ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
የመበለቲቷ ሁለት ሳንቲሞች ምን ያህል ዋጋ ነበራቸው?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ አይሁዳውያን ለቤተ መቅደሱ የሚከፍሉት ዓመታዊ ግብር ‘ሁለት ዲናር’ ሲሆን ይህም ለሁለት ቀን ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ጋር የሚመጣጠን ነበር። (ማቴዎስ 17:24) ኢየሱስ በአንድ ወቅት፣ ሁለት ድንቢጦች ለ45 ደቂቃ ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ጋር ተመጣጣኝ በሆነ “በአንድ ሳንቲም” ይሸጡ እንደነበር ተናግሯል። እንዲያውም በሁለት ሳንቲሞች ማለትም ለ90 ደቂቃ ሥራ በሚከፈል ደሞዝ አምስት ድንቢጦች ማግኘት ይቻል ነበር።—ማቴዎስ 10:29፤ ሉቃስ 12:6 NW
ኢየሱስ፣ ድሃዋ መበለት ለቤተ መቅደሱ ስትሰጥ የተመለከተው መዋጮ አምስት ድንቢጥ ከሚገዛበት ዋጋ በጣም ያነሰ ነበር። እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች ወይም ሁለት ሌፕተኖች በወቅቱ በእስራኤል ውስጥ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ ከመዳብ የተሠሩ የመጨረሻዎቹ ትንሽ ሳንቲሞች ነበሩ። እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች ከአንድ ቀን ደሞዝ 1/64ኛ ጋር ተመጣጣኝ ናቸው፤ በሌላ አነጋገር አንድ ሰው በቀን በአማካይ 12 ሰዓት ቢሠራ ለ12 ደቂቃ ሥራ ከሚከፈል ደሞዝ ያነሰ ዋጋ አላቸው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የመበለቲቱን ስጦታ “ከትርፋቸው” ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ ግምት ሰጥቶታል። ለምን? ዘገባው መበለቲቱ ‘ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች’ እንደነበሯት ይገልጻል፤ በመሆኑም አንዱን ሳንቲም በመስጠት ሌላውን ለራሷ ማስቀረት ትችል ነበር። ሆኖም “ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”—ማርቆስ 12:41-44፤ ሉቃስ 21:2-4
ሳውል፣ ጳውሎስ በሚለው ስሙ መጠራት የጀመረው መቼ ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ የሮማ ዜግነት ኖሮት የተወለደ ዕብራዊ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 22:27, 28፤ ፊልጵስዩስ 3:5) በመሆኑም ይህ ሐዋርያ ከልጅነቱ ጀምሮ ሳውል የሚለው ዕብራዊ ስምና ጳውሎስ የሚለው ሮማዊ ስም ሳይኖረው አይቀርም። አንዳንድ የጳውሎስ ዘመዶችም በተመሳሳይ ሮማዊ ስምና የግሪክ ስም ነበራቸው። (ሮሜ 16:7, 21) ከዚህም በተጨማሪ በጊዜው የነበሩ አይሁዳውያን በተለይ ደግሞ ከእስራኤል ውጭ የሚኖሩት ሁለት ስም መያዛቸው የተለመደ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 12:12፤ 13:1
ይህ ሐዋርያ ወደ ክርስትና ከተለወጠ በኋላ ባሉት ከአሥር የሚበልጡ ዓመታት፣ በብዛት የሚታወቀው ሳውል በሚለው ዕብራዊ ስሙ ይመስላል። (የሐዋርያት ሥራ 13:1, 2) ሆኖም ሳውል በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ማለትም በ47/48 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ጳውሎስ የሚለውን ሮማዊ ስሙን ለመጠቀም ሳይመርጥ አልቀረም። ሳውል ይህን ያደረገው አይሁዳዊ ላልሆኑ ሰዎች ምሥራቹን የማወጅ ተልዕኮ ተሰጥቶት ስለነበር ጳውሎስ የሚለውን ሮማዊ ስሙን ቢጠቀም የበለጠ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። (የሐዋርያት ሥራ 9:15፤ 13:9፤ ገላትያ 2:7, 8) በተጨማሪም ጳውሎስ የሚለውን ስሙን የመረጠው ሳውል የሚለው የዕብራይስጥ ስሙ የግሪክኛ አጠራር፣ መጥፎ መልእክት ከሚያስተላልፍ አንድ የግሪክኛ ቃል ጋር ስለሚመሳሰል ሊሆን ይችላል። ስሙ የተለወጠበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ‘በሚቻለው ሁሉ አንዳንዶችን ያድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ለመሆን’ ፈቃደኛ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 9:22
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሌፕተንን ትክክለኛ መጠን የሚያሳይ ፎቶ