“በጽድቅ መንገድ ይመራኛል”
“በጽድቅ መንገድ ይመራኛል”
ኦልገ ካምቤል እንደተናገረችው
“ለሌሎች ጥሩ አርዓያ የሚሆን ሰው፣ ልክ እንደ አንድ ደወል ነው። ደወሉ የሚያሰማው ድምፅ ሌሎች ጥሪውን ሰምተው እንዲመጡ ያደርጋል። አንቺ ደወሉን ደወልሽ፣ እኔም ምላሽ ሰጠሁ።” ይህን ያለችው እህቴ ኤመሊ ናት፤ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 60 ዓመት ስለሞላኝ እንኳን ደስ አለሽ ለማለት ደብዳቤ ጽፋልኝ ነበር። የልጅነት ሕይወቴ ምን እንደሚመስልና የዕድሜ ልክ ሥራዬ የሆነውን ይህን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዴት እንደጀመርኩ እስቲ ላውጋችሁ።
የተወለድኩት ጥር 19, 1927 ካናዳ ውስጥ፣ በስተ ምዕራብ አጋማሽ ላይ በምትገኘው ሳስካቺዋን ግዛት ዋካ ከተማ አቅራቢያ በግብርና ከሚተዳደር ዩክሬናዊ ቤተሰብ ነው። እኔና መንታ ወንድሜ ቢል ለቤተሰባችን ስድስተኛና ሰባተኛ ልጆች ስንሆን በጠቅላላ ስምንት ልጆች ነበርን። እኛ በዕድሜ አነስ ያልነው ታታሪ የሆነውን አባታችንን በእርሻ ቦታ እናግዘው ነበር። ምንም እንኳ እናታችን ከጊዜ በኋላ ለሞት በዳረጋት ሩማቶይድ አርትራይተስ በተባለ በሽታ ትሠቃይ የነበረ ቢሆንም በትንሿ ቤታችን ውስጥ ተንከባክባ አሳድጋናለች። እናታችን የሞተችው ገና በ37 ዓመቷ ሲሆን በወቅቱ እኔ የ4 ዓመት ልጅ ነበርኩ።
እናታችን ከሞተች ከስድስት ወር በኋላ አባታችን ሌላ ሴት አገባ። አባቴ ከዚህኛው ትዳሩ ከወለዳቸው አምስት እህቶቻችን ጋር አብረን መኖር ስለነበረብን ብዙም ሳይቆይ በቤታችን ውስጥ ውጥረት ነገሠ! በተቻለኝ መጠን ለእንጀራ እናታችን አክብሮት ለማሳየት እሞክር ነበር፤ ሆኖም ይበልጥ የተቸገረው ታላቅ ወንድሜ ጆን ነበር።
በ1930ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ እኔና ቢል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባን። ይህም ቤት ውስጥ ካለብን ውጥረት ገላገለን። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሊፈነዳ ተቃርቦ ስለነበር በአገሪቱ ውስጥ የአገር ፍቅር ስሜት ነግሦ ነበር። አዲሷ አስተማሪያችን ለባንዲራ ሰላምታ እንድንሰጥ የሚያዝ መመሪያ ያወጣች ሲሆን አንዲት ልጅ በዚህ ድርጊት ለመካፈል ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ተማሪዎቹ የስድብ መዓት አወረዱባት። እኔ ግን ያሳየችው ድፍረት አስደንቆኝ ስለነበር ለምን ሰላምታ እንዳልሰጠች ጠየቅኋት። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (የይሖዋ ምሥክሮች አንዳንድ ጊዜ በዚህ ስም ይጠሩ ነበር) እንደሆነችና ታማኝ መሆን ያለባት ለአምላክ ብቻ እንደሆነ ገለጸችልኝ።—ዘፀአት 20:2, 3፤ የሐዋርያት ሥራ 5:29
ብቻዬን መኖር ጀመርኩ
በ1943 በፕሪንስ አልበርት ከተማ አንድ ሥራ አገኘሁ። ሥራው የለስላሳ ሣጥኖችን መኪና ላይ መጫንና ለደንበኞች ማከፋፈል ነበር። መንፈሳዊ መመሪያ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ ገዛሁ፤ ሆኖም መጽሐፉን መረዳት በጣም አስቸጋሪ ሲሆንብኝ ተስፋ ከመቁረጤ የተነሳ አለቀስኩ። አለኝ የምለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ቢኖር አባታችን ሆይ የሚለው ጸሎት ብቻ ነበር።—ማቴዎስ 6:9-13
አንድ እሁድ ቀን፣ ቤተ ክርስቲያን ታዘወትር የነበረችው አከራዬ አንዲት “የመጽሐፍ ቅዱስ ሴት” መጥታ እንደነበርና ከደጃፏ ገፍትራ እንዳባረረቻት በኩራት ነገረችኝ። ‘እንዴት እንዲህ ያለ ደግነት የጎደለው ድርጊት ትፈጽማለች’ ብዬ አሰብኩ። ጥቂት እሁዶች ካለፉ በኋላ አሞኝ ስለነበር ቤተ
