በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኢየሱስ ስም መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

በኢየሱስ ስም መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ስለ ጸሎት አስተምሯል። እሱ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘በየመንገዱ ማእዘን ቆመው ይጸልዩ’ ነበር። እንዲህ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? “ለሰዎች ለመታየት ሲሉ” ነበር። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው እነዚህ ሰዎች ሃይማኖተኛ ተብለው መወደስ ይፈልጉ ነበር። ብዙዎች ‘ቃላትን ካልደጋገሙ’ በስተቀር ጸሎታቸው ተሰሚነት የማያገኝ ይመስል ሐሳባቸውን ይደጋግሙ ነበር። (ማቴዎስ 6:5-8) ኢየሱስ እንዲህ ያለው ድርጊት ከንቱ መሆኑን ከተናገረ በኋላ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በሚጸልዩበት ወቅት ምን ነገሮችን ማስወገድ እንደሚገባቸው አሳውቋቸዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በሚጸልዩበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሌለባቸው በማስተማር ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚያ ያለፈ ነገርም አድርጓል።

ኢየሱስ ጸሎቶቻችን የአምላክ ስም ተቀድሶ፣ መንግሥቱ መጥቶ እንዲሁም ፈቃዱ ተፈጽሞ ማየት እንደምንፈልግ የሚያሳዩ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯል። በተጨማሪም ከግል ጉዳዮቻችን ጋር በተያያዘ እንዲረዳን መጠየቃችን ተገቢ መሆኑን አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9-13፤ ሉቃስ 11:2-4) ኢየሱስ የምናቀርበውን ጸሎት ይሖዋ እንዲሰማልን ከፈለግን መታከት እንደሌለብን እንዲሁም እምነትና ትሕትና ሊኖረን እንደሚገባ ምሳሌዎችን ተጠቅሞ አስተምሯል። (ሉቃስ 11:5-13፤ 18:1-14) ከዚህም በላይ ራሱ ምሳሌ በመሆን ጠንከር ያለ ትምህርት ሰጥቷል።—ማቴዎስ 14:23፤ ማርቆስ 1:35

እነዚህ ትምህርቶች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የጸሎታቸውን ይዘት ማሻሻል እንዲችሉ እንደረዷቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ኢየሱስ፣ ጸሎትን በተመለከተ ከፍተኛ ትርጉም ያለውን ትምህርት የሰጣቸው በምድር ላይ ባሳለፋት በመጨረሻዋ ምሽት ነበር።

“በጸሎት ታሪክ ውስጥ የተከሰተ ትልቅ ለውጥ”

ኢየሱስ የመጨረሻዋን ምሽት በአብዛኛው ያሳለፈው ለታማኝ ሐዋርያቱ ማበረታቻ በመስጠት ነበር። ይህ ወቅት አንድ ነገር ለመግለጽ የሚያስችል አመቺ ጊዜ ነበር። ኢየሱስ “መንገዱ እኔ ነኝ፤ እውነትና ሕይወትም እኔው ነኝ፤ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናገረ። ትንሽ ቆየት ብሎ እንዲህ በማለት ቃል ገባላቸው:- “አብ በወልድ እንዲከብር፣ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማንኛውንም ነገር በስሜ ብትለምኑኝ፣ [“ብትለምኑ፣” የ1954 ትርጉም] እኔ አደርገዋለሁ።” በውይይታቸው መጨረሻ አካባቢ ደግሞ “እስከ አሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም፤ ለምኑ ትቀበላላችሁ፤ ደስታችሁም ሙሉ ይሆናል” አላቸው።—ዮሐንስ 14:6, 13, 14፤ 16:24

እነዚህ ቃላት ከፍተኛ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ሐሳብ “በጸሎት ታሪክ ውስጥ የተከሰተ ትልቅ ለውጥ” በማለት ገልጾታል። ኢየሱስ ይህንን ሲል ሰዎች ጸሎታቸውን ለአምላክ ሳይሆን ለእሱ እንዲያቀርቡ መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ አምላክ በጸሎት መቅረብ የሚችሉበትን አዲስ መንገድ ማስተዋወቁ ነበር።

