በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኖኅ የአምላክን ሞገስ እንዲያገኝ ያስቻለው ምንድን ነው? ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

ኖኅ የአምላክን ሞገስ እንዲያገኝ ያስቻለው ምንድን ነው? ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

ኖኅ የአምላክን ሞገስ እንዲያገኝ ያስቻለው ምንድን ነው? ይህ ጉዳይ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው?

አብዛኞቻችን ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን መልእክት የሰማንበትን ጊዜ እናስታውሳለን። መልእክቱን የት እንደሰማንና በወቅቱ ምን እያደረግን እንደነበረ ብቻ ሳይሆን ምን እንደተሰማን ጭምር አንረሳም። ኖኅ፣ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ጌታ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ መልእክት የተቀበለበትን ቀን ፈጽሞ እንደማይረሳው ጥርጥር የለውም። ደግሞስ ከአምላክ ከመጣ መልእክት የበለጠ ምን አስፈላጊ መልእክት ሊኖር ይችላል? ይሖዋ “ሰውን ሁሉ” ለማጥፋት እንደወሰነ ለኖኅ ነገረው። ኖኅ ራሱን፣ ቤተሰቡንና እያንዳንዱን የእንስሳ ዝርያ ከጥፋቱ ለማዳን ሲል ግዙፍ መርከብ መሥራት ይጠበቅበት ነበር።—ዘፍጥረት 6:9-21

በዚህ ጊዜ ኖኅ ምን ተሰማው? መልእክቱን ሲሰማ ተደሰተ ወይስ አጉረመረመ? ይህንንስ ለባለቤቱና ለቤተሰቡ የነገራቸው እንዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምንም አይናገርም። ከዚህ ይልቅ “ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” በማለት ይነግረናል።—ዘፍጥረት 6:22

ይህ ጥቅስ፣ ኖኅ የአምላክን ሞገስ ካስገኙለት ምክንያቶች መካከል አንዱን እንድናውቅ ስለሚረዳን በእርግጥም ትኩረት ልንሰጠው ይገባል:- ኖኅ አምላክ የጠየቀውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኗል። (ዘፍጥረት 6:8) ኖኅ በአምላክ ዘንድ ሞገስ እንዲያገኝ ያስቻለው ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቃችን አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም አምላክ በቅርቡ ክፋትን ከምድር ላይ ሲያስወግድ በሕይወት መትረፋችን የተመካው እንደ ኖኅ ዓይነት ሰዎች በመሆናችን ላይ ነው። በመጀመሪያ ግን የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት የኖኅ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር እንመልከት።

አጋንንት ወደ ምድር መጡ

ኖኅ የኖረው፣ የመጀመሪያው ሰው ከተፈጠረ ከአንድ ሺህ ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ብዙዎች እንደሚያስቡት በዚያን ዘመን የነበሩት ሰዎች ሰውነታቸው በፀጉር የተሸፈነና በዋሻ ውስጥ የሚኖሩ ኋላ ቀር ፍጥረታት አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ብረትንና ናስን አቅልጠው የተለያዩ መሣሪያዎችን ማምረት የሚችሉ ሰዎች ነበሩ፤ ኖኅም መርከቧን ለመሥራት በእነዚህ መሣሪያዎች ሳይጠቀም አልቀረም። ከዚህም በተጨማሪ በዘመኑ የሙዚቃ መሣሪያዎች ነበሩ። ሰዎቹም ይጋቡ፣ ልጆችን ያሳድጉ፣ ያርሱና ከብቶችን ያረቡ ብሎም ይገበያዩ ነበር። በመሆኑም በዚያን ዘመን የነበረው ሕይወት በዛሬው ጊዜ ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው።—ዘፍጥረት 4:20-22፤ ሉቃስ 17:26-28

ይሁን እንጂ በዚያን ዘመን የነበረው ሁኔታ በዛሬው ጊዜ ካለው ጋር የማይመሳሰልባቸው መንገዶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ፣ ሰዎች በጣም ረጅም ዘመን መኖራቸው ነው። በዚያን ጊዜ አንድ ሰው ከ800 ዓመት በላይ መኖሩ የተለመደ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ 950 ዓመት፣ አዳም 930 ዓመት እንዲሁም የኖኅ አያት የነበረው ማቱሳላ 969 ዓመት ኖረዋል። *ዘፍጥረት 5:5, 27፤ 9:29

