ልጆችን መረን በሚለቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ልጅ ማሳደግ
ልጆችን መረን በሚለቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ልጅ ማሳደግ
አንድ ልጅ ወላጁ ሊገዛለት ያልፈለገውን አሻንጉሊት እንዲገዛለት ሲወተውት አሊያም ልጁ እየተሯሯጠ መጫወት ፈልጎ ወላጁ “አርፈህ ተቀመጥ” ሲለው ተመልክተህ ታውቃለህ? እንዲህ ካሉት ሁኔታዎች መረዳት እንደምትችለው ወላጆች ምንጊዜም ለልጆቻቸው የሚጠቅመውን ነገር ለማድረግ ይፈልጋሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ልጁ እያለቀሰ ወይም እየጨቀጨቀ ሲያስቸግረው ወላጁ አይቻልም ብሎ የከለከለውን ነገር ሲፈቅድለት ይታያል።
በርካታ ወላጆች ልጆችን በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ ሲባል ልጆቹ ያሉትን ሁሉ ማድረግ ማለት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ከ12 እስከ 17 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 750 ልጆች ላይ ጥናት ተካሂዶ ነበር። በጥናቱ ላይ፣ ልጆቹ የጠየቁትን ነገር ወላጆቻቸው ሲከለክሏቸው ምን ዓይነት ምላሽ እንደሚሰጡ ሲጠየቁ 60 በመቶ የሚያህሉት ወላጆቻቸውን መወትወታቸውን እንደማያቆሙ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት አብዛኛውን ጊዜ ይህን ዘዴ ውጤታማ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል። ወላጆቻቸው፣ ልጆቹ የጠየቁትን ነገር ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆናቸው ለእነሱ ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳዩበት መንገድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና እንዲህ ያለው አመለካከት ትክክል ነው?
በጥንት ዘመን የተጻፈ አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ ምን እንደሚል ተመልከት:- “ሰው አገልጋዩን ከልጅነቱ ጀምሮ ቢያቀማጥል፣ የኋላ ኋላ ሐዘን ያገኘዋል [“ምስጋና ቢስ ይሆናል፣” NW]።” (ምሳሌ 29:21) እርግጥ ነው፣ ልጅና አገልጋይ አንድ አይደሉም። ይሁንና ይህ ምሳሌ ልጅን ከማሳደግ ጋር በተያያዘም ይሠራል ቢባል አትስማማም? የጠየቁትን ነገር ሁሉ በመስጠት ልጆችን ማቀማጠል ሲያድጉ ‘የማያመሰግኑ’ ማለትም ቀበጥ፣ ግትርና ለሚደረግላቸው ነገር ሁሉ አድናቆት የሌላቸው እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ከዚህ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው” የሚል ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 22:6) ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ይህን ምክር በመከተል ግልጽና ምክንያታዊ የሆኑ እንዲሁም የማይለዋወጡ ደንቦችን ያወጣሉ፤ በሥራ ላይ እንዲውሉም ያደርጋሉ። ልጅን መረን መልቀቅ የፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገው አያስቡም። በተጨማሪም ልጆቹ ስለተነጫነጩባቸው፣ በንዴት ስለጮኹባቸውና ስለነዘነዟቸው ብቻ የፈለጉትን ነገር ሁሉ አይሰጧቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ ኢየሱስ ከተናገረው “ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ፣ ‘አዎን’፤ አይደለም፣ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን” ከሚለው ሐሳብ ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳሉ። (ማቴዎስ 5:37) ልጆችን ማሠልጠን ሲባል ምን ነገሮችን ያጠቃልላል? እስቲ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ግሩም ምሳሌ ተመልከት።