አምላክ ምንጊዜም ቢሆን የታማኝ አገልጋዮቹን ጸሎት ይሰማ እንደነበር እሙን ነው። (1 ሳሙኤል 1:9-19፤ መዝሙር 65:2) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ጸሎታቸው እንዲሰማላቸው የሚፈልጉ ሰዎች፣ እስራኤል በአምላክ የተመረጠ ብሔር መሆኑን አምነው መቀበል ነበረባቸው። ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ ደግሞ አንድ ሰው፣ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት እንዲቀርብበት አምላክ የመረጠው ቦታ መሆኑን ማመን ነበረበት። (ዘዳግም 9:29፤ 2 ዜና መዋዕል 6:32, 33) ይሁንና ይህ ዓይነቱ የአምልኮ ሥርዓት ጊዜያዊ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ለእስራኤላውያን የተሰጠው ሕግ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች ‘ወደ ፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ናቸው እንጂ፣ እውነተኛው አካል አይደሉም።’ (ዕብራውያን 10:1, 2) ዋናው አካል ሲመጣ ጥላ የሆነው ነገር ይቀራል። (ቈላስይስ 2:17) ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ ግን አንድ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና የሙሴን ሕግ በመታዘዙ ላይ የተመካ መሆኑ ቀረ። ከዚህ ይልቅ ሕጉ ጥላ ለሆነለት ለክርስቶስ ኢየሱስ በመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ሆነ።—ዮሐንስ 15:14-16፤ ገላትያ 3:24, 25

‘ከስም ሁሉ በላይ’ የሆነ ስም

ኢየሱስ፣ ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበትን ከሁሉ የላቀ መሠረት ጥሏል። ኢየሱስ ጸሎታችን በአምላክ ዘንድ እንዲሰማልን ብሎም መልስ እንዲያገኝ መንገድ የከፈተ ኃያል ወዳጃችን እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ ይህንን ብቃት እንዲያገኝ ያስቻለው ምንድን ነው?

ሁላችንም ኃጢአተኛ ሆነን ስለተወለድን ምንም ዓይነት ሥራ ብንሠራ ወይም የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕት ብናቀርብ ከዚህ ኃጢአት ልንነጻ አሊያም ቅዱስ ከሆነው አምላካችን ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት የመመሥረት መብት ልናገኝ አንችልም። (ሮሜ 3:20, 24፤ ዕብራውያን 1:3, 4) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ የሰው ዘር ከኃጢአት ነፃ የሚሆንበትን መንገድ ከፈተ። (ሮሜ 5:12, 18, 19) ስለዚህ ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው የሚፈልጉ ሁሉ በይሖዋ ፊት ንጹሕ አቋም የማግኘት እንዲሁም “በነጻነት” ወደ አምላክ የመቅረብ አጋጣሚ አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ሊሆን የሚችለው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ጠንካራ እምነት ሲኖራቸውና በእሱ ስም ሲጸልዩ ብቻ ነው።—ኤፌሶን 3:11, 12

በኢየሱስ ስም በምንጸልይበት ወቅት እሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ካለው ቦታ መካከል ቢያንስ ሦስቱን አምነን እንደምንቀበል እናሳያለን። (1) እሱ መሥዋዕት ሆኖ የኃጢአት ይቅርታ ያስገኘልን ‘የአምላክ በግ’ ነው። (2) ይሖዋ ከሞት ያስነሳው ሲሆን በአሁኑ ወቅት ቤዛውን ጥቅም ላይ ለማዋል “ሊቀ ካህናት” ሆኖ እያገለገለ ነው። (3) በጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚቻልበት “መንገድ” እሱ ብቻ ነው።—ዮሐንስ 1:29፤ 14:6፤ ዕብራውያን 4:14, 15

