ልጆቻችሁን አስተምሩ
ጢሞቴዎስ—አምላክን ለማገልገል ዝግጁና ፈቃደኛ ነበር
“ዝግጁ ነህ?” ተብለህ ተጠይቀህ ታውቃለህ?— እንዲህ ብሎ የጠየቀህ ሰው ለሥራ መዘጋጀትህን ለማወቅ ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ግለሰቡ ‘የማጥኛ መጻሕፍትህን ይዘሃል? ትምህርቱን አንብበሃል?’ ለማለት ፈልጎ ይሆናል። ቀጥለን እንደምንመለከተው ጢሞቴዎስ ዝግጁ ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ጢሞቴዎስ ለማገልገል ፈቃደኛ ነበር። ይህ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?— ጢሞቴዎስ አምላክን እንዲያገለግል ሲጋበዝ “እነሆኝ፤ እኔን ላከኝ” ካለው የአምላክ አገልጋይ ጋር ተመሳሳይ ዝንባሌ ነበረው። (ኢሳይያስ 6:8) ጢሞቴዎስ፣ አምላክን ለማገልገል ዝግጁና ፈቃደኛ ስለነበር አስደሳች ሕይወት መርቷል። ስለ ጢሞቴዎስ ታሪክ መስማት ትፈልጋለህ?—
ጢሞቴዎስ የተወለደው ከኢየሩሳሌም በመቶዎች ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በልስጥራን ነበር። አያቱ ሎይድና እናቱ ኤውንቄ ትጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበሩ። ጢሞቴዎስ ሕፃን በነበረበት ጊዜ እንኳ ስለ አምላክ ቃል ያስተምሩት ነበር።—2 ጢሞቴዎስ 1:5፤ 3:15
ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ሳይሆን አይቀርም ሐዋርያው ጳውሎስ ከበርናባስ ጋር ሆኖ ወደ ልስጥራን ሄደ፤ ይህ ደግሞ ጳውሎስ ካደረጋቸው ረጃጅም የስብከት ጉዞዎች መካከል የመጀመሪያው ነበር። የጢሞቴዎስ እናትና አያት ክርስቲያኖች የሆኑት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራን ምን ችግር እንዳጋጠማቸው መስማት ትፈልጋለህ?— ክርስቲያኖችን የሚጠሉ ሰዎች ጳውሎስን በድንጋይ ከወገሩት በኋላ የሞተ መስሏቸው ጎትተው ከከተማው አወጡት።
ጳውሎስ፣ የሚያስተምረው ትምህርት ትክክል መሆኑን ያምኑ የነበሩ ሰዎች ከበውት እንዳለ ተነሳ። በሚቀጥለው ቀን ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራንን ለቀው ሄዱ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ወደ ከተማዋ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ንግግር አቀረበ፤ እንዲሁም ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 14:8-22) እዚህ ላይ ጳውሎስ ምን ማለት እንደፈለገ ታውቃለህ?— አንዳንድ ግለሰቦች፣ አምላክን በሚያገለግሉ ሰዎች ላይ ችግር እንደሚያደርሱ እየተናገረ ነበር። ቆየት ብሎ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በማለት ጽፎለታል።—2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ ዮሐንስ 15:20
ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራንን ለቀው ከሄዱ በኋላ ወደ አገራቸው ተመለሱ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ጳውሎስ፣ ከዚህ ቀደም በሄደባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ አዳዲስ ደቀ መዛሙርትን ለማበረታታት ሲላስን ይዞት ሄደ። ልስጥራን ሲደርሱ ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስን ድጋሚ ማየት በመቻሉ እንዴት ተደስቶ ይሆን! ጢሞቴዎስ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር እንዲያገለግል ሲጋበዝ ከዚያ የበለጠ ተደስቶ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ጢሞቴዎስም ግብዣውን ተቀበለ። አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁና ፈቃደኛ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 15:40 እስከ 16:5
ሦስቱም አንድ ላይ ሆነው ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው ከተጓዙ በኋላ በጀልባ ተሳፈሩ። ከጀልባ ከወረዱ በኋላ በግሪክ ወደምትገኘው ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ። በዚያም ብዙዎች ክርስትናን ተቀበሉ። ሌሎች ግን ስለተናደዱ በከተማው ውስጥ ሁከት እንዲነሳ አደረጉ። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ቤርያ ሄዱ።—የሐዋርያት ሥራ 17:1-10
ጳውሎስ በተሰሎንቄ የነበሩት አዳዲስ አማኞች ሁኔታ ስላሳሰበው ጢሞቴዎስን መልሶ ላከው። እንዲህ ያደረገው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— ቆየት ብሎ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ‘ማንም ተስፋ እንዳይቆርጥ እንዲያጸናችሁና እንዲያበረታችሁ ነው’ ብሏቸዋል። ጳውሎስ ወጣቱን ጢሞቴዎስን እንዲህ ወዳለ አደገኛ ስፍራ የላከው ለምን ይመስልሃል?— በዚያ ያሉት ተቃዋሚዎች ጢሞቴዎስን በደንብ የማያውቁት ከመሆኑም ሌላ ጢሞቴዎስ ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኛ ነበር። ይህ ደግሞ ትልቅ ድፍረት ይጠይቃል! ታዲያ ጢሞቴዎስ ያደረገው ጉብኝት ምን ውጤት አስገኘ? ጢሞቴዎስ ወደ ጳውሎስ ሲመለስ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ምን ያህል ታማኝ እንደሆኑ ለጳውሎስ ነገረው። በመሆኑም ጳውሎስ “በእናንተ ተጽናናን” ብሎ ጻፈላቸው።—1 ተሰሎንቄ 3:2-7
ጢሞቴዎስ ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ከጳውሎስ ጋር አብሮ አገልግሏል። በኋላም ጳውሎስ በሮም ታሰረ፤ ከእስር ከተፈታ ብዙም ያልቆየው ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር ለመሆን ወደዚያ ሄደ። ጳውሎስ በእስር ሳለ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጻፈላቸው፤ ይህን ያደረገው ጢሞቴዎስን እንደ ጸሐፊው አድርጎ በመጠቀም ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏቸዋል:- ‘ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገደው እንደ እርሱ ያለ ማንም ስለሌለኝ ጢሞቴዎስን ወደ እናንተ ልልክላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።’—ፊልጵስዩስ 2:19-22፤ ዕብራውያን 13:23
ጢሞቴዎስ ይህን ሲሰማ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ጢሞቴዎስ፣ አምላክን ለማገልገል ዝግጁና ፈቃደኛ መሆኑ በጳውሎስ ዘንድ እጅግ እንዲወደድ አድርጎታል። አንተም እንደ ጢሞቴዎስ እንድትሆን ምኞታችን ነው።