በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ”

“ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ”

“ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ”

ያኮፕ ኖይፌልድ እንደተናገረው

“ምንም ይሁን ምን ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ።” እነዚህ ቃላት በጆሮዬ እያቃጨሉ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዤ በአቅራቢያችን ወዳለው መንደር ደረስኩ። ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን ቤት ለማንኳኳት የሚያስችል ድፍረት አልነበረኝም። ለተወሰነ ጊዜ ከራሴ ጋር ስታገል ከቆየሁ በኋላ በአካባቢው ወዳለ ጫካ በመግባት ለመስበክ የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጠኝ አምላክን ተማጸንኩት። በመጨረሻም ወደ መጀመሪያው ቤት ተመልሼ በመሄድ መልእክቱን መናገር ቻልኩ።

ብቻዬን ለመስበክ ወደሞከርኩበት በፓራጓይ በረሃማ አካባቢ ወደሚገኘው ወደዚህ መንደር የመጣሁት እንዴት ነው? እስቲ ታሪኬን ከመጀመሪያው አንስቼ ላውጋችሁ። የተወለድኩት ኅዳር 1923 በዩክሬን በምትገኘው በክሮንስታል መንደር ሲሆን በዚህች መንደር ውስጥ የጀርመን ሜኖናውያን ማኅበረሰብ ይኖሩ ነበር። ሜኖናውያን፣ ከጀርመን ወደ ዩክሬን ፈልሰው የመጡት በ1700ዎቹ መገባደጃ ላይ ሲሆን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ፈቃድና የአምልኮ ነፃነት (ሃይማኖትን ማስለወጥ ግን አይቻልም) ማግኘት የቻሉ ከመሆኑም ሌላ ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ መሆንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መብቶች ነበሯቸው።

የኮሚኒስት ፓርቲ ሥልጣን ሲይዝ ግን እነዚህን መብቶች ሁሉ ተነፈጉ። በ1920ዎቹ መጨረሻ ላይ ሰፋፊ የሜኖናውያን የእርሻ ቦታዎች በገበሬ ማኅበር ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑ ተደረገ። የአካባቢው ነዋሪዎች ከመንግሥት ጋር ካልተባበሩ ምግብ የማይሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ተቃውሞ የሚያስነሳ ማንኛውም ሰው ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት ይጠብቀው ነበር። በ1930ዎቹ ዓመታት በርካታ ወንዶች በሌሊት በኬጂቢ (የሶቪየት ኅብረት የደኅንነት ኮሚቴ) እየታፈኑ ይወሰዱ የነበሩ ሲሆን ሁኔታው በመንደሮቹ ውስጥ ጥቂት ወንዶች እስኪቀሩ ድረስ ቀጥሎ ነበር። በ1938 የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ተወሰደ፤ ከዚያ በኋላ አይቼውም ሆነ ስለ እሱ ሰምቼ አላውቅም። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ታላቅ ወንድሜ ተወሰደ።

በ1941 የሂትለር ወታደሮች ዩክሬንን ወረሩ። ይህ ሁኔታ ከኮሚኒስት አገዛዝ ነፃ ለመውጣት አስቻለን። ይሁን እንጂ በአካባቢያችን ይኖሩ የነበሩ ስምንት አይሁዳውያን ቤተሰቦች የገቡበት ሳይታወቅ ቀረ። እነዚህ ነገሮች፣ ‘ይህ ሁሉ የሚሆነው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ እንዲፈጠርብኝ አደረጉ።

ሐቀኛ መሆኔ ሕይወቴን አትርፎልኛል

በ1943 የጀርመን ወታደሮች ቤተሰቦቼን ጨምሮ አብዛኞቹን ጀርመናውያን በመያዝ ወደኋላ አፈገፈጉ። ይህን ያደረጉት ለጦርነቱ ተጨማሪ ኃይል እንደሚሆኗቸው በማሰብ ነው። በወቅቱ የጀርመን ኤስ ኤስ (ሹትስስታፈል የሚባለው የሂትለር ልዩ ወታደር) እንድሆን ተመልምዬ ሩማኒያ በሚገኘው ሠራዊት ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ። በዚህ ጊዜ ያጋጠመኝ ትንሽ ነገር በሕይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።

