በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር የማይታወቅ ከሆነ በስሙ መጠቀም ለምን አስፈለገ?

የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር የማይታወቅ ከሆነ በስሙ መጠቀም ለምን አስፈለገ?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር የማይታወቅ ከሆነ በስሙ መጠቀም ለምን አስፈለገ?

በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የአምላክ ስም በትክክል ምን ተብሎ ይጠራ እንደነበር በዛሬው ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም። ሆኖም የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል። ኢየሱስ ምድር በነበረበት ጊዜ የአምላክን ስም ያሳወቀ ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱን ስለዚህ ስም መቀደስ እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 17:6) በመሆኑም ክርስቲያኖች የአምላክን ስም መጠቀማቸው በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር የማይታወቀው ለምንድን ነው? ይህ የሆነበትን ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እንመልከት።

አንደኛው ምክንያት፣ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ በፊት፣ የአምላክን ስም መጥራት ስህተት ነው የሚል አጉል እምነት በአይሁዳውያን መካከል መስፋፋት መጀመሩ ነው። አንድ ሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ የአምላክን ስም “ጌታ” በሚለው ቃል ይተካ ነበር። በዚህ ሁኔታ ሰዎች ለበርካታ መቶ ዓመታት የአምላክን ስም ሳይጠቀሙበት ስለቀሩ ቀስ በቀስ ትክክለኛው አጠራር ተረሳ።

ሁለተኛው ደግሞ የጥንት የዕብራይስጥ ቃላት ይጻፉ የነበሩት ያለ አናባቢ ነበር። አንድ ሰው በአማርኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች ውስጥ ምህጻረ ቃላትን ሲያገኝ ቀሪዎቹን ፊደላት ተክቶ እንደሚያነብ ሁሉ የጥንቱን የዕብራይስጥ ጽሑፍ የሚያነብ ሰውም አናባቢውን ከራሱ ይጨምር ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ የዕብራይስጥ ቃላት አጠራር ሙሉ በሙሉ እንዳይረሳ ለማድረግ ሲባል አንድ ዘዴ ተፈጠረ። በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት በእያንዳንዱ ቃላት ላይ አናባቢ ምልክቶች ተጨመረባቸው። በመለኮታዊው ስም ላይ ግን አንድ ሰው “ጌታ” የሚለውን ቃል ተክቶ እንዲያነብ የሚያስታውስ አናባቢ ምልክት ይጨመርበት ወይም ጭራሹኑ አናባቢ አይደረግበትም ነበር።

በመሆኑም አሁን የሚገኙት ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁት አራት የዕብራይስጥ ተነባቢ ፊደላት ብቻ ናቸው። አንድ መዝገበ ቃላት ቴትራግራማተንን እንደሚከተለው በማለት አስቀምጦታል:- “አብዛኛውን ጊዜ YHWH [የሐወሐ] ወይም JHVH ተብለው የሚጻፉ አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ሲሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛውን የአምላክን ስም ይወክላሉ።” በአማርኛ ቋንቋ በሰፊው ተቀባይነት ያለው “ይሖዋ” የሚለው ስም የተገኘው የሐወሐ በሚሉት ፊደላት ላይ አናባቢ ምልክት ተጨምሮባቸው መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

አንዳንድ ምሁራን “ያህዌህ” የሚለው አጠራር ትክክለኛ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ ስም ወደ ትክክለኛው አጠራር ይቀርባል? ማንም ሰው እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይችልም። እንዲያውም ሌሎች ምሁራን ይህንን አጠራር መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምክንያቶችን ያቀርባሉ። እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች በጊዜያችን ባሉት ቋንቋዎች ሲጠሩ ከመጀመሪያው የዕብራይስጥ አጠራር ጨርሶ የተለዩ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም አጠራሮቹ ትክክል አይደሉም ብሎ የሚቃወም ሰው የለም ማለት ይቻላል። ይህ የሆነበት ምክንያት እነዚህ ስሞች የተለመዱና የቋንቋችን ክፍል በመሆናቸው ነው። ይሖዋ የሚለውን ስም በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በአምላክ ስም የሚጠሩ ሕዝቦች ነበሩ። የአምላክን ስም ለሰዎች ያሳውቁና ስሙን እንዲጠሩ ያበረታቱ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 2:21፤ 15:14 የ1954 ትርጉም፤ ሮሜ 10:13-15) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የትኛውንም ቋንቋ እንናገር አምላክ በስሙ እንድንጠቀም፣ የስሙን አስፈላጊነት እንድንገነዘብና ስሙ ከሚወክለው ነገር ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይፈልጋል።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኛል