ቅዱስ ቁርባን—ከሥርዓቱ በስተጀርባ ያለው እውነታ
ቅዱስ ቁርባን—ከሥርዓቱ በስተጀርባ ያለው እውነታ
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች በዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ወይም በየሳምንቱ አሊያም በየቀኑ ይህን ሥነ ሥርዓት አዘውትረው ይፈጽማሉ። ይህ ሥርዓት ምስጢራዊ እምነት እየተባለ የሚጠራ ሲሆን በዚህ ሥነ ሥርዓት የሚካፈሉት አብዛኞቹ ሰዎችም ሥርዓቱ እንደማይገባቸው ይናገራሉ። ይህ ሥነ ሥርዓት ቅዱስ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ከመሆኑም በላይ ተአምራዊ እንደሆነም ይታሰባል።
እየተናገርን ያለነው ቅዱስ ቁርባን ስለሚባለው ሥነ ሥርዓት ነው፤ የካቶሊክ የቅዳሴ ሥርዓት ክፍል በሆነው በዚህ ዝግጅት ላይ ቄሱ ቂጣውንና ወይኑን ከባረከ በኋላ ምእመናኑ ቅዱስ ቁርባኑን በመውሰድ ከክርስቶስ ጋር አንድ እንዲሆኑ ይጋብዛል። * ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት አሥራ ስድስተኛ፣ ቅዱስ ቁርባን ለእኛ ለካቶሊኮች “የእምነታችን ዋና ክፍል ነው” በማለት ተናግረዋል። በቅርቡ ቤተ ክርስቲያኗ “የቅዱስ ቁርባንን ዓመት” ያከበረች ሲሆን ይህም ሰዎች “በቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓት ላይ ያላቸውን እምነት ለማጠናከር” የሚደረግ ጥረት ክፍል ነው።
አጥባቂ ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ካቶሊኮችም እንኳ በዚህ ሥርዓት ያምናሉ። ለአብነት ያህል፣ በቅርቡ ታይም በተባለው መጽሔት ላይ በወጣ ጽሑፍ፣ ወጣትና ተራማጅ ካቶሊክ እንደሆነች ተደርጋ የተገለጸች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች:- “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶች ረገድ ልዩነቶች ቢኖሩንም በካቶሊክ ሃይማኖት አንድ የሚያደርገንን ነገር ይኸውም ለቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ያለንን ቅንዓት አጥብቀን እንይዛለን።”
ይሁን እንጂ ቅዱስ ቁርባን ምንድን ነው? የክርስቶስ ተከታዮች ይህንን ሥርዓት እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸዋል? እስቲ በመጀመሪያ የቅዱስ ቁርባን ልማድ እንዴት እንደመጣ እንመልከት። ከዚያም ‘የቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ካቋቋመው በዓል ጋር ይስማማል?’ በሚለው ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ ጥያቄ ላይ ትኩረት እናደርጋለን።
ቅዱስ ቁርባንና ሕዝበ ክርስትና
ቅዱስ ቁርባን ተአምራዊ ሥርዓት እንደሆነ ተደርጎ የሚታየው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓት ላይ ቄሱ የሚያቀርበው ጸሎት ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ካቴኪዝም ኦቭ ዘ ካቶሊክ ቸርች የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ይህ ጸሎት
