በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘመናችን “እስራኤላዊቷ ልጃገረድ”

የዘመናችን “እስራኤላዊቷ ልጃገረድ”

የዘመናችን “እስራኤላዊቷ ልጃገረድ”

የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ከመከበሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት በፕራያ ግራንዴ፣ ብራዚል ውስጥ የሚኖሩት ሳለስና ቤተሰቡ በበዓሉ ላይ የሚጠሯቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር መዝግበው ነበር። ለስድስት ዓመቷ አቢጋል አንድ የመጋበዣ ወረቀት የተሰጣት ሲሆን ማንን መጋበዝ እንደምትፈልግም ጠየቋት።

አቢጋልም “ሁልጊዜ በፈገግታ የሚያየኝን ሰው” በማለት መለሰች።

ወላጆቿም “ማን ነው?” ብለው ጠየቋት።

እሷም “በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ያለው ሰውዬ” አለች።

ከአራት ቀን በኋላ አቢጋል ሰውየውን ለወላጆቿ አሳየቻቸው። ቫልተር የተባለው ይህ ሰው የሚኖረው በመንግሥት አዳራሹ አቅራቢያ ነው። ይህ ሰው ከ15 ዓመታት በፊት በ28 ዓመቱ በደረሰበት የመኪና አደጋ ምክንያት ከወገቡ በታች ሽባ ሆኗል። ቫልተር በጣም ሀብታም በመሆኑ ሁለት አጃቢዎች ነበሩት። የአቢጋል ወላጆች ቫልተርን ለማናገር ፈቃድ ከጠየቁ በኋላ ልጃቸው የመጋበዣ ወረቀት ልትሰጠው እንደምትፈልግ ነገሩት።

አቢጋል ሐሳቧን ተናግራ ከመጨረሷ በፊት እንዲህ አለችው:- “በመንግሥት አዳራሻችን የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ብዙ የመጋበዣ ወረቀቶች ተሰጥቷቸዋል፤ ለእኔ ግን የተሰጠኝ አንድ ብቻ ነው። ስለዚህ ከአንተ ሌላ የጋበዝኩት ሰው የለም። አንተ ካልመጣህ ማንም አይገኝልኝም ማለት ነው። ከመጣህ ግን በጣም ደስ ይለኛል፤ ይሖዋ ደግሞ ይበልጥ ይደሰታል።”

የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ዕለት አቢጋልን ጨምሮ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች በዚያ ምሽት ለሚከበረው በዓል የመንግሥት አዳራሹን እያጸዱ ነበር። ያን ቀን ከሰዓት በኋላ ቫልተር በዚያ በኩል ሲያልፍ አቢጋልን አያት፤ ከዚያም ሾፌሩ መኪናውን እንዲያቆም ከነገረው በኋላ መስኮቱን ከፍቶ ምን እየሠራች እንደሆነ ጠየቃት። አቢጋልም፣ እሱ ሲመጣ አዳራሹን ንጹሕ ሆኖ እንዲያገኘው እያጸዱ እንደሆነ ነገረችው።

በዚያን ዕለት ምሽት፣ የመታሰቢያው በዓል ንግግር የጀመረ ቢሆንም ቫልተር አልመጣም፤ አቢጋል በጣም ከመጨነቋ የተነሳ በር በሩን ትመለከት ጀመር። በድንገት ቫልተርና ጠባቂዎቹ ወደ አዳራሹ መጡ። አቢጋልም ስታያቸው በጣም ተደሰተች። ቫልተር ንግግሩ ካበቃ በኋላ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- ‘ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ጉዞ ጀምሬ የነበረ ቢሆንም ሐሳቤን ቀይሬ ወደ በዓሉ የመጣሁት ለአቢጋል ስል ነው።’ አክሎም “ንግግሩ ለእኔ በጣም ጠቃሚ ነበር” ብሏል። ቫልተር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን በኋላም በስብሰባዎች ላይ መገኘትና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምሯል።

በዚህ መሃል የቫልተር እህት ወንድሟ ደጋግሞ የሚያነሳትን አቢጋልን ለማየት እንደምትጓጓ ትነግረው ነበር። እህቱ ከአቢጋል ጋር ከተዋወቀች በኋላ ይህች ትንሽ ልጅ ጥሩ ባሕርያት እንዳሏት ስትገነዘብ ተደሰተች። “ወንድሜ በጣም ደስተኛ የሆነው ለምን እንደሆነ አሁን ገብቶኛል” ብላለች።

ቫልተር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱንና በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ቀጥሏል። እንዲያውም በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ የተማራቸውን ነገሮች ለሌሎች ያካፍላል። ትንሿ አቢጋል፣ ንዕማን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዲያውቅ የረዳችውን እስራኤላዊቷን ልጃገረድ እንደምታስታውሰን ምንም ጥርጥር የለውም።—2 ነገሥት 5:2-14