በዚያን ጊዜ የነበረው ዓለም ዛሬ ካለው የተለየ የሆነበት ሌላው መንገድ በዘፍጥረት 6:1, 2 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ።” እዚህ ላይ “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” የተባሉት ሥጋ ለብሰው በምድር ላይ ይኖሩ የነበሩት የሰማይ መላእክት ናቸው። እነዚህ መላእክት ወደ ምድር የመጡት ሰዎችን ለመጥቀም ብለው ወይም ከአምላክ ተልከው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በሰማይ የነበረውን “መኖሪያቸውን የተዉት” በምድር ላይ ከሚኖሩ ውብ ሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ነው። በዚህ መንገድ እነዚህ መላእክት አጋንንት ሆኑ።—ይሁዳ 6

ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የጾታ ፍላጎት የነበራቸው እንዲሁም ከሰው ልጆች የላቀ ኃይልና ችሎታ ያላቸው እነዚህ ዓመጸኛ አጋንንት በሰዎች ላይ በጣም መጥፎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። የሰው ዘር በጠቅላላ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ነበር ማለት ይቻላል። እነዚህ አጋንንት ዓላማቸውን ያከናወኑት ማንነቱን በመደበቅ መጥፎ ድርጊቶችን እንደሚፈጽም ወንጀለኛ በስውር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ያለ ምንም እፍረት በገሃድ በአምላክ ላይ ዓምጸዋል።

የአምላክ ልጆች የተባሉት እነዚህ መላእክት ከሴቶች ጋር የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ሲሆን ሴቶቹም ኃያላን ልጆች ወለዱ። እነዚህ ልጆች፣ በዕብራይስጥ “ኔፊሊም” ተብለው ይጠሩ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው።” (ዘፍጥረት 6:4) ኔፊሊሞች በሌሎች ዘንድ እጅግ ይፈሩ ነበር። “ኔፊሊም” የሚለው ቃል “የሚዘርሩ” ይኸውም ሌሎችን አንስተው የሚያፈርጡ ማለት ነው። ኔፊሊሞች ነፍሰ ገዳዮች ነበሩ፤ እንዲያውም ይፈጽሙት የነበረው የዓመጽ ድርጊት በጥንት ጊዜ ስለኖሩ ጀግና ሰዎች በሚናገሩ አፈ ታሪኮች ላይ ተንጸባርቋል።

ጻድቅ የነበሩ ሰዎች ሐዘን

መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን እጅግ ተስፋፍቶ ስለነበረው የሥነ ምግባር ዝቅጠት ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- ‘የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ ነበር። ምድርም በዐመፅ ተሞላች። ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበር።’—ዘፍጥረት 6:5, 11, 12

ኖኅ የኖረበት ዓለም ይህን ይመስል ነበር። ኖኅ በዙሪያው ከነበሩት ሰዎች በተቃራኒ ‘አካሄዱን ከአምላክ ጋር ያደረገ ጻድቅ ሰው ነበር።’ (ዘፍጥረት 6:9) ጻድቅ ለሆነ ሰው ዓመጸኛ በሆነ ኅብረተሰብ ውስጥ መኖር ቀላል አይደለም። ይህ የአምላክ አገልጋይ ሰዎች በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር አዝኖ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ኖኅ፣ ጻድቁ ሎጥ የነበረው ዓይነት ስሜት ሳይሰማው አልቀረም። ከጥፋት ውኃው በኋላ የኖረው ሎጥ በሥነ ምግባር በረከሱት የሰዶም ነዋሪዎች “መካከል ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው ነገር ነፍሱ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ድርጊታቸው [ትጨነቅ ነበር]።” ከዚህም በላይ ‘በሴሰኛ ድርጊታቸው ይሳቀቅ ነበር።’ (2 ጴጥሮስ 2:7, 8) ኖኅም እንዲሁ ተሰምቶት መሆን አለበት።

አንተስ በዜና ላይ የምትሰማቸው አስደንጋጭ ክስተቶች ወይም በአካባቢህ የሚኖሩ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች የሚፈጽሙት ድርጊቶች ያስጨንቁሃል? ከሆነ፣ የኖኅን ስሜት መረዳት ትችላለህ ማለት ነው። የጥፋት ውኃው የመጣው ኖኅ የ600 ዓመት ሰው በነበረበት ወቅት ነው፤ በመሆኑም ዓመጽ በነገሠበት ዓለም ውስጥ ይህን ያህል ዓመት ጸንቶ መኖር ለዚህ ጻድቅ ሰው ምን ያህል ተፈታታኝ ሊሆንበት እንደሚችል እስቲ አስበው! ኖኅ ክፋት የሚወገድበትን ጊዜ ለማየት ምንኛ ጓጉቶ ይሆን!—ዘፍጥረት 7:6

ኖኅ ከሌሎች የተለየ ለመሆን ድፍረቱ ነበረው

ኖኅ “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ . . . ከበደል የራቀ ሰው ነበር።” (ዘፍጥረት 6:9) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኖኅ ከበደል የራቀ ሰው እንደሆነ የገለጸው በዘመኑ በነበሩት ሰዎች አመለካከት ሳይሆን በአምላክ ፊት እንደሆነ ልብ በል። ከጥፋት ውኃው በፊት በነበረው ዓለም ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ግን ኖኅን እንግዳ የሆነ አስተሳሰብ እንዳለው አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይህ ሰው በብዙኃኑ አመለካከት እንዳልተመራ እንዲሁም አምላክን በማያስደስቱ መዝናኛዎችና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዳልተካፈለ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መርከቧን መሥራት ሲጀመር ሰዎች ምን ብለውት ሊሆን እንደሚችል ገምት! ሳይስቁበትና ሳያፌዙበት አይቀሩም። ለሰጣቸው ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ነበር።

ከዚህም በላይ ኖኅ በጥብቅ የሚከተላቸው እምነቶች የነበሩት ሲሆን እነዚህንም ለሌሎች ከማካፈል ወደኋላ አላለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” እንደነበር ይናገራል። (2 ጴጥሮስ 2:5) ኖኅ ተቃውሞ እንደሚያጋጥመው ጠብቆ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም። ቅድመ አያቱ ሄኖክ፣ አምላክ በክፉዎች ላይ የጥፋት ፍርዱን እንደሚያስፈጽም አስቀድሞ የተናገረ ጻድቅ ሰው ነበር። ሄኖክ ይህን መልእክት መናገሩ ስደት እንዳስከተለበት ግልጽ ቢሆንም አምላክ ተቃዋሚዎቹ እንዲገድሉት አልፈቀደም። (ዘፍጥረት 5:18, 21-24፤ ዕብራውያን 11:5፤ ይሁዳ 14, 15) ሰይጣን፣ አጋንንትና ኔፊሊም ባሉበት እንዲሁም አብዛኞቹ ሰዎች ግድ የለሽ ወይም ተቃዋሚ በሆኑበት በዚያ ዓለም ውስጥ ኖኅ ደፋር መሆንና ይሖዋ እሱን ለመጠበቅ ባለው ችሎታ ላይ መታመን አስፈልጎት ነበር።

የአምላክ አገልጋዮች ምንጊዜም ቢሆን እሱን በማያገለግሉ ሰዎች ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ በሰዎች ዘንድ ይጠላ ነበር፤ ተከታዮቹም ተመሳሳይ ነገር ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 10:22፤ ዮሐንስ 15:18) ኖኅ፣ በዘመኑ አምላክን የሚያገለግል ሰው ባይኖርም እንኳ እሱ ግን እንዲህ ለማድረግ ድፍረት አሳይቷል። በተቃዋሚዎቹ ዘንድ ተቀባይነት ከማግኘት ይልቅ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ኖኅ የአምላክን ሞገስ አግኝቷል።

ኖኅ አስተዋይ ነበር

ኖኅ ለሰዎች በመስበክ ረገድ ድፍረት እንዳሳየ ቀደም ሲል ተመልክተናል። እነዚህ ሰዎች ኖኅ ለነገራቸው መልእክት ምን ምላሽ ሰጡ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ [ከጥፋት ውኃው በፊት የነበሩት] ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ [ነበር]፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ [‘ሳያስተውሉ፣’ NW] ድንገት የጥፋት ውሃ [አጥለቀለቃቸው]።” እነዚህ ሰዎች የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው እርምጃ አልወሰዱም።—ማቴዎስ 24:38, 39

ኢየሱስ በዘመናችን ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ እንደሚሆን ተናግሯል። ይሖዋ ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ የገባውን ቃል ለመፈጸም የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ከአንድ መቶ ለሚበልጡ ዓመታት ይህንን ሲያስጠነቅቁ ኖረዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጡም በቢሊዮን የሚቆጠሩት ግን ለማስተዋል ፈቃደኞች አልሆኑም። እነዚህ ሰዎች የጥፋት ውኃው መምጣቱን የማይቀበሉትም ሆነ ትርጉሙን ችላ የሚሉት ሆነ ብለው ነው።—2 ጴጥሮስ 3:5, 13

ኖኅ ግን አስተዋይ ስለነበር ይሖዋ በነገረው መልእክት ላይ እምነት አሳድሯል። ይሖዋን መታዘዙ ደግሞ ሕይወቱን አትርፎለታል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር እግዚአብሔር ባስጠነቀቀው ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈርቶ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ።”—ዕብራውያን 11:7

ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌ

ኖኅ የሠራት መርከብ ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ የበለጠ ርዝመትና ከባለ አራት ፎቅ ሕንፃ ጋር የሚተካከል ቁመት ያላት ግዙፍ መርከብ ነበረች። መርከቧ እስከ ዛሬ ከእንጨት ከተሠሩት መርከቦች ሁሉ በጣም ትልቅ ከሆነችው ዋዮሚንግ ከተባለችው መርከብ በ30 ሜትር ትረዝማለች። የኖኅ መርከብ እንድትንሳፈፍ ብቻ ተደርጋ የተሠራች እንጂ እንደማንኛውም ዓይነት መርከብ አልነበረችም። የሆነ ሆኖ መርከቧን ለመሥራት ከፍተኛ ችሎታ ጠይቋል። መርከቧ ከውስጥም ሆነ ከውጪ በቅጥራን መለቅለቅ ነበረባት። ኖኅ መርከቧን ለመሥራት ከ50 ዓመት በላይ ሳይፈጅበት አልቀረም።—ዘፍጥረት 6:14-16

የኖኅ ሥራ ይህ ብቻ አልነበረም። ለቤተሰቡና ለእንስሳቱ ለዓመት የሚበቃ እህል ማከማቸት ነበረበት። የጥፋት ውኃው ከመጀመሩ በፊት እንስሳቱ መሰብሰብና መርከቡ ውስጥ መግባት ነበረባቸው። “ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።” ኖኅ ሁሉን ነገር ቦታ ቦታ ካስያዘ በኋላ ይሖዋ የመርከቧን በር ሲዘጋ ትልቅ እፎይታ ተሰምቶት መሆን አለበት!—ዘፍጥረት 6:19-21፤ 7:5, 16

ከዚያም የጥፋት ውኃው መጣ። ዝናቡ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ጣለ። በመርከቧ ውስጥ ያሉት ሁሉ ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ለአንድ ዓመት እዚያው መቆየት ነበረባቸው። (ዘፍጥረት 7:11, 12፤ 8:13-16) በዚህ መንገድ ክፉ ሰዎች በሙሉ ከምድር ገጽ ተጠራርገው ጠፉ። በጸዳችው ምድር ላይ ለመኖር የበቁት ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ።

መጽሐፍ ቅዱስ በኖኅ ዘመን የደረሰው ዓለም አቀፍ የጥፋት ውኃ ከፊታችን ለሚጠብቀን ጥፋት ‘ምሳሌ እንደሆነ’ ይናገራል። በምን መንገድ? የአምላክ ቃል “አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል” ይላል። በኖኅ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ከዚህም ጥፋት የሚተርፉ ሰዎች ይኖራሉ። በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ:- “ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸው . . . ያውቃል።”—2 ጴጥሮስ 2:5, 6, 9፤ 3:7

ኖኅ ክፉ በሆነ ትውልድ መካከል የኖረ ይሖዋን የሚያመልክ ጻድቅ ሰው ነበር። አምላክን ሙሉ በሙሉ ታዝዟል። ኖኅ፣ አምላክን ለማገልገል የማይፈልጉ ሰዎች እንደሚንቁትና እንደሚጠሉት ቢያውቅም ትክክል የሆነውን ለማድረግ ድፍረት ነበረው። እኛም የኖኅን ምሳሌ ከኮረጅን በአምላክ ፊት ሞገስ እናገኛለን፤ እንዲሁም ከጥፋት ተርፈን በቅርቡ ወደሚመጣው አዲስ ዓለም የመግባት ተስፋ ይኖረናል።—መዝሙር 37:9, 10

[የርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ሐምሌ 2007 ንቁ! መጽሔት ገጽ 30 ላይ የወጣውን “በእርግጥ ይህን ያህል ዓመት ኖረዋል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ኔፊሊሞች ይፈጽሙት የነበረው የዓመጽ ድርጊት ጥንታዊ በሆኑ አፈ ታሪኮች ላይ እንደተንጸባረቀ ይታመናል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የኖኅን ምሳሌ ከኮረጅን የአምላክን ሞገስ እናገኛለን

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Alinari/Art Resource, NY