በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቃል ከሚተላለፉ መልእክቶች ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት ጽሕፈትና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

በቃል ከሚተላለፉ መልእክቶች ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት ጽሕፈትና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

በቃል ከሚተላለፉ መልእክቶች ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት ጽሕፈትና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች

በተለያዩ ጊዜያት የኖሩ በርካታ አማኞች እስከ ዛሬ ድረስ ከተዘጋጁት ጽሑፎች ሁሉ ታዋቂ የሆኑትን በተለምዶ አዲስ ኪዳን በመባል የሚታወቁትን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማንበብ፣ በማጥናትና በመመርመር ረጅም ጊዜ አሳልፈዋል። የተቀሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጨምሮ እነዚህ ጽሑፎች ቋሚ የሥነ ምግባር ደንቦችን ለማውጣት እንዲሁም ለሥነ ጽሑፍና ለሥነ ጥበብ ሥራዎች መነሻ በመሆን ረገድ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ከሁሉም በላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድተዋል። አንተም ከእነዚህ ሰዎች መካከል ትገኝ ይሆናል።—ዮሐንስ 17:3

ወንጌሎችም ሆኑ የተቀሩት የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት ኢየሱስ ከሞተ ቆየት ብለው ነው። ማቴዎስ ወንጌሉን የጻፈው ኢየሱስ ከሞተ 7 ወይም 8 ዓመታት ገደማ ቆይቶ ሲሆን ዮሐንስ የጻፈው ደግሞ ከ65 ዓመታት ገደማ በኋላ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ያደረጋቸውንና የተናገራቸውን ነገሮች በትክክል መጻፍ የቻሉት እንዴት ነው? የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እነሱን በመምራት ረገድ ጉልህ ሚና እንደተጫወተ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 14:16, 26 የ1980 ትርጉም) ይሁንና ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች በትክክል ሊተላለፉና የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው?

ምንም ያልተማሩ ናቸው” ሊባል ይችላል?

ባለፉት መቶ ዘመናት አንዳንዶች፣ የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ያስተማራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ለሌሎች ያስተላለፉት በጽሑፍ ሳይሆን በቃል እንደነበር ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “የወንጌል ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት የጻፉት ኢየሱስ ይህን ካከናወነ ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ነው። በእነዚህ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ስለ ኢየሱስ የሚናገሩት ዘገባዎች ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉት በቃል ነበር።” እንዲያውም አንዳንድ ተመራማሪዎች፣ የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት “ምንም ያልተማሩ ናቸው ቢባል ይቀላል” ብለው ይከራከራሉ። * በተጨማሪም ኢየሱስ ስላከናወነው አገልግሎት የሚገልጹት ዘገባዎች በቃል በሚተላለፉባቸው በርካታ አሥርተ ዓመታት ውስጥ እንደተለወጡ፣ እንደተጋነኑ ወይም ሌሎች ነገሮች እንደተጨማመሩባቸው ይናገራሉ። በዚህም የተነሳ የወንጌል ዘገባዎች ከእውነት የራቁ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሌላው አመለካከት ደግሞ አይሁዳውያን የሆኑት የኢየሱስ የቅርብ ደቀ መዛሙርት፣ በቃል የሚተላለፉ መልእክቶች እንዳይበረዙ አስተዋጽኦ ያደርግ የነበረውን የረቢዎችን የማስተማር ዘዴ ሳይከተሉ አልቀሩም የሚለው ነው፤ ረቢዎች አንድን ነገር በመደጋገም በቃል የመሸምደድ ልማድ ነበራቸው። ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚናገሩትን ዘገባዎች ለሰዎች ያስተላለፉት በቃል ብቻ ነበር ወይስ በጽሑፍ? በእርግጠኝነት መናገር ባንችልም ጽሕፈት የኢየሱስን አገልግሎት ዘግቦ በማቆየት ረገድ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ሰዎች ጽሕፈትን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ይጠቀሙበት ነበር

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉም ዓይነት ሰዎች ማንበብና መጻፍ ይችሉ ነበር። የዕብራይስጥና የጥንት የሴማዊ ቋንቋዎች ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት አለን ሚለርድ ይህን አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “በግሪክ፣ በአረማይክና በዕብራይስጥ ቋንቋዎች መጻፍ የተለመደ ከመሆኑም ሌላ መጻፍ የሚችሉ ሰዎች በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ውስጥ ይገኙ ነበር። . . . ኢየሱስ ያገለግል የነበረው በእንዲህ ዓይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ነበር።”