ክርስቲያን ሳልሄድ ቀረሁ። ያን ዕለት ያቺ “የመጽሐፍ ቅዱስ ሴት” ተመልሳ መጣች።“ትጸልያለሽ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“አባታችን ሆይ የሚለውን” በማለት መለስኩላት።
ኢየሱስ የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው ስትገልጽልኝ በጉጉት አዳመጥኳት። በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ ተመልሳ እንደምትመጣ ቃል ገባችልኝ።
ቤት ያከራየችኝ ሴት ወደ ቤት ስትመለስ፣ የይሖዋ ምሥክር ስለሆነችው ስለዚያች “የመጽሐፍ ቅዱስ ሴት” በአድናቆት ነገርኳት። አከራዬ ተስፋ በሚያስቆርጥ መንገድ፣ “ረቡዕ ዕለት ተመልሳ የምትመጣ ከሆነ ሁለታችሁንም ነው ከዚህ ቤት የማባርራችሁ!” በማለት አስፈራራችኝ።
የይሖዋ ምሥክሯ፣ ወይዘሮ ራምፔል እንደምትባል አውቄ ስለነበር እሷን ለማግኘት ሰፈሩን ሳስስ ቆየሁ። ሳገኛት አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባሁ ከገለጽኩላት በኋላ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የቻለችውን ሁሉ እንድትነግረኝ ጠየቅኳት። ስንወያይ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ አንድ የቀረን ነገር ያለ አይመስልም ነበር! አምላክ ክፉ የነበረውን ዓለም እንዳጠፋ እንዲሁም ኖኅንና ቤተሰቡን አድኖ በጸዳች ምድር ላይ እንዳኖራቸው የሚናገረውን ታሪክ በማንሳት የኖኅን ጊዜ አሁን ካለንበት ዘመን ጋር እያወዳደረች አስረዳችኝ።—ማቴዎስ 24:37-39፤ 2 ጴጥሮስ 2:5፤ 3:5-7, 12
ረዘም ያለ ውይይት ካደረግን በኋላ ወይዘሮ ራምፔል እንዲህ አለች:- “እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እውነት መሆናቸውን እንደተቀበልሽ ማስተዋል ችያለሁ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ትልቅ ስብሰባ ያደርጋሉ፤ እዚያ ላይ መጠመቅ ይኖርብሻል።” ያን ዕለት ሌሊት የተማርኩትን ሳወጣና ሳወርድ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር አደርኩ። ጥምቀት ከባድ እርምጃ እንደሆነ ይሰማኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አምላክን ማገልገል እፈልጋለሁ! የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴ ውስን ቢሆንም ጥቅምት 15, 1943 በ16 ዓመቴ ተጠመቅሁ።
ከአንዱ የአገሪቱ ጫፍ ወደ ሌላኛው መጓዝ
በኅዳር ወር ወንድሜ ፍሬድ በቤት ሠራተኝነት እንዳገለግለው ጠየቀኝ። ፍሬድ የሚኖረው በምሥራቅ ካናዳ ቶሮንቶ በሚባል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንጻ ውስጥ ነበር። ወደዚያ መሄዴ ይሖዋን ለማገልገል የበለጠ ነፃነት እንደሚሰጠኝ ስለተሰማኝ ለመሄድ ተስማማሁ። ከመሄዴ በፊት በሳስካቺዋ አካባቢ የምትኖረውን አን የምትባለውን እህቴን ልጠይቃት ሄድኩ። አን እሷና ሌላዋ እህቴ ዶሪስ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደጀመሩ ነገረችኝ፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነገር ነበር። እንዲያውም እኔም እንደነሱ ማጥናት እንዳለብኝ ልታግባባኝ ሞከረች። በዚህ ጊዜ እኔም የያዝኩትን ምስጢር ማለትም የተጠመቅሁ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ነገርኳት!