በሚቀርብበት ወቅት “የክርስቶስ ተግባርና ቃሎች ያላቸው ኃይል እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል” የኢየሱስ ሥጋና ደም “በቅዱስ ቁርባኑ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኝ” ያደርጋል። ቄሱ ከቂጣውና ከወይኑ ከወሰደ በኋላ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከቁርባኑ እንዲካፈሉ ይጋብዛል፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚበሉት ቂጣውን ብቻ ነው።የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ቂጣውና ወይኑ በተአምራዊ ሁኔታ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ቃል በቃል እንደሚለወጥ ታስተምራለች፤ ይህ መሠረተ ትምህርት ምስጢረ ቁርባን ተብሎ ይጠራል። ይህ ትምህርት የመጣው በጊዜ ሂደት ሲሆን ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቺ የተሰጠውና ጥቅም ላይ የዋለው በ13ኛው መቶ ዘመን ነው። የፕሮቴስታንት ተሃድሶ በተካሄደበት ዘመን የካቶሊክ ቅዱስ ቁርባን ሥርዓት አንዳንድ ገጽታዎችን በተመለከተ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። ሉተር፣ የምስጢረ ቁርባንን መሠረተ ትምህርት በመቃወም ቂጣውና ወይኑ ራሱ የኢየሱስ ሥጋና ደም ነው እንጂ በተአምራዊ ሁኔታ አይለወጥም በማለት አስተማረ።
ከጊዜ በኋላ የቅዱስ ቁርባንን ትርጉም እንዲሁም የአከባበሩን ሥርዓትና በየስንት ጊዜ መከበር አለበት የሚሉትን ጉዳዮች በተመለከተ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ልዩነቶች ተፈጠሩ። ያም ቢሆን ግን ይህ ሥርዓት በመላው ሕዝበ ክርስትና ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ መጀመሪያ ያቋቋመው በዓል ምን ይመስል ነበር?
‘የጌታ እራት’ በዓል የተቋቋመበት መንገድ
“የጌታን እራት” ወይም የሞቱን መታሰቢያ በዓል ያቋቋመው ኢየሱስ ራሱ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 11:20, 24) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ቃል በቃል ሥጋውን የሚበሉበትና ደሙን የሚጠጡበት ምስጢራዊ ሥነ ሥርዓት አቋቁሞ ነበር?
ኢየሱስ የአይሁዳውያንን የፋሲካ በዓል አክብሮ ሲያበቃ፣ አሳልፎ የሚሰጠውን አስቆሮቱ ይሁዳ የተባለውን ሐዋርያ አሰናበተው። በቦታው ከነበሩት 11 ሐዋርያት አንዱ የሆነው ማቴዎስ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “እየበሉ ሳሉ፣ ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ ‘እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው’ አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ ‘ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።’”—ማቴዎስ 26:26-28
እንደ ማንኛውም የአምላክ አገልጋይ ሁሉ ኢየሱስም ምግቡን መባረኩ የተለመደ ነገር ነበር። (ዘዳግም 8:10፤ ማቴዎስ 6:11፤ 14:19፤ 15:36፤ ማርቆስ 6:41፤ 8:6፤ ዮሐንስ 6:11, 23፤ የሐዋርያት ሥራ 27:35፤ ሮሜ 14:6) ኢየሱስ በዚህ ወቅት ምስጋና ሲያቀርብ ተአምር ፈጽሞ ተከታዮቹ ቃል በቃል የእሱን ሥጋና ደም እንዲወስዱ አድርጓል ብሎ ለማመን የሚያበቃ ምክንያት አለ?
“ይህ . . . ማለት ነው” ወይስ “ይህ . . . ነው”?