የቡድን ኃላፊያችን ሐቀኛ መሆን አለመሆኔን ለመፈተን ስለፈለገ የደንብ ልብሱን ወደ ልብስ ንጽሕና መስጫ እንድወስድለት ጠየቀኝ። በልብሱ ኪስ ውስጥ የተወሰነ ገንዘብ ሆነ ብሎ አስቀምጦ ነበር። እኔም ኪሶቹን ስፈትሽ ገንዘቡን አገኘሁት። በኋላም ገንዘቡን ስመልስለት ልብሱ ውስጥ ምንም ነገር እንዳላስቀመጠ ገለጸልኝ። እኔም ገንዘቡን ያገኘሁት ኪሱ ውስጥ እንደሆነ አስረግጬ ነገርኩት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የቡድን ኃላፊያችን ረዳት የሆንኩ ሲሆን የወረቀት ሥራዎችን እንድሠራ፣ የጥበቃ ሠራተኞችን እንድመድብና የቡድናችንን ገንዘብ እንድቆጣጠር ኃላፊነት ተሰጠኝ።

አንድ ምሽት፣ የሩሲያ ወታደሮች ከእኔ በስተቀር ሁሉንም የቡድኑን አባላት ማረኳቸው። ከዚህ መጥፎ አጋጣሚ ያመለጥኩት አለቃችን ያዘዘኝን ሥራ ለማጠናቀቅ ቢሮ ውስጥ በመቆየቴ ነበር። እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ ከመያዝ ያመለጥኩት እኔ ብቻ ስሆን ይህም የሆነው ሐቀኛ በመሆኔና በዚህ ልዩ ሥራ ላይ በመመደቤ ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ እኔም መያዜ አይቀርም ነበር።

በመሆኑም በ1944 ላልተወሰነ ጊዜ ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ እንድሆን የሚያስችል ፈቃድ ስለተሰጠኝ እናቴን ለመጠየቅ ሄድኩ። የሥራ ምድቤን በመጠባበቅ ላይ እያለሁ የአንድ ግንበኛ ረዳት በመሆን ሙያ ተማርኩ። በዚህ ወቅት ያገኘሁት ሥልጠና የኋላ ኋላ ጠቅሞኛል። በሚያዝያ 1945 የአሜሪካ ወታደሮች በማግድበርግ አቅራቢያ የምትገኘውን ከተማችንን ተቆጣጠሯት። ከአንድ ወር በኋላ ጦርነቱ አበቃ። እኛም በሕይወት መትረፍ የቻልን ሲሆን ተስፋችንም ብሩህ ይመስል ነበር።

በሰኔ ወር ላይ አንድ ቀን፣ “የአሜሪካ ወታደሮች ትላንት ማታ ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል፤ የሩሲያ ወታደሮች ደግሞ ዛሬ ከጠዋቱ በ5:00 ወደ ከተማዋ ይደርሳሉ” የሚል ልፈፋ ሰማን። አካባቢው ዳግም በኮሚኒስት ቁጥጥር ሥር መዋሉን ስንሰማ ተስፋችን ደበዘዘ። በዚህ ጊዜ እኔና የአጎቴ ልጅ እንዴት ብለን ማምለጥ እንደምንችል ማሰብ ጀመርን። በክረምቱ ወራት አጋማሽ ላይ አሜሪካኖች ወደሚቆጣጠሩት ክልል መግባት ቻልን። ከዚያም በኅዳር ወር፣ ሁኔታው ለሕይወት አደገኛ ቢሆንም ሩሲያ ትቆጣጠረው ወደነበረው ክልል ውስጥ በመግባት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ቤተሰቦቻችንን በድብቅ ይዘን ወደመጣንበት ተመለስን።

