በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘መጨረሻህ ምን እንደሚሆን’ አስተውል

‘መጨረሻህ ምን እንደሚሆን’ አስተውል

‘መጨረሻህ ምን እንደሚሆን’ አስተውል

በሕይወት ጎዳና ላይ ስንጓዝ ምርጫ እንድናደርግ የሚጠይቁ ብዙ ነገሮች ይገጥሙናል። ማንኛውንም ጉዞ ከመጀመራችን በፊት መንገዱ የት እንደሚያደርሰን ለማወቅ መሞከራችን የጥበብ አካሄድ ነው። አንዳንዶች ባደረጉት ውሳኔ በጣም ተጸጽተዋል። አንተም ‘እንደዚህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ በፍጹም አልጀምረውም ነበር’ ያልክበት ጊዜ ይኖር ይሆናል።

የመጓዝ ልምድ ያለው አንድ መንገደኛ ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት እያንዳንዱ መንገድ ወዴት እንደሚያደርስ ማወቅ ይፈልጋል። መንገደኛው ካርታ ይመለከት እንዲሁም ስለ አካባቢው የሚያውቁ ሰዎችን ይጠይቅ ይሆናል። በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙትን የመንገድ ምልክቶች በጥንቃቄ እንደሚመለከት ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁንና በሕይወት ጎዳና ላይ ስትጓዝ ከሁሉ የተሻለው መንገድ የቱ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? አምላክ የጥንቱን የእስራኤልን ሕዝብ አስመልክቶ በሙሴ በኩል እንዲህ ብሎ ነበር:- “አስተዋዮች ቢሆኑ ኖሮ ይህን በተገነዘቡ፣ መጨረሻቸውም ምን እንደሚሆን ባስተዋሉ ነበር።”—ዘዳግም 32:29

ከሁሉ የተሻለ ምክር

አምላክ ከሁሉ የተሻለው የሕይወት መንገድ የቱ እንደሆነ ለሰው ልጆች ምክር መስጠት የሚያስችል የላቀ ችሎታ አለው። በመሆኑም በሕይወት ጉዟችን የሚያጋጥሙን መንገዶች ‘መጨረሻቸው ምን ይሆን?’ ብለን ከልክ በላይ መጨነቅ አያስፈልገንም። አምላክ የሰው ልጆች የተጓዙባቸውን ጎዳናዎች የተመለከተ ከመሆኑም በላይ ያስከተሏቸውን ውጤቶች አይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ግልጥ ነውና፤ እርሱ መሄጃውን ሁሉ ይመረምራል” ይላል።—ምሳሌ 5:21

ይሖዋ ለሚወዱት ሰዎች ያስብላቸዋል። ሊጓዙበት የሚገባው ከሁሉ የተሻለው ጎዳና የቱ እንደሆነ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይነግራቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” በመሆኑም በየትኛውም የሕይወት ጎዳና ላይ መጓዝ ከመጀመርህ በፊት ልክ እንደ ጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት የአምላክን ምክር ለማግኘት መጣርህ ጥበብ ነው፤ ዳዊት “የምሄድበትን መንገድ አሳየኝ” በማለት ጸልዮአል።—መዝሙር 32:8፤ 143:8

እምነት የሚጣልበትና ልምድ ያለው መንገደኛ የሚጠቁምህን አቅጣጫ ተከትለህ መጓዝህ የመተማመንና የደህንነት ስሜት እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም ‘የምሄድበት መንገድ የት ያደርሰኝ ይሆን?’ ብለህ አትጨነቅም። ዳዊት፣ ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጠው የጠየቀ ሲሆን የሰጠውንም መመሪያ ተከትሏል። ይህን ማድረጉ በ23ኛው መዝሙር ላይ ማራኪ በሆነ መንገድ እንደገለጸው የአእምሮ ሰላም አስገኝቶለታል። ዳዊት እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ አንዳች አይጐድልብኝም። በለመለመ መስክ ያሳርፈኛል፤ በዕረፍት ውሃ ዘንድ ይመራኛል፤ ነፍሴንም ይመልሳታል። ስለ ስሙም፣ በጽድቅ መንገድ ይመራኛል። በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ፤ ብሄድ እንኳ፣ . . . አልፈራም።”—መዝሙር 23:1-4

መጨረሻቸው ምን ይሆን?

በሕይወት መንገድ ላይ ሲጓዝ የነበረ አሳፍ የተባለ ወይም ከዘሮቹ አንዱ እንደሆነ የሚገመት መዝሙራዊ፣ ከትክክለኛው መንገድ ‘አዳልጦት ሊወድቅ ጥቂት ቀርቶት’ እንደነበር ሳይሸሽግ ተናግሯል። እንዲህ ያለው ምን አጋጥሞት ይሆን? መዝሙራዊው፣ የአታላዮችንና የዓመጸኞችን ብልጽግና የተመለከተ ከመሆኑም በላይ ‘በኃጢአተኞች ሰላም’ ቀንቶ ነበር። ምንጊዜም ‘ደስተኞች’ እንደሚሆኑ ተሰምቶት ነበር። ከሁሉ የከፋው ደግሞ በመረጠው የጽድቅ ጎዳና ላይ መመላለስ የጥበብ አካሄድ መሆኑን መጠራጠሩ ነው።—መዝሙር 73:2, 3, 6, 12, 13 የ1954 ትርጉም

ከዚያም መዝሙራዊው ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት የክፉዎች መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል በጸሎት አሰበበት። ‘መጨረሻቸውን ለማየት’ ወይም የኋላ ኋላ ምን እንደሚደርስባቸው ለማስተዋል ፈልጎ ነበር። መዝሙራዊው የቀናባቸው ሰዎች ስለሚጠብቃቸው የወደፊት ዕጣ ሲያሰላስል ምን መደምደሚያ ላይ ደርሶ ይሆን? እንዲህ ያሉ ሰዎች “በሚያዳልጥ ስፍራ” እንዳሉና ‘ፈጥነው በቅጽበት እንደሚጠፉ’ ተገነዘበ። መዝሙራዊው ይጓዝበት ስለነበረው ጎዳናስ ምን ተሰማው? ‘ኋላም [ይሖዋ] ወደ ክብር እንደሚያስገባው’ ተናግሯል።—መዝሙር 73:17-19, 24

መዝሙራዊው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክበር ወይም አጠያያቂ በሆኑ መንገዶች ለመበልጸግ የሚሞክሩ ግለሰቦች መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰሉ በትክክለኛው ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንደሆነ አረጋግጦለታል። ስለሆነም “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። በእርግጥም ከይሖዋ ጋር ተቀራርቦ መኖር ምንጊዜም ዘላቂ ጥቅም ያስገኛል።—መዝሙር 73:28

“ወዴት እንደምትሄድ እወቅ”

በዛሬው ጊዜም ምርጫ እንድናደርግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ጥሩ ገንዘብ የሚያስገኝ የንግድ ውል መፈራረምን፣ የሥራ እድገትን ወይም በአንድ አትራፊ ንግድ ውስጥ በሽርክና መሥራትን የመሳሰሉ ግብዣዎች ይቀርቡልህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ማንኛውንም አዲስ ሥራ ስንጀምር ያልጠበቅናቸው ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ያም ቢሆን ያደረግኸው ምርጫ ‘መጨረሻው ምን እንደሚሆን’ አስቀድሞ ማሰቡ የጥበብ አካሄድ ነው። እንዲህ ዓይነት ምርጫ ማድረግህ ምን ሊያስከትል ይችላል? ምናልባት ከቤተሰብህ ርቀህ እንድትሄድ ሊያደርግህና ባንተም ሆነ በትዳር ጓደኛህ ላይ ጭንቀት ሊፈጥር ይችል ይሆን? በሥራ ከምትገናኛቸው ወይም በሆቴልና በሌሎች ቦታዎች ካሉ ሰዎች ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንድትመሠርት ያደርግሃል? የምትጓዝበትን ጎዳና አስቀድመህ በጥንቃቄ መመርመርህ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ እንድታደርግ ያስችልሃል። ሰሎሞን “ወዴት እንደምትሄድ እወቅ” በማለት የሰጠንን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለብን።—ምሳሌ 4:26 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን

ይህ ምክር ለሁላችንም ጠቃሚ ቢሆንም በተለይ ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው ሊያስቡበት ይገባል። አንድ ወጣት የጾታ ስሜት የሚቀሰቅስ መሆኑን እያወቀ ፊልም ተከራየ። ከዚያ በኋላ የሆነውን ሲናገር፣ ፊልሙን መመልከቱ ስሜቱን ስለቀሰቀሰበት በአቅራቢያው ትኖር ወደነበረች ወደሚያውቃት አንዲት ሴተኛ አዳሪ ሄደ። ከዚያም ለከባድ ሐዘን፣ ለሕሊና ወቀሳና በበሽታ ተይዤ ይሆናል ለሚል ጭንቀት ተዳረገ። ይህ ወጣት የደረሰበት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ “ለዕርድ እንደሚነዳ በሬ፣ . . . ሳያንገራግር ተከተላት” በማለት ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይመሳሰላል። ይህ ወጣት ‘መጨረሻው ምን ሊሆን’ እንደሚችል አስቀድሞ ቢያስብ ኖሮ ለዚህ ሁሉ ችግር ባልተዳረገ ነበር!—ምሳሌ 7:22, 23

በመንገድ ምልክቶቹ ላይ እምነት ጣል

የመንገድ ምልክቶችን ችላ ማለት ጥበብ የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ብዙ ሰዎች ይስማማሉ። የሚያሳዝነው ግን፣ አንዳንድ ሰዎች በሕይወት ጎዳና ላይ ሲጓዙ የሚያገኟቸውን የመንገድ ምልክቶች ከምርጫቸው ጋር ሳይጣጣሙ ሲቀሩ ችላ ይሏቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በኤርምያስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር ተመልከት። በዚያን ወቅት እስራኤላውያን ውሳኔ የሚያሻው ጉዳይ ገጥሟቸው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ አምላክ “መልካሟን፣ የጥንቷን መንገድ ጠይቁ፤ በእርሷም ላይ ሂዱ” በማለት መከራቸው። ይሁንና ሕዝቡ “በእርሷ አንሄድም” በማለት መለሱ። (ኤርምያስ 6:16) የዓመጽ አካሄዳቸው ‘መጨረሻው ምን ሆነ?’ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን የኢየሩሳሌምን ከተማ ድምጥማጧን ካጠፉ በኋላ ነዋሪዎቿንም በምርኮ ወሰዷቸው።

አምላክ የሰጠንን መመሪያዎች ችላ ማለት ፈጽሞ አይበጀንም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”—ምሳሌ 3:5, 6

አምላክ የሚሰጠን ማስጠንቀቂያዎች ጠቃሚ መመሪያዎችን ይዘውልናል። ለአብነት ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ ኀጥኣን ጐዳና እግርህን አታንሣ፤ በክፉ ሰዎች መንገድ አትሂድ” ይላል። (ምሳሌ 4:14) እንዲህ ካሉ መጥፎ መንገዶች መካከል በምሳሌ 5:3, 4 ላይ የተጠቀሰው ይገኝበታል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “የአመንዝራ ሴት ከንፈር ማር ያንጠባጥባልና፤ አንደበቷም ከቅቤ ይለሰልሳል፤ በመጨረሻ ግን እንደ እሬት ትመራለች፤ ሁለት አፍ እንዳለውም ስል ሰይፍ ትሆናለች።” አንዳንዶች ከሴተኛ አዳሪም ይሁን ከሌላ ሰው ጋር የጾታ ብልግና መፈጸም አስደሳች እንደሆነ አድርገው ያስቡ ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ የሰጠንን የሥነ ምግባር ደንቦች ችላ ማለት ከጥፋት በቀር የሚያስገኘው አንዳች ነገር የለም።

እንዲህ ባለው መንገድ ላይ መጓዝ ከመጀመርህ በፊት ‘ይህ መንገድ የት ያደርሰኛል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ‘መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል’ ላፍታ ቆም ብለህ ማሰብህ ብቻ እንኳ አስከፊ መዘዝ በሚያስከትል ጎዳና ላይ ከመጓዝ ሊጠብቅህ ይችላል። የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ችላ የሚሉ ሰዎች ኤድስና በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ ውርጃ፣ የቤተሰብ መፈራረስና የሕሊና ወቀሳ የመሳሰሉ ችግሮች ይደርስባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች የጉዟቸው መጨረሻ ምን እንደሆነ በግልጽ ሲናገር “የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” ብሏል።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

“መንገዱ ይህ ነው”

