በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ልጅ መሆን

የአምላክ ልጅ መሆን

የአምላክ ልጅ መሆን

የኮሪያ ጦርነት ከተካሄደ ከ30 ዓመታት በኋላ፣ የኮሪያ የዜና ማሠራጫ በጦርነቱ ሳቢያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተለያዩ ሰዎችን ለማገናኘት የሚረዳ አንድ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። በውጤቱም ከ11,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከሚወዷቸው የቤተሰቦቻቸው አባላት ጋር የተገናኙ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከደስታቸው የተነሳ ተቃቅፈው ተላቅሰዋል። ዘ ኮሪያ ታይምስ የተባለ ጋዜጣ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል:- “የኮሪያ ሕዝብ ደስታውን በአንድ ላይ በእንባ . . . የገለጸበት እንዲህ ያለ ጊዜ በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም።”

በብራዚል፣ ሴዛር የተባለ ሕፃን ልጅ ዕዳ ለመክፈል ሲባል ለሌላ ሰው ተሰጥቶ ነበር። ሴዛር፣ ከአሥር ዓመታት ገደማ በኋላ ወላጅ እናቱን ሲያገኝ በጣም በመደሰቱ ሀብታም የነበሩትን አሳዳጊ ወላጆቹን ትቶ ከእናቱ ጋር መኖር ጀመረ።

የቤተሰብ አባላት ከተለያዩና ከተጠፋፉ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደገና ሲገናኙ በጣም ይደሰታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሰው ልጆች ከአምላክ ቤተሰብ ጋር በሚያሳዝን ሁኔታ እንዴት እንደተለያዩ ይገልጽልናል። ከዚህም በላይ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ከዚህ ቤተሰብ ጋር በሚያስደስት ሁኔታ እንዴት እየተገናኙ እንዳሉ ይነግረናል። ይህ የሆነው እንዴት ነው? አንተስ የዚህ ቤተሰብ አባል በመሆን የሚገኘውን ደስታ መቅመስ የምትችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ቤተሰብ የተለያየው እንዴት ነበር?

መዝሙራዊው፣ ፈጣሪ ስለሆነው ስለ ይሖዋ አምላክ ሲናገር ‘የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ እንደሆነ’ ገልጿል። (መዝሙር 36:9) ይሖዋ፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ታማኝ ፍጥረታት ያቀፈ ሰፊ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰብ አባት ነው። ይህ ቤተሰብ፣ በሰማይ መንፈሳዊ ልጆቹ የሆኑትን መላእክትንና በምድር ደግሞ ምድራዊ ልጆቹ የሚሆኑትን የሰው ልጆችን ያቀፈ ነው።

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው የመጀመሪያው የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ የሆነው አዳም ባመጸበት ጊዜ የሰው ዘር፣ ከአፍቃሪ አባቱና ከፈጣሪው ጋር በሚያሳዝን ሁኔታ ተለያየ። (ሉቃስ 3:38) አዳም በማመጹ ምክንያት የአምላክ ልጅ የመሆንን መብት ያጣ ከመሆኑም በላይ ገና ያልተወለዱት ዘሮቹም ይህንን መብት እንዲያጡ አደረጋቸው። አምላክ፣ ይህ ሁኔታ ያስከተለውን ውጤት በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ሲገልጽ “በእርሱ ላይ ክፋት ፈጽመዋል፤ ከነውራቸው የተነሣ ከእንግዲህ [የአምላክ ልጆች] አይደሉም” ብሏል። “ነውራቸው” ወይም ኃጢአታቸው፣ ቅዱስና በሁሉም መንገድ ፍጹም ከሆነው አምላክ ጋር አለያይቷቸዋል። (ዘዳግም 32:4, 5፤ ኢሳይያስ 6:3) በመሆኑም የሰው ዘር አባት እንደሌለውና እንደጠፋ ያህል ሆኖ ነበር።—ኤፌሶን 2:12

