በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

“ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ [ያዕቆብም] መጽናናትን እንቢ አለ፣ እንዲህም አለ:- ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።” —ዘፍጥረት 37:35 የ1954 ትርጉም

የእምነት አባት የሆነው ያዕቆብ፣ በልጁ ሞት የደረሰበት ሐዘን በጣም ከባድ ስለነበር እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ እንደማይወጣለት ተናግሮ ነበር። እንደ ያዕቆብ ሁሉ አንተም የምትወደውን ሰው በሞት ማጣትህ ያስከተለብህ ሐዘን እጅግ ከባድ ከመሆኑ የተነሳ መቼም ቢሆን እንደማይወጣልህ ይሰማህ ይሆናል። አንድ ሰው ይህን ያህል ማዘኑ በአምላክ ላይ እምነት እንደሌለው የሚያሳይ ነው ሊባል ይችላል? በጭራሽ!

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ያዕቆብ የእምነት ሰው እንደሆነ ይናገራል። እንደ አያቱ እንደ አብርሃምና እንደ አባቱ እንደ ይስሐቅ ሁሉ ያዕቆብም ታላቅ እምነት ያለው ሰው ነበር። (ዕብራውያን 11:8, 9, 13) እንዲያውም በአንድ ወቅት የአምላክን በረከት ለማግኘት ሲል ሌሊቱን ሙሉ ከአንድ መልአክ ጋር ታግሏል! (ዘፍጥረት 32:24-30) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ያዕቆብ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና የነበረው ሰው ነው። ታዲያ ያዕቆብ ማዘኑ ምን ያሳያል? በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያለው ሰውም እንኳ የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ መሪር ሐዘን ሊሰማው ይችላል። አንድ ሰው የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ ማዘኑ ተፈጥሯዊ ነው።

ሐዘን ምንድን ነው?

ሐዘን ሰዎችን በተለያየ መንገድ ሊጎዳ ቢችልም ለብዙዎቹ ግን በጣም ከባድ የሚሆንባቸው ሐዘኑ የሚያስከትልባቸውን ስሜታዊ ቀውስ መቋቋም ነው። እስቲ የሌኦናርዶን ሁኔታ እንመልከት፤ ሌኦናርዶ አባቱን በልብ ሕመም ምክንያት በድንገት ያጣው ገና የ14 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር። አክስቱ የአባቱን ሞት ያረዳችውን ቀን መቼም አይረሳውም። መጀመሪያ ላይ ነገሩን ማመን አቃተው። የአባቱን ሬሳ በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ቢመለከትም የሚያየው ነገር ሁሉ ሕልም መሰለው። ሌኦናርዶ ለስድስት ወራት ያህል አላለቀሰም ነበር፤ እንዲያውም ብዙውን ጊዜ አባቱ ከሥራ እንደሚመለስ በማሰብ ቤት ቁጭ ብሎ ይጠብቀው ነበር። የአባቱን ሞት ሙሉ በሙሉ አምኖ ለመቀበል አንድ ዓመት ገደማ ወስዶበታል። በዚህ ጊዜ ከፍተኛ የብቸኝነት ስሜት ተሰማው። ባዶ ቤት እንደ መግባት ያሉ ተራ የሚመስሉ ነገሮች እንኳ የአባቱን ሞት ያስታውሱታል። በእነዚህ ጊዜያት ስቅስቅ ብሎ ያለቅስ ነበር። በእርግጥም ሌኦናርዶ በአባቱ ሞት በጣም አዝኗል!

የምንወደው ሰው ሲሞት የሚሰማን ሐዘን ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል የሌኦናርዶ ሁኔታ በግልጽ ያሳያል። የሚያስደስተው ግን ከደረሰብን ሐዘን መጽናናት እንችላለን። ይሁን እንጂ የተወሰነ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። አንድ ከባድ ቁስል ለመዳን ጊዜ እንደሚወስድ ሁሉ ከሐዘን ለመጽናናትም ጊዜ ያስፈልጋል። ምናልባትም ወራት፣ ጥቂት ዓመታት አልፎ ተርፎም ከዚያ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ሆኖም ሁኔታው የተከሰተ ሰሞን የሚሰማህ መሪር ሐዘን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ይሄዳል፤ በተጨማሪም መጀመሪያ ላይ ተሰምቶህ የነበረው የባዶነት ስሜት ቀስ በቀስ እየጠፋ ሄዶ ሕይወት እንደገና ትርጉም ያለው ይሆንልሃል።

