በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ያገኘሁት የዕድሜ ልክ ደስታ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ያገኘሁት የዕድሜ ልክ ደስታ

የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ያገኘሁት የዕድሜ ልክ ደስታ

ቢል ያርምቸክ እንደተናገረው

ጊዜው መጋቢት 1947 ነበር። በወቅቱ ሳውዝ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ይገኝ ከነበረው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ስምንተኛው ክፍል በሚስዮናዊነት ከተመረቅሁ ጥቂት ሳምንታት አልፈዋል። ብዙም ሳይቆይ ወደተመደብኩበት አገር ማለትም በጣም ርቃ ወደምትገኘው ሲንጋፖር ለማቅናት ዝግጅት ማድረግ ጀመርኩ።

ከጊልያድ ሰባተኛው ክፍል የተመረቀ ዴቭ ፋርመር የተባለ ካናዳዊ የይሖዋ ምሥክር አብሮኝ እንዲያገለግል ተመደበ። ከዚያም ቀደም ሲል የጦር መርከብ በነበረችው በማሪን ኣደር ተሳፍረን ከሳን ፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርኒያ ጉዞ ጀመርን።

መርከባችን ሩቅ ምሥራቅ ስትደርስ መጀመሪያ የቆመችው ሆንግ ኮንግ ነበር። በዚህች አገር ያየናቸው ነገሮች በጣም አስደንጋጭ ነበሩ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው ውድመት በየቦታው ይታይ ነበር፤ አንጀታቸው በረሃብ የተጣበቀ ሞት አፋፍ ላይ የደረሱ ሰዎች በየመንገዱ ወድቀው ነበር። ወዲያውኑም ወደ መርከቧ ተመልሰን የፊሊፒንስ መዲና ወደሆነችው ማኒላ አቀናን።

በዚህች አገርም ቢሆን ጦርነቱ ያስከተላቸውን አስከፊ ውጤቶች ተመልክተናል። በሕብረ ብሔሩ የጦር አውሮፕላን የተደበደቡ መርከቦች ስብርባሪ፣ በወደቡ ላይ ተበታትኖ ይታይ የነበረ ከመሆኑም በላይ የአገሪቱ ሰዎች በከፋ ድህነት ይማቅቁ ነበር። በኋላም ከጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘን ሲሆን ወደ መንግሥት አዳራሻቸውም ወሰዱን። እነዚህ ክርስቲያኖች የተለያዩ ችግሮች ቢፈራረቁባቸውም ደስተኞች ነበሩ።

ቀጥለን ያረፍነው ደግሞ በባታቪያ (የአሁኗ ጃካርታ)፣ ኢንዶኔዢያ ውስጥ በሚገኝ ወደብ ላይ ነበር። በወቅቱ የእርስ በርስ ጦርነት ተፋፍሞ ስለነበርና ውጊያው የሚካሄደው በወደቡ አቅራቢያ ስለነበር ከመርከባችን እንድንወርድ አልተፈቀደልንም። መርከባችን ወደ ሲንጋፖር ጉዞዋን ስትቀጥል እዚያ ምን ሊጠብቀን እንደሚችል ማሰብ ጀመርኩ። አገር ለሚጎበኙ ሰዎች በተዘጋጁት ብሮሹሮች ላይ ውብ ስለሆኑት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ያነበብኩት ነገር በዓይኔ ከተመለከትኩት ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም ሆነብኝ።

በጥቂት ቀናት ውስጥ የነበረኝ ጥርጣሬ ሁሉ ተወገደ። እኔና ዴቭ ተልእኳችን የአምላክ ድጋፍ ያለው ስለመሆኑ ቅንጣት ታክል እንዳንጠራጠር የሚያደርግ አንድ አስገራሚ አጋጣሚ ተከሰተ።

በዚያ እንድቆይ የተፈቀደልን እንዴት ነበር?

