በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምድራችን ትጠፋ ይሆን?

ምድራችን ትጠፋ ይሆን?

ምድራችን ትጠፋ ይሆን?

‘የምድራችን የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ብዙ ሰዎች በዚህች ውብ ፕላኔት ላይ እየደረሰ ያለውን ነገር ሲመለከቱ ምድር መጥፋቷ እንደማይቀር ሆኖ ይሰማቸዋል።

እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እንደ ውኃና ደን የመሳሰሉት ውድ የተፈጥሮ ሀብቶች አላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ ከመሆኑም ሌላ ከባቢ አየርም ተበክሏል። በመሆኑም ምድራችን እየተበላሸች ነው። ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሳይንቲስቶች ምድራችንም ሆነች በላይዋ የሚገኙት ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ከጠፈር በሚወድቁ ተወርዋሪ አካላት፣ በከዋክብት ፍንዳታ ወይም በፀሐይ ውስጥ ያለው ሃይድሮጅን በማለቁ ምክንያት ሊጠፉ እንደሚችሉ ይናገራሉ።

ሳይንቲስቶች፣ ምድር በጊዜ ሂደት ምናልባትም ከበርካታ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ሕይወት የማይኖርባት ትሆናለች ብለው ያምናሉ። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ይህንን አስመልክቶ “ምድራችን ልትስተካከል በማትችልበት ሁኔታ ወደ ጥፋት እያመራች ነው” በማለት ተናግሯል።

የሚያስደስተው ግን፣ ይሖዋ አምላክ ምድራችን እንድትጠፋ ወይም ለመኖሪያነት የማትመች ቦታ እስክትሆን ድረስ እንድትበላሽ እንደማይፈቅድ መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ‘ታላቅ ኃይል’ ስላለው አጽናፈ ዓለም ለዘላለም እንዲኖር ማድረግ ይችላል። (ኢሳይያስ 40:26) በመሆኑም በሚከተሉት ቃላት ላይ እምነት መጣል ትችላለህ:- ‘[አምላክ] ለዘላለም እንዳትናወጥ፣ ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናት።’ “ፀሓይና ጨረቃ አመስግኑት፤ የምታበሩ ከዋክብት ሁሉ አመስግኑት። . . . እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣ . . . ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው።”—መዝሙር 104:5፤ 148:3-6

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ

ምድር በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው እንድትበላሽና እንድትበከል የአምላክ ዓላማ አልነበረም። አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ውብ በሆነ የአትክልት ስፍራ አስቀመጣቸው። እርግጥ ነው፣ ገነት የሆነው መኖሪያቸው ውበቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባ ነበር። በመሆኑም አምላክ ምድርን ‘እንዲያለሟትና እየተንከባከቡ እንዲጠብቋት’ ትእዛዝ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 2:8, 9, 15) አምላክ ፍጹም ለነበሩት ወላጆቻችን እጅግ አስደሳችና አርኪ ሥራ ሰጥቷቸው ነበር!

ይሁን እንጂ አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ በዚያን ጊዜ የነበረችውን ገነት መንከባከብ ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መላዋ ምድር ወደ ገነትነት እንድትለወጥ ይፈልግ ነበር። ስለሆነም አምላክ አዳምና ሔዋንን እንዲህ ሲል አዘዛቸው:- “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።”—ዘፍጥረት 1:28

የሚያሳዝነው ግን፣ ከጊዜ በኋላ ሰይጣን ተብሎ የተጠራ አንድ ትዕቢተኛ መልአክ የአምላክን ዓላማ ተቃወመ። ሰይጣን አዳምና ሔዋን እሱን እንዲያመልኩት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረው በእባብ በመጠቀም በአምላክ አገዛዝ ላይ እንዲያምጹ አደረጋቸው። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ራእይ 12:9) አዳምና ሔዋን አድናቆት ማጣታቸው ፈጣሪያችንን ምን ያህል አሳዝኖት ሊሆን እንደሚችል አስብ! ይሁንና ይህ ዓመጽ ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ አልለወጠውም። አምላክ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:11

ይሖዋ፣ ሰይጣን ያስነሳው ዓመጽ እስከ ዘመናችን ድረስ እንዲቀጥል የፈቀደበት በቂ ምክንያት አለው። በአሁኑ ጊዜ የሰው ዘር የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን ሞክሯል፤ ይህም የሰው ልጆች ከአምላክ ተለይተው ራሳቸውን መምራት ይችላሉ የሚለው የሰይጣን አባባል ውድቅ መሆኑን አሳይቷል። *ኤርምያስ 10:23

ሰይጣን ያስነሳው ዓመጽ መጥፎ ሁኔታዎችን ያስከተለ ቢሆንም ላለፉት መቶ ዘመናት አምላክ ቅን የሆኑ ሰዎችን ሲባርካቸው ቆይቷል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ እሱን መታዘዝም ሆነ አገዛዙን ለመቀበል አሻፈረኝ ማለት የሚያመጣው ውጤት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቀመጥልን አድርጓል። እንዲሁም ለወደፊቱ ሕይወታችን የሚጠቅሙ አስደሳች ነገሮችን አድርጎልናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የሰውን ዘር ለማዳን የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር ልኮታል። ኢየሱስ ሕይወታችንን በተሻለ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ከማስተማሩም ሌላ ቤዛ ሆኖ ሞቶልናል። (ዮሐንስ 3:16) ኢየሱስ ፍጹም ሰው በመሆኑ መሞት አይገባውም ነበር፤ በመሆኑም የእሱ ሞት አዳምና ሔዋን ያሳጡንን ነገር ማለትም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር ተስፋን መልሰን ለማግኘት የሚያስችል መሠረት ሆኗል። * ይሖዋ አምላክ መላውን የሰው ዘር የሚገዛ መንግሥት በሰማይ ያቋቋመ ሲሆን ከሞት የተነሳውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የዚህ መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። ይህ ግሩም ዝግጅት አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ እንዲፈጸም ያደርጋል።—ማቴዎስ 6:9, 10

በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት የሚከተሉት አስደሳች ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ:- “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።” “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔርም ራሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና። በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም፣ ‘እነሆ፤ እኔ ሁሉን ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ።”—መዝሙር 37:9, 29፤ ራእይ 21:3-5

መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ አይጋጭም

አንዳንዶች ‘ከላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ምድር እንደምትጠፋ የሚናገሩ ከሚመስሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር እንዴት ማስማማት ይቻላል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። እነዚህ ምሳሌዎች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ እንደማይጋጭ ማስረጃ ይሆኑናል።

ሳይንቲስቶች ሁሉም ግዑዛን ፍጥረታት ‘ወደ ጥፋት እያመሩ’ መሆናቸውን ከመግለጻቸው ከረጅም ጊዜ በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “አንተ [አምላክ] ከጥንት ምድርን መሠረትህ፤ ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፤ እነርሱም ወዲያ ይጣላሉ። አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።”—መዝሙር 102:25-27

መዝሙራዊው እንዲህ ሲል መጻፉ አምላክ ለምድር ካለው ዘላለማዊ ዓላማ ጋር የሚቃረን አይደለም። ከዚህ ይልቅ መዝሙራዊው የአምላክን ዘላለማዊነት እሱ ከፈጠራቸው ሊጠፉ ከሚችሉ ነገሮች ጋር እያነጻጸረ መናገሩ ነበር። አምላክ እነዚህን ነገሮች ለማደስ የሚያስችል ታላቅ ኃይል ባይኖረው ኖሮ የእኛን ሥርዓተ ፀሐይ ጨምሮ መላው ጽንፈ ዓለም ቀስ በቀስ መበላሸቱና መጥፋቱ አይቀርም ነበር። ፕላኔታችን ባለችበት እንድትጸናም ሆነ ብርሃንና ኃይል እንድናገኝ ያስቻለን ደግሞ ይህ እኛ ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ነው። ስለሆነም አምላክ ምድራችንን ባይንከባከባት ኖሮ ምድራችን ‘ታረጅ’ ወይም ትጠፋ ነበር።

