በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ ማየት የተሳነውን ሰው ቀስ በቀስ የፈወሰው ለምንድን ነው?

በማርቆስ 8:22-26 ላይ ኢየሱስ አንድ ማየት የተሳነውን ሰው እንደፈወሰ እናነባለን። ዘገባው እንደሚናገረው መጀመሪያ ኢየሱስ በሰውየው ዓይኖች ላይ ምራቅ በማድረግ ምን እንደሚታየው ጠየቀው። ሰውየው፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” በማለት የሰጠው ምላሽ እንደሚያሳየው ግለሰቡ በመጠኑም ቢሆን ግራ ተጋብቶ ነበር። ከዚያም ኢየሱስ እንደገና የሰውየውን ዓይኖች ዳሰሳቸው፤ በዚህ ጊዜ “ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ።” ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ሰውየውን የፈወሰው ቀስ በቀስ ወይም ደረጃ በደረጃ ነበር። ለምን?

ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የተሟላ መልስ ባይሰጥም ጉዳዩን አስመልክቶ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚታሰብ አንድ ማብራሪያ መመልከት እንችላለን። ለዓመታት ምናልባትም ዕድሜ ልኩን ማየት ተስኖት የነበረ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያይ ራሱን ከሁኔታዎች ጋር ለማላመድ ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅበታል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በአንድ ወቅት ሰዎች ድንክ ፈረሶችን ማዕድን ለማውጣት ሥራ ይጠቀሙባቸው ስለነበር በቆፈሯቸው ጉድጓዶች ውስጥ ያቆዩአቸው ነበር። ፈረሶቹ ከጨለማው ጋር በጣም ከመላመዳቸው የተነሳ ከጉድጓዱ ሲወጡ እንደገና ከቀኑ ብርሃን ጋር ለመላመድ አንድ ሙሉ ቀን ያህል ይወስድባቸው ነበር። ማየት ተስኖት የነበረ ሰው ደግሞ ከዚያ የበለጠ ጊዜ እንደሚወስድበት የተረጋገጠ ነው። በዘመናችን የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ማየት ተስኗቸው የነበሩ ሰዎችን ዓይን ችግር በማስተካከል ማየት እንዲጀምሩ ያደረጉባቸው የተወሰኑ አጋጣሚዎች አሉ። ሆኖም ብዙ ጊዜ ሕመምተኞቹ ከዓይናቸው ወደ አእምሯቸው የሚተላለፈው መረጃ እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ ተቸግረዋል። በዙሪያቸው ያሉት ነገሮች ቀለም፣ ቅርጽና አንዱ ከሌላው ያለው ርቀት ድብልቅልቅ ስለሚልባቸው ሌላው ቀርቶ በጣም የተለመዱ ነገሮችን እንኳ መለየት አልቻሉም። እርግጥ ነው፣ ከጊዜ በኋላ አእምሯቸው፣ ዓይናቸው የሚያየውን ነገር መረዳት ችሏል።

ኢየሱስ በዚህ ረገድ ሰውየውን ደረጃ በደረጃ መፈወሱ ለግለሰቡ የነበረውን ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያንጸባርቅ ነው። በመጨረሻም ሰውየው ትርጉም በሚሰጥ መንገድ “ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ።”

በኢየሱስ ዘመን ከጥቅልል ማንበብ አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው?

ጥቅልሎችን ለመሥራት ያገለግሉ የነበሩት ገጾች መጠን በአብዛኛው ከ23 እስከ 28 ሴንቲ ሜትር ርዝመትና ከ15 እስከ 23 ሴንቲ ሜትር ስፋት ነበራቸው። ሰዎች እነዚህን ገጾች ጎን ለጎን በማጣበቅ ወይም በክር በመስፋት ያገጣጥሟቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግን ረጃጅም ገጾችን ይጠቀሙ ነበር። በሙት ባሕር የተገኘው የኢሳይያስ ጥቅልል 17 ብራናዎችን በመገጣጠም የተሠራ ሲሆን አሁን ባለበት ሁኔታ ሲለካ አጠቃላይ ርዝመቱ ወደ 7 ሜትር ይጠጋል። ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኵራብ ውስጥ ያነበበው የኢሳይያስ ጥቅልል ተመሳሳይ ርዝመት ሳይኖረው አይቀርም።—ሉቃስ 4:16, 17

ከላይ ያለውን ሐሳብ በተመለከተ አለን ሚለርድ ዲስከቨሪስ ፍሮም ዘ ታይም ኦቭ ጂሰስ በተባለ መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “አንባቢው መጽሐፉን [ጥቅልሉን] ከያዘ በኋላ ጫፉን በቀኝ እጁ ይዞ በግራ እጁ ይተረትረዋል። ከዚያም ዓምድ በዓምድ እያነበበ በቀኝ በኩል እንደገና ይጠቀልለዋል። ኢየሱስ፣ ኢሳይያስ 61 ማለትም በምኵራብ አንብቦት በነበረው ምዕራፍ ላይ ለመድረስ የጥቅልሉን አብዛኛውን ክፍል በግራ በኩል ተርትሮ እንደገና በቀኝ በኩል ጠቅልሎ መሆን አለበት።”

በዚያን ጊዜ የኢሳይያስ መጽሐፍ እንደ አሁኑ በምዕራፍና በቁጥር አልተከፋፈለም። ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኵራብ ውስጥ የኢሳይያስ ጥቅልል በተሰጠው ጊዜ ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በኢሳይያስ 61:1, 2 ላይ የሚገኘውን ቦታ ፈልጎ ማውጣት ነበረበት። ኢየሱስ ሊያነበው የፈለገውን ‘ክፍል [በቀላሉ] ማግኘቱ’ የአምላክን ቃል ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበር ያሳያል።