ሳን ፍራንሲስኮን ከለቀቅን ከአንድ ወር ገደማ በኋላ መርከባችን በሴይንት ጆንስ ደሴት አረፈች፤ በወቅቱ አንድ መርከብ ወደ ሲንጋፖር እንዲገባ ፈቃድ ከማግኘቱ በፊት በዚህች ደሴት ላይ እንዲቆይ ይደረግ ነበር። የኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት መንገደኞቹ ወደ ሲንጋፖር ለመግባት አስፈላጊውን ብቃት ማሟላታቸውን ለማጣራት ወደ ደሴቲቱ የመጡ ሲሆን ፓስፖርታችንም “ይለፍ” የሚል ማኅተም ተመታበት። በነጋታው ጠዋት ወደቡ ላይ ደረስን። ከዚያም አንድ የመርከቡ ኃላፊ ሰነዶቻችንን ከመረመረ በኋላ ከመርከቧ እንድንወርድ ተፈቀደልን።

አብረውን ሲጓዙ የነበሩትን ሚስዮናውያን ለመሰናበት በማግስቱ ወደ ወደቡ ተመለስን። እነዚህ ሚስዮናውያን ወደ ሕንድና ወደ ሲሎን (የአሁኗ ስሪላንካ) ጉዟቸውን ይቀጥሉ ነበር። የመርከቧ ካፒቴን ልክ እንዳየን መጣና ከመርከቧ መውረድ እንዳልነበረብን በቁጣ ተናገረን። ገና እየተጓዝን ሳለ የኢሚግሬሽን ተቆጣጣሪ የሆኑት ሚስተር ሃክስወርዝ ከመርከቧ እንዳንወርድ ለካፒቴኑ ትእዛዝ ሰጥተውት ነበር። እኛም ሆንን ከመርከቧ እንድንወርድ የፈቀደልን ባለሥልጣን ስለዚህ ትእዛዝ የምናውቀው ነገር አልነበረም።

ከሚስተር ሃክስወርዝ ጋር ስንገናኝ በጥሩ ፊት አልተቀበሉንም። ወደ ሲንጋፖር መግባት እንደማንችል በቁጣ ገለጹልን። ወደ አገሪቱ እንዳንገባ ስለመከልከላችን ምንም የምናውቀው ነገር ስላልነበር “ይለፍ” የሚል ማኅተም የተመታበትን ፓስፖርታችንን አሳየናቸው። እሳቸውም ፓስፖርታችንን ከእጃችን መንጭቀው በመውሰድ “ይለፍ” የሚለውን ማኅተም ሰረዙት። ደስ የሚለው ግን መርከቧ ወደቡን ለቅቃ ሄዳለች! ሚስተር ሃክስወርዝ ለአንድ ዓመት ያህል ፓስፖርታችንን የወሰዱት ሲሆን በመጨረሻ ግን “ይለፍ” የሚለው ማኅተም እንደገና ተመቶበት ተመለሰልን።

በሲንጋፖር ያከናወንነው ፍሬያማ አገልግሎት

በሚያዝያ 1947 ሲንጋፖር ስንደርስ በአገሪቱ የነበረው የይሖዋ ምሥክር ጆሹዋ ብቻ ነበር። ወንድም ጆሹዋ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም አቅኚ ሆኖ አገልግሏል። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩ አንዳንድ ሰዎች ያወቁትን ነገር ለሌሎች ማካፈል ጀመሩ። በመንፈሳዊው የመከር ሥራ ተጨማሪ ሠራተኞችን ለማግኘት ያቀረብነው ጸሎት ምላሽ ማግኘት ጀመረ።—ማቴዎስ 9:37, 38

