በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማወቅ ፍላጎትህን በሚገባ ተጠቀምበት

የማወቅ ፍላጎትህን በሚገባ ተጠቀምበት

የማወቅ ፍላጎትህን በሚገባ ተጠቀምበት

“ጥያቄ መጠየቅ የሰው ተፈጥሮ ነው። ከተወለድንበት ጊዜ አንስቶ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፤ . . . እንዲያውም የሰው ዘር ታሪክ እኛ ሰዎች በፈጠርናቸው ጥያቄዎችና መልሶች የተሞላ ነው ሊባል ይችላል።” —ኦክታብዮ ፓዝ፣ የሜክሲኮ ተወላጅ የሆነ ባለቅኔ

ምግብ የሚያዘጋጅ አንድ ሰው አዲስ የምግብ ዓይነት ለመሥራት የሚነሳሳው ለምንድን ነው? አንድ አሳሽ ሩቅ ወደሆኑ ቦታዎች ለመሄድ ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ እንዲጥል የሚያደርገው ምንድን ነው? አንድ ትንሽ ልጅ ብዙ ጥያቄዎችን የሚጠይቀው ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው የማወቅ ፍላጎታቸው ነው።

አንተስ አዳዲስ ሐሳቦችን የማወቅ ፍላጎት አለህ? እንደሚከተሉት ላሉ ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ትጓጓ ይሆናል:- ‘ሕይወት የተገኘው ከየት ነው? የመኖራችን ዓላማስ ምንድን ነው? በእርግጥ አምላክ አለ?’ አብዛኞቻችን ለማወቅ ካለን ፍላጎት የተነሳ እንደነዚህ ያሉ ጥያቄዎችን ከልጅነታችን ጀምሮ ስንጠይቅ ኖረናል፤ አልፎ ተርፎም መልሶቻቸውን ለማወቅ ጥረት አድርገናል። ትኩረታችንን የሚስብ አንድ ሐሳብ ስንሰማ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ የተቻለንን ሁሉ እንጥራለን። በመሆኑም የማወቅ ፍላጎታችን በርካታ ግሩም ውጤቶችን ሊያስገኝልን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ፍላጎታችን ችግር ውስጥ ሊከተን አልፎ ተርፎም ለጥፋት ሊዳርገን ይችላል።

ጠንቃቃና ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋል

“ዓሣ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ አንድ አባባል አለ። እውነት ነው፣ ጠንቃቆች ካልሆንን አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ ያለን ፍላጎት ለአደጋ ሊያጋልጠን ይችላል። ለአብነት ያህል፣ አንድ ትንሽ ልጅ ለማወቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ የጋለ ምድጃ ሊነካ ይችላል፤ ይህ ደግሞ አስከፊ ውጤት ያስከትላል። በሌላ በኩል ግን ለማወቅ ያለን ተፈጥሯዊ ፍላጎት ለጥያቄዎቻችን መልስ እንድናገኝ ስለሚረዳን እውቀታችንን ያሰፋልናል። ይሁንና የማወቅ ፍላጎት ስላደረብን ብቻ አንድ ነገር ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ስለ ጉዳዩ ለማወቅ ጥረት ማድረጋችን ጥበብ ይሆናል?

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ጉዳት የሚያስከትል እውቀት አለ። ስለ ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች፣ ስለ መናፍስታዊ ድርጊቶች ወይም አክራሪ ቡድኖች አሊያም መናፍቃን ስለሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ለማወቅ መጓጓት ሕይወታችንን በቀላሉ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። እነዚህንና ሌሎች ሁኔታዎችን በተመለከተ “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” በማለት ወደ አምላክ የጸለየውን መዝሙራዊ ምሳሌ መኮረጅ ይኖርብናል።—መዝሙር 119:37

በሌላ በኩል ደግሞ፣ አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ጉዳት ባያስከትልም እንኳ አላስፈላጊና ፋይዳ ቢስ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ስለ ፊልም ተዋንያን ወይም ስመ ጥር ስለሆኑ ሰዎች የግል ሕይወት በማወቅ ምን ጥቅም ይገኛል? ስለ እያንዳንዱ የስፖርት ቡድንና ተጫዋች ዝርዝር ነገሮችን ማወቅ ወይም ስለ ዘመናዊ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አሊያም አዳዲስ ስለሆኑ የመኪና ሞዴሎች ማወቅ ምን ፋይዳ አለው? በርካታ ሰዎች በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ “ጠበብት” መሆናቸው ምንም ጥቅም አላስገኘላቸውም።

