አርማጌዶን—ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀረው የአምላክ ጦርነት
አርማጌዶን—ጦርነቶችን ሁሉ የሚያስቀረው የአምላክ ጦርነት
“ሰውን መግደል አረመኔያዊ ድርጊት እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ በመሆኑም በእነሱ አመለካከት ጦርነት፣ ለመረዳት የሚያዳግት ቀፋፊ ተግባር ነው፤ በቋንቋቸው ውስጥ ይህንን ድርጊት የሚገልጽ ቃል የላቸውም።”—የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ፍሪቾፍ ናንሰን የተባለ አሳሽ በግሪንላንድ የሚኖሩትን የኢንዩት ሰዎች አስመልክቶ በ1888 የሰጠው መግለጫ
ጦርነት “ለመረዳት የሚያዳግት ቀፋፊ ተግባር” እንደሆነ ተደርጎ በሚታይበት ኅብረተሰብ ውስጥ ቢኖር የማይወድ ማን አለ? ጦርነት የማይታወቅ ነገር ከመሆኑ የተነሳ ጦርነት የሚለው ቃል እንኳ በሌለበት ዓለም ውስጥ ለመኖር የማይመኝስ ማን ነው? እንዲህ ባለ ዓለም ውስጥ መኖር የሕልም እንጀራ ሊመስል ይችላል፤ በተለይ ደግሞ እንዲህ ያለውን ዓለም ያመጣሉ ብለን ተስፋችንን የምንጥለው በሰው ልጆች ላይ ከሆነ ሁኔታው የማይመስል ነገር ይሆንብናል።
ይሁን እንጂ በኢሳይያስ ትንቢት ላይ አምላክ ራሱ እንዲህ ያለውን ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “እነርሱም ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4
ይህ ትንቢት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ከተፈለገ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ወታደሮች በውጊያ ላይ በሚገኙበትና ወደ 20 ገደማ የሚሆኑ ጦርነቶች እየተካሄዱ ባሉበት በዚህ ዓለም ላይ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። በመሆኑም ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ይሖዋ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ መግባት የሚኖርበት መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይሖዋ የሚያደርገው ይህ ጣልቃ ገብነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተጠቀሰው በአርማጌዶን ይደመደማል።—ራእይ 16:14, 16
ምንም እንኳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰዎች “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል የሚጠቀሙት የሰውን ዘር ከምድር ገጽ የሚያጠፋ ዓለም አቀፍ የኑክሌር ጦርነትን ለማመልከት ቢሆንም አንድ መዝገበ ቃላት ቃሉ በዋነኝነት የሚያመለክተው “በመልካምና በክፉ ኃይሎች መካከል ታላቅና የመጨረሻ ውጊያ የሚካሄድበትን ቦታ” እንደሆነ ገልጿል። መልካም ነገር ክፋትን ያሸንፍ ይሆን ወይስ በእነዚህ ኃይላት መካከል የሚደረገው ውጊያ እንዲሁ ምናብ የፈጠረው ነገር ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ክፋት የሚያከትምበት ጊዜ እንደሚመጣ በተደጋጋሚ የሚናገር ሲሆን ይህንን ሐሳብ በመመልከትም ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን። መዝሙራዊው ‘ኀጢአን ከምድር ገጽ እንደሚጠፉ ዐመፀኞችም ከእንግዲህ እንደማይገኙ’ ትንቢት ተናግሯል። (መዝሙር 104:35) የምሳሌ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።”—ምሳሌ 2:21, 22
ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ክፉዎች ሥልጣናቸውን በሰላም እንደማይለቁ በግልጽ ይናገራል፤ በመሆኑም አምላክ ጦርነትን ጨምሮ ክፋትን ሙሉ በሙሉ መዝሙር 2:2) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ልዩ ጦርነት፣ አርማጌዶን ብሎ መጥራቱ ትኩረት የሚስብ ነው።
የሚያስወግድ የመጨረሻ ጦርነት ማካሄድ ያስፈልገዋል። (በጥንት ጊዜ በመጊዶ አቅራቢያ የተካሄዱ ውጊያዎች
“አርማጌዶን” የሚለው ቃል “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም አለው። የጥንቷ የመጊዶ ከተማና በዙሪያዋ ያለው የኢይዝራኤል ሜዳ ደግሞ ወሳኝ ውጊያዎችን በማስተናገድ ረገድ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ አላቸው። ታሪክ ጸሐፊው ኤሪክ ክላይን ዘ ባትል ኦቭ አርማጌዶን በተሰኘው መጽሐፍ ላይ “መጊዶና የኢይዝራኤል ሸለቆ፣ በታሪክ ውስጥ የሥልጣኔን አቅጣጫ የቀየሩ ውጊያዎች የተካሄዱባቸው ቦታዎች ናቸው” በማለት ጽፈዋል።
ክላይን እንደገለጹት በመጊዶ አቅራቢያ የተካሄዱት አብዛኞቹ ውጊያዎች ወሳኝ መሆናቸው ታይቷል። በ13ኛው መቶ ዘመን አብዛኛውን የእስያ ክፍል ወርሮ የነበረው የሞንጎላውያን ሠራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ የሽንፈት ጽዋ የተጎነጨው በዚህ ሸለቆ ነበር። በጄኔራል ኤድመንድ አለንቢ የሚመራው የብሪታንያ ሠራዊት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቱርክን ድል ያደረገው ከመጊዶ ብዙም ሳይርቅ ነበር። አንድ ወታደራዊ ታሪክ ጸሐፊ አለንቢ ስላገኙት ድል ሲናገሩ “በታሪክ ዘመናት በአጭር ጊዜ ውስጥ የማያዳግም ዘመቻ ከተደረገባቸው እንዲሁም ፈጽሞ የማያዳግም ውጊያ ከተካሄደባቸው ጦርነቶች አንዱ” መሆኑን ገልጸዋል።
በመጊዶ አቅራቢያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ወሳኝ ጦርነቶችም ተካሂደዋል። መስፍኑ ባርቅ፣ በሲሣራ የሚመራውን የከነዓናውያን ሠራዊት ያሸነፈው እዚህ ቦታ ላይ ነበር። (መሳፍንት 4:14-16፤ 5:19-21) ጌዴዎን 300 ተዋጊዎችን ብቻ ይዞ አንድን ታላቅ የምድያም ሠራዊት በመጊዶ አቅራቢያ ድል አድርጓል። (መሳፍንት 7:19-22) ፍልስጥኤማውያን የእስራኤልን ሠራዊት ድል ባደረጉበት ወቅት ንጉሥ ሳኦልና ልጁ ዮናታን የተገደሉት በመጊዶ አቅራቢያ በሚገኘው በጊልቦዓ ተራራ ላይ ነበር።—1 ሳሙኤል 31:1-7
መጊዶና አጠገቡ ያለው ሸለቆ፣ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስላላቸው ባለፉት 4,000 ዓመታት ውስጥ በርካታ ውጊያዎችን አስተናግደዋል። አንድ ታሪክ ጸሐፊ በዚህ ቦታ ላይ ቢያንስ 34 ውጊያዎች እንደተካሄዱ ገልጸዋል!
የመጊዶ ታሪክ እንዲሁም ቦታው ያለው ወታደራዊ ጠቀሜታ፣ “አርማጌዶን” የሚለው ቃል ካለው ምሳሌያዊ ትርጉም ጋር ግንኙነት እንደሚኖረው ምንም ጥርጥር የለውም። ምንም እንኳ አርማጌዶን የሚለው ቃል በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆንም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ቃሉ በሚገኝበት ጥቅስ ዙሪያ ያሉት ሐሳቦች፣ አርማጌዶን በምድር ላይ ያለውን የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት እንደሚነካ በግልጽ ያሳያሉ።መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አርማጌዶን ምን ይላል?
በጥንት ጊዜ በመጊዶ አቅራቢያ በርካታ ወሳኝ ጦርነቶች የተካሄዱ ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ ክፋትን ማስወገድ አልቻሉም። በዚህ ቦታ ላይ የተደረገ የትኛውም ውጊያ በጥሩና በክፉ ኃይላት መካከል የተካሄደ ነው ማለት አይቻልም። በመሠረቱ በጥሩና በክፉ ኃይላት መካከል የሚካሄደውን ውጊያ መጀመር ያለበት አምላክ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ በአንድ ወቅት እንደተናገረው “ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር [“ጥሩ፣” NW] ማንም የለም።” (ሉቃስ 18:19) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አርማጌዶን የአምላክ ጦርነት እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ‘የዓለም ሁሉ ነገሥታት ሁሉን በሚችል አምላክ ታላቅ ቀን ለሚሆነው ጦርነት’ እንደሚሰበሰቡ ይናገራል። (ራእይ 16:14) ትንቢታዊው ዘገባ አክሎም “እነርሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን * በሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው” ይላል። (ራእይ 16:16) የራእይ መጽሐፍ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ “የምድር ነገሥታትና ሰራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሰራዊቱ ጋር ለመዋጋት [እንደሚሰበሰቡ]” ይገልጻል። (ራእይ 19:19) በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ማንም ሊሆን አይችልም።—1 ጢሞቴዎስ 6:14, 15፤ ራእይ 19:11, 12, 16
ከእነዚህ ጥቅሶች ተነስተን ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? አርማጌዶን፣ በአምላክና ታዛዥ ባልሆኑ የሰው ልጆች መካከል የሚደረግ ጦርነት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ይሖዋና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ጦርነት የሚያካሂዱት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት አርማጌዶን ‘ምድርን ያጠፏትን የሚያጠፋ’ ጦርነት ራእይ 11:18) ከዚህም በተጨማሪ ይህ ጦርነት ሰላም የሰፈነበት ዓለም ማለትም ‘በአምላክ የተስፋ ቃል’ መሠረት የምንጠባበቀውን ‘ጽድቅ የሚኖርበት አዲስ ምድር’ ያመጣል።—2 ጴጥሮስ 3:13
በመሆኑ ነው። (አርማጌዶን ለምን አስፈለገ?