ፕሮፌሰር ሚለርድ፣ የወንጌል መጻሕፍት “የተጻፉት ፈጽሞ ማንበብና መጻፍ በማይችል ኅብረተሰብ ውስጥ ነው” የሚለውን ሐሳብ አስመልክተው እንዲህ ብለው ጽፈዋል:- “በየትኛውም አካባቢ ባሉ ሰዎች ዘንድ ጽሕፈት የተለመደ ስለነበር እንዲህ ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። . . . በመሆኑም በመረጃነት ለመያዝም ይሁን ለሌሎች ለመንገር ሲሉ የሰሙትን ነገር በጽሑፍ የማስፈር ልማድ ያላቸው ሰዎች ነበሩ።”

በወቅቱ፣ ሰም የተቀቡ የመጻፊያ ሰሌዳዎች በቀላሉ ይገኙ ስለነበር መረጃዎችን በጽሑፍ ለማስፈር ሳይጠቀሙባቸው አልቀሩም። በሉቃስ መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ታሪክ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። ለጊዜው የመናገር ችሎታውን አጥቶ የነበረው ዘካርያስ፣ ልጁ ማን ተብሎ እንዲጠራ እንደሚፈልግ ሲጠየቅ ቁጥር 63 እንደሚከተለው ማለቱን ይገልጻል:- “እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ [በምልክት ሳይሆን አይቀርም]፣ ‘ስሙ ዮሐንስ ነው’ ብሎ ጻፈ።” የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላቶች “ሰሌዳ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሰም እንደተቀባ የሚገመት ከእንጨት የተሠራ የመጻፊያ ፅላትን ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ። በዚያን ጊዜ ዘካርያስ ወዲያው መጻፍ የቻለው በወቅቱ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዱ የመጻፊያ ሰሌዳ ይዞ ስለነበር ሊሆን ይችላል።

በዘመኑ ሰዎች የመጻፊያ ሰሌዳዎች የመጠቀም ልማድ እንደነበራቸው የሚጠቁም ሌላ ምሳሌ እንመልከት። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ጴጥሮስ በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ ተሰብስበው የነበሩትን ሰዎች “ኀጢአታችሁ እንዲደመሰስ ንስሓ ግቡ” በማለት እንዳሳሰባቸው ይገልጻል። (የሐዋርያት ሥራ 3:11, 19) ‘መደምሰስ’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ማጥፋትና መጥረግ” የሚል ፍቺ ካለው የግሪክኛ ግስ የተገኘ ነው። ዘ ኒው ኢንተርናሽናል ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ቲኦሎጂ እንዲህ ይላል:- “በዚህም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ላይ ይህ ግስ የሚያስተላልፈው መልእክት በሰም የተቀባን አንድ የመጻፊያ ሰሌዳ በድጋሚ ጥቅም ላይ ለማዋል ሲባል በላዩ ላይ ያለውን ነገር ማጥፋትን ሳይሆን አይቀርም።”

የወንጌል ዘገባዎች፣ ከኢየሱስ ተከታዮችና አድማጮች መካከል አንዳንዶቹ ጽሕፈትን በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ይጠቀሙ እንደነበር ያሳያሉ። ለአብነት ያህል፣ ቀረጥ ሰብሳቢ የነበሩት ማቴዎስና ዘኬዎስ (ማቴዎስ 9:9፤ ሉቃስ 19:2)፤ የምኩራብ አለቃ (ማርቆስ 5:22)፤ የመቶ አለቃ (ማቴዎስ 8:5)፤ የሄሮድስ አንቲጳስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሚስት የነበረችው ዮሐና (ሉቃስ 8:3) እንዲሁም ጸሓፍት፣ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ይገኙበት ነበር። (ማቴዎስ 21:23, 45፤ 22:23፤ 26:59) ሁሉም ባይሆኑም እንኳ አብዛኞቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መጻፍ ይችሉ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ጸሐፊዎች

ደቀ መዛሙርቱ ክርስትናን ለማስተማር፣ ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሙሴ ሕግም ሆነ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት ትንቢቶች እንዴት በክርስቶስ ላይ ፍጻሜያቸውን እንዳገኙ መረዳት ያስፈልጋቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 18:5) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከተወሰኑ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገውን ውይይት ሉቃስ ዘግቧል። በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምን አደረገ? “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ስለ እርሱ የተጻፈውን አስረዳቸው።” ከዚያም ብዙ ሳይቆይ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “‘ከእናንተ ጋር በነበርሁበት ጊዜ፣ “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙር መጻሕፍት ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል” ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው’ አላቸው። በዚህ ጊዜ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያስተውሉ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:27, 44, 45) ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የነገራቸውን ነገሮች ከጊዜ በኋላ ‘ልብ ማለት’ ችለው ነበር።—ዮሐንስ 12:16

