በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ሕጉ ሞግዚታችን ሆነ’

‘ሕጉ ሞግዚታችን ሆነ’

‘ሕጉ ሞግዚታችን ሆነ’

የሚሰጣቸው መመሪያና ተግሣጽ ጠቃሚ መሆኑን የሚያስተውሉት ምን ያህል ልጆች ናቸው? ብዙዎቹ ይህንን አያስተውሉም። እንዲያውም እነዚህ ልጆች የሚጣሉባቸው ገደቦች ያበሳጯቸዋል። ይሁንና ልጆችን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ተገቢ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ብዙ ልጆች ትልቅ ከሆኑ በኋላ፣ ልጅ ሳሉ ይሰጣቸው የነበረው መመሪያ ጠቃሚ መሆኑን ይገነዘቡ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ አምላክ ሕዝቡን ለመጠበቅ የወሰዳቸውን እርምጃዎች ለማስረዳት፣ ለልጆች እንክብካቤ የሚያደርግን ሰው ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ የሮም ግዛት በሆነችው በገላትያ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች አምላክ የሚቀበለው በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጠውን ሕግ የሚታዘዙ ሰዎችን ብቻ ነው የሚል ግትር አቋም ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ የሙሴን ሕግ በማይጠብቁ ሰዎች ላይ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ተመልክቶ ስለነበር እንዲህ ያለው አመለካከት ስህተት መሆኑን ተረድቶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:12) በመሆኑም ጳውሎስ ምሳሌ በመጠቀም የተሳሳተ አመለካከታቸውን እንዲያስተካክሉ ረድቷቸዋል። ጳውሎስ በገላትያ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ” ብሏል። (ገላትያ 3:24) አንድ ምሁር እንዳሉት ሞግዚትነት “ቀደም ባሉት ዓመታት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥራ ነበር።” አንድ ሞግዚት በጥንት ዘመን የነበረውን ኃላፊነት ማወቃችን ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸውን ሐሳብ ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።

ሞግዚት የነበረው ኃላፊነት

ባለጸጋ በሆኑ ግሪካውያን፣ ሮማውያን ሌላው ቀርቶ በአይሁዳውያን ዘንድ ልጆችን የሚንከባከቡ ሞግዚቶችን መቅጠር የተለመደ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ለሞግዚትነት የሚመረጡ ሰዎች በዕድሜ የገፉና ታማኝ አገልጋይ መሆን የነበረባቸው ሲሆን የልጁን ደኅንነት የመጠበቅ እንዲሁም ልጁ አባትየው በሚፈልገው መንገድ መያዙን የመከታተል ኃላፊነት ነበረባቸው። ሞግዚቱ ቀኑን ሙሉ ከልጁ ጋር አብሮት ይሆናል፤ ንጽሕናውን ይቆጣጠራል እንዲሁም ብዙውን ጊዜ መጽሐፎቹንና ሌሎች ነገሮችን ይዞለት ወደ ትምህርት ቤት ይወስደዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጥናቱን ማጥናቱን ይከታተላል።

አብዛኛውን ጊዜ ሞግዚት የትምህርት ቤት አስተማሪ አይደለም። የሞግዚት ኃላፊነት ለልጁ የቀለም ትምህርት መስጠት ሳይሆን የአባትየውን መመሪያ በመከተል ልጁን በአደራ ተቀብሎ ማሠልጠን ነው። ያም ሆኖ ልጁን እየተከታተለና እየገሠጸ በተዘዋዋሪ መንገድ ሥልጠና ይሰጠዋል። ይህም ልጁ ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖረው ማሠልጠንን፣ መገሠጽንና ሌላው ቀርቶ በሚያጠፋበት ጊዜ መቅጣትን ያጠቃልላል። እርግጥ ነው፣ ልጁን በማስተማር ረገድ ቅድሚያውን የሚወስዱት እናቱና አባቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ልጁ እያደገ ሲሄድ ሞግዚቱ አረማመዱንና አለባበሱን በተመለከተ ሥልጠና የሚሰጠው ሲሆን ከዚህም በላይ በሥርዓት እንዲቀመጥና እንዲመገብ፣ ለታላላቆቹ እንዲነሳ፣ ወላጆቹን እንዲወድ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ ማስተማር ይጠበቅበታል።

ግሪካዊው ፈላስፋ ፕሌቶ (428-348 ከክርስቶስ ልደት በፊት) ልጆች ያለጠባቂ ሊተዉ እንደማይገባ ያምን ነበር። በመሆኑም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በጎች ወይም ሌሎች እንስሳት የግድ እረኛ እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ልጆች ያለሞግዚት፣ ባሪያም ያለጌታ ሊኖር አይችልም።” ይህ አነጋገር የተጋነነ ቢመስልም ፕሌቶ ግን እንዲህ ተሰምቶታል።

ሞግዚቶች ከልጆች ጋር የሚውሉ በመሆናቸው የማያፈናፍኑ፣ በጭካኔ የሚቀጡ፣ አላስፈላጊ ደንቦችን የሚያወጡ እንዲሁም አሰልቺ እንደሆኑና በሆነ ባልሆነው ልጆችን የሚወነጅሉ ተደርገው ይታዩ ነበር። ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ሞግዚቶች ይህን የመሰለ ስም ቢያተርፉም አብዛኞቹ ግን ለልጆቹ ሥነ ምግባራዊና አካላዊ ጥበቃ ያደርጉላቸዋል። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖር የነበረ አፒያን የተባለ ግሪካዊ ታሪክ ጸሐፊ፣ ወደ ትምህርት ቤት የሚወስደውን ልጅ ለመግደል የመጡ ሰዎችን ለመከላከል ሲል ልጁን አቅፎ አልለቅም ስላለ አንድ ሞግዚት ጽፎ ነበር። ይህ ሞግዚት ልጁን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሰዎቹ ሁለቱንም ገደሏቸው።

ግሪክ ውስጥ የሥነ ምግባር ውድቀት እጅግ ተስፋፍቶ ስለነበር ሕፃናትን በተለይም ወንዶች ልጆችን ከጾታ ጥቃት መጠበቅ ያስፈልግ ነበር። አብዛኞቹ አስተማሪዎች እምነት የሚጣልባቸው ስላልነበሩ ሞግዚቶች ልጆቹ በሚማሩበት ወቅት አብረዋቸው ይሆኑ ነበር። በዚህም ምክንያት በአራተኛው መቶ ዘመን ይኖር የነበረውና በንግግር ችሎታው ታዋቂነትን ያተረፈው ለቤኒየስ የሞግዚቶችን ኃላፊነት እንዲህ በማለት ገልጿል:- “[ሞግዚቶች] ወንዶቹን ልጆች በፍቅር ስሜት ሊቀርቧቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንዳይጠጓቸው በማድረግ፣ አጠገባቸው እንዳይደርሱ የሚያግዱና የሚከላከሉ፣ የልጆች ጠባቂዎች ናቸው።” በርካታ ልጆች እንክብካቤ ለሚያደርጉላቸው ሞግዚቶች አክብሮት አላቸው። ልጆቹ አዋቂ ከሆኑ በኋላ ተወዳጅ ለሆኑት የቀድሞ ሞግዚቶቻቸው የመታሰቢያ ሃውልት ማሠራታቸው አመስጋኝ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

የሙሴ ሕግ እንደ ሞግዚት ሆኖ አገልግሏል

ሐዋርያው ጳውሎስ የሙሴን ሕግ ከሞግዚት ጋር ያመሳሰለው ለምን ነበር? ይህን ንጽጽር መጠቀሙ ተስማሚ ነው የምንለውስ ለምንድን ነው?

