በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች መስቀልን ለአምልኮ የማይጠቀሙበት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች መስቀልን ለአምልኮ የማይጠቀሙበት ለምንድን ነው?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የይሖዋ ምሥክሮች መስቀልን ለአምልኮ የማይጠቀሙበት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለሰው ልጆች ቤዛ እንዳስገኘና በቤዛው የሚያምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደሚችሉ ጠንካራ እምነት አላቸው። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ሆኖም ብዙ ጊዜ በሥዕሎች ላይ እንደሚታየው ኢየሱስ የሞተው በመስቀል ላይ እንደሆነ አያምኑም። ኢየሱስ የተሰቀለው አናቱ አካባቢ ሌላ ጣውላ በተጋደመበት እንጨት ላይ ሳይሆን እንደ አጣና ባለ ቀጥ ያለ እንጨት ላይ እንደሆነ ያምናሉ።

ክርስቶስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት በመሰጴጦምያ የሚኖሩ ሰዎች በመስቀል ይጠቀሙ ነበር። ኢየሱስ ከመወለዱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የነሐስ ዘመን ተብሎ በሚጠራው ጊዜም እንኳ በስካንዲኔቭያ የድንጋይ ቅርጾች ላይ መስቀል ይቀረጽ ነበር። ዴንማርካዊ ታሪክ ጸሐፊ የሆኑትና ስለ ምልክቶች የሚያጠኑት ስቬን ቲቶ አከን፣ ሲምቦልስ አራውንድ አስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች መስቀልን “እንደ ምትሐታዊ ምልክት . . . [እንዲሁም] ጥበቃና መልካም ዕድል እንደሚያስገኝ” ነገር አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። በመሆኑም ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒድያ እንደሚከተለው ብሎ መናገሩ ምንም አያስገርምም:- “በቅድመ ክርስትና ዘመንም ሆነ ከክርስትና ውጪ በሚገኙ ባሕሎች ውስጥ በአብዛኛው በጽንፈ ዓለም ወይም በሰማይ ያሉ አካላትን ለማመልከት መስቀልን ይጠቀሙ ነበር።” ታዲያ አብያተ ክርስቲያናት መስቀልን እጅግ ቅዱስ እንደሆነ ምልክት አድርገው የሚያዩት ለምንድን ነው?

ዊልያም ኤድዊ ቫይን የተባሉ የተከበሩ ብሪታንያዊ ምሑር ሐቁን እንዲህ በማለት አስቀምጠውታል:- “ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ3ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ . . . አረማውያን በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ ሲሆን . . . በአብዛኞቹ አረማዊ ምልክቶቻቸው መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ ተፈቀደላቸው። በመሆኑም አብያተ ክርስቲያናት በመስቀል መጠቀም ጀመሩ።”—በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ

ቫይን አክለው እንደገለጹት መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት በግሪክኛ ቋንቋ፣ “መስቀል” የሚለው ስምና “ሰቀለ” የሚለው ግስ የሚያመለክተው “ግንድን ወይም አጠናን ሲሆን . . . [ይህ ደግሞ] በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት ካገኘው በተነባበሩ ሁለት እንጨቶች የተሠራ መስቀል የተለየ ነው።” ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ኮምፓኒየን ባይብል እንዲህ በማለት ከላይ ካለው ጋር የሚስማማ ሐሳብ አስፍሯል:- “ጌታ የሞተው ቀጥ ባለ እንጨት ላይ እንጂ በየትኛውም አቅጣጫ በተነባበሩ ሁለት እንጨቶች ላይ እንዳልሆነ . . . ማስረጃው ያሳያል።” ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለውን ልማድ ተቀብለዋል።

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ታሪክ ጸሐፊ አከን “ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በነበሩት ሁለት መቶ ዘመናት ውስጥ ክርስቲያኖች በመስቀል የመጠቀም ልማድ የነበራቸው አይመስልም” ብለዋል። አክለውም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ክርስቲያኖች መስቀል “በዋነኝነት የሚያመለክተው ሞትንና ክፋትን ነበር” ብለዋል።

ከሁሉ በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ግን፣ ኢየሱስን ለማሠቃየትና ለመግደል ያገለገለው መሣሪያ ምንም ይሁን ምን ክርስቲያኖች የዚህን መሣሪያ ምስል ወይም ምልክት ሊያመልኩት የማይገባ መሆኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጣዖት አምልኮ ሽሹ” በማለት ያዛል። (1 ቆሮንቶስ 10:14) ኢየሱስ ራሱ እውነተኛ ተከታዮቹ የሚለዩበትን ትክክለኛ ምልክት ተናግሯል። “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:35

የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ በየትኛውም የአምልኳቸው ክፍል ከሰዎች ልማድ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። (ሮሜ 3:4፤ ቈላስይስ 2:8) በዚህም የተነሳ መስቀልን ለአምልኮ አይጠቀሙበትም።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ800 ከክ.ል.በፊት ገደማ፣ አንድ አረማዊ የአሦር ንጉሥ መስቀል አድርጎ የሚያሳይ ቅርጽ

[ምንጭ]

Photograph taken by courtesy of the British Museum