‘በእጅ እንዳሉ ፍላጾች’
መጽሐፍ ቅዱስ በወላጅና በልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት የገለጸበት መንገድ ልጆች የወላጆቻቸው መመሪያ መዝሙር 127:4, 5 እንዲህ ይላል:- “በወጣትነት የተገኙ ወንዶች ልጆች፣ በጦረኛ እጅ እንዳሉ ፍላጾች ናቸው። ኰረጆዎቹ በእነዚህ የተሞሉ፣ የተባረከ ሰው ነው።” ስለዚህ ልጆች ከፍላጻ፣ ወላጆች ደግሞ ከጦረኛ ሰው ጋር ተመሳስለዋል። አንድ ቀስተኛ የሚያስፈነጥራቸው ፍላጾች ዒላማቸውን በአጋጣሚ ሊመቱ እንደማይችሉ እንደሚያውቅ ሁሉ አፍቃሪ የሆኑ ወላጆችም ልጅን ማሳደግ ጥረት ማድረግንና አስቀድሞ ማሰብን እንደሚጠይቅ ይገነዘባሉ። ልጆቻቸው “ዒላማቸውን” እንዲመቱ ማለትም ደስተኛ ሕይወት እንዲኖራቸውና ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ይመኛሉ። በተጨማሪም ልጆቻቸው ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ፣ ጥበበኛ እንዲሆኑና አላስፈላጊ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ እንዲሁም ጠቃሚ የሆነ ግብ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ይሁንና እንዲህ እንዲሆኑላቸው መመኘት ብቻ በቂ አይደለም።
እንደሚያስፈልጋቸው ያሳያል።ታዲያ አንድ ፍላጻ ዒላማውን እንዲመታ ከተፈለገ ምን ማድረግ ያስፈልጋል? ፍላጻው በጥንቃቄ መሠራት፣ በጥሩ ሁኔታ መያዝ እንዲሁም በሚገባ ታልሞ በኃይል መወንጨፍ ይኖርበታል። በተመሳሳይም ልጆች ወደ ጉልምስና የሚያደርጉት ጉዞ የተሳካ እንዲሆን በጥሩ ሁኔታ መቀረጽ፣ በጥንቃቄ መያዝና ተገቢውን መመሪያ ማግኘት ይኖርባቸዋል። እስቲ ልጆችን በማሳደግ ረገድ ሊታሰብባቸው የሚገቡትን እነዚህን ሦስት ነጥቦች በዝርዝር እንመልከት።
ፍላጻውን በጥንቃቄ መሥራት
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ቀስተኞች የሚጠቀሙባቸውን ፍላጾች በጥንቃቄ ይሠሩ ነበር። ቀላል ከሆነ የእንጨት ዓይነት የሚዘጋጀው የፍላጻው ዘንግ በእጅ የሚጠረብ ሲሆን በተቻለ መጠን ቀጥ ያለ እንዲሆን ይደረጋል። ከዚያም አንደኛው ጫፍ ሹል ይሆናል። በሌላኛው ጫፍ ደግሞ ፍላጻው ሲስፈነጠር አቅጣጫውን እንዳይቀይር ላባ ይደረግበታል።
ወላጆችም፣ ልጆቻቸው እንደነዚህ ቀጥ ያሉ ፍላጾች እንዲሆኑላቸው ማለትም ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉና አቅጣጫቸውን ሳይስቱ እንዲጓዙ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከባድ ስህተት ሲሠሩ ችላ ብለው አያልፉም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን እንዲያስተካክሉ ልጆቻቸውን በፍቅር ይረዷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” ስለሚል ማንኛውም ልጅ ማስተካከያ ሊያደርግባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ። (ምሳሌ 22:15) በመሆኑም የአምላክ ቃል፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሣጽ እንዲሰጧቸው ይመክራል። (ኤፌሶን 6:4) እርግጥ ነው፣ ተግሣጽ የልጅን አስተሳሰብም ሆነ ባሕርይ በመቅረጽና በማስተካከል ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በመሆኑም፣ ምሳሌ 13:24 “በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም። እዚህ ላይ የገባው አርጩሜ የሚለው ቃል ማንኛውንም ዓይነት እርማት ያመለክታል። አንድ ወላጅ፣ ልጁ ያሉበትን መጥፎ ልማዶች እንዲያስወግድ በፍቅር ተነሳስቶ ተግሣጽ ይሰጠዋል። ምክንያቱም እነዚህ ልማዶች ሥር ከሰደዱ የልጁን የወደፊት ሕይወት ሊያበላሹት ይችላሉ። በእርግጥም፣ ልጁን የማይገሥጽ ወላጅ ለልጁ ፍቅር የለውም።