እኔና ታናሽ እህቴ ኤመሊ ረጅም የባቡር ጉዞ በማድረግ ወደ ቶሮንቶ ሄድን። ቢል ከባቡር ጣቢያው ተቀብሎን ከፍሬድ እና ከጆን ጋር በጋራ ወደሚኖሩበት ቤት ወሰደን። በዚህ ጊዜ፣ ሌላ አብሯቸው የሚኖር ሰው እንዳለ ፍሬድን ጠየቅሁት። እሱም “መቼም በጣም እንደምትገረሚ ጥርጥር የለውም፤ አገር ቤት አብሮን የነበረውን አሌክስ ሪድን ታስታውሽዋለሽ? እሱም በላይኛው ፎቅ ላይ ይኖራል፤ ምን እንደነካው እንጃ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለማወቅ ይፈልጋል!” አለኝ። በዚህ ጊዜ ልቤ በደስታ ዘለለ።
አሌክስን ለማግኘት በቀስታ ወደ ላይኛው ፎቅ ወጣሁና በዚያው ምሽት አብረን ስብሰባ ለመሄድ ሁኔታዎችን አመቻቸን። ጊዜ ሳላጠፋ በስብሰባ ላይ መገኘት የፈለግሁት ወንድሞቼ በእምነቴ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚያስችል ጊዜ እንዳያገኙ ስል ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ ምንም እንኳ መደበኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይደረግልኝም ለመጀመሪያ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ለመካፈል አገልግሎት ወጣሁ። በልጅነቴ የተማርኩትን ቋንቋ በመጠቀም ብዙ ዩክሬናውያንን በማነጋገሬ ተደሰትኩ።
ቢል መጠበቂያ ግንብ ማንበብ ስለሚያስደስተው ብዙ ጊዜ መጽሔቶችን ክፍሉ አስቀምጥለት ነበር። በምዕራብ ካናዳ ወደምትገኘው ወደ ብሪትሽ ኮሎምቢያ ከሄደ በኋላ የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት በመግባት ስጦታ ላክሁለት። ምንም እንኳ ዝምተኛ ቢሆንም አመስጋኝነቱን ለመግለጽ አሥር ገጽ ደብዳቤ ጻፈልኝ። ከጊዜ በኋላ ሕይወቱን ለአምላክ በመወሰን ቀናተኛ የበላይ ተመልካች ሆኗል። በጣም ደስ የሚለው፣ አምስቱ ወንድሞቼና እህቶቼ ማለትም ቢል፣ አን፣ ፍሬድ፣ ዶሪስ እና ኤመሊ ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አምላኪዎች ሆነዋል!
ግንቦት 22, 1945 የካናዳ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ አነሳ። * እንደ እውነቱ ከሆነ ማስታወቂያውን እስከሰማሁበት ጊዜ ድረስ በእገዳ ሥር መሆናችንን አላውቅም ነበር። እኔና ጓደኛዬ ጁዲ ሉከስ አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል በስተ ምሥራቅ ርቃ ወደምትገኘውና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ወደሚነገርባት ወደ ኩቤክ ለመሄድ ወሰንን። ዶሪስና ኤመሊ የተባሉት እህቶቼ ስለ እቅዳችን ሲሰሙ እነሱም በብሪትሽ ኮሎምቢያ፣ ቫንኮቨር ማለትም ወደሌላኛው የአህጉሩ ክፍል ሄደው በአቅኚነት ለማገልገል ወሰኑ።
በኩቤክ የነበረው ሃይማኖታዊ ተቃውሞ
ወደ ኩቤክ ስሄድ የተቀየረብኝ አካባቢው ብቻ አልነበረም። በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በስብከቱ ሥራቸው ላይ ጠንካራ ተቃውሞ ይገጥማቸው ነበር። * ኩቤክ ለአምላክ፣ ለክርስቶስና ለነፃነት ያላት የመረረ ጥላቻ መላውን ካናዳ የሚያሳፍር ነው (እንግሊዝኛ) የተባለ ትራክት በማሰራጨቱ ዘመቻ ላይ በመካፈላችን ተደስተን ነበር። ኃይለኛ መልእክት የያዘው ይህ ትራክት የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው አጋልጧል።
