በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰማዩ አባታችን በእርግጥ ምን ዓይነት አምላክ ነው?

የሰማዩ አባታችን በእርግጥ ምን ዓይነት አምላክ ነው?

የሰማዩ አባታችን በእርግጥ ምን ዓይነት አምላክ ነው?

ብዙ ሰዎች፣ አቡነ ዘበሰማያት ወይም አባታችን ሆይ በመባል የሚታወቀውን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረውን የናሙና ጸሎት በቃላቸው ይወጡታል። (ማቴዎስ 6:9-13) ይህንን ጸሎት በሚጸልዩበት ጊዜ ሁሉ፣ አምላክን “አባታችን” በማለት ይጠሩታል። ይሁን እንጂ አምላክን በደንብ አውቀዋለሁ ሊሉ የሚችሉት ስንቶቹ ናቸው?

አንተስ፣ አምላክን ምን ያህል ታውቀዋለህ? ከእሱ ጋር የተቀራረበ ዝምድና አለህ? ወደ እሱ ትጸልያለህ? ደስታህንና ሐዘንህንስ ትገልጽለታለህ? በእርግጥ አምላክን ማወቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

ስሙ “ይሖዋ” ነው

አንድ ድክድክ የሚል ሕፃን ስለ አባቱ የሚያውቀው ነገር ቢኖር አባባ ብሎ መጥራት ብቻ ሊሆን ይችላል። እያደገ ሲሄድ ግን የአባቱን ስምና ባሕርይ እያወቀ መምጣቱ እንዲሁም በአባቱ መመካት መጀመሩ አይቀርም። በሰማይ ስላለው ፈጣሪያችንስ ምን ማለት ይቻላል? ስሙን ታውቀዋለህ? ትርጉሙንስ?

ብዙዎች አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት በሚያቀርቡበት ጊዜ “ስምህ ይቀደስ” በማለት ይጸልያሉ። ሆኖም “ይህ ስም ማነው?” ተብለው ቢጠየቁ መልስ ላይኖራቸው ይችላል። በከዋክብት የተሞላው ሰማይና ግርማ ሞገስ የተላበሰው ተራራ እንዲሁም አስደናቂ የሆኑት የባሕር ፍጥረታት አምላክ ስለመኖሩ ማስረጃ ይሆኑናል። ይሁንና የአምላክ ስም ማን እንደሆነ አይነግሩንም። ስሙን ለማወቅ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር ማለት ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ ስም “ይሖዋ” እንደሆነ ይነግረናል።— ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም

አምላክ፣ ይሖዋ የሚለውን ስሙን እንድናውቅ ይፈልጋል። ለምን? ምክንያቱም ማንነቱን ይገልጻል። ስሙ ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ይሖዋ፣ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። እስቲ ይህን ምሳሌ ተመልከት:- አንድ አባት እንደ ቤተሰቡ ሁኔታ አስተዳዳሪ፣ አማካሪ፣ ዳኛ፣ አስታራቂ፣ ጠባቂና አስተማሪ በመሆን ቤተሰቡን ይንከባከባል። በተመሳሳይም ይሖዋ የሚለው ስም፣ እሱን የሚያገለግሉትን ሰዎች ለመባረክ የገባውን ቃል ከመፈጸም የሚያግደው ነገር እንደሌለ ማረጋገጫ ይሰጠናል።

አፍቃሪው አምላካችን ከስሙ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ምን ነገሮችን እንዳከናወነ እስቲ እንመልከት። ይህም፣ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለማወቅና ወደ እሱ ለመቅረብ ምን ማድረግ እንዳለብህ ለመገንዘብ ያስችልሃል።

‘የፍቅርና የሰላም አምላክ’

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ፈጣሪያችንን ‘የፍቅርና የሰላም አምላክ’ በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 13:11) አምላክን እንዲህ ሲል የጠራው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና።” (ዮሐንስ 3:16) አምላክ ለሰው ዘር ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። ይህም በልጁ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ የኃጢአት ውጤት ከሆኑት ከሥቃይና ከመከራ ነፃ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ ያስችላቸዋል። በመሆኑም ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6:23) ታዲያ ይህ ሁኔታ አምላክን እንድንወደውና ወደ እሱ እንድንቀርብ አይገፋፋንም?