አምላክ ለምድር ካለው ዓላማ ጋር የሚጋጩ የሚመስሉ ሌሎች ጥቅሶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይና ምድር ‘እንደሚያልፉ’ ይናገራል። (ራእይ 21:1) ይህ ሐሳብ ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና” ሲል ከሰጠው ተስፋ ጋር እንደማይጋጭ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 5:5) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይና ምድር ‘ያልፋሉ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ “ምድር” የሚለውን ቃል ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን ጥቅስ ተመልከት:- “ምድርም ሁሉ በአንድ ቋንቋና በአንድ ንግግር ነበረች።” (ዘፍጥረት 11:1 የ1954 ትርጉም) እዚህ ላይ “ምድር” የሚለው ቃል በላይዋ የሚኖሩትን ሰዎች እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። ሌላኛው ምሳሌ መዝሙር 96:1 ሲሆን ጥቅሱ “ምድር ሁሉ፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ” ይላል። በዚህም ሆነ በሌሎች ጥቅሶች ላይ “ምድር” የሚለው ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ሰዎችን ለማመልከት ተሠርቶበታል።—መዝሙር 96:13

አንዳንድ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ያሉትን ገዥዎች ከሰማይ ወይም በሰማይ ላይ ከሚገኙ ግዑዝ አካላት ጋር ያመሳስላቸዋል። ለምሳሌ ያህል ጨቋኞቹ የባቢሎን ገዥዎች ራሳቸውን በዙሪያቸው ከነበሩት ሰዎች ከፍ አድርገው ይመለከቱ ስለነበር በከዋክብት ተመስለዋል። (ኢሳይያስ 14:12-14) በትንቢት በተነገረው መሠረት የባቢሎን “ሰማያት” ወይም የገዥው መደብ አባላትና ‘በምድር’ የተመሰሉት ያንን አገዛዝ ይደግፉ የነበሩት ሰዎች በ539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ጠፍተዋል። (ኢሳይያስ 51:6) ይህም ንስሐ የገቡ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱና ጻድቅ በሆኑ ሰዎች ማለትም ‘በአዲስ ምድር’ ላይ የሚገዛ ‘አዲስ ሰማይ’ ወይም አዲስ አገዛዝ እንዲቋቋም በር ከፍቷል።—ኢሳይያስ 65:17

መጽሐፍ ቅዱስ ሰማይና ምድር እንደሚያልፉ ሲናገር፣ በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ብልሹ የሆነ ሰብዓዊ አስተዳደርም ይሁን ይህንን ሥርዓት የሚደግፉ አምላካዊ ፍርሃት የሌላቸው ሰዎች በሙሉ እንደሚጠፉ ማመልከቱ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:7) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን።” በመሆኑም አሁን ያለንበት ሥርዓት መጥፋቱ፣ አምላክ በሰማይ ያቋቋመው አዲስ መንግሥት ጻድቅ በሆነው አዲስ ኅብረተሰብ ላይ በረከት ማፍሰስ እንዲችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።—2 ጴጥሮስ 3:13

በመሆኑም አምላክ መኖሪያችን የሆነችው ምድር ለዘላለም እንደምትኖር በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ይኑርህ። መጽሐፍ ቅዱስ መላዋ ምድር ገነት በምትሆንበት በዚያ አስደሳች ጊዜ ለመኖር ከፈለግህ ምን ማድረግ እንደሚገባህ ይነግርሃል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድርም ሆነ ስለ ሰው ዘር የወደፊት ዕጣ የሚያስተምረውን ነገር ለመመርመር ለምን ግብ አታወጣም? በዚህ ረገድ በአካባቢህ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 106-114⁠ን ተመልከት።

^ አን.11 ስለ ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 47-56⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ ምድራችን ለዘላለም እንደምትኖር ተስፋ ይሰጣል

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከጀርባ ያለው ሉል:- NASA/The Visible Earth (http://visibleearth.nasa.gov/); የዋልታ ድብ:- © Bryan and Cherry Alexander Photography