በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥንቷ የልድያ መንግሥት በዛሬው ጊዜ የምታሳድረው ተጽዕኖ

የጥንቷ የልድያ መንግሥት በዛሬው ጊዜ የምታሳድረው ተጽዕኖ

የጥንቷ የልድያ መንግሥት በዛሬው ጊዜ የምታሳድረው ተጽዕኖ

ስለ ጥንቷ የልድያ መንግሥት ፈጽሞ ሰምተህ አታውቅ ይሆናል፤ በመሆኑም የልድያ ሰዎች ያገኙት ነገር በዓለም ላይ ንግድ የሚካሄድበትን መንገድ እንዴት እንደለወጠው ስታውቅ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ሰዎችም በልድያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው ነገር፣ አንድን ግራ የሚያጋባ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ለመረዳት እንደሚያስችል ሲያውቁ ይገርማቸው ይሆናል። የልድያ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደረጉት ነገር ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት ጨርሶ ተረስታ ስለነበረችው ስለ ልድያ መንግሥት አንዳንድ ነገሮችን መመልከቱ ጠቃሚ ነው።

የልድያ ነገሥታት በአገሪቱ ዋና ከተማ በሰርዴስ ሆነው ይገዙ ነበር፤ ሰርዴስ የምትገኘው በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ተብላ በምትጠራው በትንሿ እስያ ምዕራባዊ ክፍል ነበር። የልድያ የመጨረሻው ንጉሥ ክሪሰስ ከፍተኛ ሀብት አከማችቶ የነበረ ቢሆንም በ546 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ፋርስን ይገዛ የነበረው ታላቁ ቂሮስ ግዛቱን ወሰደበት፤ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የባቢሎንን መንግሥት ድል ያደረገውም ይኸው ቂሮስ ነበር።

አዲስ ነገር የመፍጠር ችሎታ ያላቸው የልድያ ነጋዴዎች በሳንቲሞች በመጠቀም የመጀመሪያዎቹ እንደሆኑ ይነገራል። ሰዎች ለረጅም ጊዜ ወርቅንና ብርን እንደ ገንዘብ ይጠቀሙባቸው ነበር፤ ሆኖም ሰዎች የሚገበያዩበት ወርቅ ክብደት እኩል ባለመሆኑ የንግድ ልውውጥ በሚያደርጉበት ጊዜ ሁሉ ገንዘቡን መመዘን ነበረባቸው። ለአብነት ያህል፣ በእስራኤል የአምላክ ነቢይ የነበረው ኤርምያስ መሬት ከገዛ በኋላ ‘ዐሥራ ሰባት ሰቅል ብር መዝኖ እንደሰጠ’ ጽፏል።—ኤርምያስ 32:9

በኤርምያስ ዘመን በልድያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ንግድን ቀለል ባለ መንገድ ለማካሄድ የሚያስችል ዘዴ አግኝተው ነበር፤ እነዚህ ሰዎች በሳንቲም መጠቀም የጀመሩ ሲሆን የሳንቲሞቹ ክብደት ቋሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ሲሉ በእያንዳንዱ ሳንቲም ላይ የባለ ሥልጣን ማኅተም ያደርጋሉ። በልድያ የመጀመሪያዎቹ ሳንቲሞች የተሠሩት ኤሌክትረም ተብሎ ከሚጠራ በተፈጥሮ የሚገኝ የወርቅና የብር ቅይጥ ነበር። ክሪሰስ ሲነግሥ እነዚህ ሳንቲሞች በንጹሕ ብርና በንጹሕ ወርቅ በተሠሩ ሳንቲሞች እንዲተኩ አደረገ። የልድያ ሰዎች ከሁለት የተለያዩ ማዕድኖች የተሠሩ ሳንቲሞችን የሚጠቀሙበት አሠራር የፈጠሩ ሲሆን 12 የብር ሳንቲሞች ከአንድ የወርቅ ሳንቲም ጋር እኩል ዋጋ ነበራቸው። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ የንግድ ልውውጥ አስተማማኝ አልነበረም፤ አንዳንዶች ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ማዕድኖችን ከወርቅ ጋር በመቀላቀል የሐሰት ሳንቲሞችን ይሠሩ ነበር። በመሆኑም ነጋዴዎች፣ ወርቁ ንጹሕ መሆኑን ለመፈተን የሚያስችላቸው ቀላል ዘዴ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር።