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአምላክ ቤተሰብ ውጪ ያሉትን ሰዎች “ጠላቶች” ብሎ በመጥራት የሰው ዘር ከአምላክ ምን ያህል እንደራቀ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። (ሮሜ 5:8, 10) ከአምላክ የተለዩት የሰው ልጆች በጨካኙ የሰይጣን አገዛዝ ሥር በመሆናቸው ከመሠቃየታቸውም በላይ የወረሱት ኃጢአትና አለፍጽምና ሞት እያስከተለባቸው ነው። (ሮሜ 5:12፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ታዲያ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የአምላክ ቤተሰብ አባል መሆን ይችላሉ? ፍጽምና የጎደላቸው ፍጡራን ሙሉ በሙሉ የአምላክ ልጆች መሆን ማለትም አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት የነበሩበት ደረጃ ላይ መድረስ ይችላሉ?

ከአምላክ የተለዩትን ልጆች መሰብሰብ

ይሖዋ እሱን ለሚወዱት ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ጥቅም ሲል በፍቅር ተነሳስቶ አንዳንድ ዝግጅቶችን አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 2:9) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 5:19) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ አምላክ፣ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለኃጢአታችን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ሐዋርያው ዮሐንስ ለዚህ ዝግጅት ያለውን አድናቆት ሲገልጽ እንደሚከተለው ብሏል:- “የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው!” (1 ዮሐንስ 3:1) በመሆኑም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች እንደገና የይሖዋ ቤተሰብ አባል የመሆን አጋጣሚ ተዘርግቶላቸዋል።

በአምላክ ቤተሰብ ውስጥ የሚሰበሰቡ የሰው ልጆች በሙሉ በሰማይ በሚገኘው አባታቸው እንክብካቤ ሥር በመሆን ግሩም አንድነት ይኖራቸዋል፤ ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች በሁለት ቡድኖች እየተሰበሰቡ መሆኑን ገልጿል። የሚከተለውን ጥቅስ ልብ በል:- “በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው [የአምላክ ሐሳብ] በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌሶን 1:9, 10) አምላክ ነገሮችን በዚህ መንገድ የሚያከናውነው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ልጆቹን በሁለት ቡድን የለያቸው ቢሆንም እንዲህ ማድረጉ ለቤተሰቡ አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። የዚህንም ምክንያት መረዳት አስቸጋሪ አይደለም። የአምላክ ቤተሰብ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከአንድ ብሔር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በየትኛውም ብሔር ውስጥ ሕዝቦች ሰላም አግኝተው፣ ሥርዓት በሰፈነበትና ሕግ በሚከበርበት ሁኔታ እንዲኖሩ የሚያስተዳድሯቸው ጥቂት ሰዎች ይመረጣሉ። እርግጥ ነው፣ የትኛውም ሰብዓዊ መንግሥት እውነተኛ ሰላም ሊያመጣ አልቻለም፤ ይሁን እንጂ አምላክ ለቤተሰቡ ፍጹም የሆነ መንግሥት አዘጋጅቷል። የመጀመሪያው ቡድን ማለትም ‘በሰማይ ያሉት ነገሮች’ ይሖዋ በሰማይ መስተዳድር ወይም መንግሥት ለማቋቋም የመረጣቸውን የአምላክ ልጆች ያቀፈ ነው። እነሱም በሰማይ ሆነው “በምድር ላይ ይነግሣሉ።”—ራእይ 5:10

በምድር ያሉት የአምላክ ልጆች

ይሖዋ “በምድርም ያሉትን ነገሮች” ማለትም በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ምድራዊ ልጆቹ ወደመሆን ደረጃ እንዲደርሱ እየሰበሰባቸው ነው። እንደ አንድ ደግ አባት፣ ፍቅርን ስለሚያስተምራቸው ከተለያየ ብሔር የተውጣጡ ቢሆኑም በአንድነት ተስማምተው እየኖሩ ነው። ዓመጸኞች፣ ራስ ወዳዶች፣ በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ሕይወት የሚመሩ እንዲሁም አምላክን የማይታዘዙ ሰዎች እንኳ ‘ከአምላክ ጋር እንዲታረቁ’ እየተጋበዙ ነው።—2 ቆሮንቶስ 5:20