አፍቃሪ የሆነ ወላጅ አንድን ትእዛዝ የሰጠበትን ምክንያት ለልጁ ያስረዳዋል። በመሆኑም ተግሣጽ መስጠት ሲባል ማዘዝና መቅጣት ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ልጁ የተሰጠውን ትእዛዝ በሚገባ እንዲያስተውል መርዳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው” ይላል።—ምሳሌ 28:7
ቀስተኛው ከፍላጻው ኋላ የሚያያይዘው ላባ ፍላጻው ከደጋኑ ላይ ከተስፈነጠረ በኋላ ቀጥ ብሎ እንዲሄድ ያስችለዋል። በተመሳሳይም የቤተሰብ መሥራች የሆነው አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ትምህርቶች ልጆች ከቤት ከወጡ በኋላም እንኳ ሊጠቅሟቸው ይችላሉ። (ኤፌሶን 3:14, 15) ይሁንና ቀስተኛው ከፍላጻው ኋላ ላባ እንደሚያያይዝ ሁሉ ወላጆችም እነዚህ ትምህርቶች ከልጆቻቸው ጋር ‘እንዲያያዙ’ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
በሙሴ ዘመን፣ አምላክ ለእስራኤላውያን ወላጆች የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር ልብ በሉ:- “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው [“በልጆችህም ልብ ውስጥ ቅረጻቸው፣” NW]።” (ዘዳግም 6:6, 7) ስለዚህ ወላጆች ሁለት ነገሮች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በመጀመሪያ፣ እነሱ ራሳቸው የአምላክን ቃል በመማርና በሥራ ላይ በማዋል ሕጎቹን መውደዳቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 119:97) ይህን ማድረጋቸው ደግሞ በጥቅሱ ላይ ቀጥሎ የተገለጸውን ሐሳብ ለመፈጸም ማለትም የአምላክን ሕግ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ‘ለመቅረጽ’ ያስችላቸዋል። ይህም ሲባል ጥሩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀምና በመደጋገም ልጆቻቸው እነዚህ ሕጎች ያላቸውን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል ማለት ነው።
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለልጆች ማስተማርም ሆነ ከባድ
ስህተት ሲፈጽሙ በፍቅር ተግሣጽ መስጠት ኋላ ቀርነት አይደለም። እነዚህ ነገሮች፣ ውድ የሆኑትን “ፍላጾች” አቅጣጫቸውን ሳይስቱ ወደ ጉልምስና ደረጃ እንዲደርሱ የሚረዷቸው ጠቃሚ እርምጃዎች ናቸው።ፍላጾቹን በጥንቃቄ መያዝ
እስቲ በመዝሙር 127:4, 5 ላይ የሚገኘውን ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። ቀስተኛው ፍላጾቹን ኮረጆው ውስጥ እንደሚያስቀምጣቸው መገለጹን አስታውስ። ፍላጾቹ ከተሠሩ በኋላ በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ቀስተኛው ፍላጾቹ እንዳይበላሹ ወይም እንዳይሰበሩ በኮሮጆው ውስጥ ያስቀምጣቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መሲሑ ትንቢት ሲናገር፣ መሲሑን አባቱ ‘በሰገባው ውስጥ እንደሸሸገው’ የተወለወለ ፍላጻ አድርጎ መግለጹ ትኩረት የሚስብ ነው። (ኢሳይያስ 49:2) ከማንም በላይ አፍቃሪ የሆነው አባት ማለትም ይሖዋ አምላክ፣ የሚወደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን፣ ልክ በትንቢት እንደተነገረው መሲሑ የሚገደልበት ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ከማንኛውም ጉዳት ጠብቆታል። ሌላው ቀርቶ አምላክ ልጁን ለዘለቄታው ሞቶ ከመቅረት የጠበቀው ሲሆን ለዘላለም እንዲኖር ወደ ሰማይ መልሶታል።
በተመሳሳይም፣ ጥሩ የሆኑ ወላጆች በሥነ ምግባር በረከሰው በዚህ ዓለም ውስጥ ካሉት አደገኛ ሁኔታዎች ልጆቻቸውን ይጠብቃሉ። ይህን የሚያደርጉት፣ ልጆቻቸው ለመጥፎ ተጽዕኖዎች እንዳይጋለጡ ሲሉ አንዳንድ ነገሮችን እንዳያደርጉ በመከልከል ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል” የሚለውን መመሪያ በቁም ነገር ይመለከቱታል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ደንብ ከማያከብሩ እኩዮቻቸው ጋር ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ ማድረግ ለችግር አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳርጋቸው የሚችል ከባድ ስህተት ከመሥራት ይጠብቃቸዋል።
ልጆች ወላጆቻቸው የሚያደርጉላቸውን ጥበቃ ሁልጊዜ በአድናቆት ላይመለከቱት ይችላሉ። እንዲያውም አብዛኛውን ጊዜ ልጆችህን ከጉዳት ለመጠበቅ ስትል የጠየቁትን ነገር ስለምትከለክላቸው፣ አንዳንድ ጊዜ ለምታወጣቸው ደንቦች ጥላቻ ሊያድርባቸው ይችላል። የልጆችን አስተዳደግ አስመልክተው በርካታ መጻሕፍትን የጻፉ አንዲት ታዋቂ ደራሲ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- ‘ልጆች ስለተሰጣቸው ምክር ምን እንደተሰማቸው ባይገልጹም እንዲሁም በወቅቱ ባያመሰግኑም፣ ወላጆቻቸው ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚረዳቸው አስተማማኝ መመሪያ እንዲሰጧቸው ይፈልጋሉ። እኛም ወላጅ እንደመሆናችን ባሕርያቸውን በጥብቅ በመቆጣጠርና ኃላፊነታችንን በቁም ነገር በመመልከት እንዲህ ማድረግ እንችላለን።’
አዎን፣ ልጆቻችሁን ሰላማቸውን ሊያሳጣቸው እንዲሁም ንጽሕናቸውን ወይም በአምላክ ፊት ያላቸውን አቋም ሊያበላሽባቸው ከሚችል ከማንኛውም ነገር መጠበቅ እንደምትወዷቸው የምታሳዩበት ዋነኛ መንገድ ነው። ልጆቻችሁ እያደጉ ሲሄዱ ሕጎቹን ያወጣችሁበትን ምክንያት ይገነዘቡ ብሎም ፍቅራዊ ጥበቃችሁን ያደንቁ ይሆናል።
ፍላጾቹን ወደ ዒላማው ማስወንጨፍ
መዝሙር 127:4, 5 ወላጆችን ከአንድ “ጦረኛ” ጋር እንዳነጻጸራቸው ልብ በል። ይህ ሲባል ግን በልጆቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችለው አባት ብቻ ነው ማለት ነው? በፍጹም። በዚህ ምሳሌ ላይ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት ለሁለቱም ማለትም ለአባትም ሆነ ለእናት ሌላው ቀርቶ ለነጠላ ወላጅ እንኳ ይሠራል። (ምሳሌ 1:8) “ጦረኛ” የሚለው ቃል ፍላጻውን ማስፈንጠር ከፍተኛ ኃይል እንደሚጠይቅ ያሳያል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን፣ አንዳንድ ጊዜ ደጋኖች በመዳብ ይለበጡ ነበር። ቀስተኛው ፍላጻውን ለማስፈንጠር ምናልባትም ደጋኑን በእግሩ በመያዝ ጅማቱን ሲወጥር ‘ቀስቱን ገተረ’ ይባል ነበር። (ኤርምያስ 50:14, 29) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ፍላጻውን ወደ ዒላማው ለማስፈንጠር የደጋኑን ጅማት መወጠር ከፍተኛ ኃይልና ጉልበት ይጠይቃል!