በኢየሱስ ስም መጸለያችን ለእሱ ክብር ያመጣለታል። “ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ” የይሖዋ ፈቃድ በመሆኑ ለኢየሱስ እንዲህ ያለውን ክብር መስጠታችን ተገቢ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:10, 11) ከሁሉም በላይ ግን በኢየሱስ ስም መጸለያችን ልጁን ለእኛ ሲል ለሰጠው ለይሖዋ ክብር ያመጣለታል።—ዮሐንስ 3:16

በዘልማድ ሳይሆን ‘በፍጹም ልባችን’ መጸለይ ይኖርብናል

ኢየሱስ ያለውን ቦታ መረዳት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩ ማዕረጎችንና ስሞችን ይጠቀማል። እነዚህ ስሞች ኢየሱስ ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው፣ በአሁኑ ጊዜ እያደረጋቸው ባሉትና ወደፊት በሚያደርጋቸው ነገሮች አማካኝነት የምናገኛቸውን እጅግ ብዙ በረከቶች እንድናስተውል ይረዱናል። (” “ ኢየሱስ የሚጫወተው ወሳኝ ሚና” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በእርግጥም ኢየሱስ ‘ከስም ሁሉ በላይ የሆነ ስም’ * ተሰጥቶታል። በሌላ አነጋገር ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶታል።—ፊልጵስዩስ 2:9፤ ማቴዎስ 28:18

ጸሎታችን የዘልማድ መሆን አይገባውም

በእርግጥም ጸሎታችን በይሖዋ ዘንድ ተሰሚነት እንዲኖረው የምንፈልግ ከሆነ በኢየሱስ ስም መቅረብ ይኖርበታል። (ዮሐንስ 14:13, 14) ይሁን እንጂ “በኢየሱስ ስም” የሚለውን አገላለጽ እንዲያው ልማድ ስለሆነብን ብቻ ልንጠቅሰው አንፈልግም። ለምን?

እስቲ አንድ ምሳሌ ተመልከት። ከአንድ ነጋዴ ደብዳቤ ተላከልህ እንበል፤ ደብዳቤው የሚደመደመው “ከሰላምታ ጋር” በሚለው የተለመደ አባባል ነው። ይህ ሐረግ የነጋዴውን እውነተኛ ስሜት ይገልጻል ብለህ ታስባለህ? ወይስ ግለሰቡ ይህን ያለው ደብዳቤን በዚህ መንገድ መዝጋት የተለመደ ስለሆነ ነው? በጸሎታችን ውስጥ የኢየሱስን ስም የምንጠቀምበት መንገድ ከአንድ የንግድ ድርጅት ከተላከ ደብዳቤ የመዝጊያ ሐሳብ የበለጠ ትርጉም እንዲኖረው እንፈልጋለን። ‘ሳናቋርጥ መጸለይ’ የሚገባን ቢሆንም ይህን የምናደርገው በዘልማድ ሳይሆን ‘በፍጹም ልባችን’ መሆን ይኖርበታል።—1 ተሰሎንቄ 5:17፤ መዝሙር 119:145

“በኢየሱስ ስም” የሚለውን አገላለጽ በዘልማድ የምትጠቀም ከሆነ እንዲህ ያለውን ልማድ እንዴት ማስቀረት ትችላለህ? አስደሳች በሆኑት የኢየሱስ ባሕርያት ላይ ለምን አታሰላስልም? ኢየሱስ ከዚህ በፊት ባደረገልህና ወደፊትም በፈቃደኝነት በሚያደርግልህ ነገሮች ላይ አስብ። በጸሎትህ ላይ ይሖዋን አመስግን እንዲሁም በልጁ በኩል ስላደረገልህ ነገሮች አወድሰው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ኢየሱስ “አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ሲል የገባው ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ዮሐንስ 16:23

^ አን.14 በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ወርድስ “ስም” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ስም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገልጻቸውን ነገሮች በሙሉ ማለትም ሥልጣንን፣ ባሕርይን፣ ማዕረግን፣ ግርማዊነትን፣ ኃይልን [እና] ክብርን” ሊያመለክት እንደሚችል ተናግሯል።