በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማል?

አምላክ እንስሳት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ቀስ በቀስ እየተለወጡ ሰዎች እንዲሆኑ አድርጎ ሊሆን ይችላል? አምላክ በመጀመሪያ አንድ ባክቴሪያ ቀስ በቀስ ዓሣ እንዲሆን፣ ከዚያም ዓሣው ወደ ተሳቢና አጥቢ እንስሳት እንዲቀየርና በመጨረሻም የዝንጀሮዎች ዘር የሰው ልጆች እንዲሆኑ አድርጓል? አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንትና የሃይማኖት መሪዎች በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት በሚናገረው ዘገባ እንደሚያምኑ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ዘገባ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው ይላሉ። አንተም ‘ሰው የተገኘው ከእንስሳ ነው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል?’ ብለህ ጠይቀህ ይሆናል።

ስለ ማንነታችን፣ ወደፊት ስለሚጠብቀን ሁኔታና ሕይወታችንን መምራት ስለምንችልበት መንገድ ለማወቅ እንዴት ወደ ሕልውና እንደመጣን መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። ይህን ካልተገነዘብን አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያትም ሆነ ለሰው ልጆች ያለውን የወደፊት ዓላማ መረዳት አዳጋች ይሆንብናል። ፈጣሪያችን አምላክ መሆኑን የምንጠራጠር ከሆነ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ልንመሠርት አንችልም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ዘር አመጣጥ እንዲሁም የሰው ልጅ አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታና ወደፊት ስለሚጠብቀው ነገር ምን እንደሚል እንመርምር። ከዚያም የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይስማማ እንደሆነና እንዳልሆነ እንመለከታለን።

አንድ ሰው ብቻ ነበር

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች፣ በአንድ ወቅት በምድር ላይ አንድ ሰው ብቻ እንደነበረ በመካድ ብዙ እንስሳት ቀስ በቀስ እየተለወጡ ብዙ ሰዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከዚህ በጣም የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም የተገኘነው ከአንድ ሰው ማለትም ከአዳም እንደሆነ ይናገራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አዳም በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው እንደነበር የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ የሚስቱንና የአንዳንድ ልጆቹን ስም ይጠቅሳል። በተጨማሪም ምን እንዳደረገና ምን እንደተናገረ እንዲሁም የኖረበትንና የሞተበትን ጊዜ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦችን ይነግረናል። ኢየሱስ ይህ ዘገባ ላልተማሩ ሰዎች የተጻፈ ምሳሌያዊ ትረካ እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተውም። ከዚህ ይልቅ የተማሩ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?” ሲል ጠይቋቸዋል። (ማቴዎስ 19:3-5) ከዚያም ኢየሱስ በዘፍጥረት 2:24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ስለ አዳምና ሔዋን የሚናገረውን ሐሳብ ጠቅሶላቸዋል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነውና ታሪካዊ ክንውኖችን በጥንቃቄ የሚዘግበው ሉቃስ፣ አዳም ልክ እንደ ኢየሱስ በሕይወት የኖረ ሰው እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። ሉቃስ የኢየሱስን የዘር ሐረግ እስከ መጀመሪያው ሰው ማለትም እስከ አዳም ድረስ በዝርዝር ጽፏል። (ሉቃስ 3:23-38) ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሪክ ውስጥ በሚገኙ ታዋቂ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ፈላስፋዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በተገኙበት ንግግር ባቀረበ ጊዜ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ . . . የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን [“ከአንድ ሰው፣” የ1980 ትርጉም] ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ አደረገ” ብሎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 17:24-26) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው “ከአንድ ሰው” እንደተገኘን ነው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የሚሰጠው ማብራሪያ ከዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ይስማማል?

የሰው ልጅ ፍጽምናውን አጣ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ የመጀመሪያውን ሰው ፍጹም አድርጎ እንደሠራው ይናገራል። አምላክ የሚሠራው ነገር ሁሉ እንከን እንደሌለበት የታወቀ ነው። ስለ ፍጥረት የሚናገረው ዘገባ እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ . . . እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:27, 31) ፍጹም ሰው ሲባል ምን ማለት ነው?

ፍጹም የሆነ ሰው የመምረጥ ነጻነት ያለው ከመሆኑም ባሻገር የአምላክን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ መኮረጅ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ መቀየሳቸውን’ ይናገራል። (መክብብ 7:29) አዳም በአምላክ ላይ ማመጽን መርጧል። በዚህም ምክንያት እሱም ሆነ ዘሮቹ ፍጽምናን አጡ። ትክክል የሆነውን ማድረግ እየፈለግንም እንኳ ብዙውን ጊዜ የማይሳካልን ፍጽምና ስለጎደለን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁ” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 7:15

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ፍጹም የሆነ ሰው የተሟላ ጤንነት ኖሮት ለዘላለም መኖር ይችላል። የመጀመሪያው ሰው አምላክን ቢታዘዝ ኖሮ እንደማይሞት አምላክ ለአዳም ከተናገረው ነገር በግልጽ ማየት ይቻላል። (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:22, 23) ሰው ከመጀመሪያው በሽታ ሊያጠቃው የሚችል ወይም የማመጽ ዝንባሌ የሚታይበት ከነበረ፣ ይሖዋ የሰው አፈጣጠር “እጅግ መልካም” ነበር በማለት ሊናገር አይችልም። የሰው አካል አስደናቂ ሆኖ የተሠራ ቢሆንም እንኳ ፍጽምና ስለጎደለው የአካል ጉዳት ይደርስበታል እንዲሁም በበሽታ ይጠቃል። ዝግመተ ለውጥ አሁን ያለው ሰው የተገኘው እየተሻሻለ ከመጣ እንስሳ ነው ብሎ ሲያስተምር፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሰው ዘር ከፍጽምና እየራቀ ቢመጣም እንኳ የተገኘው ፍጹም ከነበረ አንድ ሰው እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማማም።

በተጨማሪም፣ አምላክ ሰውን ለመፍጠር በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ባሕርያት ከሚናገረው ነገር ጋር ይጋጫል። አምላክ ዝግመተ ለውጥ እንዲካሄድ አድርጓል ከተባለ የሰውን ዘር አሁን ወዳለበት አስከፊ ሁኔታ የመራው እሱ ነው ማለት ይሆናል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው። በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ ልጆቹ አይደሉም።” (ዘዳግም 32:4, 5) በመሆኑም፣ የሰው ዘር በአሁኑ ጊዜ ለሚመራው የሥቃይ ሕይወት ተጠያቂው አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው በአምላክ ላይ በማመጽ ራሱም ሆነ ዘሮቹ ፍጽምናን እንዲያጡ በማድረጉ የመጣ ነው። እስካሁን አዳምን በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦችን አንስተናል፤ ቀጥለን ደግሞ ስለ ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው ጋር ይስማማል?

በዝግመተ ለውጥም በክርስትና ትምህርትም ማመን ትችላለህ?

“ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ።” ይህ ሐሳብ ከክርስትና መሠረታዊ ትምህርቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ሳታውቅ አትቀርም። (1 ቆሮንቶስ 15:3፤ 1 ጴጥሮስ 3:18) የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከዚህ ትምህርት ጋር የማይጣጣመው ለምን እንደሆነ ለመረዳት በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ኃጢአተኞች ሲል የሚጠራን ለምን እንደሆነና ኃጢአት ምን እንዳስከተለብን ማወቅ ያስፈልገናል።

ኃጢአተኞች ተብለን የተጠራነው እንደ ፍቅርና ፍትሕ ያሉትን የአምላክ ድንቅ ባሕርያት ፍጹም በሆነ መልኩ ማንጸባረቅ ስለማንችል ነው። በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ይላል። (ሮሜ 3:23) መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 15:56 ላይ “የሞት መንደፊያ ኀጢአት ነው” በማለት ሞት የኃጢአት ውጤት መሆኑን ይናገራል። የምንታመምበት ዋነኛ ምክንያትም ይኸው ነው። ኢየሱስ በሽታና ኃጢአት የተያያዙ ነገሮች እንደሆኑ ጠቁሟል። ሽባ ለነበረ አንድ ሰው “ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” በማለት የነገረው ሲሆን ሰውየውም ከበሽታው ተፈውሷል።—ማቴዎስ 9:2-7

ታዲያ የኢየሱስ ሞት የሚጠቅመን እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አዳምን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በማነጻጸር ሲናገር “ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 15:22) ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት በማድረግ ከአዳም ለወረስነው ኃጢአት ቤዛ ከፍሎልናል። በመሆኑም በኢየሱስ የሚያምኑና እሱን የሚታዘዙ ሁሉ አዳም ያሳጣንን ለዘላለም የመኖር መብት ያገኛሉ።—ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 6:23

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ከክርስትና ትምህርቶች ምን ያህል የራቀ እንደሆነ ተመለከትክ? “ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ” ካላመንን ‘ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን እንደሚሆኑ’ እንዴት ተስፋ ማድረግ እንችላለን?

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ብዙዎችን የሚማርከው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ዝግመተ ለውጥን የመሰሉ ትምህርቶች በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ትምህርት የማይቀበሉበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ለገዛ ምኞቶቻቸው የሚስማማውን፣ የሚያሳክክ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገውን እንዲነግሯቸው በዙሪያቸው ብዙ አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ። እውነትን ከመስማት ጆሮአቸውን ይመልሳሉ፤ ወደ ተረትም ዘወር ይላሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ምንም እንኳ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ብዙውን ጊዜ በሳይንሳዊ ቃላት የሚገለጽ ቢሆንም እውነታው ሲታይ ግን ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለው ትምህርት ነው። ሰዎች ስለ ሕይወትና ስለ አምላክ ሊኖራቸው የሚገባውን አመለካከት ያስተምራል። የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ራስ ወዳድ የሆነውንና በራስ የመመራት ፍላጎት ያለውን የሰው ልጅ እንዲማርክ ተደርጎ በዘዴ የቀረበ ነው። በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ በርካታ ሰዎች በአምላክም እንደሚያምኑ ይናገራሉ። ይሁንና አምላክ ፈጣሪ እንዳልሆነ፣ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባና በሰዎች ላይ የፍርድ እርምጃ እንደማይወስድ አድርገው ያስባሉ። ብዙዎች ደግሞ ጆሮአቸው ሊሰማ የሚፈልገው እንዲህ ያለውን ትምህርት ነው።

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አቀንቃኞች፣ በአብዛኛው ይህን ትምህርት ለመደገፍ የሚያነሳሳቸው ትክክለኛ መረጃዎችን ማግኘታቸው ሳይሆን ‘የራሳቸው ምኞት’ ነው። ይህን እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ዝግመተ ለውጥን ከፍ አድርጎ በሚመለከተው የሳይንሱ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት ሊሆን ይችላል። የሴልን ውስብስብ አሠራር በማጥናት አብዛኛውን ዕድሜያቸውን ያሳለፉትና የባዮኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይክል ቢሂ፣ በሴል ውስጥ ዝግመተ ለውጥ ይካሄዳል ብለው የሚያስተምሩ ሰዎች፣ ለዚህ ሐሳባቸው ይህ ነው የሚባል ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችሉ ገልጸዋል። ዝግመተ ለውጥ በሞለኪዩል ደረጃ በምትገኝ አንዲት ሴል ውስጥ ሊካሄድ ይችላል? ቢሂ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በሞለኪዩሎች ውስጥ ዝግመተ ለውጥ ይካሄዳል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በሳይንሳዊ መረጃዎች የተደገፈ አይደለም። በሞለኪዩል ውስጥ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ተጨባጭነት ያለውና ውስብስብ የሆነ ባዮኬሚካላዊ ለውጥ ተካሄዶ እንደነበር ወይም ተካሂዶ ሊሆን እንደሚችል የሚገልጽ አንድም ሳይንሳዊ ጽሑፍ (ታዋቂ የሆኑ መጽሔቶች፣ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ የሚዘግቡ መጽሔቶች ወይም መጻሕፍት) የለም። . . . በሞለኪዩል ውስጥ ዝግመተ ለውጥ ተካሂዷል የሚለው የዳርዊን አባባል ከንቱ ልፈፋ ነው።”

የዝግመተ ለውጥ አራማጆች ለሚያምኑበት ነገር በቂ ማስረጃ ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ፣ ይህን ትምህርት ለማስፋፋት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት ለምንድን ነው? ቢሂ እንዲህ ብለዋል:- “እውቅ የሆኑና ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው በርካታ የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ከፍጥረት በስተጀርባ ከፍተኛ ኃይል ያለው አንድ አካል አለ የሚለውን ሐሳብ መቀበል አይፈልጉም።”

የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ፣ ምሑራን መስለው ለመታየት የሚፈልጉ በርካታ ቀሳውስትን ይማርካል። እነዚህ ቀሳውስት ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የገለጻቸውን ሰዎች ይመስላሉ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ . . . ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ።” (ሮሜ 1:19-22) በእነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ከመታለል መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

በፈጣሪ ላይ በማስረጃ የተደገፈ እምነት ማሳደር

መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነት ፍቺ ሲሰጥ የማስረጃን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ ይገልጻል፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “እምነት ተስፋ ያደረግነው ነገር እንደሚፈጸም እርግጠኛ የምንሆንበት፣ የማናየውም ነገር እውን መሆኑን የምንረዳበት ነው።” (ዕብራውያን 11:1) በአምላክ ላይ የሚኖረን እውነተኛ እምነት ፈጣሪ በእርግጥ መኖሩን በግልጽ በሚያሳዩ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ማስረጃዎች ከየት ማግኘት እንደምትችል ይነግርሃል።

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 139:14) የገዛ አካላችን እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ሌሎች ፍጥረታት ባላቸው አስደናቂ ንድፍ ላይ ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን ፈጣሪያችን ባለው ጥበብ እንድንደመም ያደርገናል። የደም ዝውውር ሥርዓትን የመሰሉ በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ በርካታ ሥርዓቶች፣ እርስ በርስ ተቀናጅተው መሥራታቸው እኛን በሕይወት ለማቆየት ታስበው የተፈጠሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። በተጨማሪም ግዑዙ ጽንፈ ዓለም በሂሳብ ቀመርና ሥርዓት በጠበቀ መንገድ እንደተሠራ በሚያረጋግጡ ማስረጃዎች የተሞላ ነው። ዳዊት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።”—መዝሙር 19:1

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ስለ ፈጣሪ በርካታ ማስረጃዎችን የያዘ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑት 66 መጻሕፍት ስላላቸው ስምምነትና የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች የላቁ ስለመሆናቸው እንዲሁም በውስጡ ስለሚገኙት ትንቢቶች አፈጻጸም ጊዜ ወስደህ በመመርመር፣ መጽሐፉን ያጻፈው ፈጣሪ ራሱ ለመሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን ማግኘት ትችላለህ። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች መረዳትህ ይህ መጽሐፍ በእርግጥም የፈጣሪ ቃል መሆኑን እንድታምን ያደርግሃል። ለምሳሌ ያህል፣ መከራና ሥቃይ ስለመጣበት ምክንያት፣ ስለ አምላክ መንግሥት፣ ስለ ሰው ዘር የወደፊት ተስፋና ደስታ ስለሚገኝበት መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ስትረዳ የአምላክ ጥበብ ግልጽ ሆኖ ይታይሃል። አንተም “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!” በማለት እንደጻፈው እንደ ጳውሎስ ይሰማህ ይሆናል።—ሮሜ 11:33

ማስረጃዎቹን እየመረመርክ ስትሄድ እምነትህ ይጎለብታል፤ ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ ፈጣሪን እየሰማህ እንዳለህ ሆኖ እንዲሰማህ ያደርጋል። ፈጣሪ እንዲህ ብሏል:- “ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤ እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤ የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።” (ኢሳይያስ 45:12) በእርግጥም፣ ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ መሆኑን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ፈጽሞ አያስቆጭህም።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሐዋርያው ጳውሎስ ለተማሩ ግሪካውያን ‘አምላክ የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ሰው እንደፈጠረ’ ነግሯቸዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዝግመተ ለውጥ፣ አሁን ያለው ሰው የተገኘው እየተሻሻለ ከመጣ እንስሳ ነው ብሎ ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን፣ የሰው ዘር ከፍጽምና እየራቀ ቢመጣም እንኳ የተገኘው ፍጹም ከነበረ አንድ ሰው እንደሆነ ይናገራል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በሞለኪዩሎች ውስጥ ዝግመተ ለውጥ ይካሄዳል የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በሳይንሳዊ መረጃዎች የተደገፈ አይደለም”

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ የሚንጸባረቀው አስደናቂ ንድፍ ፈጣሪያችን ባለው ጥበብ እንድንደመም ያደርገናል