በአምላክ ስም መጠቀም ስህተት ነው?
በአምላክ ስም መጠቀም ስህተት ነው?
አብዛኛውን ጊዜ “ብሉይ ኪዳን” ተብለው በሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ יהוה (የሚነበቡት ከቀኝ ወደ ግራ ነው) በሚሉት ፊደላት የተቀመጠው የአምላክ ስም ወደ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል። ይህ የአምላክ ስም ዮድ፣ ሄ፣ ዋው እና ሄ በሚሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት የተወከለ ሲሆን በተለምዶም የሐወሐ ተብሎ ይጻፋል።
ከረጅም ጊዜ በፊት አይሁዳውያን በአምላክ ስም መጠቀም ተገቢ አይደለም የሚል አጉል እምነት መከተል ጀመሩ። በዚህም የተነሳ የአምላክን ስም መጥራት ያቆሙ ሲሆን በጽሑፎቻቸውም ላይ ይህን ስም በሌላ መተካት ጀመሩ። ያም ሆኖ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህን ስም “ያህዌህ” ወይም “ይሖዋ” ብለው ተርጉመውታል። ከእነዚህ ትርጉሞች መካከል በካቶሊኮች የተዘጋጀው ጀሩሳሌም ባይብል ይገኝበታል። ሙሴ፣ እስራኤላውያን ወደ እነሱ የላከው ማን እንደሆነ ቢጠይቁት ምን ብሎ እንደሚመልስላቸው አምላክን ጠይቆት ነበር፤ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ አምላክ የሰጠውን መልስ እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል:- “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው:- ‘የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው ያህዌህ ወደ እናንተ ልኮኛል።’ ስሜም ለዘላለም ይህ ነው፤ ወደፊት በሚመጣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው።”—ዘፀአት 3:15
ኢየሱስ “ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ” በማለት ወደ አምላክ መጸለዩ በመለኮታዊው ስም መጠቀሙን ያሳያል። አቡነ ዘበሰማያት ወይም የጌታ ጸሎት ተብሎ በሚታወቀው ጸሎት ላይ ኢየሱስ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ” ብሏል።—ዮሐንስ 17:26 የ1954 ትርጉም፤ ማቴዎስ 6:9
ሊቀ ጳጳስ ቤነዲክት 16ኛ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ በሚል ርዕስ በቅርቡ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ በመለኮታዊው ስም መጠቀምን አስመልክተው እንዲህ ማለታቸው የሚያስገርም ነው:- “እስራኤላውያን . . . የሐወሐ በሚሉት ፊደላት የሚወከለውን አምላክ ለራሱ ያወጣውን ስም እንደ ማንኛውም አረማዊ አምላክ በመጥራት ክብሩን ዝቅ ላለማድረግ ሲሉ በስሙ ላለመጠቀም መወሰናቸው ፍጹም ትክክል ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ምንጊዜም ሚስጥራዊና ሕቡዕ እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩት ይህ ስም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ እንደ ተራ ስም መጠቀሱ ስህተት ነው።”
አንተስ ምን ይመስልሃል? በአምላክ ስም መጠቀም ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ይሖዋ ራሱ “ስሜም ለዘላለም ይህ ነው፤ ወደፊት በሚመጣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው” ብሏል፤ ታዲያ እሱ እንዲህ ካለ በስሙ መጠቀም ስህተት ነው የምንል እኛ ማን ነን?
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ሲጸልይ በመለኮታዊው ስም ተጠቅሟል