“በጥሞና አዳምጥና ለማወዳደር ሞክር”

በዚያን ጊዜ ምዕራብ ጀርመን ተብሎ ይጠራ በነበረው አገር መኖር ጀመርን። ከጊዜ በኋላ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እያደረብኝ ሄደ። እሁድ እሁድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወደ ጫካ እሄድ ነበር። ሆኖም የማነበው ነገር እንግዳ የሆነብኝ ሲሆን በጥንት ዘመን ስለተፈጸሙ ክንውኖች ብቻ የሚናገርም መሰለኝ። በዚህ ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ በተጨማሪ የተጠመቅኩ ሜኖናዊ ለመሆን ስል የሃይማኖት ትምህርት መከታተል ጀመርኩ። የሃይማኖት ትምህርት በምንማርበት መጽሐፍ ውስጥ የሚከተለውን ሐሳብ ሳነብ እጅግ ተገረምኩ:- “አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው።” መጽሐፉ በመቀጠል “ታዲያ ሦስት አምላኮች አሉ?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ከዚያም መልሱን ሲሰጥ “በፍጹም፣ ሦስቱም አንድ ናቸው” ይላል። እኔም አገልጋዩን ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ጠየቅኩት። እሱም እንዲህ አለኝ:- “አንተ ወጣት፣ አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ማድረግ የለበትም። አንዳንዶች እንዲህ ሲያደርጉ አእምሯቸው ተነክቷል።” እኔም ወዲያው፣ ላለመጠመቅ ወሰንኩ።

ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ከዚህ በፊት አይቼው የማላውቀው አንድ ሰው የአክስቴን ልጅ ሲያነጋግራት ሰማሁ። ስለ ሁኔታው ለማወቅ ጉጉት ስላደረብኝ በውይይታቸው ውስጥ ጣልቃ ገብቼ አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቅኩት። ይህ ሰው ከቬቭልስበርግ የማጎሪያ ካምፕ በሕይወት ከተረፉት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ኤሪክ ኒኮላይዚግ መሆኑን የተገነዘብኩት ከጊዜ በኋላ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም አዎንታዊ ምላሽ ስሰጠው፣ የሚያስተምረኝ ትምህርት ሁሉ እውነት መሆኑን ከራሴ መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ እንደሚሰጠኝ አረጋገጠልኝ።

ኤሪክ ጥቂት ጊዜ እየተመላለሰ ከጠየቀኝ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ እንዲህ ያለውን ስብሰባ ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ሳይሆን አይቀርም። ስብሰባው እጅግ ያስደነቀኝ ከመሆኑም በላይ ተናጋሪዎቹ የሚጠቅሷቸውን ጥቅሶች በሙሉ በማስታወሻዬ ላይ አሰፍር ነበር። ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን መማር ኃላፊነት እንደሚያስከትል ስለተገነዘብኩ ጥናቴን ለማቆም ወሰንኩ። ከዚህም በተጨማሪ እውነተኛ ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው የሚለውን ትምህርት ለመረዳት ከብዶኝ ነበር። ኤሪክ፣ ቀድሞ እሄድበት ወደነበረው ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ መወሰኔን ሲያውቅ የሚከተለውን ምክር ሰጠኝ:- “በጥሞና አዳምጥና ለማወዳደር ሞክር።”

የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልጋዮች ሁለት ጊዜ ካነጋገርኳቸው በኋላ የሚያስተምሩትን እንደማያውቁና እውነት ፈጽሞ እነሱ ጋር እንደሌለ ተረዳሁ። ለበርካታ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችን ጽፌ ላኩላቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ “ዳግም ስላልተወለድክ መጽሐፍ ቅዱስን የመመርመር መብት የለህም” በማለት መለሰልኝ።

በወቅቱ ከአንዲት ሴት ጋር ለመጋባት እየተጠናናን የነበረ ሲሆን ልጅቷም አንድ ከባድ ምርጫ ከፊቴ አስቀመጠችልኝ። ይህች ልጅ፣ ዳግም ልደት ተብሎ የሚጠራ የሜኖናውያን እምነት አባል ነበረች። ልጅቷ የይሖዋ ምሥክሮችን ይጠሉ የነበሩ ወላጆቿ ባሳደሩባት ተጽዕኖ ስለተንበረከከች አዲሱን ሃይማኖቴን መመርመሬን ካልተውኩ ከእኔ ጋር መጠናናቷን እንደምታቆም ነገረችኝ። በዚህ ወቅት ማድረግ ያለብኝ ትክክለኛ ውሳኔ ምን መሆኑን በሚገባ ተገንዝቤ ስለነበር ከእሷ ጋር መገናኘቴን አቆምኩ።

ብዙም ሳይቆይ ኤሪክ ተመልሶ ሊጠይቀኝ መጣ። በቀጣዩ ሳምንት የጥምቀት ሥነ ሥርዓት እንደሚከናወን ከነገረኝ በኋላ መጠመቅ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት እውነት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ ስለደረስኩ ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ፈልጌ ነበር። በመሆኑም ግብዣውን ተቀብዬ በግንቦት 1948 በመታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅኩ።

ከተጠመቅኩ ብዙም ሳይቆይ ቤተሰቦቼ በደቡብ አሜሪካ ወደምትገኘው ወደ ፓራጓይ ለመሄድ ወሰኑ፤ እናቴም አብሬያቸው እንድሄድ ለመነችኝ። ይሁን እንጂ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትና ሥልጠና ለማግኘት ፈልጌ ስለነበር ልመናዋን ለመቀበል አቅማማሁ። በቪዝባድን የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ስጎበኝ ከኦገስት ፒተርስ ጋር ተገናኘሁ። ፒተርስ፣ ቤተሰቤን የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለብኝ እንዳስተውል የረዳኝ ከመሆኑም በላይ የሚከተለውን ምክር ሰጠኝ:- “ምንም ይሁን ምን ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ። ይህን ማድረግህን የምትዘነጋ ከሆነ እንደ ሌሎቹ የሕዝበ ክርስትና አባላት ትሆናለህ።” ይህ ምክር አሁንም ድረስ የጠቀመኝ ሲሆን “ከቤት ቤት” እየሄዱ የመስበክን አስፈላጊነት አስገንዝቦኛል።—የሐዋርያት ሥራ 20:20, 21

በፓራጓይ “ሐሰተኛ ነቢይ” ተባልኩ

ከኦገስት ፒተርስ ጋር ከተነጋገርኩ ብዙም ሳይቆይ ከቤተሰቤ ጋር በመርከብ ተሳፍረን ወደ ደቡብ አሜሪካ አቀናን። በመጨረሻም ፓራጓይ ውስጥ ወደምትገኘው ግራን ቻኮ ደረሰን፤ በዚህም አካባቢ የሜኖናውያን ማኅበረሰብ ይኖሩ ነበር። እዚያ ከደረስን ከሁለት ሳምንት በኋላ በመግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት በአቅራቢያችን ባለው መንደር ውስጥ ብቻዬን ለመስበክ ተጓዝኩ። በአካባቢውም ‘በቅርቡ ከመጡት ሰዎች መካከል “ሐሰተኛ ነቢይ” አለ’ የሚል ወሬ በፍጥነት ተሰራጨ።