ለ16 ቀናት ያለማቋረጥ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እየተነሳን ድምፅ ሳናሰማ በየሰዉ በር ሥር ትራክቶችን እንከት ነበር። አንድ አፓርታማ ውስጥ እንዲህ እያደረግን ሳለን ፖሊሶች ሊይዙን እየመጡ እንደሆነ ሰማን። በሕንፃዎቹ መካከል ባለ ጠባብ መተላለፊያ ውስጥ በመደበቅ አመለጥን። በሚቀጥለው ቀን ከመንገድ ወደ መንገድ በመሄድ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችን ማበርከታችንን ቀጠልን። ወራት እያለፉ ሲሄዱ፣ መቁጠር እስኪያቅተን ድረስ ለበርካታ ጊዜያት ታስረናል፤ እንዲያውም ልታሰር እንደምችል ስለሚሰማኝ ሁልጊዜ የጥርስ ብሩሼንና የእርሳስ ኩሌን እይዝ ነበር።
ኅዳር 1946 ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት ይመራ የነበረው ናታን ኖር ከብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በመምጣት ጎበኘን። በኩቤክ እናገለግል የነበርነውን 64 አቅኚዎች በሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል ውስጥ ገብተን እንድንማር ግብዣ አቀረበልን። በዚህ ትምህርት ቤት ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለአምስት ወር ተከታትለናል። ነሐሴ 1947 ከተመረቅን በኋላ አዳዲስ ጉባኤዎችን እንድናቋቁም ኩቤክ ወደሚገኙት ከተሞች በሙሉ ተላክን።
አርኪ አገልግሎት
ወጣት ከነበርነው ሴቶች አራታችን ሼርብሩክ ወደተባለ ከተማ ተላክን። ፈረንሳይኛ ቋንቋ ለመናገር ስንል ወደ አገልግሎት ክልላችን በገባንና በወጣን ቁጥር ቃላቶችን ደግመን ደጋግመን በመጥራት ጠንክረን ተለማመድን። አንዳንድ ጊዜ ምሳ ሰዓት ላይ ምግብ ለመግዛት ገንዘብ ስለማይኖረን ወደቤት በመሄድ ቋንቋውን እናጠናለን። የአገልግሎት ጓደኛዬ ኬይ ሊንድሆርስት ጥሩ የሰዋስው እውቀት ነበራት። የፈረንሳይኛን ሰዋስው በደንብ መረዳት እንድችል በመጀመሪያ የእንግሊዝኛን ሰዋስው አስተማረችኝ።
በወቅቱ 15,000 ገደማ ነዋሪዎች ባሉባት ቪክቶሪያቪሌ በምትባለው ከተማ በአቅኚነት ያሳለፍኩትን ጊዜ ከሁሉም በላይ ጉልህ ሥፍራ እሰጠዋለሁ። ከጥቂት ሰዎች በስተቀር እንግሊዝኛ የሚናገር ሰው አለመኖሩ ፈረንሳይኛችንን ለማሻሻል ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮልናል። እዚያ በሄድን በመጀመሪያው ሳምንት የገጠመን ነገር አስደናቂ ነበር፤ በሄድንበት ሁሉ ሰዎች ጽሑፎቻችንን ተቀበሉን። በሌላ ጊዜ ተመልሰን ስንሄድ ግን በሮቹ በሙሉ የተዘጉ ከመሆኑም በላይ የመስኮቶቹም መጋረጃዎች ተጋርደዋል። በዚህ ጊዜ ምን ተፈጥሮ ይሆን ብለን አሰብን።
ይህ የሆነው የአካባቢው ቄስ ሕዝቡ እኛን እንዳይሰሙ አስጠንቅቋቸው ስለነበረ ነው። በመሆኑም ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ ልጆች በቅርብ ርቀት እየተከተሉን ድንጋይና በረዶ
ወረወሩብን። ያም ሆኖ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የመስማት ፍላጎት ነበራቸው። መጀመሪያ ላይ፣ እነዚህ ሰዎች ምሽት ላይ ብቻ እንድንመጣ ይፈልጉ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው እያደገ ሲመጣ ግን ምንም እንኳ ጎረቤቶቻቸው ባይደሰቱም በይፋ ማጥናት ጀመሩ።በ1950ዎቹ ዓመታት እኔና እህቶቼ ለእረፍት ወደ ዋካ ተመለስን። በአንድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ የአገልግሎት ተሞክሯችንን ተናገርን። የጉባኤው ሽማግሌ፣ “እናታችሁ ከሞት በምትነሳበት ጊዜ ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑላት ስታውቅ በጣም ትደሰታለች!” አለን። ከመሞቷ በፊት ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ እንደነበር ነገረን። ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት የነበራት መሆኑን ስናውቅ ዓይናችን እንባ አቀረረ፤ በአጭር ባትቀጭ ኖሮ ያገኘችውን እውነት ለእኛም ታካፍል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም።
