ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች
ከአፍሪካ የተገኙ ተሞክሮዎች
አገሮች 57
የሕዝብ ብዛት 827,387,930
አስፋፊዎች 1,086,653
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች 2,027,124
ኮት ዲቩዋር በአገሪቱ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው የቢኑዋን መንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለእውነት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። አንዳንዶች ወደ እርሻቸው ከመሄዳቸው በፊት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ከጠዋቱ 12:00 ላይ አስፋፊዎቹን ከእንቅልፋቸው ይቀሰቅሷቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከጉባኤ ስብሰባዎች በኋላ ምሽት ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኗቸው ይጠይቃሉ። ማንበብ የማትችል አንዲት ሴት፣ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እንዲሰጣት አንድን ወንድም የጠየቀችው ሲሆን መጽሐፉን ባለቤቷ እንደሚያነብላት ነገረችው። ወንድም መጽሐፉን የሰጣት ከመሆኑም በላይ በሚቀጥለው ቀን ሊጠይቃት ቤቷ ሄደ። ይህች ሴትና ባለቤቷ፣ ወንድምን በትዕግሥት እየጠበቁት ነበር። እሷና ባለቤቷ ሌሊቱን ሙሉ መጽሐፉን ሲያነቡ ስላደሩ ባለቤቷ ወደ እርሻ አልሄደም። ስላነበበው ነገር ከወንድም ጋር ለመወያየት ፈልጎ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል።
ቤኒን በአንድ ገለልተኛ አካባቢ የሚኖር አንድ ትልቅ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። አባትየው ባሕላዊ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቄስ ነበር። ጥናት በጀመሩ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። ቅዳሜ ምሽት ላይ የበኩር ልጃቸው በድንገት ትታመምና ትሞታለች። አባትየው በልጁ አሟሟት ቢያዝንም በእሁዱ ፕሮግራም ላይ ተገኘ። ሰኞ ዕለት ስለ ልጁ ሞት ሲናገር “ሰይጣን እኛን ተስፋ ለማስቆረጥ ያደረገው ነገር ነው፤ ቤተሰቤ ግን ተስፋ አይቆርጥም” ብሏል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይጠቀምባቸው የነበሩትን ነገሮች በሙሉ ማለትም የቅስና ልብሱን፣ ቆቡን፣ ቀበቶውን፣ ቅብዓ ክህነቱንና በትሩን ሰብስቦ አወጣ። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ትሠራ የነበረችው ሚስቱም ተመሳሳይ ነገር አደረገች። ቄስ የነበረው ይህ ሰው “ከዚህ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረንን ግንኙነት አቁመናል” በማለት ተናገረ። ከዚያም ልክ በሐዋርያት ሥራ 19:19 ላይ እንዳለው በሕዝብ ፊት ዕቃዎቻቸውን ሁሉ አቃጠለ። አሁን ይህ ቤተሰብ ጥሩ እድገት እያደረገ ነው።
ማዳጋስካር በ2006፣ አምስት መቶ ነዋሪዎች ባሉበት መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ሰባኪ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ የሌላ መንደር ነዋሪ ከሆነች የይሖዋ ምሥክር አገኘ። ይህ ሰባኪ መጽሐፉን በደንብ ካነበበው በኋላ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ በመሆን ያወቀውን ነገር ለቤተ ክርስቲያኑ አባላት ማካፈል ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ እሱ፣ ቤተሰቡና 20 የሚያህሉ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቀው የወጡ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት መሰብሰብ ጀመሩ። ልዩ አቅኚዎችም እነሱን ለመርዳት ወደዚህ አካባቢ መጡ። አቅኚዎቹ ፍላጎት ካላቸው ብዙ ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩ ሲሆን የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በቋሚነት እንዲካሄድ ዝግጅት አደረጉ። በጥቅምት ወር አምስት ሰዎች ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ከመሆናቸውም ሌላ በአሁኑ ወቅት አቅኚዎቹ የሕዝብ ስብሰባና የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት አድርገዋል። በአማካይ 40 የሚያህሉ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ20 በላይ የሚሆኑ ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስ እያጠኑ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ሄኒ እና ባለቤቱ ከቤት ወደ ቤት እያገለገሉ እያለ በአንድ ቤት አጠገብ ሲያልፉ አንድ ኃይለኛ ውሻ በአጥሩ መሃል ጭንቅላቱን አሾልኮ የሄኒን እጅ ነከሰው። ደሙ ሊያቆም ስላልቻለ በፍጥነት ወደ ቤት ሄዱና ባለቤቱ ቁስሉን ጠራርጋ አሰረችለት። ሄኒም በኋላ ላይ ሐኪም ቤት ለመሄድ ቀጠሮ አስያዘ። ውሻ አገልግሎቱን እንዲያስቆመው እንደማይፈልግ ለባለቤቱ ነገራት፤ ከአንድ ሰዓት በኋላ ወደ ክልሉ ተመልሰው በመሄድ ኃይለኛ ውሻ ከነበረበት ቤት ቀጥሎ ያሉትን ቤቶች ማንኳኳት ጀመሩ። ጥቂት ቤቶችን ካንኳኩ በኋላ አንድ ሰው ቤቱ እንዲገቡ ጋበዛቸው። ሰውየው በጥሞና ያዳመጣቸው ከመሆኑም በላይ ሌላ ጊዜም እንዲመጡ ጠየቃቸው። ከዚያም ሰውየው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በስብሰባዎች
ላይ ዘወትር ይገኝ ጀመር። ከነበረበት የደች የተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ሲለቅ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ለረጅም ዓመት የቆየ አንድ ሰው ሊጠይቀው የመጣ ሲሆን ዲያቆን እንዲሆንም ግብዣ አቀረበለት። ሰውየው ግን ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቆ ለመውጣት በነበረው አቋም ጸና። ጥሩ እድገት እያደረገ ሲሆን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ለማቅረብም ተመዝግቧል።ታንዛኒያ በጥቅምት 2005 በገለልተኛ አካባቢዎች በሚገኙ ክልሎች ለማገልገል በተካሄደው ዘመቻ ወቅት የኢሪንጋ ጉባኤ አባላት የሆኑ ዘጠኝ ወንድሞች፣ 75 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ፓዋጋ የተባለ መንደር ሄደው ነበር። በዚህ ገለልተኛ አካባቢ የሚኖር አንድ አስፋፊ እንዳለ ሰምተው ስለነበር እሱን ለማግኘት ፍለጋ ጀመሩ። ብዙ ሰዎችን ካጠያየቁ በኋላ ወንድምን አገኙት፤ ይህ ወንድም በዚህ አካባቢ ከ20 ዓመት በላይ እንደኖረና በታንዛኒያ የመንግሥቱ ሥራ አሁንም በእገዳ ሥር እንዳለ ያስብ እንደነበር ነገራቸው። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ለሌሎች ይመሰክር እንደነበርና የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከልብ የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉም ገለጸላቸው። የኢሪንጋ ጉባኤ ወንድሞች፣ በፓዋጋ ያሉትን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለመርዳት በሚሄዱበት ጊዜ ሁሉ ለሁለት ሳምንት ለመቆየት ፈቃደኞች መሆናቸውን ገለጹ። በ2006፣ ሁለት የዘወትር አቅኚዎች በዚህ ፍሬያማ ክልል እንዲያገለግሉ ተላኩ። በዚያ የነበረውን ወንድም በመንፈሳዊ የረዱት ሲሆን በፓዋጋ የተቋቋመው አነስተኛ ቡድንም ዘጠኝ አስፋፊዎች አሉት። በአሁኑ ጊዜ ስብሰባቸውን የሚያደርጉት በዛፍ ሥር ቢሆንም በአካባቢው በሚገኝ የግንባታ ቁሳቁስ ተጠቅመው አነስተኛ የመሰብሰቢያ ቦታ ለመሥራት ዝግጅት ላይ ናቸው።
ሩዋንዳ ጄንቲሌ የተባለች አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጅ፣ እግር ኳስ ስትጫወት ግብ በማግባት ችሎታዋ የታወቀች ነበረች። የአካባቢዋ ሰዎች ሜናዪቢቴጎ ብለው የሚጠሯት ሲሆን በኪንያሩዋንዳ ቋንቋ “የግቦች አምላክ” ማለት ነው። አንዳንድ ጣሊያናውያን ችሎታዋን ሲመለከቱ ተጨማሪ ሥልጠና ሰጧት። ከዚያም ጣሊያን ሄዳ እግር ኳስ እንድትጫወት ጋበዟት። ወደ አውሮፓ መሄድ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች የመሆን አጋጣሚ ማግኘት ያጓጓል። ይሁን እንጂ ጄንቲሌ ይህንን ግብዣ ከተቀበለች ቤተሰቧን ትታ መሄድ እንዳለባት አወቀች። እናቷ የይሖዋ ምሥክር ስትሆን ጄንቲሌም መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታለች፤ ሆኖም የተማረችውን ነገር በቁም ነገር አትመለከተውም ነበር። በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው ለእግር ኳስ ነበር። ጄንቲሌ በጉዳዩ ላይ ከእናቷ ጋር ከተወያየች በኋላ ግብዣውን መቀበሏ በመንፈሳዊ ሁኔታ ለአደጋ እንደሚያጋልጣት ተገነዘበች። በመሆኑም ግብዣውን ላለመቀበልና ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች በሕይወቷ ውስጥ ቅድሚያ ለመስጠት ወሰነች። ጄንቲሌ በቅርብ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠምቃለች።