በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት

ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት

ከኢየሱስ ምን እንማራለን?

ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት

ደግነት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?

ሰዎች አሳቢነት የጎደለው ድርጊት ቢፈጽሙብህም እንኳ ደግነት ማሳየትህን ትቅጥላለህ? የኢየሱስን አርዓያ ለመኮረጅ የምንፈልግ ከሆነ ለሚጠሉን ሰዎችም እንኳ ደግነት ማሳየት ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “የሚወዷችሁን ብትወዱ ምን የተለየ ዋጋ ታገኛላችሁ? ኀጢአተኞችም እንኳ የሚወዷቸውን ይወዳሉና። . . . ነገር ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ . . . የልዑልም ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ቸር ነውና።”—ሉቃስ 6:32-36፤ 10:25-37

ይቅር ባዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

ኃጢአት ስንሠራ አምላክ ይቅር እንዲለን እንፈልጋለን። ኢየሱስ፣ አምላክ ይቅር እንዲለን መጸለያችን ተገቢ እንደሆነ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:12) ይሁንና ኢየሱስ፣ አምላክ ይቅር የሚለን ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ከሆንን ብቻ መሆኑን ገልጿል። እንዲህ ብሏል:- “እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን ኀጢአት ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም ኀጢአታችሁን ይቅር አይልላችሁም።”—ማቴዎስ 6:14, 15

ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት መምራት የሚቻለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ያላገባ ቢሆንም የቤተሰብን ሕይወት አስደሳች ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ከእሱ ብዙ መማር እንችላለን። ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ልንኮርጀው የሚገባ ምሳሌ ትቶልናል። እስቲ የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች ልብ በል:-

1. አንድ ባል ሚስቱን እንደ ራሱ ሊወዳት ይገባል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ለባሎች ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል:- “አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤ እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።” (ዮሐንስ 13:34) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ መመሪያ ለባሎች የሚሠራው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው።”—ኤፌሶን 5:25, 28, 29

2. የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን አለባቸው። ከጋብቻ ውጪ የጾታ ግንኙነት መፈጸም በአምላክ ላይ ኃጢአት መሥራት ሲሆን ቤተሰብም እንዲፈርስ ያደርጋል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “አላነበባችሁምን? . . . ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው። . . . እላችኋለሁ፤ በትዳሯ ላይ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል።”—ማቴዎስ 19:4-9

3. ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ አለባቸው። ኢየሱስ ፍጹም የነበረ ቢሆንም እንኳ ልጅ ሳለ ፍጹማን ላልሆኑት ወላጆቹ ይታዘዝላቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ “አብሮአቸው [ከወላጆቹ ጋር] ወደ ናዝሬት ወረደ፤ ይታዘዝላቸውም ነበር” ይላል።—ሉቃስ 2:51፤ ኤፌሶን 6:1-3

እነዚህን መመሪያዎች በተግባር ላይ ማዋል ያለብን ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ካስተማራቸው በኋላ “እነዚህን ነገሮች ዐውቃችሁ ብትፈጽሙ ትባረካላችሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:17) በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች ለመሆን፣ ኢየሱስ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ የሰጣቸውን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:35

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ ደግና ይቅር ባይ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ያስተምረናል።—ሉቃስ 15:11-32

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ታማኝ መሆን አለባቸው