሱስ] ግን አንዱን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ፣ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠላቶቹ የእግሩ መረገጫ እስኪሆኑ ድረስ ይጠብቃል።” (ዕብራውያን 10:12, 13) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ መጠበቅ ነበረበት። በመጨረሻም ይሖዋ አምላክ ልጁን ከረጅም ጊዜ በፊት በተነገረለት መሲሐዊ መንግሥት ላይ ሲያነግሠው ይህ ጊዜ አበቃ። የክርስቶስ መገኘት የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። ታዲያ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች ይህን አስደናቂ ክስተት ይመለከታሉ?

2. የክርስቶስ መገኘት በሰብዓዊ ዓይን አይታይም። ኢየሱስ ስለ መገኘቱ ምልክት እንደተናገረ ልብ በል። (ማቴዎስ 24:3) የክርስቶስ መገኘት በሰብዓዊ ዓይን የሚታይ ቢሆን ኖሮ ምልክት መስጠት ያስፈልገው ነበር? ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ሐይቅ ለማየት እየተጓዝክ ነው እንበል። በመንገድ ላይ እያለህ ወደዚያ የሚመሩህ አቅጣጫ የሚጠቁሙ ምልክቶች ይታዩህ ይሆናል፤ ሆኖም ሐይቁ ያለበት ቦታ ከደረስክ በኋላ ዳርቻው ላይ ቆመህ ከፊትህ የተዘረጋውን ውኃ እየተመለከትህ እያለ “ሐይቅ” የሚል ትልቅ ምልክት አገኛለሁ ብለህ ትጠብቃለህ? እንደማትጠብቅ የታወቀ ነው! በቀላሉ በዓይንህ ልትመለከተው የምትችለውን ነገር የሚጠቁም ምልክት ለምን ያስፈልጋል?

ኢየሱስ የመገኘቱን ምልክት የተናገረው ሰዎች በዓይናቸው ሊያዩት የሚችሉትን ነገር ለመጠቆም ሳይሆን በሰማይ የሚከናወነውን ሁኔታ ማስተዋል እንዲችሉ ለመርዳት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት በሚታዩ ምልክቶች አትመጣም” ብሏል። (ሉቃስ 17:20) ታዲያ ምልክቶቹ የክርስቶስ መገኘት መጀመሩን በምድር ላሉት ሰዎች የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

3. የኢየሱስ መገኘት በምድር ላይ በሚከናወኑ በጣም አስጨናቂ ሁኔታዎች ተለይቶ ይታወቃል። ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በምድር ላይ ጦርነት፣ ረሃብ፣ የምድር መናወጥና ቸነፈር እንደሚኖር እንዲሁም ክፋት እንደሚገን ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7-12፤ ሉቃስ 21:10, 11) የዚህ ሁሉ መከራ መንስኤ ምንድን ነው? ክርስቶስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት በመጀመሩ “የዚህም ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ያውቃል፤ በዚህም የተነሳ ሰይጣን በጣም እንደተቆጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዮሐንስ 12:31፤ ራእይ 12:9, 12) በዘመናችን ሰይጣን መቆጣቱንና ክርስቶስ መገኘቱን የሚጠቁሙ በግልጽ የሚታዩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። በተለይም ታሪክ ጸሐፊዎች ታላቅ ለውጥ የታየበት ወቅት እንደሆነ ከሚናገሩለት ከ1914 ጀምሮ ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ እነዚህ ማስረጃዎች ታይተዋል።

ይህ ሁሉ መጥፎ ዜና ቢመስልም ሁኔታው ከዚህ የተለየ ነው። እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው መሲሐዊው መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ መሆኑን ይጠቁማሉ። በቅርቡ ይህ መንግሥት መላውን ምድር መግዛት ይጀምራል። ይሁን እንጂ ሰዎች የዚህን መንግሥት አገዛዝ ተቀብለው ተገዢዎቹ ለመሆን እንዲችሉ ስለ መንግሥቱ እንዴት ማወቅ ይችላሉ?

4. የኢየሱስ መገኘት በዓለም ዙሪያ በሚከናወን የስብከት ሥራ ተለይቶ ይታወቃል። ኢየሱስ መገኘቱን ‘ከኖኅ ዘመን’ * ጋር አመሳስሎታል። (ማቴዎስ 24:37-39) ኖኅ መርከብ ከመሥራቱም በላይ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ፣ አምላክ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድ ሕዝቡን አስጠንቅቋል። ኢየሱስ፣ በእሱ መገኘት ወቅት በምድር ላይ የሚኖሩ ተከታዮቹ ተመሳሳይ ሥራ እንደሚያከናውኑ ተናግሯል። “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:14

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው የአምላክ መንግሥት የዓለም መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋል። የስብከቱ ሥራ፣ በሰማይ የተቋቋመው ይህ መንግሥት በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ ሰዎችን የሚያስጠነቅቅ ሲሆን ይህም ሁሉም ሰው ከሚመጣው ጥፋት ለመትረፍና የዚህ መንግሥት ተገዥ ለመሆን እንዲችል አጋጣሚ ይሰጠዋል። እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘አንተ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?’ የሚል ይሆናል።

የአምላክ መንግሥት ለአንተ የምሥራች ነው?

ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ተወዳዳሪ የሌለው ተስፋ የያዘ ነበር። በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤድን ከተነሳው ዓመጽ በኋላ ይሖዋ አምላክ ነገሮችን የሚያስተካክል መንግሥት ለማቋቋም አሰበ፤ በዚህ መንግሥት አማካኝነት አምላክ፣ መጀመሪያ ከነበረው ዓላማ ጋር በሚስማማ መልኩ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች በምድር ላይ በገነት ለዘላለም እንዲኖሩ ያደርጋል። ከረጅም ጊዜ በፊት ቃል የተገባለት ይህ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በሰማይ እየገዛ መሆኑን ከማወቅ የበለጠ ምን አስደሳች ነገር አለ? የአምላክ መንግሥት ግልጽ ያልሆነና የማይጨበጥ ሐሳብ ሳይሆን እውን መስተዳድር ነው!

በአሁኑ ወቅት አምላክ የሾመው ንጉሥ በጠላቶቹ መካከል እየገዛ ነው። (መዝሙር 110:2) ከአምላክ በራቀው በዚህ ምግባረ ብልሹ ዓለም ውስጥ መሲሑ፣ አምላክን ለማወቅ እንዲሁም እሱን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ የሚፈልጉ ሰዎችን ሁሉ ለማግኘት ጥረት በማድረግ የአባቱን ፈቃድ እየፈጸመ ነው። (ዮሐንስ 4:24) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለዘላለም የመኖር ተስፋ፣ ዘርም ሆነ ዕድሜ እንዲሁም የኑሮ ደረጃ ሳይለይ ለሁሉም ሰዎች ተዘርግቷል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) እንግዲያው የቀረበልህን ድንቅ አጋጣሚ እንድትጠቀምበት እናበረታታሃለን። በአምላክ መንግሥት ጽድቅ የሰፈነበት አገዛዝ ሥር ለዘላለም ለመኖር እንድትችል ስለ አምላክ መንግሥት አሁኑኑ ተማር!—1 ዮሐንስ 2:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 የኢየሱስ አነጋገር፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “መገኘት” የሚለውን ቃል የተረጎሙበት መንገድ የሚያስተላልፈውን የተሳሳተ ሐሳብ ለማስተካከል ያስችላል። እንደ አማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ያሉ አንዳንድ ትርጉሞች ይህን ቃል “መምጣት፣” “ምጽዓት” ወይም “መመለስ” ብለው ያስቀመጡት ሲሆን እነዚህ ቃላት ደግሞ አጠር ያለ ጊዜ ያመለክታሉ። ሆኖም ኢየሱስ፣ መገኘቱን ያመሳሰለው ‘ከኖኅ ዘመን’ ጋር እንጂ በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው የጥፋት ውኃ ጋር እንዳልሆነ ልብ በል፤ የጥፋት ውኃው አንድ ጊዜ የተፈጸመ ክስተት ሲሆን የኖኅ ዘመን ግን ታላቅ ክንውን የተፈጸመበት ወቅት ነበር። ልክ እንደ ኖኅ ዘመን ሁሉ በክርስቶስ መገኘት ወቅትም ሰዎች በዕለት ተዕለት የሕይወት ጉዳዮቻቸው በጣም ስለሚጠላለፉ የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ልብ አይሉም።

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በየዕለቱ የምንሰማቸው መጥፎ ዜናዎች በቅርቡ መልካም ነገሮች እንደሚመጡ ያረጋግጣሉ

[ምንጭ]

Antiaircraft gun: U.S. Army photo