በ1949 ሚስተር ሃክስወርዝ ረዘም ያለ እረፍት ወስደው ወደ እንግሊዝ በሄዱበት ወቅት ከጊልያድ 11ኛው ክፍል የተመረቁ ስድስት ሚስዮናውያን ወደ ሲንጋፖር መጡ። በዚህ መሃል ለበርካታ ዓመታት በሚስዮናዊነት አብሮኝ ያገለገለው ዴቭ ባጋጠመው የጤና እክል ምክንያት ሲንጋፖርን መልቀቅ ግድ ሆነበት። ዴቭ ወደ አውስትራሊያ የሄደ ሲሆን በዚያም በሞት እስካንቀላፋበት እስከ 1973 ድረስ በታማኝነት አገልግሏል። አዲስ ከመጡት ስድስት ሚስዮናውያን መካከል አንዷ አይሊን ፍራንክስ ስትሆን ከእሷም ጋር በ1956 ተጋባን።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ሲሆን ከእነዚህም አብዛኞቹ ከነልጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። አንዳንዶቹ በዛሬው ጊዜም እንኳ ከአገራቸው ውጪ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። በሲንጋፖር ይኖሩ ከነበሩት አሜሪካዊ ባልና ሚስት ጋር በተያያዘ ያጋጠመንን አስደሳች ተሞክሮ ላካፍላችሁ። ሌስተር እና ጆኒ ሃይነስ ከተባሉት ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመርነው በ1950ዎቹ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ፈጣን መንፈሳዊ እድገት ካደረጉ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመልሰው ተጠመቁ። ከጊዜ በኋላ ሌስተር እና ጆኒ ፍሬያማ አገልግሎት ማከናወን ችለዋል። ሦስቱን ልጆቻቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲሆኑ ረድተዋል።

ጆኒ እንዲህ ብላ ጽፋለች:- “በሲንጋፖር ያሳለፍነው ያ ዓመት የሕይወታችንን አቅጣጫ በእጅጉ ለውጦታል። እናንተ ባትንከባከቡን ኖሮ ምናልባት ዛሬም ከቦታ ቦታ ስንዘዋወር እንገኝ ነበር። ለሌስተር እውነትን ያስተማርከው አንተ በመሆንህ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው አንስቶ ይሖዋንና ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ከልብ እንዲወድ ረድተኸዋል። ይህ ፍቅሩ አሁንም ድረስ አልቀዘቀዘም።”

በቤተሰብ ሆነን በሲንጋፖር ማገልገል

በ1962 በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ለውጥ ያስከተለ አንድ ያልተጠበቀ አጋጣሚ ተከሰተ። የቤተሰባችን ሐኪም፣ አይሊን እንዳረገዘች ነገራት። በሚስዮናዊነት ሥራችን መቀጠል እንፈልጋለን፤ ያም ሆኖ ልጅ እያሳደግን ይህን ሥራ እንዴት መወጣት እንችላለን? በወቅቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በበላይነት ይከታተል የነበረው ወንድም ናታን ኖር፣ በሲንጋፖር መቆየት እንድንችል ሰብዓዊ ሥራ ብይዝ ጥሩ እንደሚሆን የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈልን። ሥራ የማግኘቱ ጉዳይ ግን ያን ያህል ቀላል አልነበረም።

አብዛኞቹ የውጪ ዜጎች የሚቀጠሩት በውጪ አገር ድርጅቶች ውስጥ ሲሆን በኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲሠሩም ይመደቡ ነበር። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የገባሁት ከ23 ዓመት ገደማ በፊት ትምህርቴን እንደጨረስኩ ስለሆነ ስለ ንግዱ ዓለም ምንም እውቀት አልነበረኝም። በዚህም ምክንያት፣ በውጪ አገር ተመድቤ የማገለግል የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆኔን የሚገልጽ መረጃ (ካሪኩለም ቪቴ) እንዲያዘጋጅልኝ በለንደን ለሚገኝ አንድ ሥራ አስቀጣሪ ድርጅት ገንዘብ ከፈልኩ፤ በኋላም ይህ ድርጅት፣ ያዘጋጀውን መረጃ በሲንጋፖር ለሚገኙ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች ላከልኝ።

“ለእርስዎ የሚመጥን የሥራ ምድብ ባለማግኘታችን እናዝናለን” የሚል መልስ በተደጋጋሚ ይደርሰኝ ነበር። እነዚህ ድርጅቶች ሥራው ከሚጠይቀው በላይ ተሞክሮ እንዳካበትኩ ተሰምቷቸው ነበር። ከወራት በኋላ ልጃችን ጁዲ ተወለደች። በዚህ ጊዜ ወንድም ኖር ሲንጋፖርን እየጎበኘ ስለነበር ጁዲንና እናቷን ለማየት ወደ ሆስፒታል ሄደ። ወንድም ኖር፣ “ቢል ሥራ እስኪያገኝ ድረስ በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ መቆየት ትችላላችሁ” አለን።

