በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በልብህ ውስጥ ነው?

የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በልብህ ውስጥ ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በልብህ ውስጥ ነው?

በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ከላይ ለቀረበው ጥያቄ አዎን የሚል መልስ ይሰጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ “የአምላክ መንግሥት ሲባል . . . አምላክ ልባችንን የሚመራበት መንገድ ማለት ነው” ብሏል። ቀሳውስትም ይህንኑ ሐሳብ ሲያስተምሩ መስማት የተለመደ ነገር ነው። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ እንደሚኖር ያስተምራል?

አንዳንዶች የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በሰዎች ልብ ውስጥ ነው የሚለውን ሐሳብ ያስተማረው ኢየሱስ ራሱ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እውነት ነው፣ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ሲል ተናግሯል። (ሉቃስ 17:21) አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን ጥቅስ “የአምላክ መንግሥት በውስጣችሁ ናት” በማለት ተርጉመውታል። ይህ ትርጉም የኢየሱስን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል? በእርግጥ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በሰዎች ልብ ውስጥ ነው ማለቱ ነበር?

በመጀመሪያ፣ የሰው ልብ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ምሳሌያዊው ልብ ውስጣዊ ማንነትን እንዲሁም የአንድ ሰው ሐሳብ፣ ዝንባሌና ስሜት የሚመነጭበትን ቦታ ለማመልከት ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰዎችን ይለውጣል ወይም የተሻሉ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ከሚለው አስተሳሰብ አንጻር ሲታይ የአምላክ መንግሥት በሰዎች ልብ ውስጥ ያለ ነው መባሉ ማራኪ ሊመስል ይችላል። ይሁንና እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም” በማለት ይናገራል። (ኤርምያስ 17:9) ኢየሱስም እንዲህ ብሏል:- “ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣ መስገብገብ፣ ክፋት . . . ናቸው።” (ማርቆስ 7:20-22) እስቲ አስብ፣ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የምናየው አብዛኛው መከራ ኃጢአተኛ ከሆነው የሰው ልጅ ልብ የመነጨ አይደለም? ታዲያ ፍጹም የሆነው የአምላክ መንግሥት እንዴት ከዚህ ዓይነት ልብ ሊወጣ ይችላል? ኩርንችት በለስ ሊያፈራ እንደማይችል ሁሉ የአምላክ መንግሥትም በሰው ልጅ ልብ ውስጥ ሊኖር አይችልም።—ማቴዎስ 7:16

በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ በሉቃስ 17:21 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ለማን እንደተናገረ ልብ በል። ቀደም ብሎ ያለው ቁጥር “ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ እንደምትመጣ ኢየሱስን በጠየቁት ጊዜ እንዲህ ሲል መለሰላቸው” ይላል። (ሉቃስ 17:20) ፈሪሳውያን የኢየሱስ ጠላቶች ነበሩ። እንዲያውም ኢየሱስ እነዚህ ግብዞች ወደ አምላክ መንግሥት እንደማይገቡ ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:13) ፈሪሳውያን ወደ አምላክ መንግሥት የማይገቡ ከሆነ መንግሥቱ በልባቸው ውስጥ ሊኖር ይችላል? በጭራሽ! ታዲያ ኢየሱስ ማለት የፈለገው ምንድን ነው?

በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጁ በርካታ ትርጉሞች፣ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ ከአዲስ ዓለም ትርጉም ጋር በሚመሳሰል መልኩ የአምላክ መንግሥት “በእናንተ ዘንድ” ወይም “በመካከላችሁ” ናት ሲሉ ተርጉመውታል። ታዲያ የአምላክ መንግሥት ፈሪሳውያንን ጨምሮ በዚያን ጊዜ በነበሩት ሰዎች መካከል የነበረው እንዴት ነው? ይሖዋ አምላክ፣ የመንግሥቱ ንጉሥ እንዲሆን የሾመው ኢየሱስን ነው። እጩ ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ በመካከላቸው ይኖር የነበረ ከመሆኑም በላይ ሕዝቡን ስለ አምላክ መንግሥት አስተምሯል፤ እንዲያውም መንግሥቱ ወደፊት የሚያከናውነውን ነገር በጥቂቱ ለማሳየት ተአምራት ሠርቷል። ከዚህ አንጻር ሲታይ የአምላክ መንግሥት በመካከላቸው ነበር ማለት ይቻላል።

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የአምላክ መንግሥት የሚገኘው በሰው ልብ ውስጥ ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስችል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የለም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ መንግሥት፣ ነቢያት አስቀድመው እንደተናገሩት በምድር ላይ አስደናቂ ለውጦችን የሚያመጣ እውን መስተዳድር ነው።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 2:44