ምድራችን በቅርቡ ትጠፋ ይሆን?
ምድራችን በቅርቡ ትጠፋ ይሆን?
ለሚከተለው ጥያቄ ምን መልስ ትሰጣለህ?
በምድር ላይ ያሉት ሁኔታዎች በቅርቡ ምን ይሆናሉ?
(ሀ) ይሻሻላሉ
(ለ) ምንም ለውጥ አይኖራቸውም
(ሐ) እየተባባሱ ይሄዳሉ
የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ አዎንታዊ አመለካከት አለህ? እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ብዙ ጥቅሞች አሉት። አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ጥሩ የማሰብ ችሎታና የተሻለ ጤንነት እንደሚኖራቸው ጥናቶች አመልክተዋል። እንዲያውም ለረጅም ጊዜ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በልብ በሽታ የመያዝ አጋጣሚያቸው አሉታዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ይልቅ አነስተኛ ነው። እነዚህ ጥናቶች መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት ከተናገረው ከሚከተለው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ:- “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል።”—ምሳሌ 17:22
ይሁን እንጂ በርካታ ሰዎች፣ የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ምድራችን የወደፊት ሁኔታ የሚናገሩትን ሲሰሙ ብሩሕ አመለካከት መያዝ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ሰዎችን ስጋት ላይ ከጣሏቸው የዜና ዘገባዎች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት።
አደጋ የተደቀነባት ፕላኔት
በስቶክሆልም የሚገኝ አንድ ታዋቂ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም፣ በ2002 ባወጣው ዘገባ ላይ እንደገለጸው የኢኮኖሚውን እድገት ለመጠበቅ ሲባል በተፈጥሮ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ቸል ማለት “የፕላኔቷን የአየር ንብረትና ሥነ ምህዳር በከፍተኛ ደረጃ ሊያቃውሱ የሚችሉ ክስተቶች” እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። ይህ ተቋም
ያወጣው ሪፖርት አክሎ እንደገለጸው ድህነት፣ ኢፍትሐዊነትና የተፈጥሮ ሀብቶች አላግባብ ጥቅም ላይ መዋል የሕብረተሰቡን “ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣላቸውም ሌላ አካባቢያዊና ማህበራዊ ቀውስ አስከትለዋል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ ከቀን ወደ ቀን በመባባስ ላይ ናቸው።”በ2005 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምድርን የአካባቢ ሁኔታ አስመልክቶ ሚሊኒየም ኢኮሲስተም አሴስመንት ሲንተስስ ሪፖርት በሚል ርዕስ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅቶ ነበር። ከ95 አገራት የተውጣጡ ከ1,360 በላይ የሚሆኑ ምሑራን የተሳተፉበትና በዓለም ዙሪያ ለአራት ዓመት በተካሄደ ጥናት ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀው ይህ ጽሑፍ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይዞ ነበር:- “የሰው ልጆች በምድር ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ በመሆናቸው የፕላኔታችን ሥነ ምህዳር መጪውን ትውልድ ያኖራል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።” አክሎም ሪፖርቱ ይህን አደጋ ማስቀረት የሚቻልበትን መንገድ አስመልክቶ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በፖሊሲዎች እንዲሁም በሕብረተሰቡ ባሕልና ልማዶች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል። ይሁንና በዛሬው ጊዜ እንዲህ ሲደረግ አይታይም።”
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠፈራ ማስተባበሪያ ፕሮግራም ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አና ቲባዩካ፣ “አሁን ባለው መንገድ ከቀጠልን ከፊታችን አስጊ ሁኔታ ይጠብቀናል” ብለዋል። በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ተመራማሪዎች ቁጥር ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ሄዷል።
አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል ምክንያት
ይህን መጽሔት የሚያዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮችም በቅርቡ በምድር ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያስከትሉ ክንውኖች እንደሚከሰቱ ያምናሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ክንውኖች ምድርን ከማጥፋት ይልቅ በፕላኔቷ ላይ ከዚህ በፊት ታይተው የማያውቁ ጥሩ ሁኔታዎች እንዲኖሩ መንገድ ይጠርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የመሰለ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ስለሚያምኑ ነው። ከእነዚህ ተስፋዎች ውስጥ አንዱ ምን እንደሚል ተመልከት:- “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11
እንዲህ ያለው ተስፋ የሕልም እንጀራ ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠታችን በፊት እስቲ በሚከተለው ሐሳብ ላይ በቁም ነገር አሰላስል:- በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ የምናያቸው አስጨናቂ ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ተናግሯል። በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ የሚገኙትን ጥቅሶች እያነበብክ በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ ከሚታየው ሁኔታ ጋር እንድታወዳድር እናበረታታሃለን። ይህን ማድረግህ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ሁኔታ በትክክል እንደሚተነብይ ያለህን እምነት ይበልጥ ያጠናክርልሃል።