በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እቅድህ ከአምላክ ዓላማ ጋር ይስማማል?

እቅድህ ከአምላክ ዓላማ ጋር ይስማማል?

እቅድህ ከአምላክ ዓላማ ጋር ይስማማል?

ግራጫ መልክ ያላት ክላርክስ ነትክራከር የተባለችውን የወፍ ዝርያ በሰሜን አሜሪካ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኙት ደኖች ውስጥ ማየት የተለመደ ነው። በዝማሬዋ የምትታወቀው ይህች ወፍ በየዓመቱ እስከ 33,000 የሚደርሱ ፍሬዎችን ከየስፍራው በመልቀም ወደ 2,500 በሚጠጉ ቦታዎች ታጠራቅማለች፤ ይህንንም የምታደርገው ኃይለኛ ቅዝቃዜ በሚኖርባቸው ወራት የምትበላውን ላለማጣት ስትል ነው። በእርግጥም ይህች ወፍ ለወደፊቱ ጊዜ የሚሆናትን ምግብ ማጠራቀሟ ‘እጅግ ጠቢብ’ እንደሆነች ያሳያል።—ምሳሌ 30:24

የሰው ልጆች ከዚህች ወፍ እጅግ የላቀ ችሎታ አላቸው። ይሖዋ ከፈጠራቸው የምድር ፍጥረታት ሁሉ ከተሞክሮ በመማርና በዚያ ላይ ተመርኩዘው ለወደፊቱ ጊዜ እቅድ በማውጣት ረገድ የሰው ልጆችን የሚወዳደራቸው የለም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ሰዎች ብዙ ነገር ያቅዳሉ” በማለት ተናግሯል።—ምሳሌ 19:21 የ1980 ትርጉም

ምንም እንኳ የሰው ልጆች ከተሞክሮ የመማር ችሎታ ቢኖራቸውም አብዛኛውን ጊዜ እቅድ የሚያወጡት ይሆናል ብለው በሚያስቡት ነገር ላይ ተመሥርተው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ነገ ፀሐይ እንደምትወጣና አንተ በሕይወት እንደምትኖር በማሰብ ነገ ስለምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እቅድ ታወጣለህ። ፀሐይ እንደምትወጣ ማሰብህ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ነገ በሕይወት ስለመኖርህ ግን እርግጠኛ መሆን አትችልም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ የሆነው ያዕቆብ ይህንን እውነታ እንዲህ በማለት ገልጾታል:- ‘ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን አታውቁም።’—ያዕቆብ 4:13, 14

ይሖዋ አምላክ ግን “የመጨረሻውን ከመጀመሪያው” ስለሚያውቅ ከሰዎች የተለየ ነው። ያወጣው ዓላማ በእርግጠኝነት እንደሚፈጸም ሲገልጽ “ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ” ብሏል። (ኢሳይያስ 46:10) ታዲያ የሰው ልጆች ያወጧቸው እቅዶች ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ውጤቱ ምን ይሆናል?

የሰዎች እቅድ ከአምላክ ዓላማ ጋር ሲጋጭ

ከ4,000 ዓመታት ገደማ በፊት የባቤልን ግንብ ለመገንባት የተነሱት ሰዎች፣ የሰው ዘር በአንድ ቦታ ብቻ ተወስኖ እንዲኖር ለማድረግ እቅድ አወጡ። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ብለው ነበር:- “ለስማችን መጠሪያ እንዲሆንና በምድር ላይ እንዳንበተን፣ ኑ፤ ከተማና ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለራሳችን እንሥራ።”—ዘፍጥረት 11:4

አምላክ ለምድር ያወጣው ዓላማ ግን ከዚህ የተለየ ነበር። ለኖኅና ለልጆቹ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 9:1) ታዲያ አምላክ ዓመጸኛ በሆኑት የባቤል ሰዎች ላይ ምን እርምጃ ወሰደ? እርስ በርስ መግባባት እንዳይችሉ ቋንቋቸውን ደባለቀ። በዚህም የተነሳ “እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ በታተናቸው።” (ዘፍጥረት 11:5-8) የባቤልን ግንብ ለመገንባት የተነሱት ሰዎች አንድ ቁም ነገር ለመማር ተገድደዋል። ሰዎች የሚያወጧቸው እቅዶች ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ‘ተፈጻሚነት የሚያገኘው የአምላክ ሐሳብ’ ወይም እቅድ ነው። (ምሳሌ 19:21) አንተስ እቅድ ስታወጣ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ግምት ውስጥ ታስገባለህ?

ሞኝ የነበረ ሀብታም ሰው

ምናልባት አንተ እንደ ባቤል ሰዎች ግንብ የመገንባት እቅድ አይኖርህ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ጡረታ ከወጡ በኋላ የተደላደለ ሕይወት ለመምራት በማሰብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በባንክ ለማጠራቀምና ቁሳዊ ንብረቶችን ለማከማቸት እቅድ ያወጣሉ። አንድ ሰው ከሥራው እርካታ ለማግኘት መፈለጉ ያለ ነገር ነው። ሰሎሞን “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ [“ስጦታ፣” የ1954 ትርጉም] ነው” ሲል ጽፏል።—መክብብ 3:13

ይህን ስጦታ ማለትም ለፍተን ያገኘነውን መልካም ነገር የምንጠቀምበት መንገድ በይሖዋ ፊት ያስጠይቀናል። ከዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ይህንን ነጥብ ጎላ አድርጎ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ዕርሻው እጅግ ፍሬያማ የሆነችለት አንድ ሀብታም ነበረ፤ ይህም ሰው፣ ምርቴን የማከማችበት ስፍራ ስለሌለኝ ምን ላድርግ? ብሎ በልቡ አሰበ። ‘እንዲህም አለ፤ እንደዚህ አደርጋለሁ፤ ያሉኝን ጐተራዎች አፈርስና ሌሎች ሰፋ ያሉ ጐተራዎች እሠራለሁ፤ በዚያም ምርቴንና ንብረቴንም ሁሉ አከማቻለሁ፤ ነፍሴንም፣ “ነፍሴ ሆይ፤ ለብዙ ዘመን የሚበቃሽ ሀብት አከማችቼልሻለሁ፤ እንግዲህ ዕረፊ፤ ብዪ፤ ጠጪ፤ ደስም ይበልሽ” እላታለሁ።’” (ሉቃስ 12:16-19) የሀብታሙ ሰው እቅድ ምክንያታዊ ይመስላል፤ አይመስልም እንዴ? በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰችው ወፍ ሁሉ በምሳሌው ላይ የተገለጸው ይህም ሰው ወደፊት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ሊሆን ይችላል።

ይሁንና ይህ ሰው እንዲህ ብሎ ማሰቡ ስህተት ነበር። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “እግዚአብሔር ግን፣ አንተ ሞኝ፤ ነፍስህን በዚህች ሌሊት ከአንተ ሊ[ወ]ስዱ ይፈልጓታል፤ እንግዲህ፣ ለራስህ ያከማቸኸው ለማን ይሆናል? አለው።” (ሉቃስ 12:20) ኢየሱስ እዚህ ላይ የተናገረው ሐሳብ ሰሎሞን በሥራ የሚገኘው መልካም ውጤት የአምላክ ስጦታ እንደሆነ ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ነው? በጭራሽ! ታዲያ ኢየሱስ ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ ለራሱ ሀብት የሚያከማች፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሀብታም ያልሆነ ሰው መጨረሻው ይኸው ነው።”—ሉቃስ 12:21

ኢየሱስ ለአድማጮቹ እያስተማረ ያለው ቁም ነገር፣ ይሖዋ እቅድ ስናወጣ የእሱን ዓላማ ግምት ውስጥ እንድናስገባ ይፈልጋል የሚለው ነው። ሀብታሙ ሰው ጥበብን፣ ፍቅርንና ለአምላክ የማደርን ባሕርይ በማዳበር በአምላክ ዘንድ ሀብታም መሆን ይችል ነበር። ይህ ሰው እነዚህን ባሕርያት ስለ ማዳበር የተናገረው ነገር የለም፤ በተጨማሪም ድሆች እንዲቃርሙ የተወሰነ እህል ስለመተዉ አሊያም ለይሖዋ መሥዋዕት ስለማቅረቡ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ይህ ሀብታም ሰው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆኑትንና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙትን እነዚህን ተግባራት አይፈጽምም ነበር። እቅዶቹ ያተኮሩት የራሱን ምኞት በማሳካትና ምቾቱን በመጠበቅ ላይ ብቻ ነበር።

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በርካታ ሰዎችና ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሀብታም ሰው በሕይወታቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ተመሳሳይ መሆናቸውን አስተውለሃል? ሀብታምም ሆንን ድሃ ማንኛችንም በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ በቀላሉ ልንወድቅ እንችላለን፤ ይህ የሚሆነው መሠረታዊ ፍላጎታችንን እና የምንመኘውን ነገር ለማሟላት የምናደርገው ጥረት፣ መንፈሳዊነታችንን ችላ እስክንል ድረስ ትኩረታችንን እንዲሰርቅብን በምንፈቅድበት ጊዜ ነው። ታዲያ በዚህ ወጥመድ ላለመውደቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

“የተለመደውን” የአኗኗር ዘይቤ ለመከተል እቅድ ማውጣት

ኢየሱስ በምሳሌው ላይ ከገለጸው ሀብታም ሰው በተቃራኒ አንተ የኢኮኖሚ ችግር ይኖርብህ ይሆናል። የሆነ ሆኖ ባለትዳር ከሆንክ ለቤተሰብህ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች የማሟላት ከተቻለም ልጆችህን ጥሩ ትምህርት ቤት የማስተማር እቅድ እንደሚኖርህ ምንም ጥርጥር የለውም። ያላገባህ ከሆንክ ደግሞ የሌሎች ሸክም ላለመሆን ስትል ሥራ ፈልገህ ለማግኘት አሊያም ያለህን ሥራ ላለማጣት እቅድ ታወጣ ይሆናል። እንደነዚህ ያሉ እቅዶች ደግሞ ተገቢ ናቸው።—2 ተሰሎንቄ 3:10-12፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8

ያም ሆኖ እንደ መሥራት፣ መብላትና መጠጣት ያሉት የተለመዱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች እንኳ አንድ ሰው የአምላክን ፈቃድ እንዲጥስ ሊያደርጉት ይችላሉ። እንዴት? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ልክ በኖኅ ዘመን እንደ ሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል፤ ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡ እንደ ነበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስም ምን እንደሚመጣ ሳያውቁ [“ሳያስተውሉ፣” NW] ድንገት የጥፋት ውሃ እንዳጥለቀለቃቸው፣ የሰው ልጅ ሲመጣም እንደዚሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:37-39

የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት ሰዎች በብዙዎች ዘንድ የተለመዱትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ያከናውኑ ነበር። ይሁን እንጂ ዋነኛ ችግራቸው አምላክ ዓለም አቀፍ ይዘት ባለው የጥፋት ውኃ አማካኝነት ያንን ክፉ ዓለም የማጥፋት ዓላማ እንዳለው ‘አለማስተዋላቸው’ ነበር። የኖኅ የአኗኗር ዘይቤ እንግዳ ሆኖባቸው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ይኖሩ የነበሩት ኖኅና ቤተሰቡ መሆናቸው የጥፋት ውኃው በመጣበት ጊዜ ተረጋግጧል።

በዛሬው ጊዜ የሚታዩት ማስረጃዎች በሙሉ በመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር በግልጽ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:3-12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በቅርቡ የአምላክ መንግሥት በዛሬው ጊዜ ያሉትን ብሔራት “ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል።” (ዳንኤል 2:44) በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። በዚያን ጊዜ በሽታም ሆነ ሞት ይወገዳሉ። (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3-5) ከዚህም በላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ፍጥረታት በሙሉ ተስማምተው የሚኖሩ ሲሆን ረሃብም አይኖርም።—መዝሙር 72:16፤ ኢሳይያስ 11:6-9

ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ከዓላማዎቹ አንዱ እንዲፈጸም ይኸውም ‘ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን የአምላክ መንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ እንዲሰበክ’ ይፈልጋል። (ማቴዎስ 24:14) ከዚህ ዓላማ ጋር በመስማማት በ236 አገሮች ውስጥ የሚገኙ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ከአራት መቶ በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይህን ምሥራች በመስበክ ላይ ናቸው።

በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች አኗኗር እንግዳ ሊሆንባቸው አልፎ ተርፎም ሞኝነት እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። (2 ጴጥሮስ 3:3, 4) ከጥፋት ውኃው በፊት እንደነበሩት ሰዎች ሁሉ እነዚህ ሰዎችም በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የተጠመዱ ናቸው። በተጨማሪም በኅብረተሰቡ ዘንድ የተለመደ ነው ተብሎ የሚታመነውን የአኗኗር ዘይቤ የማይከተልን ሰው ሚዛናዊ እንዳልሆነ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል። አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ለሚያሳድሩ ሰዎች ግን አምላክን በማገልገል ላይ ያተኮረ ሕይወት መምራት በእርግጥም ሚዛናዊ ነው።

ስለዚህ ሀብታምም ሆንክ ድሃ አሊያም መካከለኛ ኑሮ ያለህ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያወጣኸውን እቅድ በየጊዜው መመርመርህ ጥበብ ነው። እንዲህ ስታደርግ ‘ያወጣሁት እቅድ ከአምላክ ዓላማ ጋር ይስማማል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች የሚያወጧቸው እቅዶች ከአምላክ ዓላማ ጋር በሚጋጩበት ጊዜ ተፈጻሚነት የሚያገኘው የይሖዋ እቅድ ነው

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በምሳሌው ላይ የጠቀሰው ሀብታም ሰው እቅድ ሲያወጣ የአምላክን ዓላማ ግምት ውስጥ አላስገባም