ከጥቂት ወራት በኋላ በአንድ ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ድርጅት ውስጥ የሽያጭ ወኪል ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ድርጅቱ የሚከፍለኝ ገንዘብ በጣም አነስተኛ ስለሆነ የዕለት ጉርሳችንን ከመሸፈን አያልፍም ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ በአንድ የአሜሪካ አየር መንገድ ድርጅት ውስጥ ሥራ ያገኘሁ ሲሆን ደሞዜም ከበፊቱ እጥፍ ሆነ። ልምድ እያካበትኩ ስሄድ በአየር መንገድ ድርጅት ውስጥ የተደላደለ ቦታ ማግኘት ቻልኩ፤ ይህም ለቤተሰቤና ለክርስቲያናዊው አገልግሎት የበለጠ ጊዜ መስጠት እንድችል ረድቶኛል።

ቤተሰባችን ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጥ ስለነበር ሕይወታችን በይሖዋ አገልግሎት የተጠመደ ነበር። ይህ ደግሞ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ በርካታ መብቶችን እንዳገኝ አስችሎኛል። አይሊንም በድጋሚ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገባች። በእነዚህ ጊዜያት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው የስብከት ሥራ በመላው ሲንጋፖር ተስፋፍቶ ነበር። በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ መሃል ከተማ የሚገኝ ግሩም የሆነ ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃ የገዛን ሲሆን ይህ ሕንፃ አራት ጉባኤዎች የሚሰበሰቡበት የመንግሥት አዳራሽ ሆኖ ያገለግል ነበር።

ሥራችን ታገደ!

ከጊዜ በኋላ በሲንጋፖር የስደት ዳመና ያንዣብብ ጀመር። ጥር 14, 1972 እንደተለመደው ስብሰባ ለማድረግ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄድን። ያም ሆኖ የመንግሥት አዳራሹ ዋና በር በሰንሰለት ተቆልፎ ነበር። በሲንጋፖር የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ከእንግዲህ ወዲህ ሕጋዊ ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጽ ማስታወቂያ ተለጥፎበት ነበር። በዚህ መንገድ ሥራችን ታገደ! *

የመንግሥት አዳራሹ መታሸግ ይሖዋን ከማምለክ ወደኋላ እንድንል አላደረገንም፤ ይሁን እንጂ ‘ከቤተሰቤ ጋር በተያያዘ የአምላክ ፈቃድ ምን ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይጉላላ ነበር። ‘አገሪቱን ለቅቀን እንድንወጣ ከተደረግን በሲንጋፖር የሚገኙትን ወዳጆቻችንን ዳግመኛ አናያቸውም ማለት ነው?’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም ቤተሰባችን ወደ ሲንጋፖር እንደ ልብ መመላለስ እንዲችል አለቃዬን ክዋላ ላምፑር፣ ማሌዥያ ውስጥ መሥራት እችል እንደሆነ ጠየቅኩት። የሚገርመው ነገር፣ አለቃዬ ክዋላ ላምፑር በሚገኘው ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ሆኜ እንድሠራ ግብዣ አቀረበልኝ፤ ይህ ደግሞ ደሞዜን በእጥፍ የሚያሳድግልኝ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችንም ያስገኝልኝ ነበር።

ከዚያም ‘አምላክ በሲንጋፖር ከሚገኙት ወንድሞቻችን እንድንለይ ይፈልጋል ማለት ነው?’ ብዬ አሰብኩ። ከቤተሰቤ ጋር በመሆን ጉዳዩን አስመልክተን ወደ ይሖዋ ጸለይን። ወደ ሲንጋፖር እንድንመጣ ያደረገው ይሖዋ ነው። በመሆኑም እዚሁ መቆየት አለብን የሚል ውሳኔ ላይ ደረስኩ። አለቃዬ ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝልኝን ይህን ሥራ እንደማልቀበል ስገልጽለት በጣም ደነገጠ።

ተይዘን እንታሠራለን የሚል ስጋት ዕለት ዕለት ያስጨንቀን ስለነበር በእገዳ ሥር ሆነን የምንመራው ሕይወት ውጥረት ነግሦበት ነበር። “እግዚአብሔርን በሚፈሩት ዙሪያ የእግዚአብሔር መልአክ ይሰፍራል፤ ያድናቸዋልም” የሚለውን በመዝሙር 34:7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንድናደንቅ ያደረጉን በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ።

አዲስ የአገልግሎት ምድብ

ከ46 ዓመታት በላይ በሲንጋፖር ካገለገልን በኋላ በ1993 ወደ ኒው ዚላንድ እንድንዛወር ግብዣ ቀረበልን፤ በዚህች አገር ማገልገል ደግሞ የሲንጋፖርን ያህል ውጥረትና ጭንቀት አይፈጥርብንም። ይሁን እንጂ እጅግ ከምንወዳቸው በሲንጋፖር የሚገኙ ውድ ወዳጆቻችን መለየት ቀላል አልነበረም። ያም ሆኖ የእነዚህ ክርስቲያኖች እምነት እሳትን መቋቋም በሚችሉ ቁሳቁሶች በተሠራ ጠንካራ መሠረት ላይ እንደተገነባ ማወቃችን አበረታቶናል። ይህ እምነታቸው እስከ አሁን ድረስ እየደረሰባቸው ያለውን ፈተና በጽናት እንዲወጡት አስችሏቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 3:12-14

በአሁኑ ጊዜ በኒው ዚላንድ መኖር ከጀመርን ከ14 ዓመት በላይ ሆኖናል፤ ምንም እንኳ ዕድሜያችን ቢገፋም እኔና አይሊን በልዩ አቅኚነት እያገለገልን ነው። ታላላቅ ወንድሞቼ የሆኑት የ94 ዓመቱ ማይክና የ90 ዓመቱ ፒተር፣ ካናዳ ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው።

በ1998 ልጃችን ጁዲ ወደ ሩቅ ምሥራቅ የተመለሰች ሲሆን በዚያም ለበርካታ ዓመታት አገልግላለች። በዚያ ሳለች ከጻፈችልን ደብዳቤዎች ውስጥ አንዱ እንዲህ ይላል:- “እዚህ የማገልገል ግሩም መብት በማግኘቴ ይሖዋን በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ! ለሰጣችሁኝ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ሥልጠና እንዲሁም ለዚህ እንድበቃ ቀደም ሲል ለከፈላችሁትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ለምትከፍሉት መሥዋዕትነት ሁለታችሁንም አመሰግናችኋለሁ።” ጁዲ፣ በ2003 እኔንና አይሊንን ለመርዳት ወደ ኒው ዚላንድ ተመልሳ መጣች። *

የመከሩ ጌታ ተጨማሪ ሠራተኞችን ወደ መከሩ ለመላክ ያቀረበውን ግብዣ እንድንቀበል ሁኔታዎቹ ስለተመቻቹልን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ግብዣውን መቀበላችን ወደር የሌለው ደስታ አስገኝቶልናል። ወደፊት ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ይህ ዓለም እንደሚያልፍና የአምላክን ፈቃድ የሚፈጽም ለዘላለም እንደሚኖር’ የሚናገረው አስደናቂ ተስፋ ሲፈጸም የማየት አጋጣሚ ይኖረናል።—1 ዮሐንስ 2:17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.25 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሰኔ 1, 1972 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 341-349 ተመልከት።

^ አን.32 ውዷ እህታችን አይሊን ይህ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እያለ ጥር 24, 2008 አርፋለች።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1947 ሲንጋፖር ስንደርስ በአገሪቱ የነበረው የይሖዋ ምሥክር ጆሹዋ ብቻ ነበር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1947 ከዴቭ ፋርመር ጋር ወደ ሲንጋፖር ስንጓዝ በሆንግ ኮንግ የተነሳነው ፎቶ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከአይሊን ጋር በ1958

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጃችን ከጁዲ ጋር

[ምንጭ]

Kimroy Photography

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Kimroy Photography