ሕጉ ከሞግዚት ጋር የሚመሳሰልበት አንዱ መንገድ እንደ ጠባቂ ሆኖ ማገልገሉ ነው። ጳውሎስ አይሁዳውያን “በሕግ ጥበቃ ሥር” እንደነበሩ ገልጿል። አይሁዳውያን ልክ በሞግዚት ጥበቃ ሥር እንዳሉ ያህል ነበር። (ገላትያ 3:23 የታረመው የ1980 ትርጉም) ሕጉ በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ላይ ተጽዕኖ ያሳድር ነበር። የጾታ ስሜታቸውንና ሥጋዊ ፍላጎታቸውን እንዲቆጣጠሩ ይረዳቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ አኗኗራቸውን በተመለከተ መመሪያ የሚሰጣቸው ሲሆን ስሕተት በሚሠሩበት ጊዜ ሁሉ ይወቅሳቸው ነበር። ይህም እያንዳንዱ እስራኤላዊ ፍጹም አለመሆኑን እንዲገነዘብ ያደርገዋል።

በተጨማሪም ሕጉ እስራኤላውያንን በዙሪያቸው ያሉት ብሔራት ከነበራቸው ልቅ ሥነ ምግባርና ሃይማኖታዊ ልማድ እንዲሁም ከሌሎች መጥፎ ተጽዕኖዎች ጠብቋቸዋል። ለምሳሌ ያህል አምላክ ከሌሎች አሕዛብ ጋር በጋብቻ እንዳይተሳሰሩ የሰጣቸው ትእዛዝ የብሔሩን መንፈሳዊ ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ነበረው። (ዘዳግም 7:3, 4) እነዚህ ደንቦች የአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ ንጽሕና እንዲጠበቅና መሲሑን ለመቀበል ዝግጁ እንዲሆኑ አስችለዋቸዋል። በእርግጥም ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው! ሙሴ እስራኤላውያን ወገኖቹን “ሰው ልጁን እንደሚቀጣ፣ አምላክህ እግዚአብሔርም አንተን እንደሚቀጣህ በልብህ ዕወቅ” በማለት አሳስቧቸዋል።—ዘዳግም 8:5

ይሁን እንጂ የሐዋርያው ጳውሎስ ምሳሌ በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው ሞግዚቱ ጊዜያዊ ሥልጣን ያለው በመሆኑ ላይ ነው። አንድ ልጅ ካደገ በኋላ የሞግዚቱ ቁጥጥር አያስፈልገውም። ግሪካዊው ታሪክ ጸሐፊ ዜኖፎን (431-352 ከክርስቶስ ልደት በፊት) እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንድ ልጅ ትልቅ ሲሆን ሌሎች ሰዎች [ከሞግዚቱም] ሆነ [ከአስተማሪው] ነፃ እንዲሆን ያደርጉታል። ከዚያ በኋላ ልጁ በእነሱ ቁጥጥር ሥር አይሆንም፤ ከዚህ ይልቅ የራሱን ሕይወት እንዲመራ ይፈቀድለታል።”

የሙሴ ሕግ የሚያከናውነው ተግባር ከአንድ ሞግዚት ሥራ ጋር ተመሳሳይ ነው። ሕጉ የሚሰጠው አገልግሎት ጊዜያዊ ሲሆን ይህም “ተስፋ የተሰጠው ዘር [ኢየሱስ ክርስቶስ] እስኪመጣ ድረስ ክፉ ሥራ ምን መሆኑን ለማመልከት ነው።” ሐዋርያው ጳውሎስ ሕጉ አይሁዳውያንን ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት’ እንደሆነ ገልጿል። በጳውሎስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለጉ ኢየሱስ በአምላክ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና መቀበል ነበረባቸው። የኢየሱስን ሚና አምነው ሲቀበሉ የሞግዚት አስፈላጊነት ያበቃል።—ገላትያ 3:19 የ1980 ትርጉም፣ 24, 25

አምላክ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ሕግ ፍጹም ነበር። ሕጉ የተሰጠበትን ዓላማ ፈጽሟል። የሕጉ ዓላማ ሕዝቡን መጠበቅና የአምላክን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደንቦች እንዲያውቁ መርዳት ነበር። (ሮሜ 7:7-14) ሕጉ ጥሩ ሞግዚት የነበረ ቢሆንም በሕጉ ሥር የነበሩ አንዳንዶች ግን ሸክም እንደሆነ ሳይሰማቸው አልቀረም። በመሆኑም ጳውሎስ አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ‘ክርስቶስ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል’ በማለት ጽፏል። ሕጉ ‘ርግማን’ የሆነው ፍጹማን ያልሆኑት አይሁዳውያን ሙሉ በሙሉ ሊጠብቋቸው የማይችሏቸውን ትእዛዛት ስለያዘ ነው። ሕጉ የአምልኮ ሥርዓቶችን በጥብቅ እንዲከተሉ ያዛል። አንድ አይሁዳዊ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የተደረገለትን ግሩም ዝግጅት ከተቀበለ የሞግዚቱን መመሪያ መጠበቅ አያስፈልገውም።—ገላትያ 3:13፤ 4:9, 10