ትዳር መሥርቶ በአንድነት ማገልገል
በ1956፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ ታስሮ ከነበረ ሜርተን ካምቤል ከተባለ የይሖዋ ምሥክር ጋር ተዋወቅሁ። ብሩክሊን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አሥር ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሲያገለግል ቆይቷል። ሜርተን ብዙ ግሩም የሆኑ መንፈሳዊ ባሕርያት ስላሉት ጥሩ ባል ይሆነኛል ብዬ አሰብኩ። ለተወሰኑ ወራት በደብዳቤ ስንገናኝ ቆየን። እንከባበርና እንቀራረብ ስለነበር ተዋደድን።
በመሆኑም መስከረም 24, 1960 ከሜርተን ጋር ተጋባን። ያለፉትን 47 ዓመታት ግሩም ከሆነ መንፈሳዊ ሰው ጋር ማሳለፍ መቻሌ እንዴት ያለ በረከት ነው! ሜርተን፣ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ ጉባኤዎች ድጋፍና መመሪያ በሚሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ለ58 ዓመታት ሠርቷል። ብሩክሊን ቤቴል በቆየሁባቸው ጊዜያት ከ30 ዓመታት በላይ ሥራዬ መጀመሪያ ላይ የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎችን ከጊዜ በኋላ ደግሞ በኒው ዮርክ ከተማና በአካባቢው የሚገኙትን ትላልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ማስዋብ ነበር። ከዚያም በ1995 እኔና ሜርተን ከኒው ዮርክ ከተማ በስተ ሰሜን 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ፓተርሰን የትምህርት ማዕከል ተዛወርን።
በ12 ዓመቴ ከቤት ስወጣ አንድ ቀን የሥጋ ወንድሞቼንና እህቶቼን ጨምሮ የአንድ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል እሆናለሁ ብዬ ጨርሶ አላሰብኩም ነበር። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ፣ በእናታችን ዙሪያ ተሰብስበን አንቀላፍታ በነበረችባቸው ዓመታት ምን ነገሮች እንደተከናወኑ በተለይ ደግሞ ይሖዋ አምላክ የልጆቿን መንፈሳዊ ፍላጎት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በማሟላት እንዴት እንደተንከባከበላት የምናጫውታትን ጊዜ እናፍቃለሁ። ይሖዋ “በጽድቅ መንገድ” ስለመራን ምንኛ ደስተኞች ነን!—መዝሙር 23:3
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.21 የይሖዋ ምሥክሮች በነበራቸው የገለልተኝነት አቋም ምክንያት መንግሥት በሐምሌ 4, 1940 ድርጅታቸውን አግዶት ነበር።
^ አን.23 በኩቤክ ስለነበረው ሃይማኖታዊ ስደት የበለጠ ለማወቅ የሚያዝያ 22, 2000 ንቁ! መጽሔት (እንግሊዝኛ) ገጽ 20-23ን ተመልከት።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆቼ እንዲሁም ከሰባቱ ወንድሞቼና እህቶቼ ጋር ያደግንበት ቤት
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1952 ኦታዋ ውስጥ ከአገልግሎት ጓደኞቼ ጋር
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር (ከግራ ወደ ቀኝ):- አን፣ ሜሪ፣ ፍሬድ፣ ዶሪስ፣ ጆን፣ እኔ፣ ቢል እና ኤመሊ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሜርተን ጋር በአሁኑ ጊዜ