በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተገነዘብኩ

ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተገነዘብኩ

ሕይወት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ተገነዘብኩ

ዕለቱ ሚያዝያ 16, 2007 ነበር። ቨርጂኒያ ቴክ ወይም ቨርጂኒያ ፖሊቴክኒክ ኤንድ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው በኖሪስ ሆል ሕንፃ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ አንድ ጥግ ሥር ቁጢጥ ብዬ ነበር። እዚህ ቦታ ሆኜ በሕይወት ለምንኖርበት ለእያንዳንዱ ውድ ቀን ምን ያህል አመስጋኝ መሆን እንዳለብኝ በድጋሚ ተገነዘብኩ።

ያን ዕለት ጠዋት፣ ወደ ሁለተኛው ፎቅ ሄጄ የተላኩልኝን ፖስታዎች ለማምጣት እየተዘጋጀሁ ነበር። በዚህ ጊዜ አንድ ፕሮፌሰር ወደ ቢሮዬ በመምጣት ኮምፒውተሩን እንዳስተካክልለት ጠየቀኝ። ወደ ቢሮው በማምራት ላይ ሳለን ከሁለተኛው ፎቅ የጥይት እሩምታ ሰማን። በመሆኑም ምን እየተፈጸመ እንዳለ ስላላወቅን በፍጥነት ወደ ቢሮው በመግባት በሩን ቆለፍነው። በጭንቀት ተውጠን ምን ሊከሰት እንደሚችል መጠባበቅ ጀመርን። ከዚያም አንድ ጥግ ሆኜ፣ የሚያጋጥመኝን ነገር ሁሉ መወጣት እንድችል ይሖዋ አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረብኩ።

የሚሆነውን በመጠባበቅ ላይ ሳለን ከ15 ዓመት በፊት ያጋጠመኝ ነገር ትውስ አለኝ። በአንድ ጋራዥ ውስጥ መካኒክ ሆኜ እሠራ ነበር። አንድ ቀን የሥራ ባልደረባዬ በአነስተኛ ዕቃ ይዞት የነበረው ነዳጅ ድንገት በእሳት ተያያዘ፤ እሱም በድንጋጤ ፊቴ ላይ ወረወረው! በጭሱ ከመታፈኔም ሌላ ከወገቤ በላይ ከፍተኛ ቃጠሎ ደረሰብኝ። ከዚያም በእሳት የተቃጠሉ ሰዎች ወደሚታከሙበት ሆስፒታል በሄሊኮፕተር የተወሰድኩ ሲሆን በዚያም ልዩ የሕክምና ክትትል በሚደረግበት ክፍል ውስጥ ሕይወቴ በቋፍ ላይ ሆኖ ለሦስት ወር ተኩል ያህል ቆየሁ። ለአምስት ወራት ስታከም ከቆየሁ በኋላ በሕይወት መትረፌን እያመሰገንኩ ወደ ቤቴ ተመለስኩ። ይህ ሁኔታ በሕይወት የምኖርበት እያንዳንዱ ቀን ምን ያህል ውድ እንደሆነ አስገንዝቦኛል። ከዚህም በተጨማሪ ፈጣሪዬ የሆነው ይሖዋ አምላክን፣ ምሥክሩ በመሆን ለማገልገል ያደረግኩትን ቁርጥ ውሳኔ አጠናክሮልኛል።—መዝሙር 90:12፤ ኢሳይያስ 43:10

በደረሰብኝ አደጋ ሳቢያ መካኒክ ሆኜ መሥራት ስላልቻልኩ የኮምፒውተር ጥገና ተምሬ በቨርጂኒያ ቴክ ተቀጠርኩ። ቀደም ሲል የጠቀስኩት ሁኔታ በተከሰተበት ዕለት በኖሪስ ሆል ሕንፃ የተገኘሁት ለዚህ ነበር።

የጥይቱ እሩምታ የቀጠለ ሲሆን ከነበርንበት በታች ባለው ፎቅ ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ከተከሰቱት ሁሉ እጅግ አሰቃቂ የሆነው ግድያ እየተካሄደ መሆኑን አላወቅንም ነበር። ግድያው ያቆመው መሣሪያ የያዘው ሰው የ32 ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት ካጠፋና ራሱን ከገደለ በኋላ ነበር። ተኩሱ ከተጀመረ ከ20 ደቂቃ ገደማ በኋላ በኮሪደሩ ላይ የፖሊሶች ድምፅ ሰማን። ፖሊሶቹን ጠራናቸውና ከሕንፃው በሰላም እንድንወጣ ረዱን።

ይህ አሰቃቂ ሁኔታ፣ ሕይወት አስተማማኝ እንዳልሆነና እንደ ጉም በኖ እንደሚጠፋ አስገንዝቦኛል። (ያዕቆብ 4:14) የሕይወት ምንጭ በሆነው በይሖዋ አምላክ ላይ መተማመናችንና እያንዳንዱን ቀን ከእሱ እንዳገኘነው ውድ ስጦታ አድርገን መቁጠራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—መዝሙር 23:4፤ 91:2

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/The Roanoke Times, Alan Kim