ቴል ዓራድ ያለ ድምፅ ምሥክርነት ይሰጣል
ቴል ዓራድ ያለ ድምፅ ምሥክርነት ይሰጣል
የጠፋች ከተማ፣ አስደናቂ ቤተ መቅደስ እንዲሁም የጥንታዊ ጽሑፎች ክምችት። እነዚህ ነገሮች በአንድ ጥንታዊ ፊልም ውስጥ የሚገኙ ሊመስሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂስቶች በቴል ዓራድ፣ እስራኤል በአሸዋ ውስጥ ተቀብረው ካገኟቸው በርካታ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።
በዛሬው ጊዜ በርካታ ጎብኚዎች፣ ዓራድን የቱሪስት መስህብ ከሆኑት የእስራኤል ከተሞች አንዷ አድርገው ይመለከቷታል። ሃያ ሰባት ሺህ ነዋሪዎች ያሏት ይህች ከተማ የምትገኘው በሙት ባሕር በስተ ምዕራብ ባለው የይሁዳ ምድረ በዳ ነው። ይሁን እንጂ በእስራኤል ውስጥ የምትገኘው የጥንቷ የዓራድ ከተማ የምትገኘው ከዚህ ስፍራ በስተ ምዕራብ ስምንት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው። አርኪኦሎጂስቶች በዚህ አካባቢ የሚገኘውን አሸዋ በጥንቃቄ በማንሳት በርካታ ታሪካዊ ሕንፃዎችንና ጽሑፎችን ማግኘት ችለዋል።
እነዚህ ጥንታዊ ጽሑፎች ለመጻፊያነት በሚያገለግሉ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ ተቀርጸው የሚገኙ ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በሸክላ ስብርባሪዎች ላይ መጻፍ የተለመደ ነበር። በቴል ዓራድ በቁፋሮ የተገኙት የሸክላ ስብርባሪዎች በእስራኤል ውስጥ ከተገኙት ሁሉ በብዛታቸው ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ይነገርላቸዋል። ከእነዚህ ግኝቶች ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
እነዚህ ግኝቶች ከመሳፍንት ጊዜ አንስቶ ባቢሎናውያን አይሁዳውያንን በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት እስካጠፉበት ጊዜ ድረስ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይሸፍናሉ። በመሆኑም ግኝቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ይረዳሉ። ከዚህም በላይ የጥንት እስራኤላውያን ለአምላክ ስም ምን ዓይነት አመለካከት እንደነበራቸው ያሳያሉ።
ዓራድና መጽሐፍ ቅዱስ
እውነት ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዓራድ እምብዛም አይናገርም። ያም ሆኖ ቁልፍ በሆነ ቦታ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄድባት ነበር። በመሆኑም ታሪካዊ ዘገባዎችና አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች፣ ይህች ጥንታዊት ከተማ በተደጋጋሚ ጊዜ
መወረሯን፣ መጥፋቷንና መገንባቷን የሚጠቁሙ መሆናቸው አያስገርምም። ዓራድ በተደጋጋሚ ጊዜ መገንባቷ ቴል ወይም በፍርስራሽ ክምር የተሞላች ከተማ የሚል ቅጽል ስም እንዲሰጣት ምክንያት ሆኗል።ዓራድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰችው እስራኤላውያን በምድረ በዳ የ40 ዓመት ጉዟቸውን ለማጠናቀቅ በተቃረቡበት ወቅት ነበር። የሙሴ ወንድም አሮን ከሞተ ብዙም ሳይቆይ የአምላክ ሕዝቦች በተስፋይቱ ምድር ደቡባዊ ድንበር አቅራቢያ አለፉ። ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥም በምድረ በዳ ይንከራተቱ የነበሩትን እስራኤላውያን በቀላሉ ሊያሸንፋቸው እንደሚችል በማሰብ ጥቃት ሰነዘረባቸው። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን የተሰነዘረባቸውን ጥቃት በይሖዋ አምላክ እርዳታ በመመከት ዓራድን ሙሉ በሙሉ አጠፏት፤ ያም ሆኖ ጥቂት ሰዎች በሕይወት ተርፈዋል።—ዘኍልቍ 21:1-3
ከነዓናውያን ቁልፍ በሆነ ቦታ ላይ የምትገኘው ከተማቸውን በፍጥነት መልሰው ገነቧት። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኢያሱ ከሰሜን አንስቶ ድል በማድረግ ከነዓናውያንን ‘ከተራራማው ከኔጌቭ አገር’ እያሳደደ ወደዚህ አካባቢ ሲደርስ፣ ሊወጉት ከወጡት ጠላቶቹ መካከል አንዱ “የዓራድ ንጉሥ” ነበር። (ኢያሱ 10:40፤ 12:14) ቆየት ብሎም፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ወቅት ሊረዷቸው የወጡት የቄናዊው የኦባብ ዝርያዎች ኔጌቭ ውስጥ በሚገኘው በዚህ አካባቢ ሰፍረዋል።—መሳፍንት 1:16
አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች
ቆየት ብለው ከተከናወኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ጋር በተያያዘ በቴል ዓራድ የተገኙት ፍርስራሾች አስገራሚ መረጃዎችን ይዘዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አርኪኦሎጂስቶች በርካታ ምሽጎችን አግኝተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የተሠሩት፣ የተለያዩ ግንባታዎችን ያካሂድ በነበረው በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን ሳይሆን አይቀርም። (1 ነገሥት 9:15-19) በአንዱ ምሽግ ውስጥ በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት መጀመሪያ ላይ በአካባቢው ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰ የሚጠቁም ማስረጃ ተገኝቷል። ይህ ደግሞ ሰሎሞን ከሞተ ከአምስት ዓመት በኋላ የግብጹ ንጉሥ ሺሻቅ በአካባቢው ወረራ ካካሄደበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው። በደቡብ ግብጽ በሚገኘው በካርናክ ከተማ ውስጥ ባለ አንድ ግድግዳ ላይ ይህንን ወረራ ለማስታወስ የተቀረጹ ምስሎች ይገኛሉ። በምስሎቹ ላይ ሙሉ በሙሉ የተደመሰሱ ከተሞች ስም የተጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ዓራድ ትገኝበታለች።—2 ዜና መዋዕል 12:1-4
ወደ 200 በሚያህሉ የሸክላ ስብርባሪዎች ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ እንደ ጳስኮር፣ መሪሞትና የቆሬ ወንዶች ልጆች ያሉ የዕብራይስጥ ስሞች መስፈራቸው ትኩረት የሚስብ ነው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የአምላክ ስም የተቀረጸባቸው መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያስገርማል። አብዛኛውን ጊዜ ቴትራግራማተን ተብለው በሚጠሩት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት (יהוה ወይም የሐወሐ) የሚወከለው ይህ ስም፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ብቻ የሚጠራበት ነው። ቆየት ብሎም በርካታ ሰዎች የአምላክን ስም መጥራት ወይም መጻፍ እሱን የሚያቃልል ድርጊት እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ ማሰብ ጀመሩ። ይሁን እንጂ እንደ ሌሎቹ ሁሉ፣ በቴል ዓራድ የተገኙት ማስረጃዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንዲሁም ሰላምታ ሲለዋወጡና ሌሎችን ሲባርኩ በአምላክ ስም የመጠቀም ልማድ እንደነበራቸው ያረጋግጣሉ። ለአብነት ያህል፣ አንዱ ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ለጌታዬ ለኤልያሺብ። ያህዌህ [ይሖዋ] ደህንነትህን ይጠብቅልህ ዘንድ እመኛለሁ። . . . በአሁኑ ጊዜ በያህዌህ ቤተ መቅደስ ውስጥ እየኖረ ነው።”
በመግቢያችን ላይ ስለተጠቀሰው አስደናቂ ቤተ መቅደስስ ምን ማለት ይቻላል? ብዙዎች ግምታዊ አስተያየት ቢሰነዝሩም ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው በቴል ዓራድ የተገኘው ፍርስራሽ በይሁዳ ዘመን የተገነባ ቤተ
መቅደስ ነው፤ ቤተ መቅደሱ ሌሎች ክፍሎችን ጨምሮ መሠዊያም ነበረው። ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ከነበረው የሰሎሞን ቤተ መቅደስ እጅግ የሚያንስ ቢሆንም በቤተ መቅደሶቹ መካከል ብዙ ተመመሳሳይነት አለ። ይህ የዓራድ ቤተ መቅደስ የተገነባው ለምንና መቼ ነበር? በዚያስ ምን ይከናወን ነበር? አርኪኦሎጂስቶችና የታሪክ ምሑራን ለእነዚህ ጥያቄዎች በእርግጠኝነት መልስ መስጠት አልቻሉም።ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ዓመታዊ በዓላትን ማክበርም ሆነ መሥዋዕቶችን ማቅረብ ያለባቸው በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ ብቻ መሆን እንዳለበት አዟል። (ዘዳግም 12:5፤ 2 ዜና መዋዕል 7:12) በመሆኑም የዓራድ ቤተ መቅደስ የተገነባው የአምላክን ትእዛዝ በመጻረር ነበር። ይህ የሆነው እስራኤላውያን፣ ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ ከማምለክ ይልቅ ሌሎች መሠዊያዎችን በመሥራት ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር በጀመሩበት ጊዜ ሊሆን ይችላል። (ሕዝቅኤል 6:13) ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ደግሞ የሐሰት አምልኮ የሚካሄድበት ይህ ቤተ መቅደስ የፈራረሰው በስምንተኛውና በሰባተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም በሕዝቅያስ ወይም በኢዮስያስ የግዛት ዘመን ሳይሆን አይቀርም።—2 ዜና መዋዕል 31:1፤ 34:3-5, 33
በእርግጥም፣ በዓራድ የተገኙት እነዚህ ቅርሶች ጠቃሚ ትምህርት ይዘውልናል። ለበርካታ ዘመናት በአሸዋ ውስጥ ተቀብረው የነበሩት ቅርሶች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም ሌላ እውነተኛውን አምልኮ ለመበረዝ ተደርጎ ስለነበረው ያልተሳካ ጥረት ማስረጃ ይሰጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች የይሖዋን ስም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው አክብሮት በተሞላበት መንገድ ይጠቀሙበት እንደነበር ያመለክታሉ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኢየሩሳሌም
ሙት ባሕር
ዓራድ
ቴል ዓራድ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በካርናክ፣ ግብጽ ውስጥ በግድግዳ ላይ የተቀረጸ ምስል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይህ ጽሑፍ በከፊል እንዲህ ይላል:- “ያህዌህ [ይሖዋ] ደህንነትህን ይጠብቅልህ ዘንድ እመኛለሁ”
[ምንጭ]
Photograph © Israel Museum, Jerusalem; courtesy of Israel Antiquities Authority
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቴል ዓራድ የሚገኘው ቤተ መቅደስ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቴል ዓራድ የሚገኘው ምሽግ በምሥራቅ በኩል ሲታይ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Todd Bolen/Bible Places.com