ምሳሌ የሚሆን ሰው

እርግጥ ነው፣ ለማወቅ ጉጉት ማሳደር ሁልጊዜ ጎጂ ነው ማለት አይደለም። የ19ኛው መቶ ዘመን ጀርመናዊ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪና አሳሽ የነበረውን የአሌክሳንደር ቮን ሃምቦልትን ሁኔታ እንመልከት፤ በደቡብ አሜሪካ ምዕራባዊ ጠረፍ አቅራቢያ የሚገኘው ሃምቦልት ከረንት የተባለው ቦታ የተሰየመው በዚህ ሰው ስም ነው።

ሃምቦልት “ከልጅነቴ ጀምሮ አውሮፓውያን እምብዛም ወዳልሄዱባቸው ራቅ ያሉ ቦታዎች የመጓዝ ከፍተኛ ጉጉት ነበረኝ” በማለት በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ያደረበት “ሊማራቸው የሚችላቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ [ስለተሰማውና] ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት” ስለነበረው እንደሆነ ገልጿል። ሃምቦልት በ29 ዓመቱ ወደ ማዕከላዊና ደቡባዊ አሜሪካ ጉዞ ያደረገ ሲሆን በዚያም ለአምስት ዓመታት ቆይቷል። በኋላም ያሰባሰባቸውን መረጃዎች በማጠናቀር ስላደረገው ጉዞ የሚተርክ ባለ 30 ጥራዝ ጽሑፍ አዘጋጅቷል።

የሃምቦልትን ትኩረት ከሳቡት ነገሮች መካከል የውቅያኖሱ ሙቀት፣ በውስጡ የሚኖሩት ዓሦች እንዲሁም በጉዞው ወቅት የተመለከታቸው ዕፅዋት ይገኙበታል። ሃምቦልት ተራሮችን ወጥቷል፣ ወንዞችን እየተዘዋወረ ተመልክቷል እንዲሁም በውቅያኖሶች ላይ በመርከብ ተጉዟል። ይህ ሰው ያካሄደው ጥናት ለተለያዩ የሳይንስ መስኮች መሠረት ሆኖ አገልግሏል። ይህን ሁሉ እንዲያደርግ ያነሳሳው በውስጡ የነበረው ከፍተኛ የማወቅ ጉጉትና በሕይወቱ ሙሉ ያልተለየው እውቀት የማግኘት ጥማት ነው። አሜሪካዊው ደራሲ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን እንደገለጸው ከሆነ “ሃምቦልት የሰው አእምሮ ያለውን ችሎታ ካስገነዘቡን አልፎ አልፎ ብቅ ካሉ . . . ድንቅ ሰዎች መካከል አንዱ ነው።”

ምርምር ሊደረግበት የሚገባ መስክ

አብዛኞቻችን አሳሽ የመሆን ወይም ለሳይንሳዊ ግኝቶች አስተዋጽኦ የማበርከት አጋጣሚያችን ጠባብ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የማሰብ ችሎታችንን በመጠቀም ልናገኘው የምንችለው አንድ የእውቀት መስክ አለ፤ ማንኛውንም እውቀት ለማግኘት የምናደርገው ጥረት ይህንን እውቀት በመረዳት ከምናገኘው አስደሳች ውጤት ጋር ሲወዳደር ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን እውቀት አስመልክቶ በሰማይ ወደሚገኘው አባቱ ሲጸልይ “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3

የማወቅ ጉጉት ላለው ሰው፣ እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከማወቅ የበለጠ ግሩም ውጤቶችን የሚያስገኝለት ሌላ የእውቀት መስክ ሊኖር አይችልም። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ ሕይወትን አስመልክተው የተነሱትን ጥያቄዎች መለስ ብለህ አስብ። የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳታችንም ተገቢ ነው:- ‘በዓለም ላይ ሥቃይና መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው? ሰዎች ምድርን ያጠፏት ይሆን? እንዲሁም አምላክ፣ የሰው ልጆችን ከሚደርስባቸው መከራ ለመገላገል ምን ዝግጅት አድርጓል?’ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት የምናደርገው የማወቅ ፍላጎት ስላለን ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንደተናገረው መልሶቹን ማወቃችን “የዘላለም ሕይወት” ያስገኝልናል። ስለዚህ ነገር እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

ይህ ሐዋርያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል እውቀት በውስጡ እንደያዘ መናገሩን ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ነገሮችን በአምላክ ዓይን መመልከት እንድንችል ይረዳናል። የአምላክ እውቀትና ጥበብ ደግሞ ከማንም የላቀ መሆኑን እናውቃለን። አምላክ ትልቅ መልእክት ያዘለውን የሚከተለውን ሐሳብ እንዲጽፍ ነቢዩ ኢሳይያስን በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “‘ሐሳቤ እንደ ሐሳባችሁ፣ መንገዴ እንደ መንገዳችሁ አይደለምና’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ሰማያት ከምድር ከፍ እንደሚሉ፣ መንገዴ ከመንገዳችሁ፣ ሐሳቤም ከሐሳባችሁ እንዲሁ ከፍ ያለ ነው።’”—ኢሳይያስ 55:8, 9

ተወዳዳሪ ስለማይገኝላቸው የአምላክ መንገዶችና ሐሳቦች ማወቅ ትፈልጋለህ? የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ መንገዶችና ሐሳቦች ምን እንደሚል የማወቅ ጉጉት አለህ? አምላክ መከራንና ሥቃይን ለማስወገድ ስለሚወስደው እርምጃ እንዲሁም ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ስላዘጋጀው መልካም ነገር ማወቅ ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ግብዣ ያቀርብልሃል:- “[ይሖዋ] ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ፤ እርሱን መጠጊያ የሚያደርግ ምንኛ ቡሩክ ነው!”—መዝሙር 34:8

በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ቅን ልብ ባለው ሰው ላይ የሚያሳድሩት ስሜት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ማየት የቻለ ሰው ብርሃን ሲያይ ከሚኖረው ስሜት ጋር ይመሳሰላል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ለማለት ተገፋፍቷል:- “የእግዚአብሔር የጥበቡና የዕውቀቱ ባለ ጠግነት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ አይመረመርም፤ ለመንገዱም ፈለግ የለውም!” (ሮሜ 11:33) የአምላክን እውቀትና ጥበብ ሙሉ በሙሉ መረዳት ፈጽሞ እንደማንችል እሙን ነው። በየጊዜው አዳዲስ ነገሮችን እየተማርን የምንኖርበት ፈጽሞ የማይሰለች አስደሳች ጊዜ ከፊታችን ይጠብቀናል።

የማወቅ ፍላጎትህ እንዲጠፋ አትፍቀድ!

አብዛኞቻችን ዝነኛ አሳሾች ወይም ታዋቂ የፈጠራ ሰዎች መሆን እንደማንችል የታወቀ ነው። ከዚህም በላይ ካለን ዕድሜ አንጻር ማወቅ የምንፈልገውን ሁሉ ማወቅ አንችልም። እንዲህ ሲባል ግን የማወቅ ፍላጎትህን ማጨለም አለብህ ማለት አይደለም። አፍቃሪ የሆነው አምላክ የማወቅ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ስለፈጠረን ይህ ፍላጎትህ እንዲጠፋ አትፍቀድ።

ከአምላክ ያገኘኸውን ድንቅ ስጦታ ማለትም የማወቅ ፍላጎትህን በሚገባ ተጠቀምበት፤ እንዲሁም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት ስለተጻፈው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት አዳብር። እንዲህ ካደረግህ በአሁኑ ጊዜ ትርጉም ያለውና አስደሳች ሕይወት የምትመራ ከመሆኑም በላይ እውቀት እያገኘህ ለዘላለም የምትኖርበትን ጊዜ በጉጉት መጠባበቅ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “[አምላክ] ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም።”—መክብብ 3:11

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ይህን ታውቅ ነበር?

• ኮሎምበስና ማጂላን ምድር ምን ዓይነት ቅርጽ እንዳላት ከመናገራቸው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ይህች ፕላኔት ጠፍጣፋ ሳትሆን ክብ መሆኗን ገልጿል።—ኢሳይያስ 40:22

• የጠፈር ተመራማሪዎች ምድር ያለምንም ድጋፍ እንደቆመች ከመግለጻቸው ከረጅም ዘመናት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በባዶ ላይ እንደተንጠለጠለች ተናግሯል።—ኢዮብ 26:7

• እንግሊዛዊው ሐኪም ዊልያም ሃርቬይ፣ በሰውነት ውስጥ የሚካሄደውን የደም ዝውውር ሥርዓት በተመለከተ ግኝት ላይ ከመድረሳቸው ከ2,500 ዓመታት ቀደም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ ልብ የሕይወት ምንጭ እንደሆነ ተናግሯል።—ምሳሌ 4:23

• ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የውኃ ዑደት፣ ሕይወት እንዲቀጥል የሚያስችለው የምድር ሥነ ምሕዳር አንዱ ክፍል መሆኑን ሁሉም ሰው ሊረዳው በሚችለው መንገድ ገልጿል።—መክብብ 1:7

እነዚህም ሆኑ ሌሎች ግኝቶች በሳይንስ ከመታወቃቸው ከረጅም ዘመናት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መገለጻቸው የሚያስገርም አይደለም? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሕይወት አስፈላጊ የሆነና በዋጋ ሊተመን የማይችል የእውቀት ክምችት ይገኛል፤ አንተም ይህን እውቀት እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሌክሳንደር ቮን ሃምቦልት