በሌላ በኩል ግን ሐዘን አንድን ሰው እንዲጽናና ብሎም ሁኔታውን አምኖ እንዲቀበል የሚረዳው አንደኛው አስፈላጊ መንገድ እንደሆነ ይነገራል። የምንወደውን ሰው በሞት ማጣታችን እንደሚያጎድለን ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ከዚህ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልገናል። ሐዘን፣ ስሜትህን አውጥተህ መግለጽ እንድትችል ይረዳህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ሰው ሁሉ ሐዘኑን የሚገልጸው ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ አንድ ሐቅ አለ:- ሐዘንን አምቆ መያዝ አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ታዲያ ሐዘንህን ጤናማ በሆነ መንገድ መግለጽ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ይዟል። *

የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም

የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ በርካታ ሰዎች ስሜታቸውን አውጥተው መናገራቸው እፎይታ አስገኝቶላቸዋል። ለአብነት ያህል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰውን የኢዮብን ታሪክ ተመልከት፤ ይህ ሰው አሥሩንም ልጆቹን በሞት ያጣ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች አሳዛኝ ችግሮች ተፈራርቀውበታል። ኢዮብ እንዲህ ብሏል:- “ሕይወቴን እጅግ ጠላሁ፤ ስለዚህም ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።” (ኢዮብ 1:2, 18, 19፤ 10:1) እዚህ ላይ ኢዮብ ጭንቀቱን ‘ያለ ገደብ መልቀቅ’ አስፈልጎት እንደነበር ልብ በል። ይህን ያደረገው እንዴት ነበር? ስሜቱን አውጥቶ ‘በመናገር’ እንደሆነ ገልጿል።

እናቱን በሞት ያጣው ፓውሎ “[እንድጽናና] ከረዱኝ ነገሮች አንዱ ስለ እናቴ ማውራቴ ነው” በማለት ተናግሯል። በመሆኑም ለምታምነው ወዳጅህ የልብህን አውጥተህ መናገርህ በተወሰነ መጠን እፎይታ ያስገኝልሃል። (ምሳሌ 17:17) ዮኔ እናቷን በሞት ካጣች በኋላ ክርስቲያን ወንድሞቿ ከበፊቱ ይበልጥ እየመጡ እንዲያጫውቷት ጠየቀቻቸው። ዮኔ “ስሜቴን አውጥቼ መናገሬ ሐዘኔን እንድቋቋም አስችሎኛል” ብላለች። አንተም ስሜትህን ለሚረዳልህ ሰው የልብህን አውጥተህ መናገርህ ሐዘንህ እንዲቀልልህ ያደርጋል።

ከዚህም በተጨማሪ ሐሳብህን በጽሑፍ ማስፈር ጠቃሚ ይሆናል። ስሜታቸውን አውጥተው በቃላት መግለጽ የሚከብዳቸው አንዳንድ ሰዎች ሐሳባቸውን በጽሑፍ ማስፈር ሊቀላቸው ይችላል። ታማኝ የነበረው ዳዊት፣ የሳኦልና የዮናታን ሞት ያስከተለበትን ጥልቅ ሐዘን የሚገልጽ መዝሙር ጽፏል። ይህ የሐዘን እንጉርጉሮ ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በሁለተኛ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ ተካትቷል።—2 ሳሙኤል 1:17-27

ማልቀስም ስሜትህን ሊያረጋጋልህ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለማልቀስ ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4) ‘ከምናለቅስባቸው ጊዜያት’ አንዱ ደግሞ የምንወደው ሰው ሲሞት ነው። ሐዘንን በእንባ መግለጽ ምንም አያሳፍርም። መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘናቸውን ያለ ምንም ኃፍረት በእንባ የገለጹ የበርካታ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ታሪክ ይዟል። (ዘፍጥረት 23:2፤ 2 ሳሙኤል 1:11, 12) ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጁ አልዓዛር ወደተቀበረበት መቃብር ሲደርስ ‘እንባውን አፍስሷል።’—ዮሐንስ 11:33, 35

ስሜትህ ቶሎ ቶሎ ስለሚለዋወጥ ከሐዘንህ ለመጽናናት ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። በማልቀስህ የምታፍርበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አስታውስ። በርካታ ታማኝ ሰዎች፣ ሐዘንን በእንባ መግለጽ ያለ ነገር እንደሆነና ለመጽናናትም እንደሚረዳ ተገንዝበዋል።

ወደ አምላክ ቅረብ

መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕቆብ 4:8) ወደ አምላክ የምንቀርብበት ዋነኛው መንገድ ጸሎት ነው። የጸሎትን ጥቅም አቅልለህ አትመልከተው! መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” የሚል ማጽናኛ ይዟል። (መዝሙር 34:18) ከዚህም በላይ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” የሚል ዋስትና ይሰጣል። (መዝሙር 55:22) እስቲ አስበው፤ ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ብዙዎች ለሚያምኑት ወዳጃቸው የልባቸውን አውጥተው መናገራቸው ጠቅሟቸዋል። ታዲያ ልባችንን ለማጽናናት ቃል ለገባልን አምላክ ስሜታችንን አውጥተን መናገራችን ይበልጥ ጠቃሚ አይሆንም?—2 ተሰሎንቄ 2:16, 17

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፓውሎ የሚከተለውን ሐሳብ ተናግሯል:- “ጭንቀቴ ከአቅሜ በላይ ሲሆንብኝና ልቋቋመው እንደማልችል ሲሰማኝ ተንበርክኬ ወደ አምላክ እጸልያለሁ፤ እንዲረዳኝም አጥብቄ እለምነዋለሁ።” ፓውሎ ወደ አምላክ መጸለዩ እንደረዳው ገልጿል። አንተም አዘውትረህ የምትጸልይ ከሆነ ‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ሐዘንህን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና ጥንካሬ ይሰጥሃል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ ሮሜ 12:12

የትንሣኤ ተስፋ

ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል” ብሏል። (ዮሐንስ 11:25) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሙታን በሕይወት የሚኖሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ያስተምራል። * ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሙታንን ማስነሳት እንደሚችል አሳይቷል። በአንድ ወቅት፣ የ12 ዓመት ልጅ ከሞት አስነስቷል። በዚህ ጊዜ የልጅቷ ወላጆች ምን ተሰማቸው? “የሚሆኑት እስኪጠፋቸው ድረስ በጣም ተደሰቱ።” (ማርቆስ 5:42 NW) ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ መንግሥት ሥር ይህ ነው የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሰላምና ጽድቅ በሚሰፍንበት ምድር ላይ እንዲኖሩ ከሞት ያስነሳቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) የሞቱ ሰዎች ሲነሱና ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር ሲገናኙ የሚሆኑት እስኪጠፋቸው ድረስ በጣም እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም!

በአውሮፕላን አደጋ ሬናቶ የተባለውን ልጇን ያጣችው ክላውዴቲ የልጇን ፎቶ ፍሪጅ ላይ አስቀምጣዋለች። ፎቶውን በተመለከተች ቁጥር ‘በትንሣኤ መገናኘታችን አይቀርም’ ትለዋለች። ሌኦናርዶ ደግሞ አምላክ ተስፋ በሰጠው አዲስ ዓለም ውስጥ አባቱን በትንሣኤ ሲቀበል በዓይነ ሕሊናው ይታየዋል። አዎን፣ የትንሣኤ ተስፋ ለእነዚህም ሆነ የሚወዱትን ሰው በሞት ለተነጠቁ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች እውነተኛ ማጽናኛ ሆኖላቸዋል። ለአንተም እውነተኛ ማጽናኛ ሊሆንልህ ይችላል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ልጆች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው ያስከተለባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ መርዳት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በዚህ መጽሔት ገጽ 18-20 ላይ የሚገኘውን “ልጃችሁ የደረሰበትን ሐዘን እንዲቋቋም እርዱት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው የትንሣኤ ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘የመጽናናት ሁሉ አምላክ’

“የርኅራኄ አባት፣ የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ።”—2 ቆሮንቶስ 1:3

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ አምላክ ታማኝ የሆኑ አገልጋዮቹ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ችግር ወይም ተፈታታኝ ሁኔታ መቋቋም እንዲችሉ እንደሚረዳቸው ይጠቁማል። ይሖዋ፣ የእኛ ዓይነት እምነት ባላቸው የቤተሰባችን አባላት ወይም ወዳጆቻችን ተጠቅሞ ማጽናኛ ይሰጠናል።

አባቱን በሞት ያጣው ሌኦናርዶ ብርታትና ማጽናኛ ያስገኘለትን አንድ አጋጣሚ ያስታውሳል። ልክ ቤቱ እንደደረሰ ማንም ሰው አለመኖሩን ሲያስታውስ ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። ከዚያም ከቤት ወጥቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ መናፈሻ በመሄድ ቁጭ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። በዚህ መሃል አምላክ እንዲረዳው ልመና አቀረበ። በኋላም በድንገት አንድ መኪና መጥቶ አጠገቡ ቆመ፤ ሌኦናርዶም ሲመለከት ሾፌሩ ከክርስቲያን ወንድሞቹ አንዱ እንደሆነ ተገነዘበ። መኪናውን የሚነዳው ወንድም ለደንበኞች ዕቃ በማድረስ ላይ የነበረ ሲሆን ወደዚህ ቦታ የመጣውም መንገድ ተሳስቶ ነበር። ሌኦናርዶ ይህን ወንድም ማግኘቱ ብቻ እንኳ አጽናንቶታል።

የትዳር ጓደኛቸውን በሞት የተነጠቁ አንድ አረጋዊ፣ የብቸኝነት ስሜት ተሰምቷቸው በከፍተኛ ጭንቀት ተውጠው የነበሩበትን ጊዜ ያስታውሳሉ። በዚያን ዕለት ለቅሷቸውን ማቆም እስኪያቅታቸው ድረስ ነገር ዓለሙ ሁሉ ጨለመባቸው። በዚህ መሃል አምላክ እንዲረዳቸው አጥብቀው ጠየቁት። ገና ጸሎታቸውን ሳይጨርሱ ስልክ ጮኸ። የደወለችው የልጅ ልጃቸው ነበረች። እኚህ ሰው እንዲህ ብለዋል:- “በዚያች አጭር ጊዜ ውስጥ ያደረግነው ውይይት እንደገና እንድበረታታ ረድቶኛል። ይህ አጋጣሚ አምላክ ለጸሎቴ የሰጠኝ መልስ ነው ከማለት ውጭ ምንም ማለት አልችልም።”

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሌሎችን ማጽናናት

“እኛ ራሳችን ከእግዚአብሔር በተቀበልነው መጽናናት፣ በመከራ ያሉትን ማጽናናት እንድንችል፣ [አምላክ] በመከራችን ሁሉ ያጽናናናል።”—2 ቆሮንቶስ 1:4

በርካታ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከላይ ያለው ጥቅስ በሕይወታቸው ሲፈጸም ተመልክተዋል። እነዚህ ሰዎች የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣታቸው ካስከተለባቸው ሐዘን መጽናናት የቻሉ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎችን ማበረታታትና ማጽናናት ችለዋል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነቷን አዘውትራ ለሌሎች የምታካፍለውን ክላውዴቲን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ክላውዴቲ፣ ልጇ ሬናቶ ከመሞቱ በፊት በሉኬሚያ በሽታ ልጇን ወዳጣች ሴት ትሄድ ነበር። ሴትየዋ ከክላውዴቲ ጋር የምታደርገው ውይይት የሚያስደስታት ቢሆንም ስሜቷን ሙሉ በሙሉ እንደማትረዳላት ይሰማት ነበር። ሬናቶ ሲሞት ግን የክላውዴቲ እምነት ተዳክሞ እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ እሷ ሄደች። ይህች ሴት፣ ክላውዴቲ ባላት ጠንካራ እምነት በመገረሟ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትራ ማጥናት የጀመረች ሲሆን ከአምላክ ቃልም ብዙ ማጽናኛ አግኝታለች።

ሌኦናርዶ አባቱን በሞት ካጣ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን አጽናኝ መልእክት፣ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ለማካፈል ሲል የምልክት ቋንቋ ለመማር ወሰነ። እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ያደረገው ጥረት በእጅጉ እንደጠቀመው ገልጿል። ሌኦናርዶ እንዲህ ብሏል:- “መስማት የተሳናቸውን ሰዎች ስለ አምላክ እንዲያውቁ ለመርዳት የነበረኝ ፍላጎት ሐዘኔን እንድቋቋም ረድቶኛል። ጉልበቴን ሳልቆጥብ እነሱን በመርዳት ብዙ ጊዜ አሳልፌያለሁ። የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ሲጠመቅ ሐዘኔ ወደ ደስታ ተለወጠ! እውነቱን ለመናገር፣ አባቴ ከሞተ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የደስታ ስሜት የተሰማኝ በዚህ ቀን ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ በተወሰነ መጠን እፎይታ ያስገኝልሃል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐሳብን በጽሑፍ ማስፈር ሐዘንን ለመግለጽ ይጠቅማል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ትንሣኤ ተስፋ በማንበብ እውነተኛ ማጽናኛ ማግኘት ይቻላል

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ በእሱ የሚያምኑ ሰዎችን በትንሣኤ እንደሚያስነሳቸው ቃል ገብቷል