በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከፍ አድርጎ የሚመለከተን አምላክ

ከፍ አድርጎ የሚመለከተን አምላክ

ወደ አምላክ ቅረብ

ከፍ አድርጎ የሚመለከተን አምላክ

ሉቃስ 12:6, 7

‘ልባችን በእኛ ላይ ይፈርድብናል።’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ይህ ሐሳብ አንዳንድ ጊዜ ልባችን ከልክ በላይ ራሳችንን እንድንኮንን ሊያደርገን እንደሚችል ይገልጻል። እንዲያውም ልባችን፣ የአምላክን ፍቅርም ሆነ እንክብካቤ ማግኘት የማይገባን ሰዎች እንደሆንን ሁልጊዜ እንድናስብ ያደርገን ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉን ነገር ያውቃል” የሚል ማጽናኛ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 3:19, 20) አምላክ፣ እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በላይ ያውቀናል። እሱ እኛን የሚያይበት መንገድ እኛ ራሳችንን ከምንመለከትበት መንገድ በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ አምላክ ስለ እኛ ያለው አመለካከት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው፤ ታዲያ እሱ ስለ እኛ ምን አመለካከት አለው? የዚህ ጥያቄ መልስ ኢየሱስ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች በተናገረው ልብ የሚነካ ምሳሌ ላይ ይገኛል።

ኢየሱስ በአንድ ወቅት፣ ‘ሁለት ድንቢጦች በአንድ ሳንቲም እንደሚሸጡ’ ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 10:29, 31) ሉቃስ 12:6, 7 እንደሚገልጸው ደግሞ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “አምስት ድንቢጦች በዐሥር ሳንቲም [በሁለት ኢሳሪያ፣ የግርጌ ማስታወሻ] ይሸጡ የለምን? ይሁን እንጂ ከእነርሱ አንዷ እንኳ በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም። . . . እንግዲህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች የበለጠ ዋጋ አላችሁ።” ቀላል ቢሆንም ኃይለኛ መልእክት የያዘው ይህ ምሳሌ ይሖዋ እሱን የሚያመልኩ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንደሚመለከታቸው ያስተምረናል።

ድንቢጥ፣ ለምግብነት ከሚውሉ ወፎች ሁሉ በጣም ርካሽ ናት። ኢየሱስ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሴቶች ምናልባትም እናቱ፣ ቤተሰባቸውን ለመመገብ እነዚህን ትንንሽ ወፎች ከገበያ ሲገዙ እንደተመለከተ ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ሰው፣ በዛሬው ጊዜ ከአምስት ሳንቲም ያነሰ ዋጋ ባለው አንድ ኢሳሪያ ሁለት ድንቢጦችን መግዛት ይችል ነበር። እነዚህ ወፎች በጣም ርካሽ ከመሆናቸው የተነሳ በሁለት ሳንቲም አራት ሳይሆን አምስት ድንቢጦችን መግዛት ይችላል፤ አንደኛዋ ድንቢጥ በምርቃት መልክ ትሰጥ ነበር።

ኢየሱስ አንዷም ድንቢጥ ብትሆን “በእግዚአብሔር ዘንድ አትዘነጋም” ወይም ያለ አምላክ ፈቃድ “ምድር ላይ አትወድቅም” ብሏል። (ማቴዎስ 10:29) ይሖዋ አንዷ ድንቢጥ እንኳ ጉዳት ደርሶባት ስትወድቅ አሊያም ምግብ ፍለጋ መሬት ላይ ስታርፍ ይመለከታል። ይሖዋ እነዚህን ብዙም ጥቅም የሌላቸው የሚመስሉ ወፎች ዋጋ እንደሌላቸው በማሰብ ከመፍጠር ወደኋላ አላለም፤ አሁንም ዋጋ እንደሌላቸው በማሰብ አይዘነጋቸውም። እንዲያውም እነዚህ ወፎች ውድ ሕያዋን ፍጥረታት ስለሆኑ አምላክ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። የኢየሱስ ምሳሌ የያዘውን ትምህርት አስተዋልክ?

ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ሁለት ነገሮችን በማወዳደር አነስተኛ ስለሆነው ነገር የሰጠው ትምህርት ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ እንዴት እንደሚሠራ ይጠቁም ነበር። ለምሳሌ ያህል እንዲህ ብሎ ነበር:- “ቁራዎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ ማከማቻ ወይም ጐተራ የላቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ይመግባቸዋል። እናንተማ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን?” (ሉቃስ 12:24) ኢየሱስ ድንቢጦችን አስመልክቶ በተናገረው ምሳሌ ላይ ሊያስተላልፈው የፈለገው ትምህርት አሁን ግልጽ ነው:- ይሖዋ ለእነዚህ ትንንሽ ወፎች የሚያስብ ከሆነ እሱን ለሚወዱትና ለሚያመልኩት የሰው ልጆችማ ምን ያህል የበለጠ ያስባል!

ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ መረዳት እንደምንችለው “ከልባችን ይልቅ ታላቅ” በሆነው አምላክ ዓይን ውስጥ የማንገባ እንዲሁም የእሱን እንክብካቤ ማግኘት ፈጽሞ የማይገባን ሰዎች እንደሆንን አድርገን ማሰብ አይኖርብንም። እኛ ስለ ራሳችን የማናየውን ነገር ፈጣሪያችን እንደሚመለከት ማወቅ የሚያጽናና አይደለም?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ድንቢጦች:- © ARCO/D. Usher/age fotostock