የልድያ ሰዎች በአካባቢያቸው የሚገኝ የልድያ ድንጋይ ተብሎ የሚጠራ ጥቁር ድንጋይ ይህን ችግር ለመፍታት እንደሚያስችላቸው ተገነዘቡ። በተወሰነ መጠን ሸካራ በሆነው በዚህ ወጥ ድንጋይ ላይ አንድ ሳንቲም ሲፈገፈግ ምልክት ይተዋል። በሳንቲሙ ውስጥ ምን ያህል ወርቅ እንዳለ ለማወቅ ሳንቲሙ ድንጋዩ ላይ ሲፈገፈግ የሚተወውን ምልክት ለናሙና የተዘጋጁ ሌሎች ሳንቲሞች በድንጋዩ ላይ ሲፈገፈጉ ከሚተዉት ምልክት ጋር ያወዳድሩታል፤ ለናሙና የተዘጋጁት ሳንቲሞች ውስጥ ያለው የወርቅ መጠን የታወቀ በመሆኑ ምልክቶቹን በማስተያየት በአንድ ሳንቲም ውስጥ ያለውን የወርቅ መጠን ለማወቅ ይቻላል። የሳንቲሞች ጥራት በልድያ ድንጋይ የሚፈተንበት ይህ ዘዴ በሳንቲም መጠቀም አስተማማኝ እንዲሆን አስችሏል። ታዲያ ስለዚህ ጥቁር ድንጋይ ማወቃችን መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ምሳሌያዊ ጥቁር ድንጋይ

የወርቅን ጥራት ለመፈተን በጥቁር ድንጋይ መጠቀም በነጋዴዎች ዘንድ እየተለመደ ሲመጣ “ጥቁር ድንጋይ” የሚለው ቃል የመፈተኛ ዘዴን ያመለክት ጀመር። የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በተጻፉበት በግሪክኛ ቋንቋ፣ ይህ ቃል ሰዎች በሚመረመሩበት ጊዜ የሚደርስባቸውን ሥቃይ ለማመልከትም ይሠራበት ነበር።

እስረኞችን የሚያሠቃዩት የወኅኒ ቤት ኃላፊዎች ስለሆኑ “ጥቁር ድንጋይ” ከሚለው ሐረግ የተወሰደው ቃል እነዚህን ሰዎች ለማመልከትም ያገለግል ነበር። በመሆኑም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ፣ ለተደረገለት ነገር አመስጋኝ ያልነበረው ባሪያ “ለአሳሪዎች” ወይም በአንዳንድ ትርጉሞች መሠረት “ለሚያሠቃዩት” እንደተሰጠ የሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እናገኛለን። (ማቴዎስ 18:34የ1980 ትርጉም፣ የ1954 ትርጉም) ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒድያ ይህንን ጥቅስ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “መታሰር በራሱ እንደ ‘ሥቃይ’ ይታይ የነበረ ይመስላል (ደግሞም ሥቃይ እንደሚያስከትል የታወቀ ነው)፤ ‘የሚያሠቃዩት’ የተባሉትም አሳሪዎቹ ናቸው።” ይህ ሐሳብ አንድን ትኩረት የሚስብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለመረዳት ያስችለናል።

እንቆቅልሹ ተፈታ

መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ቅን ሰዎች ‘የሰይጣን መጨረሻ ምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ግራ ሲያጋባቸው ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።” (ራእይ 20:10) ይሖዋ አንድን ፍጡር ለዘላለም ያሠቃያል ብሎ ማሰብ ከፍቅሩና ከፍትሑ ጋር ይጋጫል። (ኤርምያስ 7:31) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ለዘላለም መኖርን እንደ ስጦታ እንጂ እንደ ቅጣት አድርጎ አይገልጸውም። (ሮሜ 6:23) እንግዲያው ራእይ 20:10 በምሳሌያዊ መንገድ እንደተጻፈ በግልጽ መመልከት ይቻላል። አውሬውና የእሳቱ ባሕር ምሳሌያዊ ናቸው። (ራእይ 13:2፤ 20:14) ታዲያ ከላይ የተጠቀሰው ሥቃይ ምሳሌያዊ ነው? ይህ አባባል ምን ትርጉም አለው?