በዚህ ወቅት፣ ቀደም ሲል ግንበኛ ለመሆን የወሰድኩት ሥልጠና ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ወደ አካባቢው ተሰዶ የመጣው እያንዳንዱ ቤተሰብ ቤት ያስፈልገው ነበር። እነዚህ ቤቶች የሚሠሩት ከጡብ ሲሆን የሣር ክዳንም ይኖራቸዋል። ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት በሥራ ተወጥሬ የነበረ ሲሆን መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችም ነበሩኝ። ሰዎቹ በባሕርያቸው ሰው አክባሪ ቢሆኑም የቤታቸውን ግድግዳ ሠርቼ እንደጨረስኩ ከአጠገባቸው እንድርቅላቸው ይፈልጉ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጀርመን ተጨማሪ ሜኖናውያን ስደተኞች በመርከብ መጡ። ከእነሱ መካከል ካትሪና ሼለንበርግ የተባለች ወጣት ትገኝበታለች። ይህች ወጣት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘችው ለጥቂት ጊዜ ቢሆንም የሚያስተምሩት እውነት መሆኑን መገንዘብ ችላ ነበር። ያልተጠመቀች ብትሆንም በጉዞ ላይ ሳለች የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች በመናገሯ አብረዋት ይጓዙ የነበሩ ጀርመናውያን ከእነሱ ጋር እንዳትኖር ከለከሏት። በመሆኑም የፓራጓይ ዋና ከተማ በሆነችው በአሱንሲዩን የቤት ሠራተኛ ሆና የተቀጠረች ሲሆን ስፓንኛም ተማረች። ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጋ ካገኘቻቸው በኋላ ተጠመቀች። በጥቅምት 1950 ከዚህች ቆራጥ ሴት ጋር ተጋባን። አብረን በኖርንባቸው በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ካትሪና ግሩም ረዳት ሆናልኛለች።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንዘብ በማጠራቀም ጋሪና ሁለት ፈረሶችን መግዛት ቻልኩ። የኦገስት ፒተርስ ምክር ምንጊዜም ከአእምሮዬ ስለማይጠፋ ጋሪውን ለስብከቱ ሥራ እጠቀምበት ነበር። በዚህ ጊዜ፣ የይሖዋ ምሥክር የነበረችው እህቴ ከእኛ ጋር ለመኖር መጣች። ብዙውን ጊዜ ከሌሊቱ በ10:00 ከመኝታችን በመነሳት ለአራት ሰዓታት የምንጓዝ ሲሆን ለሁለት ወይም ለሦስት ሰዓታት ስንሰብክ ከቆየን በኋላ ወደ ቤታችን እንመለስ ነበር።

በጽሑፎቻችን ውስጥ የሕዝብ ንግግር እንደሚደረጉ አንብቤ ስለነበር እኔም እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራም አዘጋጀሁ። በጀርመን ሳለሁ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ስለማላውቅ የሕዝብ ንግግሩ እንዴት ሊቀርብ እንደሚችል ገመትኩ፤ ከዚያም ስለ አምላክ መንግሥት ንግግር አቀረብኩ። በዚህ ስብሰባ ላይ ስምንት ሰዎች የተገኙ ሲሆን ይህ ደግሞ የሜኖናውያን ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን አበሳጫቸው። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋዮች፣ አበርክተናቸው የነበሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከሕዝቡ አንድም ሳይቀር ለመሰብሰብ ዘመቻ ያዘጋጁ ከመሆኑም በላይ በፍጹም ሰላም እንዳይሉን ትእዛዝ አስተላለፉ።

ከዚያም ወደ አካባቢው የአስተዳደር ቢሮ ከተጠራሁ በኋላ አስተዳዳሪውና ከካናዳ የመጡ ሁለት የሃይማኖት አገልጋዮች ለበርካታ ሰዓታት ጥያቄዎች አቀረቡልኝ። በመጨረሻም ከመካከላቸው አንዱ እንዲህ አለኝ:- “አንተ ወጣት፣ በፈለግከው ማመን ትችላለህ ሆኖም ስለ እምነትህ ለማንም ሰው እንደማትናገር ቃል መግባት ይኖርብሃል።” ይህ ደግሞ ፈጽሞ ላደርገው የማልችለው ነገር ነው። በመሆኑም “በታማኝ ወንድሞች” መካከል “ሐሰተኛ ነቢይ” ስለማይፈልጉ አካባቢውን ለቅቄ እንድሄድ ነገሩኝ። ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ስነግራቸው ለቤተሰባችን በሙሉ የጉዞ ወጪ እንደሚሸፍኑልን ገለጹልኝ። ይሁንና በአቋሜ በመጽናት አካባቢውን ለቅቄ እንደማልሄድ ነገርኳቸው።