ስለሆነም ጳውሎስ የሙሴን ሕግ ከሞግዚት ጋር ሲያወዳድር ይበልጥ ትኩረት ያደረገው ሕጉ ጠባቂ ሆኖ በማገልገሉና ጊዜያዊ በመሆኑ ላይ ነው። የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የሚቻለው ሕጉን በመጠበቅ ሳይሆን ኢየሱስን በማወቅና በእሱ በማመን ነው።—ገላትያ 2:16፤ 3:11

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ጠባቂዎች” እና “መጋቢዎች”

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሞግዚት ከመጻፉም በተጨማሪ ‘ስለ ጠባቂዎችና ስለ መጋቢዎች’ የሚናገሩ ምሳሌዎችንም ተጠቅሟል። ገላትያ 4:1, 2 (የ1954 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “ወራሹ ሕፃን ሆኖ ባለበት ዘመን ሁሉ፣ ምንም የሁሉ ጌታ ቢሆን ከቶ ከባሪያ አይለይም፣ ነገር ግን አባቱ እስከ ቀጠረለት ቀን ድረስ ከጠባቂዎችና ከመጋቢዎች በታች ነው።” ‘የጠባቂዎችና የመጋቢዎች’ ኃላፊነት ከሞግዚቶች የሚለይ ቢሆንም ጳውሎስ ለማስተላለፍ የፈለገው ሐሳብ ግን ተመሳሳይ ነው።

በሮማውያን ሕግ መሠረት ‘ጠባቂ፣’ ወላጆቹን በሞት ያጣን ልጅ እንዲጠብቅና እስኪያድግ ድረስ ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲከታተልለት በሕግ የሚሾም ሰው ነው። ስለሆነም ጳውሎስ እንደተናገረው፣ እንዲህ ያለው ልጅ በውርሻ ባገኘው ንብረት ላይ “ጌታ” ቢሆንም እንኳ እስኪያድግ ድረስ በሀብቱ ላይ ከአንድ ባሪያ የተለየ ሥልጣን አይኖረውም።

በሌላው በኩል አንድ ‘መጋቢ’ ከልጁ ንብረት ጋር የተያያዙ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት። ፍላቭየስ ጆሴፈስ የተባለው አይሁዳዊ ታሪክ ጸሐፊ፣ ኸርኬነስ የተባለ አንድ ወጣት የሚያስፈልገውን ነገር ለመግዛት እንዲችል ገንዘብ እንዲሰጠው ለመጋቢው ደብዳቤ እንዲጽፍለት አባቱን መጠየቁን ጽፏል።

አንድ ልጅ በሞግዚት፣ ‘በጠባቂ’ ወይም ‘በመጋቢ’ ቁጥጥር ሥር መሆኑ እስከሚያድግ ድረስ ነፃነት እንደሌለው ይጠቁማል። ይህ ልጅ አባቱ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በሌሎች ቁጥጥር ሥር ይሆናል።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምርኩዝ የያዘን አንድ ሞግዚት የሚያሳይ በአበባ ማስቀመጫ ላይ የተሳለ ጥንታዊ የግሪክ ሥዕል

[ምንጭ]

National Archaeological Museum, Athens

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ሞግዚት (ምርኩዝ የያዘው ነው) በእሱ ኃላፊነት ሥር ያለው ልጅ ግጥምና ሙዚቃ በሚማርበት ጊዜ አብሮት ሲከታተል የሚያሳይ፣ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከክ. ል. በፊት በተሠራ ዋንጫ ላይ ያለ ሥዕል

[ምንጭ]

Bildarchiv Preussischer Kulturbesitz/Art Resource, NY