ከላይ እንዳየነው ሥቃይ የሚለው የግሪክኛ ቃል “ጥቁር ድንጋይ” ከሚለው ሐረግ የተወሰደ ሲሆን መታሰር የሚያስከትለውን “ሥቃይ” ሊያመለክት ይችላል። በመሆኑም ሰይጣን ለዘላለም እንደሚሠቃይ የሚገልጸው ጥቅስ፣ መውጫ በሌለው ወኅኒ ቤት ውስጥ የተዘጋበት ያህል በሞት አማካኝነት ለዘላለም እንደሚዘጋበት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

የልድያ ሰዎች ይጠቀሙበት የነበረው ጥቁር ድንጋይ፣ ከአምላክ ፍቅር ጋር በማይጋጭ ሁኔታ ሰይጣን ለዘላለም ስለሚደርስበት “ሥቃይ” ተጨማሪ ነገር ለመረዳት ያስችለናል። በልድያ፣ ጥቁሩ ድንጋይ የገንዘቡን ትክክለኛነት ለመፈተን ያገለግል እንደነበረ ሁሉ በሰይጣን ላይ የሚደርሰው ዘላለማዊ “ሥቃይ” ወይም ሞት ወደፊት በይሖዋ ላይ ዓመጽ ቢነሳ እንደ ዘላለማዊ ማስረጃ ሆኖ ያገለግላል። ከዚያ በኋላ የይሖዋን አገዛዝ የሚገዳደር ማንኛውም አካል ስህተት መሆኑን ለመፈተን ወይም ለማረጋገጥ ረዘም ያለ ጊዜ መስጠት አስፈላጊ አይሆንም።

የልድያ ሰዎች የፈጠሩት የወርቅን ጥራት በጥቁር ድንጋይ የመፈተን ዘዴ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ነጋዴዎች መጠቀም የጀመሩበትን ምክንያትና በዚህ ዘዴ ላይ የተመሠረቱትን ምሳሌያዊ አገላለጾች መረዳታችን ሰይጣን ምን እንደሚደርስበት ለማወቅ ያስችለናል። አምላክ ዓመጽ ቢነሳ እንደገና መታገሥ እንዳያስፈልገው በሰይጣን ላይ የደረሰው ነገር እንደ ጥቁሩ ድንጋይ የፍርድ መፈተኛ ሆኖ ለዘላለም ያገለግላል።—ሮሜ 8:20

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰይጣን በምሳሌያዊ ሁኔታ መሠቃየቱ በእሱ ላይ የተበየነው ፍርድ እንደ ጥቁሩ ድንጋይ ለዘላለም መፈተኛ ሆኖ እንደሚያገለግል ያሳያል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ጥቁር ባሕር

ልድያ

ሰርዴስ

የሜድትራኒያን ባሕር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥንቷ ሰርዴስ ፍርስራሽ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት ጊዜ ገንዘብን ለመመዘን በሚዛን ይጠቀሙ ነበር

[ምንጭ]

E. Strouhal/Werner Forman/Art Resource, NY

[በገጽ 22, 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥቁር ድንጋይ የወርቅን ጥራት የመፈተን ዘዴ በዘመናችንም ይሠራበታል

[ምንጭ]

ሳንቲሞች:- Courtesy Classical Numismatic Group, Inc.; touchstone: Science Museum/Science & Society Picture Library

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከኤሌክትረም የተሠራው ሳንቲም:- Courtesy Classical Numismatic Group, Inc.