አንድ መንገድ ወዴት እንደሚወስድ ማወቅ አስቸጋሪ የሚሆንበት ጊዜ አለ። በመሆኑም አምላክ ፍቅራዊ አሳቢነት ስለሚያሳየንና ግልጽ መመሪያ ስለሚሰጠን እጅግ አመስጋኝ መሆን ይኖርብናል። ይሖዋ “መንገዱ ይህ ነው፤ በእርሱ ሂድ” ብሏል። (ኢሳይያስ 30:21) ይሖዋ ባሳየን መንገድ መጓዛችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ኢየሱስ፣ ይህ መንገድ ጠባብና አስቸጋሪ ቢሆንም ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚወስደን ተናግሯል።—ማቴዎስ 7:14

እስቲ እየተጓዝክበት ስላለኸው መንገድ ቆም ብለህ አስብ። እየተጓዝክ ያለኸው በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው? መንገዱ የሚወስድህ ወዴት ነው? ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው። ‘በመንገድ ካርታ’ የተመሰለውን መጽሐፍ ቅዱስን አንብብ። ሌላው ቀርቶ ልምድ ያለውን መንገደኛ ማለትም የአምላክን መመሪያ ለመከተል የሚጥርን ሰው መጠየቅ እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል። በመሆኑም አቅጣጫህን ማስተካከል እንዳለብህ ከተሰማህ ሳትዘገይ እርምጃ ውሰድ።

አብዛኛውን ጊዜ፣ አንድ መንገደኛ በትክክለኛው ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንዳለ የሚጠቁሙ የመንገድ ምልክቶችን ሲያይ ይበልጥ ይበረታታል። እየተጓዝክበት ያለኸውን የሕይወት ጎዳና ስትመረምር በጽድቅ መንገድ ላይ እንደሆንክ ካረጋገጥክ በዛው እንድትቀጥል እናበረታታሃለን። በዚህ መንገድ ላይ በመጓዝህ የምታገኘው ታላቅ በረከት ከፊትህ ይጠብቅሃል።—2 ጴጥሮስ 3:13

ሁሉም መንገዶች ወደ አንድ ቦታ ማድረሳቸው አይቀርም። ታዲያ የመረጥከው ጎዳና የት ያደርስህ ይሆን? ‘ወይኔ፣ ሌላ መንገድ መርጬ ቢሆን ኖሮ!’ እያሉ መቆጨት የሚፈይደው ነገር የለም። በመሆኑም ከዚህ በኋላ በሕይወት ጎዳና ላይ ስትጓዝ አንድ እርምጃ ከመራመድህ በፊት የመንገዱ ‘መጨረሻ ምን ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘መጨረሻው ምን ይሆን?’

ወጣቶች የተለመዱ የሚመስሉ ነገሮችን እንዲያደርጉ አብዛኛውን ጊዜ ይፈተናሉ ብሎም ጫና ይደረግባቸዋል። ሊያጋጥሙ የሚችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

አንድ ሰው ሲጋራ የማታጨሰው ወኔ ስለሌለህ እንደሆነ ቢነግርህ

አንድ አስተማሪ በቅን ልቦና ተነሳስቶ ዩኒቨርሲቲ ገብተህ ከፍተኛ ትምህርት እንድትከታተል ቢገፋፋህ

የአልኮል መጠጥ ምናልባትም ዕፅ በቀላሉ ወደሚገኝበት አንድ ግብዣ ቦታ ላይ እንድትገኝ ብትጋበዝ

“ፎቶህን ጨምሮ ስለ ማንነትህ የሚገልጹ መረጃዎችን በኢንተርኔት ላይ ለምን አታወጣም?” በማለት አንዱ ሐሳብ ቢያቀርብልህ

ጓደኛህ ዓመጽና የሥነ ምግባር ብልግና ያለበት ፊልም እንድታይ ቢጋብዝህ

ምን ታደርጋለህ? ለፈተናው እጅህን ትሰጣለህ ወይስ ‘መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል’ በጥንቃቄ ታስባለህ? ራስህን እንዲህ ብለህ መጠየቅህ ጥበብ ነው:- “ለመሆኑ ልብሱ ሳይቃጠል፣ በጕያው እሳት መያዝ የሚችል ሰው አለን? አንድ ሰው እግሮቹ ሳይቃጠሉ፣ በፍም ላይ መሄድ ይችላልን?”—ምሳሌ 6:27, 28