በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኖኅ እና የጥፋት ውኃ አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ?

ኖኅ እና የጥፋት ውኃ አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ?

ኖኅ እና የጥፋት ውኃ አፈ ታሪክ ነው ወይስ እውነተኛ ታሪክ?

ሰዎች እርስ በርስ ተስማምተው የሚኖሩበትን እንዲሁም ጦርነት፣ ወንጀልም ሆነ ጭቆና የሌለበትን የተሻለ ዓለም ለመመልከት ትናፍቃለህ? ከሆነ፣ አንድን ታሪካዊ ዘገባ በመመርመር ማበረታቻ ማግኘት ትችላለህ፤ ምናልባት ይህን ታሪክ በደንብ ታውቀው ይሆናል። ታሪኩ ጥሩ ሰው ስለነበረው ስለ ኖኅ የሚገልጸው ዘገባ ነው፤ ኖኅ ክፉዎችን ጠራርጎ ካስወገደው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ራሱንና ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ ሠርቷል።

የኖኅን ታሪክ ያህል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ታሪክ የለም ማለት ይቻላል። በኖኅ ዘመን ስለተከሰተው ሁኔታ የሚገልጸው ዘገባ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የዘፍጥረት መጽሐፍ ከምዕራፍ 6 እስከ 9 ላይ ሠፍሯል፤ ይኸው ታሪክ በቁርዓን ውስጥ የሚገኝ ከመሆኑም ሌላ በምድር ዙሪያ የሚገኙ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሕዝቦች ስለ ኖኅ የሚናገሩ አፈ ታሪኮች አሏቸው። የጥፋት ውኃው በእርግጥ ተከስቷል? ወይስ ሰዎች ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ ለማበረታታት የተነገረ የፈጠራ ታሪክ ነው? የሃይማኖት ምሑራንና የሳይንስ ሊቃውንት በዚህ ጉዳይ ላይ ለበርካታ ዘመናት ሲከራከሩ ቆይተዋል። ያም ሆኖ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ክንውን፣ እውነተኛ ታሪክ እንጂ አፈ ታሪክ እንዳልሆነ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎችን ይዟል። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

የዘፍጥረት ዘገባ የጥፋት ውኃው የጀመረበትን፣ መርከቧ ያረፈችበትንና ውኃው ከምድር ላይ የደረቀበትን ዓመት፣ ወርና ቀን በትክክል የሚናገር ከመሆኑም ባሻገር መርከቧ የት እንዳረፈች ይገልጻል። በተጨማሪም የመርከቧን አሠራር፣ መጠኗን እና የተሠራችባቸውን ቁሳቁሶች አስመልክቶ የተሰጡት ዝርዝር ሐሳቦች ትክክል ናቸው። ከዚህ በተቃራኒ ግን አፈ ታሪኮች የሚሰጡት ማብራሪያ አብዛኛውን ጊዜ የተድበሰበሰ ነው።

ስለ ትውልድ ሐረግ የሚዘረዝሩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ ኖኅ በእርግጥ በሕይወት የኖረ ሰው መሆኑን ያረጋግጣሉ። (1 ዜና መዋዕል 1:4፤ ሉቃስ 3:36) እነዚህን ዘገባዎች ያጠናቀሩት ዕዝራና ሉቃስ ደግሞ ጠንቃቃ ጸሐፊዎች ነበሩ። ሉቃስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በኖኅ የዘር ሐረግ በኩል እንደሆነ ጽፏል።

ነቢያት የነበሩት ኢሳይያስና ሕዝቅኤል እንዲሁም ክርስቲያን ሐዋርያት የነበሩት ጳውሎስና ጴጥሮስ ስለ ኖኅ ወይም ስለ ጥፋት ውኃው ጠቅሰው ጽፈዋል።—ኢሳይያስ 54:9፤ ሕዝቅኤል 14:14, 20፤ ዕብራውያን 11:7፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ 2 ጴጥሮስ 2:5

ኢየሱስ ክርስቶስ የጥፋት ውኃን ጠቅሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው ሁሉ፣ በሰው ልጅ ዘመንም እንደዚሁ ይሆናል። ኖኅ ወደ መርከቡ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ፣ ያገቡና ይጋቡ ነበር፤ የጥፋትም ውሃ መጥቶ ሁሉንም አጠፋቸው።” (ሉቃስ 17:26, 27) የጥፋት ውኃው ያልተከሰተ ነገር ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ “በሰው ልጅ ዘመን” እንደሚፈጸም የተናገረው ሐሳብ ትርጉም የለሽ ይሆን ነበር።

ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ነገር የሚያቃልሉ “ዘባቾች” እንደሚመጡ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ጴጥሮስ ‘እነዚህ ሰዎች በኖኅ ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ እንደጠፋ ይክዳሉ’ በማለት ጽፏል። እኛስ ይህን እውነታ መካድ ይኖርብናል? በፍጹም! ጴጥሮስ አክሎ እንደጻፈው “አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል።”—2 ጴጥሮስ 3:3-7

አምላክ በኖኅ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ክፉዎችን ያጠፋል፣ የሚታዘዙትን ሰዎች ደግሞ ከጥፋቱ ይታደጋቸዋል። እኛም የኖኅን ምሳሌ ከኮረጅን ከጥፋቱ ተርፈው ወደተሻለው ዓለም ከሚገቡት ጻድቃን መካከል ልንሆን እንችላለን።