ከአምላክ ጋር ታርቀው ልጆቹ እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ግብዣ የማይቀበሉ ሰዎችስ ምን ይሆናሉ? ይሖዋ የቤተሰቡን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ ሲል በእነዚህ ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ይወስዳል። ‘ኀጢአተኞች የሚጠፉበት የፍርድ ቀን’ ይመጣል። (2 ጴጥሮስ 3:7) አምላክ ዓመጸኞችን ከምድር ያስወግዳል። ይህ ለሚታዘዙት እንዴት ያለ እፎይታ ያመጣል!—መዝሙር 37:10, 11

ከዚያም የሰው ልጆች ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ለሺህ ዓመት የሚኖሩ ሲሆን በዚህ ጊዜም ለአምላክ ፍቅር ምላሽ የሰጡ ሁሉ አዳም ወደነበረበት የፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። የሞቱት ሰዎች እንኳ ይነሳሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ራእይ 20:6፤ 21:3, 4) በመሆኑም አምላክ፣ ሰው “ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት” እንደሚደርስ የገባውን ቃል ይፈጽማል።—ሮሜ 8:21

በሰማይ ከሚገኘው አባትህ ጋር መገናኘት

ቀደም ብለን የጠቀስናቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኮሪያውያንም ሆኑ ሴዛር ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት እርምጃ መውሰድ ነበረባቸው። በኮሪያ የነበሩት ሰዎች በፕሮግራሙ መታቀፍ የነበረባቸው ሲሆን ሴዛርም አሳዳጊ ወላጆቹን መተው ነበረበት። በተመሳሳይ አንተም በሰማይ ከሚገኘው አባትህ፣ ከይሖዋ አምላክ ጋር ለመታረቅና የቤተሰቡ አባል ለመሆን ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርብህ ይሆናል። ታዲያ ምን እርምጃ መውሰድ ያስፈልግሃል?

አምላክን እንደ አባትህ አድርገህ ለመቅረብ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አለብህ፤ ይህም በእሱና በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ጠንካራ እምነት እንድታሳድር ይረዳሃል። እንዲሁም አምላክ እንድታደርገው የሚነግርህ ነገር ለጥቅምህ እንደሆነ እየተገነዘብክ ትሄዳለህ። እሱ የሚሰጥህን እርማትና ተግሣጽ መቀበልም ይኖርብሃል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል:- “እግዚአብሔር እንደ ልጆቹ ይዞአችኋልና . . . ለመሆኑ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው?”—ዕብራውያን 12:7

እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰድህ አኗኗርህን ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “በአእምሮአችሁ መንፈስ [ታደሱ]፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው [ልብሱ]።” (ኤፌሶን 4:23, 24) በመቀጠልም እንደሚከተለው የሚለውን የሐዋርያው ጴጥሮስን ምክር ተግባራዊ አድርግ:- “ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ።”—1 ጴጥሮስ 1:14

እውነተኛ ቤተሰብህን ማግኘት

ሴዛር፣ ወላጅ እናቱን ሲያገኝ ወንድምና እህት እንዳሉትም ማወቁ በጣም አስደስቶት ነበር። በተመሳሳይም በሰማይ ወደሚገኘው አባትህ ስትቀርብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ይኖሩሃል። ከእነሱ ጋር ወዳጅነት ስትመሠርት እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ከሥጋዊ ዘመዶችህ የበለጠ እንደሚቀርቡህ ይሰማህ ይሆናል።—የሐዋርያት ሥራ 28:14, 15፤ ዕብራውያን 10:24, 25

አንተም፣ ከእውነተኛ አባትህ እንዲሁም ከወንድሞችህና እህቶችህ ጋር የመቀላቀል ግብዣ ቀርቦልሃል። ሴዛርም ሆነ በሺህ የሚቆጠሩ ኮሪያውያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲገናኙ የተሰማቸውን ዓይነት ታላቅ ደስታ ማግኘት ትችላለህ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሴዛር በ19 ዓመቱ ከእናቱ ጋር

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወደ አምላክ ለመቅረብ እርምጃዎችን ውሰድ