በተመሳሳይም ልጆችን ማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። ፍላጻው በራሱ ኃይል ወደ ዒላማው እንደማይስፈነጠር ሁሉ ልጆችም ያለ ወላጆች እርዳታ ጥሩ ሆነው ማደግ አይችሉም። የሚያሳዝነው ግን፣ በዛሬው ጊዜ በርካታ ወላጆች ልጆችን በተገቢው መንገድ ለማሳደግ ጥረት አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ ቀላል ሆኖ ያገኙትን መንገድ ለመከተል ይመርጣሉ። ቴሌቪዥን፣ ትምህርት ቤትና የዕድሜ እኩዮቻቸው ልጆቻቸውን ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር እንዲሁም ስለ ሥነ ምግባርና ስለ ጾታ እንዲያስተምሯቸው ይፈቅዳሉ። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቻቸው የጠየቋቸውን ሁሉ ያደርጉላቸዋል። ልጆቻቸው አንድ ነገር በሚፈልጉበት ወቅት አይሆንም ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ሲሰማቸው የልጆቻቸውን ስሜት መጉዳት እንደማይፈልጉ በመግለጽ የፈለጉትን ሁሉ ያደርጉላቸዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን በልጆቻቸው ላይ ዘላቂ ጉዳት የሚያስከትለው መረን መለቀቃቸው ነው።
ልጆችን ማሳደግ ከባድ ሥራ ነው። በአምላክ ቃል እየተመሩ ልጆችን ማሳደግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ ግን የሚክስ ነው። ፓረንትስ የተባለ አንድ መጽሔት እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “ጥናቶች እንደሚያሳዩት . . . አፍቃሪ ቢሆኑም ኃላፊነታቸውን በቁም ነገር የሚመለከቱ ማለትም ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ የሚሰጡ ሆኖም ጥብቅ የሆኑ ደንቦችን የሚያወጡ ወላጆች፣ ልጆቻቸው በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት የሚያመጡ፣ ተግባቢዎችና ለራሳቸው ጥሩ ግምት ያላቸው ሲሆኑ መረን ከተለቀቁ አሊያም በጣም ጥብቅ የሆኑ ወላጆች ካሳደጓቸው እኩዮቻቸው ይልቅ ደስተኞችም ናቸው።”
ኃላፊነታቸውን በሚገባ የሚወጡ ወላጆች ከዚህ የበለጠ አስደሳች ውጤትም ያገኛሉ። “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው” የሚለውን የምሳሌ 22:6ን የመጀመሪያ ክፍል ቀደም ሲል ተመልክተን ነበር። ጥቅሱ በመቀጠል “በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” ይላል። ታዲያ ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምሳሌ ልጅን በሚሄድበት መንገድ መምራት ሁልጊዜ ጥሩ ውጤት ያስገኛል የሚል ዋስትና መስጠቱ ነው? እንደዚያ ማለት አይቻልም። ልጅህ የመምረጥ ነፃነት ያለው ሲሆን ሲያድግ ይህንን ነፃነቱን በፈለገው መንገድ ሊጠቀምበት ይችላል። ይሁንና ይህ ጥቅስ ለወላጆች ግሩም ማጽናኛም ይሰጣቸዋል።
ልጆችህን በመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መሠረት ካሠለጠንካቸው ሲያድጉ ደስታና እርካታ ያለው ሕይወት የሚመሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ምቹ የሆነ ሁኔታ ፈጥረህላቸዋል ማለት ነው። (ምሳሌ 23:24) በመሆኑም እነዚህን ውድ “ፍላጾች” በጥሩ ሁኔታ ለመቅረጽ፣ በጥንቃቄ ለመያዝና በተገቢው መንገድ ለመምራት የቻልከውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብሃል። እንዲህ በማድረግህ ፈጽሞ አትቆጭም።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆች ልጆቻቸው የጠየቋቸውን ሁሉ ማድረጋቸው የፍቅር መግለጫ ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አፍቃሪ የሆነ ወላጅ አንድን ደንብ ያወጣበትን ምክንያት ለልጁ ያስረዳል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥሩ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በሥነ ምግባር በረከሰው በዚህ ዓለም ውስጥ ካሉት አደገኛ ሁኔታዎች ይጠብቃሉ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆችን ማሳደግ ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም ውጤቱ ግን የሚክስ ነው