በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ኮኮ ወንዝ ስትደርስ ወደ ቀኝ ታጠፍ”

“ኮኮ ወንዝ ስትደርስ ወደ ቀኝ ታጠፍ”

ከኒካራጓ የተላከ ደብዳቤ

“ኮኮ ወንዝ ስትደርስ ወደ ቀኝ ታጠፍ”

“የመስክ መኪና፣ መጎተቻ ካቦና ተጨማሪ ነዳጅ መያዝ ያስፈልግሃል። እስከ መኪናው ሻንሲ የሚደርስ ጭቃ ሊያጋጥምህ እንደሚችል መጠበቅ አለብህ። ኮኮ ወንዝ ስትደርስ ወደ ቀኝ ታጠፍ።”

እንደ እኔው ሚስዮናዊ የሆነ አንድ የይሖዋ ምሥክር የተናገራቸው እነዚህ ቃላት ፍርሃት እንዳሳደሩብኝ አልክድም። ያም ሆኖ፣ አንድ ቀን ጠዋት በሰሜን ኒካራጓ በምትገኘው ዋንብላን በምትባል አነስተኛ ከተማ ውስጥ በሚደረገው ትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ጉዞ ጀመርኩ።

ዕለቱ ማክሰኞ ሲሆን ጎህ ሲቀድ አሮጌ ሆኖም ጠንካራ የሆነው መኪናዬን አስነስቼ ለጥ ባለው የፓን አሜሪካ አውራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀመርኩ። ሂኖቴጋ ወደተባለው ከተማ ስደርስ የአካባቢው ሰዎች ፌኦ ማለትም አስቀያሚ ብለው ወደሚጠሩት ኮረኮንች መንገድ ገባሁ። ከተማዋን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት የአምላክ ተአምርና ትንሣኤ የሚል ስም ያላቸው ሁለት ሱቆችን ተመለከትኩ።

መንገዱ ጠመዝማዛ እንዲሁም አቀበትና ቁልቁለት የበዛበት ነበር። በሸለቆው ውስጥ በቀስታ እየነዳው አለፍኩ። በደመና በተሸፈነ ተራራ ላይ ባለ ትልቅ ሐይቅ አጠገብ ተጓዝኩ። በጉሙ ውስጥ ስፓኒሽ ሞስ በተባለ የእንጨት ሽበትና በአበባዎች የተሸፈኑ ዛፎችን አየሁ።

አንድ አደገኛ ኩርባ ላይ ስደርስ መሃል መንገዱን ይዞ ሲታጠፍ ከነበረ አውቶቡስ ጋር ከመጋጨት ለጥቂት ተረፍኩ። አውቶቡሱ የሚያወጣው ጭስ ኃይለኛ ከመሆኑም በላይ ጎማዎቹ ድንጋይ ያስፈነጥሩ ነበር። ኒካራጓ ውስጥ በአውቶቡሶቹ የፊት መስታወት ላይ ሹፌሮቹ ምን ያህል ጠበኞች እንደሆኑ የሚገልጹ ድል አድራጊ፣ ጊንጥ፣ ዘንዶ ወይም አዳኝ የሚሉ ቅጽል ስሞችን ማየት የተለመደ ነው።

ቀትር ላይ የፓንታስማን ለጥ ያለ ሜዳ እያቋረጥኩ ነበር። በዚያም ግቢው የተጠረገ ከእንጨት የተሠራ ቤት ተመለከትኩ። አንድ አረጋዊ በአግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጠዋል። አንድ ውሻ ደግሞ ዛፍ ሥር ተኝቶ የነበረ ሲሆን በሁለት በሬዎች የሚጎተት ከእንጨት የተሠራ ጎማ ያለው ጋሪም ቆሞ ነበር። በአንድ አነስተኛ ከተማ ሳልፍ ደግሞ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሲለቀቁ ተመለከትኩ። ጥቁር ሰማያዊ ዩኒፎርም የለበሱት ተማሪዎች ዋናውን መንገድ እንደ ጎርፍ አጥለቀለቁት።

ዊዊሊ ስደርስ ፀሐይዋ ፍንትው ብላ ትታይ የነበረ ሲሆን የኮኮ ወንዝን ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለከትኩ። ያለማቋረጥ የሚፈሰው ይህ ትልቅ ወንዝ ለከተማዋ ልዩ ውበት ሰጥቷታል። በተሰጠኝ መመሪያ መሠረት ወደ ቀኝ በመታጠፍ ወደ ዋንብላን የሚወስደውን 37 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍነውን አስቸጋሪ መንገድ ተያያዝኩት።

መንገዱ ኮረኮንችና የመኪና ጎማ የቆፋፈረው ሲሆን ስምንት ወይም ዘጠኝ የሚሆኑ ጅረቶችንም ማቋረጥ ነበረብኝ። ጉድጓዶች ውስጥ ላለመግባት በማደርገው ጥረት አካባቢው አቧራ በአቧራ ይሆን ነበር። የአካባቢው ሰዎች እንደሚሉት “አቧራውን ቃምኩት።” በመጨረሻም በደን ወደተሸፈነችው ዋንብላን ደረስኩ።

በማግሥቱ፣ ሰው ሁሉ ከሌሊቱ በ10:30 ከእንቅልፉ የተነሳ ይመስላል። ማቆሚያ የሌለው የአውራ ዶሮ ጩኸት ከእንቅልፌ ስለቀሰቀሰኝ ከተኛሁበት ተነስቼ በዋናው መንገድ ላይ በእግሬ መጓዝ ጀመርኩ። ከድንጋይ በተሠራ ምድጃ ላይ የሚጋገረው ቶርቲላ የተባለው ቂጣ ሽታ አካባቢውን አውዶታል።

በአካባቢው ያለ አንድ ሠዓሊ የሳላቸው ገነትን የሚያሳዩ በቀለማት ያሸበረቁ ሥዕሎች በየግድግዳዎቹ ላይ ይታያሉ። በየመንገዱ ዳር ላይ የሚገኙ ፑልፔሪያ የሚባሉት ሱቆች የተለያዩ የለስላሳ መጠጦችን የሚያስተዋውቁ ምልክቶች አሏቸው። ያለፉት ሦስት መንግሥታት ለሕዝቡ እንፈጽመዋለን ብለው የገቡትን ቃል የሚያስታውሱ ወረቀቶች በከተማው ውስጥ ተለጥፈው ይታያሉ። ወለላቸው ሲሚንቶ የሆነና በቆርቆሮ የተሠሩ መጸዳጃ ቤቶችም ይገኛሉ።

የአካባቢውን ሰዎች ሳገኝ አዲዮስ በማለት ሰላምታ እሰጥ ነበር። አዲዮስ በስፓንኛ ለስንብት የሚጠቀሙበት ቃል ሲሆን በኒካራጓ ቋንቋ ግን ሰላምታ ለመስጠት ያገለግላል። ሰዎቹም በምላሹ ፈገግ በማለት ወዳጃዊ በሆነ ስሜት ያነጋግሩኝ ነበር። በአካባቢው በሚያልፉት የፈረሶችና የበቅሎዎች ኮቴ የተነሳ ጮክ ብለን እናወራ ነበር።

ዓርብ ማታ ላይ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከተለያዩ ቦታዎች ሰዎች መምጣት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የመጡት በእግራቸው፣ በፈረስና በጭነት መኪና ነበር። አንዳንድ ትንንሽ ልጆች ኮንጎ ጫማ አድርገው ለስድስት ሰዓታት ያህል ተጉዘዋል። ወንዙ ውስጥ አልቅትና የተቀበሩ ፈንጂዎች ቢኖሩም በድፍረት አቋርጠዋል። አንዳንዶቹ የመጡት ራቅ ካሉ አካባቢዎች ሲሆን የያዙትም ምግብ በአሳማ ሥጋ የተሠራ ጥቂት ሩዝ ብቻ ነበር። ይሁንና እነዚህ ሰዎች ወደ ስብሰባው የመጡት ለምን ነበር?

እነዚህ ሰዎች የመጡት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸውን ብሩህ ተስፋ ለማጠናከርና መጽሐፍ ቅዱስ ሲብራራ ለማዳመጥ እንዲሁም አምላክን ለማስደሰት ነው።

በጉጉት ስንጠብቀው የነበረው ቅዳሜ ደረሰ። ቆርቆሮ ክዳን ባለው መጠለያ ውስጥ ከ300 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች በአግዳሚዎችና በፕላስቲክ ወንበሮች ላይ ተቀምጠዋል። እናቶች ልጆቻቸውን ሲመግቡ ይታያሉ። በአቅራቢያው ባለው የእርባታ ጣቢያ ውስጥ ያሉት አሳማዎችና ዶሮዎች ሲጮሁ ይሰማሉ።

ሙቀቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ቆየት ብሎም ለመቋቋም አስቸጋሪ ሆነ። ይሁንና ተሰብሳቢዎቹ የሚሰጠውን ምክርና መመሪያ በትኩረት ያዳምጡ ነበር። እንዲሁም ተናጋሪዎቹ የሚያነቧቸውን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው አውጥተው ይከታተሉ፣ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረቱትን መዝሙሮች ይዘምሩ ብሎም እነሱን በመወከል የሚቀርበውን ጸሎት በአክብሮት ያዳምጡ ነበር።

የዕለቱ ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ ከአንዳንድ ወንድሞች ጋር ሆነን ከልጆቹ ጋር አባሮሽ ተጫወትን። ከዚያም ልጆቹ የጻፏቸውን ማስታወሻዎች ከለስን። እኔም በኮምፒውተሬ ውስጥ የነበሩትን የከዋክብትንና የጋላክሲዎችን ፎቶግራፎች አሳየኋቸው። ልጆቹም ሆኑ ወላጆቻቸው በሁኔታው ተደሰቱ።

ምንም ሳይታወቀን ስብሰባው አለቀ፤ እናም ሁሉም ሰው ወደየቤቱ መሄድ ነበረበት። እኔም በነጋታው ጠዋት፣ ልቤ አስደሳች በሆኑ ትዝታዎችና አዲስ ባገኘኋቸው ወዳጆቼ ፍቅር ተሞልቶ ወደ መጣሁበት ለመመለስ ጉዞ ጀመርኩ። የእነሱን ምሳሌ ለመኮረጅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጌ የነበረ ሲሆን ባለኝ መርካትና አምላክን በትዕግሥት መጠበቅ እንዳለብኝም ተምሬያለሁ።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ ቤተሰቦች በዋንብላን በሚደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘዋል