በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ እውነተኛው አምላክ

ስለ እውነተኛው አምላክ

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

ስለ እውነተኛው አምላክ

አምላክ ስም አለው?

ኢየሱስ፣ አምላክ ስም እንዳለው አስተምሯል። እንዲህ ብሎ ነበር:- “እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ።’” (ማቴዎስ 6:9) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ይነግረናል። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም፤ መዝሙር 83:18 NW) ኢየሱስ “ስምህን አስታወቅኋቸው” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስመልክቶ ወደ አባቱ ጸልዮ ነበር።—ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም

ይሖዋ ማን ነው?

ይሖዋ፣ ፈጣሪ በመሆኑ ምክንያት ኢየሱስ ‘አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ ነህ’ ብሎታል። (ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስ፣ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን?” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:4) ከዚህ በተጨማሪም “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:24) በመሆኑም አምላክን ማየት አንችልም።—ዘፀአት 33:17-20

አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

አንድ ሰው ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ ኢየሱስን በጠየቀው ጊዜ እንዲህ በማለት መለሰለት:- “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’”—ማርቆስ 12:28-31

አምላክን እንደምንወድ እንዴት ማሳየት እንችላለን?

ኢየሱስ፣ ‘አብን እወዳለሁ’ ሲል ተናግሯል። ኢየሱስ አምላክን እንደሚወድ ያሳየው እንዴት ነበር? ‘አባቴ ያዘዘኝን አደርጋለሁ’ በማለት መልሱን ይነግረናል። (ዮሐንስ 14:31) በተጨማሪም ኢየሱስ ‘ምንጊዜም የሚያስደስተውን አደርጋለሁ’ ብሏል። (ዮሐንስ 8:29) ስለ አምላክ በመማር እሱን ማስደሰት እንችላለን። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲጸልይላቸው እንዲህ ብሎ ነበር:- “አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆንኸውንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4

ስለ አምላክ መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ስለ አምላክ ማወቅ ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ የሠራቸውን ነገሮች መመልከት ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እስቲ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” ኢየሱስ እዚህ ላይ ማስጨበጥ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት ያለብን ጭንቀት አምላክን ማገልገላችንን እንድናቆም ሊያደርገን አይገባም።—ማቴዎስ 6:26-33

አምላክን ለማወቅ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ነው። ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ‘የአምላክ ቃል’ በማለት ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 8:21) ኢየሱስ አምላክን “ቃልህ እውነት ነው” ብሎታል።—ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21

ኢየሱስ ሰዎች ስለ ይሖዋ እውነቱን እንዲያውቁ ረድቷል። ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ ኢየሱስን በሚመለከት “በመንገድ ሳለን፣ እያነጋገረን ቅዱሳት መጻሕፍትንም ገልጦ ሲያስረዳን፣ ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረምን?” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 24:32) ስለ አምላክ ማወቅ ከፈለግን በትሕትና ለመማር ፈቃደኞች መሆን አለብን። ኢየሱስ “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተለወጣችሁ እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ ፈጽሞ ወደ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም” በማለት ተናግሯል።—ማቴዎስ 18:3

ስለ አምላክ ማወቅ ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን እንዴት ነው?

አምላክ ስለ ሕይወት ዓላማ ለማወቅ ያለንን ፍላጎት ያረካልናል። ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3 NW) ይሖዋ ከሁሉ የተሻለው የሕይወት ጎዳና የትኛው እንደሆነ ያስተምረናል። ኢየሱስ ‘የአምላክን ቃል ሰምተው የሚታዘዙት ደስተኞች ናቸው’ ብሏል።—ሉቃስ 11:28፤ ኢሳይያስ 11:9

ለበለጠ መረጃ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 1⁠ን ተመልከት። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ስምህን አስታወቅኋቸው።”—ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ፍጥረትን በመመልከትና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ አምላክ መማር እንችላለን