በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኢየሱስ ሞት ሊያድንህ የሚችለው እንዴት ነው?

የኢየሱስ ሞት ሊያድንህ የሚችለው እንዴት ነው?

ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ማለትም በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአይሁዳውያን የፋሲካ በዓል ሲከበር አንድ ንጹሕ ሰው የሌሎችን ሕይወት ለማዳን ሲል መሥዋዕት ሆኖ ሞተ። ይህ ሰው ማን ነበር? የናዝሬቱ ኢየሱስ በመባል ይታወቃል። ኢየሱስ ከፈጸመው ታላቅ ድርጊት ጥቅም የሚያገኘው ማን ነው? መላው የሰው ዘር መጠቀም ይችላል። በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ ሕይወት ለማዳን ሲባል የተከፈለውን ይህን መሥዋዕት እንደሚከተለው ሲል በአጭሩ ይገልጸዋል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።”—ዮሐንስ 3:16

ብዙዎች ይህን ጥቅስ የሚያውቁት ቢሆንም ትርጉሙን በሚገባ የሚረዱት ግን ጥቂቶች ናቸው። ብዙ ሰዎች ‘ክርስቶስ ለእኛ መሥዋዕት መሆኑ ለምን አስፈለገ? የአንድ ሰው መሞት የሰውን ዘር ዘላለማዊ ዕጣው ከሆነው ከሞት እንዴት ሊታደገው ይችላል?’ በማለት ይጠይቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች ግልጽና አጥጋቢ መልስ ይሰጣል።

ሞት በሰው ዘር ላይ የነገሠው እንዴት ነው?

አንዳንዶች ‘የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ ለአጭር ጊዜ እንዲኖሩ፣ በመከራ ውስጥ እንዲያልፉ፣ ጥቂት ደስታ እንዲያገኙና እንዲሞቱ ከዚያም ወደ ተሻለ ሥፍራ እንዲሄዱ ነው’ የሚል እምነት አላቸው። እንደ እነሱ አመለካከት ከሆነ ሞት፣ አምላክ ለሰው ልጆች ካለው ዓላማ አንዱ ነው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች የሚሞቱት በሌላ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻል። እንዲህ ይላል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።” (ሮሜ 5:12) ይህ ጥቅስ ሰዎች የሚሞቱት በኃጢአት ምክንያት መሆኑን ያሳያል። ይሁንና የሰውን ዘር ለመከራና ለሞት የዳረገው ኃጢአት ወደ ዓለም እንዲመጣ ምክንያት የሆነው “አንድ ሰው” ማን ነው?

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ በርካታ ሳይንቲስቶች የሰው ልጆች በሙሉ ከአንድ የዘር ግንድ የመጡ ናቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጿል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የዘር ግንድ ወይም “አንድ ሰው” ማን እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። ዘፍጥረት 1:27 እንደሚከተለው ይላል:- “እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በምድር ላይ ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ የላቀ ክብር እንዳላቸው ይገልጻል።

የዘፍጥረት ዘገባ ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ከፈጠረ በኋላ የሰው ልጆች ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጣል። በዚህ ዘገባ ውስጥ አምላክ፣ ሞትን የገለጸው ያለመታዘዝ ውጤት እንደሆነ አድርጎ ብቻ ነው። (ዘፍጥረት 2:16, 17) የአምላክ ፍላጎት ሰዎች ውብ በሆነች ገነት ውስጥ በምድር ላይ ደስተኛና ጤናማ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። ሰዎች የዕድሜ መግፋት በሚያመጣቸው ችግሮች እንዲሠቃዩ ከዚያም እንዲሞቱ ፍላጎቱ አልነበረም። ታዲያ ሞት በሰው ልጆች ላይ ሊነግሥ የቻለው እንዴት ነው?

ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ሕይወት ሰጪያቸው የሆነውን ይሖዋ አምላክን ሆነ ብለው ላለመታዘዝ መምረጣቸውን ይገልጻል። በዚህም ምክንያት አምላክ ቀደም ብሎ የነገራቸው የቅጣት ፍርድ እንዲፈጸምባቸው አደረገ። አምላክ ለአዳም “ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ” አለው። (ዘፍጥረት 3:19) ልክ እንደተናገረውም ታዛዥ ያልሆኑት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከጊዜ በኋላ ሞቱ።

ይሁን እንጂ ይህ ዓመጽ ያስከተለው ውጤት በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ብቻ አላቆመም። የእነሱ አለመታዘዝ ልጆቻቸውም የነበራቸውን ፍጹም ሕይወት የማግኘት ተስፋ አሳጥቷቸዋል። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን እንደሚከተለው ብሎ የባረካቸው ገና ያልተወለዱ ሰዎችን ጭምር ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው:- “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) ከጊዜ በኋላ የሰው ልጆች ምድርን መሙላትና በደስታ ለዘላለም መኖር ይችሉ ነበር። ይሁንና የመጀመሪያው አባታቸው ማለትም “አንድ ሰው” ተብሎ የተጠቀሰው አዳም ለኃጢአት ባርነት ሸጣቸው፤ በመሆኑም ሞት የማይቀር ዕጣቸው ሆነ። የአዳም ዘር የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ” ሲል ጽፏል።—ሮሜ 7:14

አንዳንድ ጊዜ ወሮበሎች በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን እንደሚያበላሹ ሁሉ አዳምም ኃጢአት በመፈጸም የአምላክ ድንቅ የፍጥረት ሥራ የሆነው የሰው ልጆች ሕይወት እንዲበላሽ አድርጓል። የአዳም ልጆች የራሳቸውን ልጆች የወለዱ ሲሆን ልጆቻቸውም እንዲሁ ልጆችን ወለዱ፤ ሕይወት በዚህ መልኩ ቀጠለ። በእያንዳንዱ ትውልድ ሰዎች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ዘር ይተካሉ ከዚያም ይሞታሉ። ይሁንና ሁሉም የሚሞቱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአዳም ልጆች ስለሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በአንድ ሰው መተላለፍ [ምክንያት] ብዙዎች ሞቱ’ ይላል። (ሮሜ 5:15) ሕመም፣ እርጅና፣ መጥፎ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌ እንዲሁም ሞት አዳም ቤተሰቡን መክዳቱ ያስከተላቸው አሳዛኝ ውጤቶች ናቸው። እኛ ደግሞ የዚህ ቤተሰብ አባላት ነን።

ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ራሱን ጨምሮ ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ልጆች ስላሉበት አሳዛኝ ሁኔታና ኃጢአት ካመጣባቸው መዘዝ ጋር ስለሚያደርጉት ተስፋ አስቆራጭ ትግል ገልጿል። ጳውሎስ “እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?” በማለት ገልጿል። ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ አይደለም እንዴ? ታዲያ ጳውሎስን ጨምሮ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለመላቀቅ የሚጓጉ ሰዎችን ማን ሊያድናቸው ይችላል? ጳውሎስ ራሱ ‘በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል [የመዳን ዝግጅት ላደረገልን] አምላክ ምስጋና ይሁን’ በማለት መልሱን ሰጥቷል። (ሮሜ 7:14-25) አዎን፣ ፈጣሪያችን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት መዳን የምንችልበትን ዝግጅት አድርጎልናል።

አምላክ ሰዎችን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ኢየሱስ የሚጫወተው ሚና

ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለሞት ከሚዳርጋቸው የኃጢአት ባርነት ነፃ በማውጣት ረገድ ስለሚጫወተው ሚና ሲገልጽ “የሰው ልጅ . . . ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቶአል” ብሏል። (ማቴዎስ 20:28) የኢየሱስ ሕይወት ቤዛ ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው? የእሱ መሞት ጥቅም የሚያስገኝልንስ እንዴት ነው?

ኢየሱስ የሞተው የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸውን ክፉ መዘዞች ለማስወገድ ነው

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ ‘ምንም ኃጢአት እንዳልሠራና’ “ከኀጢአተኞች የተለየ” እንደሆነ ይገልጻል። ኢየሱስ ሕይወቱን ሙሉ የአምላክን ሕግ በፍጹም ልቡ ታዟል። (ዕብራውያን 4:15፤ 7:26) በመሆኑም፣ ኢየሱስ የሞተው እንደ አዳም ኃጢአት ስላለበትና ታዛዥ ሳይሆን ስለቀረ አይደለም። (ሕዝቅኤል 18:4) ከዚህ ይልቅ አባቱ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመታደግ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ሞት የማይገባው ቢሆንም ለሌሎች መሥዋዕት ሆኗል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ኢየሱስ ‘ነፍሱን ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ’ በፈቃደኝነት መጥቷል። ኢየሱስ ‘ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን በመቅመስ’ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ የማይታወቅ ፍቅር አሳይቷል።—ዕብራውያን 2:9

ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ የሰጠው ሕይወት አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ካጣው ሕይወት ጋር ፍጹም ተመጣጣኝ ነው። የኢየሱስ ሞት ምን ውጤት አስገኝቷል? ይሖዋ የኢየሱስን መሥዋዕት፣ ‘ለሰው ሁሉ እንደተሰጠ ተመጣጣኝ ቤዛ’ አድርጎ ተቀብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:6 NW) በመሆኑም አምላክ የኢየሱስን ሕይወት የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ለመዋጀት ወይም ነፃ ለማውጣት ተጠቅሞበታል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ስላሳየው ስለዚህ ታላቅ የፍቅር መግለጫ በተደጋጋሚ ጊዜ ያወሳል። ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ‘በዋጋ እንደተገዙ’ ነግሯቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 6:20፤ 7:23) ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አምላክ ከሞት የዋጃቸው በወርቅ ወይም በብር ሳይሆን በልጁ ደም እንደሆነ ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 1:18, 19) ይሖዋ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት የሰው ልጆችን ለዘላለም ሞቶ ከመቅረት አድኗቸዋል።

ከክርስቶስ ቤዛ ተጠቃሚ ትሆናለህ?

ሐዋርያው ዮሐንስ የክርስቶስ ቤዛ ያለውን ትልቅ ጥቅም አስመልክቶ ሲጽፍ “[ኢየሱስ ክርስቶስ] የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም” ብሏል። (1 ዮሐንስ 2:2) አዎን፣ ሁሉም የሰው ዘር ከኢየሱስ መሥዋዕት ተጠቃሚ መሆን ይችላል። ይህ ሲባል ግን ማንኛውም ሰው በዋጋ ሊተመን ከማይችለው ከዚህ ግሩም መብት ይጠቀማል ማለት ነው? በፍጹም። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን ሕይወት የማዳን ተግባር አስታውስ። ሕይወት አድን ሠራተኞቹ፣ መውጫ አጥተው መሬት ውስጥ ተቀብረው የነበሩትን ማዕድን ቆፋሪዎች ለማዳን ከሽቦ የተሠራ በርሜል ያሉበት ድረስ ልከውላቸው ነበር። ይሁንና እያንዳንዱ ሠራተኛ ለመዳን ከፈለገ የተላከለት የሽቦ በርሜል ውስጥ መግባት ነበረበት። በተመሳሳይም ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።

አምላክ ሰዎች ምን እርምጃ እንዲወስዱ ይጠብቅባቸዋል? ዮሐንስ 3:36 እንዲህ ይላል:- “በወልድ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት አለው፤ በወልድ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቊጣ በላዩ ይሆናል እንጂ ሕይወትን አያይም።” አምላክ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዲኖረን ይፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ትእዛዛቱን በመፈጸም [ኢየሱስን] ማወቃችንን’ እንድናሳይ ይጠበቅብናል። (1 ዮሐንስ 2:3) በመሆኑም ከኃጢአትና ከሞት ለመዳን በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመንና ትእዛዛቱን መፈጸም እንዳለብን ግልጽ ነው።

በኢየሱስ ቤዛ ላይ እምነት እንዳለን ከምናሳይባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ የሞቱን መታሰቢያ እሱ ባዘዘን መሠረት ማክበር ነው፤ ይህም ለተከፈለልን መሥዋዕት አክብሮት እንዳለን ያሳያል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ሥጋውን የሚወክለውን ቂጣ ለታማኝ ሐዋርያቱ ከሰጣቸው በኋላ “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 22:19) የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ልጅ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ከመሆኑም ሌላ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ የሰጣቸውን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። በዚህ ዓመት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ቅዳሜ መጋቢት 13, 2000 (March 22, 2008) ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ይከበራል። የኢየሱስን ትእዛዝ በማክበር በዚህ ልዩ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብልሃለን። በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በዓሉ የሚከበርበትን ቦታና ሰዓት ሊነግሩህ ይችላሉ። በመታሰቢያው በዓል ላይ የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ካስከተለብን መዘዝ ነፃ የሚያወጣን እንዴት እንደሆነ ትማራለህ።

በዛሬው ጊዜ፣ ፈጣሪና ልጁ ሰዎችን ከሞት ለማዳን የከፈሉትን ታላቅ መሥዋዕት በሚገባ የሚረዱና የሚያደንቁ ሰዎች ጥቂት ናቸው። በቤዛው ላይ እምነት ያላቸው ሰዎች ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ስለ እምነት አጋሮቹ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “በእርሱ ታምናላችሁ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና።” (1 ጴጥሮስ 1:8, 9) ኢየሱስ ክርስቶስን በመውደድና በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ እምነት በማሳደር በአሁኑ ጊዜ ደስተኛ ሕይወት መምራት ትችላለህ፤ ወደፊት ደግሞ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ትወጣለህ።