ቀደም ሲል የተጠቀሱት ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ ስለ ጌታቸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያዩትንና የሰሙትን ነገር ሙሉ በሙሉ መረዳት እንዲችሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተግተው መመርመርና ማጥናት ነበረባቸው። (ሉቃስ 1:1-4፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11) በቨርጂንያ ዩኒቨርስቲ የሃይማኖት ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ሃሪ ጋምብል ይህንን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከመጀመሪያው አንስቶ የአይሁዳውያንን [የዕብራይስጥ] ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ለመረዳት ምናልባትም በቡድን ሆነው ሳይሆን አይቀርም በትጋት የሚያጠኑ ክርስቲያኖች እንደነበሩ አያጠራጥርም። እነዚህ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ማስረጃ የሚሆኑ ጥቅሶችን ከአይሁድ [ከዕብራይስጥ] ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያሰባስቡ የነበረ ከመሆኑም ሌላ በስብከቱ ሥራቸውም ላይ ይጠቀሙባቸው ነበር።”

ይህ ሁሉ እንደሚያሳየው የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መልእክቱን በቃል በማስተላለፍ ከመወሰን ይልቅ ያጠኑ፣ ያነቡና ይጽፉ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎችና ጸሐፊዎች ነበሩ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ አመራር የሚታመኑ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ሰዎች ነበሩ። ኢየሱስ “የእውነት መንፈስ” ‘እሱ የነገራቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲያስታውሱ እንደሚያደርጋቸው’ ቃል ገብቶላቸዋል። (ዮሐንስ 14:17, 26 የ1980 ትርጉም) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደ ተራራው ስብከት ያሉ ረጃጅም ንግግሮችን ጨምሮ ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያከናወናቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ እንዲሁም በጽሑፍ ላይ እንዲያሰፍሩ ረድቷቸዋል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 5 እስከ 7) ከዚህም በተጨማሪ መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት አንዳንድ ጊዜ ምን ይሰማው እንደነበረና ምን ብሎ እንደጸለየ እንዲዘግቡ የወንጌል ጸሐፊዎችን መርቷቸዋል።—ማቴዎስ 4:2፤ 9:36፤ ዮሐንስ 17:1-26

በመሆኑም የወንጌል ጸሐፊዎች በቃልና በጽሑፍ የተላለፉ መረጃዎችን መጠቀማቸው የማያጠራጥር ቢሆንም በጽሑፍ ያሰፈሯቸው ነገሮች እጅግ አስተማማኝ ከሆነውና ከሁሉ ከላቀው ምንጭ ማለትም ከይሖዋ አምላክ የተገኙ ናቸው። ስለሆነም “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው” እንዲሁም አምላክን የሚያስደስቱ ነገሮችን እንድናደርግ ሊያስተምሩንና ሊመሩን የሚችሉ መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—2 ጢሞቴዎስ 3:16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል ጽሕፈትን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ይጠቀሙ የነበሩ ሰዎች ሳይገኙበት አይቀሩም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የጥንቶቹን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጌታቸው የተናገራቸውንና ያከናወናቸውን ነገሮች እንዲያስታውሱ እንዲሁም በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ ረድቷቸዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ሐዋርያት ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር?

ገዥዎችና የኢየሩሳሌም ሽማግሌዎች፣ ‘ጴጥሮስና ዮሐንስ በድፍረት ሲናገሩ ባዩአቸው ጊዜ፣ ያልተማሩ ተራ ሰዎች መሆናቸውን ተረድተው ተደነቁ።’ (የሐዋርያት ሥራ 4:13) በእርግጥ ሐዋርያቱ ያልተማሩ ወይም ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ነበሩ? ይህንን አስመልክቶ ዘ ኒው ኢንተርፕሪተርስ ባይብል የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል:- “ጴጥሮስ [እና ዮሐንስ] መደበኛ ትምህርት ያልተከታተሉ እንዲሁም ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ስለሚያስመስል ይህ አነጋገር ቃል በቃል መወሰድ የለበትም። ሰዎቹ እንዲህ ያሉት ሐዋርያቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸው ቦታ በእነሱ ላይ ለመፍረድ ከተቀመጡት ሰዎች እጅግ የተለየ መሆኑን ለመግለጽ ነው።”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተሠራ የሚገመት ሰም የተቀባ የመጻፊያ ሰሌዳና መጻፊያዎቹ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እርሱም መጻፊያ ሰሌዳ እንዲሰጡት ለምኖ፣ ‘ስሙ ዮሐንስ ነው’ ብሎ ጻፈ”

[ምንጭ]

© British Museum/Art Resource, NY