በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ዛሬ ማታ ቁጭ ብዬ አነበዋለሁ”

“ዛሬ ማታ ቁጭ ብዬ አነበዋለሁ”

ከአውስትራሊያ የተላከ ደብዳቤ

“ዛሬ ማታ ቁጭ ብዬ አነበዋለሁ”

በአውስትራሊያ ስለሚገኙት ገጠራማ አካባቢዎች ስናስብ ወደ አእምሯችን የሚመጣው ጭልጥ ያለው ምድረ በዳ፣ ኃይለኛው ሙቀትና ገላጣ የሆነው ሜዳ ነው። ያም ሆኖ ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ውስጥ አንድ በመቶ ገደማ የሚሆነው ማለትም 180,000 የሚያህለው ሕዝብ የሚኖረው በእነዚህ አካባቢዎች ነው።

ልጅ ሳለሁ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት ወላጆቼ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ወደነዚህ ገጠራማ አካባቢዎች ይዘውኝ ሄደው ነበር። እጅግ ሰፊና ወጣ ገባ የሆነው ይህ አካባቢ የነበረው ውበት ከአእምሮዬ አልጠፋም። ጠንካራ ሠራተኛ የሆኑት የአካባቢው ሰዎች ደግሞ ዘና ያለ መንፈስ ያላቸው መሆኑ እንድወዳቸው አድርጎኛል። በአሁኑ ጊዜ የራሴን ቤተሰብ መሥርቻለሁ፤ ስለሆነም ባለቤቴም ሆነች የ10 እና የ12 ዓመት ልጆቼ እኔ የቀመስኩትን ደስታ እንዲያጣጥሙ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ይዣቸው ለመሄድ አሰብኩ።

ለጉዞው ዝግጅት ማድረግ

በቅድሚያ ‘ለዚህ ጉዞ ምን ያህል ገንዘብ መመደብ ይኖርብናል? እዚያስ የምንቆየው ለምን ያህል ጊዜ ነው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች በማንሳት ለጉዟችን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ጀመርን። በጉባኤያችን የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት እንዲሁም ሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አብረውን መጓዝ እንደሚፈልጉ ገለጹልን። ከዚያም ጉዟችንን ትምህርት ቤት ሲዘጋ ለማድረግ ተስማማን። በኋላም ማገልገል የምንችልበትን ቦታ ለማወቅ በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ ጻፍን። ከዚያም ጉንዲዊንዲ በተባለች ገጠራማ ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ ገለልተኛ አካባቢ እንድናገለግል ተመደብን፤ ጉንዲዊንዲ የምትገኘው እኛ ከምንኖርበት ከብሪዝበን በስተ ምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው።

በጉንዲዊንዲ ጥቂት አባላት ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መኖሩን ስናውቅ ይበልጥ ተደሰትን። ከክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ጋር ተገናኝተን የምናሳልፈው ጊዜ ጉልህ ስፍራ እንደሚይዝ ጥርጥር የለውም። በአካባቢው ለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ልንመጣ እንደሆነ ስንነግራቸው የተሰማቸው ከፍተኛ ደስታ በጉጉት እንደሚጠብቁን እንድንገነዘብ አስችሎናል።

ጉዞ ከመጀመራችን በፊት ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች ለአካባቢው ነዋሪዎች መስበክ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ተወያየን። በተለይ ደግሞ ልናገኛቸው የምንችላቸውን የአቦርጂኒ ጎሣዎች ባሕልና ልማድ ማክበር እንዳለብን ተነጋገርን። ለምሳሌ አንዳንድ ጎሣዎች፣ የሚኖሩበትን አካባቢ የኅብረተሰቡ የጋራ ቤት አድርገው ይመለከቱታል። በመሆኑም ሳያስፈቅድ ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚገባ ሰው ጨዋነት የጎደለው እንደሆነ ተደርጎ ይታያል።

በገጠራማው አካባቢ ያሳለፍነው ጊዜ

በመጨረሻም በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ቀን ደረሰ። ዕቃዎቻችንን የጫኑትን ሁለት መኪኖች ይዘን ወደ ጉንዲዊንዲ አቀናን። መጀመሪያ ላይ እርሻዎችን የተመለከትን ሲሆን ጉዟችንን እየቀጠልን ስንሄድ ግን አለፍ አለፍ ብለው የተተከሉ ባሕር ዛፎች የሚታዩባቸው በሣር የተሸፈኑ ሜዳዎችን ተመለከትን። ፀሐይዋ ጥርት ባለው ሰማይ ላይ ፍንትው ብላ ወጥታለች። ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ጉንዲዊንዲ ደረስን፤ ከዚያም ምሽቱን ለማሳለፍ ወደ አንድ ማረፊያ ሥፍራ ሄድን።

በማግስቱ እሁድ፣ ቀኑ ብሩሕ አየሩም ደስ የሚል ስለነበር የስብከቱን ሥራ ለማከናወን እጅግ ተስማሚ ነበር። በዚህ አካባቢ በበጋው ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል! በመጀመሪያ የሄድነው ካለንበት አካባቢ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ወደሚገኝ አንድ የአቦርጂኒዎች መንደር ነው። ከዚያም የመንደሩ መሪ ከሆኑት ጄኒ የተባሉ አረጋዊ ሴት ፈቃድ እንድንጠይቅ ተነገረን። እኚህ አረጋዊት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐሳብ ስናካፍላቸው በጥሞና ያዳመጡን ከመሆኑም በላይ ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ (እንግሊዝኛ) * የተባለውን መጽሐፍ በደስታ ተቀበሉን። በኋላም ለመንደሩ ነዋሪዎች እንድንሰብክ ፈቀዱልን።

የአካባቢው ልጆች የእኛን መምጣት ለማስታወቅ ከፊት ከፊታችን ይሮጡ ነበር። ያገኘናቸው ሰዎች ሁሉ መልእክታችንን በአክብሮት የተቀበሉ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንም ወስደዋል። ብዙም ሳይቆይ የያዝናቸው ጽሑፎች ያለቁብን ከመሆኑም ሌላ የጉባኤ ስብሰባ ለማድረግ ወደ ጉንዲዊንዲ የምንመለስበት ሰዓት ደርሶ ነበር። አካባቢውን ለቅቀን ከመሄዳችን በፊት ያላገኘናቸውን ሰዎች ለማነጋገር ሌላ ጊዜ ተመልሰን እንደምንመጣ ገለጽን።

የዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ግሩም ጭውውት እናደርግ ስለነበር የመንግሥት አዳራሹ ሞቅ ብሎ ነበር። በአካባቢው የሚገኙት 25 የይሖዋ ምሥክሮች፣ 30,000 ካሬ ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ገጠራማ ክልል ተሰበጣጥረው ለሚኖሩ ወደ 11,000 የሚጠጉ ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት በቅንዓት እያዳረሱ ነው። አመስጋኝ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር “ወደዚህ መጥታችሁ እኛን ለመርዳት ጥረት ስላደረጋችሁ እናመሰግናችኋለን” ብሏል። አስደሳች ስብሰባ ካደረግን በኋላ ሻይ ቡና ለማለት ወጣ አልን። የዚያን ዕለት ምሽት ከመተኛታችን በፊት ባረፍንበት ቦታ ለሚገኙት ፖሰም የተባሉ የካንጋሮ ዝርያዎች ምግብ ሰጠናቸው።

“ዛሬ ማታ ቁጭ ብዬ አነበዋለሁ”

በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በክዊንስላንድ ኒው ሳውዝ ዌልስ ድንበር ላይ ወዳሉ ገለልተኛ አካባቢዎች ተጓዝን፤ በእነዚህ አካባቢዎች ከአንዱ ቤት ተነስቶ ሌላኛው ቤት ለመድረስ ብዙ ኪሎ ሜትር መጓዝ ይጠይቃል። አብዛኛው የገጠሩ ክፍል፣ በጎችና ከብቶች በሚግጧቸው ለጥ ያሉ መስኮች የተሸፈነ ሲሆን ደረቅ የባሕር ዛፍ ቁጥቋጦዎችም አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ። በጉዟችን ወቅት ያየናቸው ካንጋሮዎች ድምፃችንን ሲሰሙ ጆሯቸውን ይቀስሩ ነበር። ግርማ ሞገስ ያለው ኢሙ የተባለው የወፍ ዝርያም ከሩቅ በሚታየው አቧራማ ሜዳ ላይ ወዲያ ወዲህ ይንጎራደድ ነበር።

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ አንድ የከብት መንጋ መንገድ ላይ በዝግታ ሲጓዝ ተመለከትን። እረኞች፣ በተለይ በድርቅ ወቅት ከብቶቻቸውን ወደዚህ አካባቢ ይዘው የመምጣት ልማድ አላቸው። ብዙም ሳይቆይ ፈረስ ላይ የተቀመጡ አንድ አረጋዊ እረኛ አገኘን። መኪናውን ወደ ዳር አቆምኩና ሰላምታ ሰጠኋቸው። እሳቸውም “ጤና ይስጥልኝ” በማለት መለሱልኝ። እኚህ ሰው ከብት የሚያግድ ውሻ አብሯቸው የነበረ ሲሆን እኔን ለማናገርም ቆም አሉ።

ስለ ድርቁ ጥቂት ከተወያየን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክታችንን አካፈልኳቸው። አረጋዊውም “ከልጅነቴ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ እንደሚል ሰምቼ አላውቅም!” በማለት ተናገሩ። እኚህ ሰው፣ በዓለም ላይ ለሚታየው የሥነ ምግባር ዝቅጠት ተጠያቂዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ናቸው የሚል አመለካከት ቢኖራቸውም መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቅ ያከብራሉ። አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ካደረግን በኋላ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የሚለውን መጽሐፍ ሰጠኋቸው። መጽሐፉን ተቀብለውኝ ሸሚዛቸው ኪስ ውስጥ ከከተቱት በኋላ “ይህ መጽሐፍ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር የሚነግረኝ ከሆነ ዛሬ ማታ ቁጭ ብዬ አነበዋለሁ” አሉ።

ወደ ቤት መመለስ

ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች በዚያን ዕለት ምሽት በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አካፈልናቸው። እነሱም ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች ተመልሰው እንደሚጠይቋቸው ቃል ገቡልን። ስብሰባው ሲያልቅ ከወንድሞች መለየቱ በጣም ከባድ ሆኖብን ነበር። በመካከላችን ጠንካራ ፍቅር ነበር። ሁላችንም በመንፈሳዊ እርስ በርሳችን መበረታታት በመቻላችን እንደተባረክን ተሰምቶናል።—ሮሜ 1:12

በቀጣዩ ቀን ወደ ቤታችን ተመለስን። ስላደረግነው ጉዞ ስናስብ ይሖዋ ጥረታችንን አብዝቶ እንደባረከው ይሰማናል። በመንፈሳዊም ይበልጥ ተነቃቅተናል። ቤት ስንደርስ ልጆቹን፣ “ለሚቀጥለው እረፍት የት መሄድ ትፈልጋላችሁ? ወደ ተራሮቹ ነው?” በማለት ጠየቅኳቸው። እነሱም “አይደለም አባባ፣ እኛ የምንፈልገው ወደ ገጠራማው አካባቢ ሄዶ ማገልገል ነው” አሉኝ። ባለቤቴም ቀበል አድርጋ “እኔም እስማማለሁ። እስከ ዛሬ ካሳለፍነው የእረፍት ጊዜ ሁሉ ይህ በጣም የተለየ ነው!” አለች።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.11 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

^ አን.17 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።