‘የፍቅር አምላክ’ የሆነው ይሖዋ “የሰላም ልዑል” የሆነውን ልጁን ጦርነት እንዲያካሂድ ይሾመዋል ብሎ ማሰቡ ያስቸግርህ ይሆን? (2 ቆሮንቶስ 13:11፤ ኢሳይያስ 9:6) እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸውን ምክንያት ማወቅህ ነገሮችን ግልጽ ያደርግልሃል። የመዝሙር መጽሐፍ ኢየሱስን በፈረስ ላይ እንደተቀመጠ ተዋጊ አድርጎ ይገልጸዋል። ኢየሱስ የሚዋጋው ለምንድን ነው? ክርስቶስ የሚጋልበው “ስለ እውነት፣ ስለ ትሕትና ስለ ጽድቅ” ብሎ እንደሆነ መዝሙራዊው ተናግሯል። ኢየሱስ ጦርነት የሚያካሂደው ጽድቅን ስለሚወድና ዐመፃን ስለሚጠላ ነው።—መዝሙር 45:4, 7
በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ በሰዎች ላይ ስለሚደርሰው ግፍ ምን እንደሚሰማው ይገልጻል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር ተመለከተ፤ ፍትሕ በመታጣቱም ዐዘነ። ጽድቅን እንደ ጥሩር አጠለቀ፤ የድነትን ቍር በራሱ ላይ ደፋ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤ መጐናጸፊያ እንደሚደረብም ቅናትን ደረበ።”—ኢሳይያስ 59:15, 17
ክፉ ሰዎች በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ጻድቃን ሰላምና ደኅንነት ሊኖራቸው አይችልም። (ምሳሌ 29:2፤ መክብብ 8:9) እንደ እውነቱ ከሆነ ምግባረ ብልሹነትንና ክፋትን፣ ድርጊቱን ከሚፈጽሙት ሰዎች ለይተን ማየት አንችልም። በመሆኑም ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ ሊገኝ የሚችለው ክፉ ሰዎች ከተወገዱ ብቻ ነው። ሰሎሞን “ክፉ ሰው ለጻድቅ . . . ወጆ ይሆናል” በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 21:18
ዳኛው አምላክ እንደመሆኑ መጠን በክፉዎች ላይ የሚወሰደው እያንዳንዱ እርምጃ ጽድቅ የሚንጸባረቅበት እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አብርሃም “የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?” ሲል የጠየቀ ሲሆን ይሖዋ ምንጊዜም ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግ ተገንዝቧል! (ዘፍጥረት 18:25) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ክፉዎችን በማጥፋት እንደማይደሰትና ይህን እርምጃ እንደ መጨረሻ አማራጭ እንደሚጠቀምበት ይገልጻል።—ሕዝቅኤል 18:32፤ 2 ጴጥሮስ 3:9
አርማጌዶንን በቁም ነገር መመልከት
በዚህ ወሳኝ ጦርነት ከማን ጎን እንቆማለን? አብዛኞቻችን ምንም ሳናመነታ ከጥሩ ኃይሎች ጎን እንደምንሰለፍ እንገልጽ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ እንደምናደርግ እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ነቢዩ ሶፎንያስ “ጽድቅንና ትሕትናን ፈልጉ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቶናል። (ሶፎንያስ 2:3) ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” መሆኑን ተናግሯል።—1 ጢሞቴዎስ 2:4
ለመዳን የሚያስፈልገው የመጀመሪያው እርምጃ ስለ ይሖዋ እንዲሁም ክፋትን ከምድር ላይ ለማስወገድ ስላለው ዓላማ እውነቱን መማር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጽድቅን ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ ይህም የአምላክን ሞገስና ጥበቃ ያስገኝልናል።
እነዚህን አስፈላጊ እርምጃዎች ከወሰድን በሰው ልጆች መካከል የሚካሄዱ ጦርነቶችን የሚያስቀረውን አርማጌዶንን በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን። ይህ ውጊያ ሲደመደም በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ጦርነትን ለመረዳት የሚያዳግት ቀፋፊ ተግባር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። “ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም።”—ኢሳይያስ 2:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.17 አርማጌዶን ቃል በቃል የሚገኝ ቦታ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ገጽ 31 ላይ የሚገኘውን “አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ በሰው ልጆች ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚወስደው እርምጃ አርማጌዶን ይባላል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጌዴዎንና ወታደሮቹ በመጊዶ አቅራቢያ በተደረገ ወሳኝ ውጊያ ድል ተቀዳጅተዋል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጊዶ
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከአርማጌዶን በኋላ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች ጦርነትን ለመረዳት የሚያዳግት ቀፋፊ ተግባር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለመዳን የሚያስፈልገው የመጀመሪያው እርምጃ ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው እውነቱን መማር ነው