ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው?
ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው?
የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በርካታ ሰዎች ሕይወት ምድር ላይ የተገኘው በአጋጣሚ እንደሆነ የሚገልጽ ትምህርት ተምረዋል። ስሜት፣ የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ እንዲሁም ስለ ሕይወት ጥልቅ የሆኑ ነገሮችን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ያለው የሰው ልጅ በተከታታይ በተፈጸሙ ድንገተኛ ክስተቶች አማካኝነት በዝግመተ ለውጥ እንደተገኘ ተነግሯቸዋል።
እስቲ አስበው፣ ወደ ሕልውና የመጣነው በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ከሆነና ፈጣሪ ከሌለ የሰው ዘር ወላጅ አልባ ነው ማለት ነው። የሰው ልጅ ሊያማክረው የሚችለው ታላቅ ጥበብ ያለውና ችግሮቻችንን እንድንፈታ ሊረዳን የሚችል አካል የለም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ በተፈጥሮ ላይ እየደረሰ ላለው ቀውስ መፍትሔ ለማምጣት፣ ፖለቲካዊ ግጭቶችን ለመፍታትና በግል የሚያጋጥሙንን ሌሎች ችግሮች ለማስወገድ በሰው ልጅ ጥበብ ላይ መታመን ይኖርብናል ማለት ነው።
በሰው ልጅ ጥበብ ላይ ብቻ መመካት የአእምሮ ሰላም የሚያስገኝልህ ይመስልሃል? የማያስገኝልህ ከሆነ ሌላውን አማራጭ ተመልከት። ይህ አማራጭ ይበልጥ ማራኪ ከመሆኑም ሌላ ምክንያታዊ ጭምር ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጅ በቀጥታ በአምላክ እንደተፈጠረ ያስተምራል። ስሜት አልባ የሆነውና ምንም የማሰብ ችሎታ የማይንጸባረቅበት የዝግመተ ለውጥ ውጤቶች አይደለንም። ከዚህ ይልቅ አፍቃሪ የሆነና የማሰብ ችሎታ ያለው አባት ልጆች ነን። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በግልጽ የተቀመጡትን እነዚህ አባባሎች እስቲ ልብ በላቸው:-
ዘፍጥረት 1:27፦ “ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።”
መዝሙር 139:14፦ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።”
ማቴዎስ 19:4፦ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25፦ “ዓለምንና በውስጡ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነው፤ ስለዚህም እርሱ የሰው እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም። እርሱ ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም።”
ራእይ 4:11፦ “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፤ ክብርና ሞገስ፣ ኀይልም ልትቀበል ይገባሃል፤ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና፤ በፈቃድህም ተፈጥረዋልና፤ ሆነዋልምና።”
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ እውነተኛ የአእምሮ ሰላም የሚያስገኘው እንዴት ነው?
‘በሰማይና በምድር ያለው ቤተሰብ ሁሉ ስያሜውን’ ያገኘው ከአምላክ መሆኑን ማወቃችን ሌሎች ሰዎችን በምንመለከትበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል። (ኤፌሶን 3:15) በተጨማሪም እንዲህ ያለው እውቀት ለራሳችንም ሆነ ለሚያጋጥሙን ችግሮች በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህ እውቀት ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ጉዳዮች ረገድ በሚኖረን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
ከባድ ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ ሲያጋጥመን እርስ በርሱ በሚጋጨው የሰው ልጅ አስተሳሰብ ከልክ በላይ አንጨነቅም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ምክር ሙሉ በሙሉ እንታመናለን። ለምን? ምክንያቱም “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በተግባር ላይ ማዋል ጥረትና ራስን መገሠጽ ይጠይቃል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው መመሪያ ከእኛ ፍላጎት ተቃራኒ የሆነ ነገር እንድናደርግ የሚጠይቅ ይሆናል። (ዘፍጥረት 8:21) ይሁን እንጂ፣ በሰማይ በሚኖር አፍቃሪ አባት እንደተፈጠርን የምናምን ከሆነ ልንከተለው የሚገባንን ከሁሉ የተሻለ ጎዳና ያውቃል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ አይከብደንም። (ኢሳይያስ 55:9) ቃሉ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) ይህንን ምክር በተግባር ላይ የምናውል ከሆነ ችግሮችና ውሳኔ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ከመጠን በላይ ከመጨነቅ እንድናለን።
መድሎ ሲፈጸምብን፣ ይህ የሆነው ከእኛ የተለየ ብሔር ወይም አስተዳደግ ካላቸው ሰዎች ያነስን በመሆኑ እንደሆነ አድርገን በማሰብ በበታችነት ስሜት አንሠቃይም። ከዚህ ይልቅ ለራሳችን ተገቢ የሆነ አክብሮት ለማዳበር ጥረት እናደርጋለን። ለምን? ምክንያቱም አባታችን ይሖዋ አምላክ “ለማንም እንደማያዳላ” እንዲያውም ‘እሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ እንደሚቀበላቸው’ እናውቃለን።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35
ከዚህም በተጨማሪ ይህንን ማወቃችን፣ የሚፈጸምብን በደል ለሌሎች ሰዎች ያለንን አመለካከት እንዳያዛባብን ይረዳናል። አምላክ “የሰውን ዘር ሁሉ ከአንድ ወገን ፈጥሮ በምድር ሁሉ ላይ እንዲኖሩ” ማድረጉን ጠንቅቀን ስለምናውቅ ከሌላው ዘር እንበልጣለን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት እንደሌለን እንረዳለን።—የሐዋርያት ሥራ 17:26
በእርግጥም የይሖዋ ፍጥረቶች መሆናችንንና ፈጣሪያችን እንደሚያስብልን ማወቃችን እውነተኛ የአእምሮ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል። ይሁን እንጂ የአእምሮ ሰላም እንዲኖረን ከተፈለገ ከዚህ የበለጠ ነገር ያስፈልገናል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሰው የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈጣሪያችን እንደሚያስብልን ማወቃችን እውነተኛ የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል