“እንዲህ ያለ ፍቅር አግኝቼ አላውቅም”
ከዶሚኒካን ሪፑብሊክ የተላከ ደብዳቤ
“እንዲህ ያለ ፍቅር አግኝቼ አላውቅም”
ኒዩርካ በዚህ ሳምንት በጉባኤያችን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት አቀረበች። ትምህርቱን የተዘጋጀችው፣ የምትናገረውን ነገር በብሬይል ከጻፈች በኋላ ሐሳቡን በቃሏ በመያዝ ነበር። እኔም፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመማር ፍላጎት ያለው ሰው ሆኜ ከእሷ ጋር ለመወያየት መድረኩ ላይ አብሬአት ነበርኩ። እኔ በማይክሮፎን ስናገር እሷ ደግሞ በጆሮዋ ላይ ባደረገችው የማዳመጫ መሣሪያ ተጠቅማ ትሰማኝ ነበር። ውይይታችንን ስንደመድም እዚያ የነበሩት በአድናቆት የተሞሉት አድማጮች እሷ እስክትሰማው ድረስ አጨበጨቡ። ፈገግታዋ ከፍተኛ ደስታና እርካታ እንደተሰማት ያሳይ ነበር። እኔም በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። ሚስዮናዊ ሆኖ ማገልገል እንዴት አስደሳች ነው!
ከኒዩርካ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበትን ወቅት አስታውሳለሁ። ይህ የሆነው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር። አቧራማ በሆኑት የገጠር መንገዶች ላይ ለግማሽ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ኒዩርካን በአንድ አነስተኛ ቤት በረንዳ ላይ ተቀምጣ አየኋት። ቤቱ ከእንጨትና ከብሎኬት የተሠራ ሲሆን ጣሪያውም ዝጓል። በአካባቢው የፍየሎች፣ የጥንቸሎችና የውሾች ድምፅ የሚሰማ ከመሆኑም በላይ አካባቢው የእነዚህ እንስሳት ጠረን አለው። ኒዩርካ ብቸኛ እንደሆነችና እንደተጨነቀች በሚያሳይ መንገድ አንገቷን አቀርቅራ ተቀምጣለች። ከመጎሳቆሏ የተነሳ ስትታይ የ34 ዓመት ሴት አትመስልም ነበር።
ትከሻዋን በቀስታ መታ መታ አደረግኳት፤ እሷም ቀና ብላ ከ11 ዓመት በፊት በታወሩት ዓይኖቿ ወደ እኛ ተመለከተች። ወደ ጆሮዋ ተጠግቼ ጮክ ብዬ በመናገር የእኔንና የአገልግሎት ጓደኛዬን ስም አስተዋወቅኳት። ከጊዜ በኋላ፣ ኒዩርካ ማርፋን ሲንድሮም በሚባል በዘር የሚተላለፍ በሽታ ምክንያት ትሠቃይ እንደነበር ተገነዘብን። በተጨማሪም ኒዩርካ ባለባት ከባድ የስኳር በሽታ ምክንያት በሰውነቷ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ሳይታሰብ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ስለሚችል የማያቋርጥ ክትትል ያስፈልጋት ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ስሰጣት ምን መሆኑን ወዲያውኑ ያወቀች ሲሆን የማየት ችሎታዋን ከማጣቷ በፊት ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብ ያስደስታት እንደነበር ነገረችን። ታዲያ ለዚህች ብቸኛ፣ ትሑትና ምስኪን ሴት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መንፈስ የሚያድስ እውነት ላካፍላት የምችለው እንዴት ነው? ኒዩርካ ፊደል ታውቅ ስለነበር ከፕላስቲክ የተሠሩ ፊደሎችን እጅዋ ላይ አደርግላት ጀመር። ብዙም ሳይቆይ ፊደሎቹን መለየት ቻለች። ከዚያም በእጆቼ የማሳያትን ምልክቶች በመዳሰስ እያንዳንዱ ፊደል በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በምን ዓይነት ምልክት እንደሚወከል ማወቅ ቻለች። ቀስ በቀስም ሌሎች ምልክቶችን ተማረች። እኔም ራሴ የምልክት ቋንቋ መማር የጀመርኩት በቅርቡ ስለነበር ከእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ በፊት ትምህርቱን ለረጅም ሰዓት መዘጋጀት ነበረብኝ። ይሁን እንጂ እኔም ሆንኩ እሷ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረን የምልክት ቋንቋ ችሎታችን በፍጥነት ተሻሻለ።
ኒዩርካ አንድ በጎ አድራጊ ድርጅት የማዳመጫ መሣሪያ በእርዳታ ሲሰጣት ከፍተኛ እድገት አደረገች። የተሰጣት መሣሪያ ዘመናዊ ባይሆንም ከፍተኛ እርዳታ አበርክቶላታል። ኒዩርካ የማየት ችሎታዋን ካጣችና የመስማት ችግር ከገጠማት ከአሥር ዓመት በላይ ስለሆናት ብቸኝነት ይሰማት ነበር። ይሁንና የይሖዋ መንፈስ አእምሮዋንና ልቧን በእውቀት፣ በተስፋና በፍቅር ስለሞላው መንፈሷ ተነቃቃ። ከዚያም ብዙም ሳትቆይ ኒዩርካ ማየት የተሳናቸው ሰዎች የሚይዙትን ዘንግ በመጠቀም ወደ ጎረቤቶቿ እየሄደች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ታካፍላቸው ጀመር።
ኒዩርካ አክስቷንና ሁለት ዘመዶቿን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናለች። እያንዳንዱን ትምህርት ለማስታወስ እንድትችል በደንብ ትዘጋጃለች። መጽሐፍ ቅዱስን የምታስጠናቸው ሰዎች አንቀጹን ሲያነቡላት እሷ ደግሞ በብሬይል ከተዘጋጀው መጽሐፏ ላይ ጥያቄውን ታነባለች። አብሯት የሚያስጠናው ሰው ደግሞ ተማሪዎቹ የሰጡትን መልስ ወደ ጆሮዋ ጠጋ በማለት ጮክ ብሎ ይነግራት አሊያም በምልክት ቋንቋ ያስረዳት ነበር።
በጉባኤ ውስጥ ያሉት ሁሉ ኒዩርካን ይረዷታል እንዲሁም ያበረታቷታል። በርካታ ክርስቲያን ወንድሞቿ ወደ ጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች ይዘዋት ይሄዳሉ። ሌሎች ደግሞ አብረዋት ያገለግላሉ። በቅርቡ ኒዩርካ “እንዲህ ያለ ፍቅር አግኝቼ አላውቅም” በማለት ነግራኛለች። በሚቀጥለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመጠመቅ ታስባለች።
በአንድ ወቅት ኒዩርካ ወደምትኖርበት አካባቢ ስንሄድ በረንዳ ላይ ተቀምጣ አንገቷን ቀና አድርጋ ፀሐይ ስትሞቅ አገኘናት፤ በፊቷ ላይ ፈገግታ ይነበባል። ፈገግ ያሰኛት ምን እንደሆነ ስጠይቃት “ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ስለሚኖረው ሁኔታ እያሰብኩ ነው። እኔም በዚያ እንዳለሁ ያህል ተሰምቶኝ ነበር” በማለት ነገረችኝ።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኒዩርካና አንዳንድ የጉባኤያችን አባላት ከመንግሥት አዳራሻችን ፊት ለፊት
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኒዩርካ የተማረቻቸውን ነገሮች ለሌሎች ታካፍላለች