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ “እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው” እንዲሁም “ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ . . . ደሜ ይህ ነው” በማለት አስቀምጠውታል። (ማቴዎስ 26:26-28፤ የ1954 ትርጉም፣ የ1980 ትርጉም) እንዲሁም “መሆን” የሚል ትርጉም ያለው ኤስቲን የሚለው የግሪክኛ ግስ “ነው” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ሆኖም ይኸው ግስ “ማመልከት” የሚል ትርጉምም ሊሰጠው ይችላል። በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ ይህ ግስ “ማለት ነው” ወይም “ያመለክታል” ተብሎ በተደጋጋሚ ጊዜያት መተርጎሙ ትኩረት የሚስብ ነው። * ትክክለኛውን አተረጓጎም የሚወስነው በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ በማቴዎስ 12:7 ላይ የሚገኘው ኤስቲን የሚለው ቃል “ማለት እንደ ሆነ” ተብሎ ተተርጉሟል:- “‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ’ የሚለው ቃል ምን ማለት እንደ ሆነ ብታውቁ ኖሮ፣ በንጹሐን ላይ ባልፈረዳችሁ ነበር።”
በዚህ ረገድ በርካታ የተከበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ
ምሑራን “ይህ . . . ነው” የሚለው ቃል የኢየሱስን ሐሳብ በትክክል እንደማያስተላልፍ ይስማማሉ። ለምሳሌ፣ ዣክ ዱፖን የተባሉ የሃይማኖት ምሑር፣ ኢየሱስ የኖረበትን ባሕልና ማኅበረሰብ ግምት ውስጥ በማስገባት የዚህ ጥቅስ “ትክክለኛ” አተረጓጎም “ይህ ሥጋዬ ማለት ነው” ወይም “ይህ ሥጋዬን ይወክላል” መሆኑን ገልጸዋል።ያም ሆነ ይህ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን ቃል በቃል ሥጋውን እንዲበሉና ደሙን እንዲጠጡ ማዘዙ ሊሆን አይችልም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በኖኅ ዘመን ከደረሰው የጥፋት ውኃ በኋላ የሰው ልጆች የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ ተፈቅዶላቸዋል። ከዚህም በላይ አምላክ፣ የሰው ልጆች ደም እንዳይበሉ በቀጥታ አዝዟቸዋል። (ዘፍጥረት 9:3, 4) ይህ ትእዛዝ በሙሴ ሕግ ውስጥ የተደገመ ሲሆን ኢየሱስም ይህንን ሕግ ሙሉ በሙሉ ታዝዟል። (ዘዳግም 12:23፤ 1 ጴጥሮስ 2:22) ሐዋርያት፣ ደም መብላትን የሚከለክለውን ሕግ በመንፈስ አነሳሽነት እንደገና ስላስተላለፉ ይህ ሕግ በክርስቲያኖች ላይም ይሠራል። (የሐዋርያት ሥራ 15:20, 29) ታዲያ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ያወጣውን ቅዱስ ሕግ እንዲጥሱ የሚያደርግ በዓል ያቋቁማል? ፈጽሞ አያደርገውም!
እንግዲያው ኢየሱስ ቂጣና ወይኑን በምሳሌያዊ መንገድ እንደተጠቀመበት በግልጽ ለመመልከት ይቻላል። ያልቦካው ቂጣ፣ ኃጢአት የሌለበትንና መሥዋዕት የሆነውን ሥጋውን ይወክላል። ቀዩ ወይን ደግሞ “ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ” የሚፈሰውን ደሙን ያመለክታል።—ማቴዎስ 26:28
የጌታ እራት ትርጉም
ኢየሱስ የመጀመሪያውን የጌታ እራት በዓል የደመደመው “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት ነበር። (ሉቃስ 22:19) በእርግጥም ይህ በዓል ኢየሱስንና በሞቱ ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች እንድናስታውስ ይረዳናል። በዓሉ፣ ኢየሱስ የአባቱን የይሖዋን ሉዓላዊነት እንዳስከበረ ያስታውሰናል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ሰው ሆኖ በመሞቱ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል።’ በእሱ መሥዋዕት የሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ከኃጢአት ነፃ እንዲሆኑና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ እንደከፈተ እንድናስታውስ ያደርገናል።—ማቴዎስ 20:28
በዋነኝነት ግን የጌታ እራት የኅብረት ማዕድ ነው። በዚህ ማዕድ የሚካፈሉት (1) ቤዛውን ያዘጋጀው ይሖዋ አምላክ፣ (2) ቤዛውን ያቀረበውና “የእግዚአብሔር በግ” የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም (3) የኢየሱስ መንፈሳዊ ወንድሞች ናቸው። የኢየሱስ ወንድሞች ከቂጣውና ከወይኑ በመካፈል ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆናቸውን ያሳያሉ። (ዮሐንስ 1:29፤ 1 ቆሮንቶስ 10:16, 17) ከዚህም በተጨማሪ በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ መሆናቸው መጠን ‘በአዲሱ ኪዳን’ ውስጥ እንደታቀፉ ያሳያሉ። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ይሆናሉ።—ሉቃስ 22:20፤ ዮሐንስ 14:2, 3፤ ራእይ 5:9, 10
ታዲያ የመታሰቢያው በዓል መከበር ያለበት መቼ ነው? ኢየሱስ ይህን በዓል ለማቋቋም አንድ የተወሰነ ቀን ማለትም የፋሲካ በዓል የሚከበርበትን ቀን መምረጡን ማስታወሳችን መልሱን ግልጽ ያደርግልናል። የአምላክ ሕዝቦች ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት በአይሁዳውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት በየዓመቱ ኒሳን 14 ይሖዋ ለሕዝቦቹ ያደረገውን አስደናቂ የመዳን ዝግጅት ሲያከብሩ ቆይተዋል። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ኢየሱስ፣ አምላክ በክርስቶስ ሞት አማካኝነት የሚያደርገውን ታላቅ የመዳን ዝግጅት ተከታዮቹ በዚህ ቀን እንዲያስታውሱት ማዘዙ ነበር። በመሆኑም የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የጌታ እራትን በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት በየዓመቱ ኒሳን 14 ላይ ያከብራሉ።
ይህንን የሚያደርጉት እንዲያው ሥርዓቱን ለማክበር ስለሚፈልጉ ነው? ግልጹን ለመናገር የቅዱስ ቁርባንን ሥርዓት የሚያከብሩት አብዛኞቹ ሰዎች የሚማርካቸው ሥነ ሥርዓቱ ነው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው ታይም መጽሔት ላይ የወጣው ጽሑፍ ደራሲ የሆነችው ሴት “ብዙዎች በሚያከብሯቸው ጥንታዊ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን መካፈል በጣም ያረጋጋል” ብላለች። በዛሬው ጊዜ እንደሚገኙ በርካታ ካቶሊኮች ሁሉ ይህች ሴትም ቀደም ባሉት ዘመናት ይደረግ እንደነበረው ሥነ ሥርዓቱ በላቲን ቋንቋ ቢካሄድ ትመርጣለች። ለምን? “ቅዳሴ በእንግሊዝኛ ሲካሄድ አብዛኛውን ጊዜ የምሰማውን ነገር ስለማልወደው በማላውቀው ቋንቋ ሲቀደስ መስማት እፈልጋለሁ” በማለት ጽፋለች።
የይሖዋ ምሥክሮችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች፣ የሚኖሩት በየትኛውም ቦታ ቢሆን የጌታ እራት በዓል በራሳቸው ቋንቋ ሲካሄድ መስማት ያስደስታቸዋል። የክርስቶስ ሞት ያለውን ትርጉምና ጥቅም በተመለከተ ግንዛቤያቸውን ማስፋት ይፈልጋሉ። እንደዚህ ያለውን እውነት ዓመቱን ሙሉ ልናሰላስልበትና ልንወያይበት ይገባል። የይሖዋ ምሥክሮች፣ ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰዎች ያሳዩትን ጥልቅ ፍቅር ለማስታወስ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር እንደሆነ ይሰማቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው “ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን [ለመናገር]” ያስችላቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 11:26
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ይህ ሥነ ሥርዓት የጌታ እራት፣ እንጀራ መቁረስ፣ ቅዱስ መሥዋዕት፣ ቅዱስና መለኮታዊ ሥነ ሥርዓት እንዲሁም ሥጋ ወደሙ ተብሎም ይጠራል።
^ አን.15 ለአብነት ያህል፣ ማቴዎስ 13:38ን፤ 27:46ን፤ ሉቃስ 8:11ን እንዲሁም ገላትያ 4:24ን ተመልከት።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኢየሱስ መጀመሪያ ያቋቋመው በዓል ምን ይመስል ነበር?
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቁሟል
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት በዓል ሲከበር