በ1953 ክረምት ላይ በአሱንሲዮን ወደሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመካፈል ሄድኩ። በዚያም ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የመጣውን ናታን ኖርን አገኘሁት። እሱም፣ በሜኖናውያን ማኅበረሰብ ውስጥ የምናካሄደው አገልግሎት ፍሬያማ ስላልነበር ወደ ዋናው ከተማ ተዛውረን በዚያ ካሉት ጥቂት ሚስዮናውያን ጋር ብናገለግል የተሻለ እንደሆነ ሐሳብ አቀረበልኝ።

የአምላክን መንግሥት ማስቀደም

በዚያን ጊዜ በመላው ፓራጓይ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች 35 ብቻ ነበሩ። ባለቤቴ ወደ ትልቅ ከተማ መዛወሩ ያን ያህል ባያስደስታትም ወደዚያ በመሄድ አዲስ ሕይወት ለመጀመር ፈቃደኛ ነበረች። በ1954 እኔና ካትሪና በትርፍ ጊዜያችን ብቻችንን ሆነን የጡብ ቤት ሠራን። እንደዛም ሆኖ ከስብሰባዎች ፈጽሞ ቀርተን የማናውቅ ከመሆኑም ሌላ ዘወትር ቅዳሜና እሁድ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች እንናገር ነበር።

ካገኘኋቸው መብቶች አንዱ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ከሚያገለግለው የወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር አብሬ በመሄድ ጀርመንኛ በሚናገሩ አንዳንድ የፓራጓይ አካባቢዎች ንግግር ሲሰጥ ማስተርጎም ነበር። ከተቀበልኳቸው ኃላፊነቶች ሁሉ እጅግ ከባድ የሆነብኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የስፓንኛን ንግግር ወደ ጀርመንኛ እንድተረጉም የተጠየቅኩበት ጊዜ ነበር፤ በወቅቱ ስፓንኛ እምብዛም ስለማልችል ይህ ለእኔ ፈታኝ ነበር።

በባለቤቴ ጤንነት ምክንያት በ1957 ወደ ካናዳ ሄድን። ከዚያም በ1963 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተዛወርን። የትም እንኑር የት በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ ለመስጠት እንጥር ነበር። (ማቴዎስ 6:33) ይሖዋ አምላክ፣ ገና ወጣት ሳለሁ ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን እንዳውቅ ስለረዳኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። ያገኘሁት መንፈሳዊ ሥልጠና በመላው ሕይወቴ በብዙ መንገዶች ጠቅሞኛል!

ታላቅ መጽናኛ ያስገኙልኝን ግሩም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሌሎች እንዲያውቁ መርዳት ትልቅ መብት ነው። ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ ደግሞ ሁሉም ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጠና ማግኘታቸው ነው። ከረጅም ጊዜ በፊት ፒተርስ “ምንም ይሁን ምን ከቤት ወደ ቤት ማገልገልህን ፈጽሞ እንዳትረሳ” በማለት የሰጠኝን ምክር በመከተል ላይ ናቸው።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ከምንም በላይ የሚያስደስተኝ ሁሉም ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ከሕፃንነታቸው ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጠና ማግኘታቸው ነው

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል1]

እኔና ካትሪና በ1950 ከመጋባታችን ከጥቂት ጊዜ በፊት

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1952 በፓራጓይ በሚገኘው ቤታችን ከመጀመሪያ ልጃችን ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልጆቻችንና ከልጅ ልጆቻችን ጋር በዛሬው ጊዜ

[ምንጭ]

Photo by Keith Trammel © 2000

[ገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photo by Keith Trammel © 2000