አምላክ ለሰው ዘር በአጠቃላይ ብቻ ሳይሆን ታማኝ ለሆኑ ሰዎችም በግለሰብ ደረጃ ፍቅሩን አሳይቷል። ዓመጸኛ ለነበሩት እስራኤላውያን ሙሴ እንዲህ ብሏቸዋል:- “አንተ ተላላና ጥበብ የጐደለህ ሕዝብ፣ ለእግዚአብሔር የምትመልስለት በዚህ መንገድ ነውን? አባትህ ፈጣሪህ፣ የሠራህና ያበጀህ እርሱ አይደለምን?” (ዘዳግም 32:6) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ተገንዝበሃል? ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ድክመት እንዳለባቸው ቢያውቅም ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ተንከባክቧቸዋል። እንዲሁም ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን በሙሉ አሟልቶላቸዋል።

ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ውጣ ውረዶች ያጋጥሙናል። ስለሆነም አንዳንድ ጊዜ ልንጨነቅ አልፎ ተርፎም በሐዘን ልንዋጥ እንችላለን። በዚህ ጊዜ ሁኔታችንን እና ችግሮቻችንን በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን ሰው እንፈልጋለን። ታዲያ ማን ሊረዳን ይችላል? ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ፍቅራዊ ምክር ይሰጠናል፤ እንዲሁም ይንከባከበናል። ቅዱስ ቃሉ፣ ይህን ያህል ሥቃይ የሚደርስብን ለምን እንደሆነና ሁኔታውን እንዴት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም እንደምንችል ይገልጽልናል። አንድ አፍቃሪ አባት ልጁ ሲወድቅ ጎንበስ ብሎ እንደሚያነሳው ሁሉ ይሖዋም የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት ራሱን ዝቅ በማድረግ ታላቅ ፍቅሩን ያሳየናል። በእርግጥም፣ ይሖዋ በእሱ የሚያምኑትን ለመርዳት እጁ አጭር አይደለም።—ኢሳይያስ 59:1

አምላክ ‘ጸሎት ሰሚ’ መሆኑም ለእኛ ያለውን ፍቅር ያሳያል። (መዝሙር 65:2) እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋር ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለማንኛውም ነገር አትጨነቁ። ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) አንተም ከልብ የመነጨ ጸሎት ለአምላክ በማቅረብና በቃሉ ላይ ያሉትን መመሪያዎች በመከተል ‘ከማስተዋል በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሰላም’ ማግኘት ትችላለህ።

“አምላክ ሁሉን ያውቃል”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ አምላክ “በዕውቀቱ ፍጹም” እንደሆነ ይገልጻል። ‘አምላክ ሁሉን የሚያውቅ’ እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጆችን አፈጣጠርም ሆነ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ከማንም በተሻለ ያውቃል። (ኢዮብ 36:4፤ 1 ሳሙኤል 2:3 የ1980 ትርጉም) አምላክ በአገልጋዩ በሙሴ አማካኝነት “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው በእያንዳንዱ ቃል እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ እንደማይኖር” ተናግሯል። (ዘዳግም 8:3፤ ማቴዎስ 4:4) ይህም በሕይወታችን እውነተኛ እርካታ ማግኘት ከፈለግን ከቁሳዊ ነገሮች የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልገን ይጠቁማል።

ፈጣሪያችን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችንና ምክሮችን ይሰጠናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና እንዲሁም ምክሩን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ስናደርግ ‘ከእግዚአብሔር አፍ ከሚወጣው ከእያንዳንዱ ቃል’ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን። ለአብነት ያህል፣ ዙዛና የተባለች አንዲት ክርስቲያን የቤተሰቧን ሕይወት አስመልክታ ስትናገር እንዲህ ትላለች:- “አብረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘታችን እንዲሁም ያወቅናቸውን ነገሮች ለሌሎች መናገራችን ትዳራችንን አጠናክሮልናል። አምላክ የሚሰጠንን መመሪያ መታዘዛችን አንድ ዓይነት ግብ እንዲኖረንና በመካከላችን ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር ረድቶናል።”

አንተስ፣ አምላክ ከሚሰጠው ምክርና መመሪያ ጥቅም ማግኘት ትፈልጋለህ? መጽሐፍ ቅዱስን አዘወትረህ በማጥናትና ምክሩን ተግባራዊ በማድረግ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ በረከት ማግኘት ትችላለህ።—ዕብራውያን 12:9

‘አዳኝ የሆነ አምላክ’

ዓለማችን ሁከት የነገሠበት ነው። ነገ ስለሚሆነው ነገር ማወቅ አንችልም። በጦርነት በሚታመስ አገር ውስጥ የምትኖር ከሆነ ሰላም እንዲመጣ ትናፍቅ ይሆናል። በበርካታ የዓለማችን ክፍል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ወንጀል፣ ዓመጽ፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋትና የአሸባሪዎች ጥቃት ያስጨንቃቸዋል። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ማን ሊያድነን ይችላል? በዛሬው ጊዜ፣ የሰው ልጆች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጥበቃ የሚያደርግላቸውና የሚታደጋቸው ያስፈልጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም ጽኑ ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ በመሮጥ ተገን ያገኝበታል” ይላል። (ምሳሌ 18:10) የአምላክን ስም ማወቃችን እንዲሁም በስሙ መታመናችን፣ አምላክ በእሱ የሚያምኑትን ለማዳን ያከናወነውንና ወደፊትም የሚወስደውን እርምጃ እንድናስብ ያደርገናል። ይሖዋ ሕዝቡን ማዳን የሚችል አምላክ እንደሆነ አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የፈርዖንን ሠራዊትና የጦር ሠረገሎች በማጥፋት እስራኤላውያንን አድኗቸዋል። ይሖዋ በመከራ ያሉትን የሚያስታውስና ለእነሱ ሲል እርምጃ የሚወስድ ታማኝ አምላክ መሆኑን አስመስክሯል።—ዘፀአት 15:1-4

የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው ይሖዋ አዳኝ አምላክ መሆኑን በማመናችን ላይ ነው። ብዙ መከራዎችን ያሳለፈው የጥንቷ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊትም “አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህ” በማለት በይሖዋ ማዳን ላይ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (መዝሙር 25:5) ሐዋርያው ጴጥሮስም “ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸው . . . ያውቃል” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል።—2 ጴጥሮስ 2:9

አምላክ ለእርዳታ ወደ እሱ የሚጮህን ሰው አስመልክቶ “ወዶኛልና እታደገዋለሁ፤ ስሜን አውቆአልና እከልለዋለሁ” ብሏል። (መዝሙር 91:14) በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት በሕይወታቸው ተመልክተውታል። በፖላንድ የሚኖሩት ሄንሪክ፣ መከራና ስደት ቢደርስባቸውም ለ70 ዓመታት በታማኝነት ይሖዋን አገልግለዋል። ሄንሪክ በ16 ዓመታቸው አባታቸው ወደ ኦሽዊትስ ማጎሪያ ካምፕ ተላኩ። ሄንሪክና ወንድማቸው ደግሞ በናዚ የወጣቶች የፀባይ ማረሚያ ተቋም ውስጥ ገቡ። ከዚያ በኋላ ሄንሪክ በተለያዩ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታስረዋል። በዚያን ጊዜ ስለነበሩት ሁኔታዎች ሲያስታውሱ እንዲህ ይላሉ:- “በእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሁሉ ይሖዋ ፈጽሞ አልተወኝም። ከሞት ጋር የተፋጠጥኩባቸው በርካታ ጊዜያት ቢኖሩም በታማኝነት እንድጸና ምንጊዜም ይረዳኝ ነበር።” አዎን፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ መጽናት እንዲችሉ እምነትና ጥንካሬ ይሰጣቸዋል።

በቅርቡ አምላክ በእሱ የሚያምኑትንና ማዳኑን የሚጠባበቁትን ሰዎች ሁሉ ያድናቸዋል። “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም” በማለት ተናግሯል። (ኢሳይያስ 43:11) ‘ሁሉን በሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ላይ ይሖዋ ክፉዎችን ከምድር ገጽ የሚያጠፋቸው ሲሆን ጻድቃንን ግን ያድናቸዋል። (ራእይ 16:14, 16፤ ምሳሌ 2:21, 22) ይሖዋ፣ “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—መዝሙር 37:11

‘የአምላክ ልጆች’ መሆን

በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን እስራኤላውያን ይሖዋ አባታቸው እንደሆነ ይናገሩ ነበር። ይሁንና የረከሰ ምግብ እንዲሁም ዕውርና አንካሳ እንስሳትን ለመሥዋዕት በማቅረብ ለይሖዋ አክብሮት ብሎም ታማኝነት እንደጎደላቸው አሳይተው ነበር። ስለሆነም ይሖዋ “እኔ አባት ከሆንሁ፣ መከበሬ የት አለ?” በማለት ጠይቋቸዋል።—ሚልክያስ 1:6

አንተም ታማኝ ያልነበሩት እስራኤላውያን የሠሩትን ዓይነት ስህተት መሥራት የለብህም። ከዚህ ይልቅ ስለ ይሖዋ አምላክ እንድታውቅና ወደ እሱ እንድትቀርብ እናበረታታሃለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ብሏል።—ያዕቆብ 4:8

ይሖዋን እንደ አባትህ መመልከትህ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ያስከትልብሃል። በማንኛውም የሕይወትህ ዘርፍ አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በታማኝነት በማሟላት እሱን ለማክበር የምትጥር ከሆነ የምታደርገውን ጥረት ፈጽሞ አይረሳውም። እንዲያውም ‘ሞት፣ ሐዘን፣ ልቅሶ ወይም ሥቃይ ወደማይኖርበት’ አዲስ ዓለም በሚወስደው ትክክለኛ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ ይረዳሃል። (ራእይ 21:4) በዚያን ጊዜ ታዛዥ የሆኑት የሰው ልጆች ‘ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥተው ለአምላክ ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት ይደርሳሉ።’—ሮሜ 8:21

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አምላክ፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “ይሆናል” የሚል ፍቺ ያለውን ይሖዋ የሚለውን ስሙን እንድናውቅ ይፈልጋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ ይሖዋ ፈጽሞ አልተወኝም።”—ሄንሪክ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አብረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መገኘታችን እንዲሁም ያወቅናቸውን ነገሮች ለሌሎች መናገራችን ትዳራችንን አጠናክሮልናል።”—ዙዛና