ስለ ዘመናችን የተነገሩ ትንቢቶች
ስለ ዘመናችን የተነገሩ ትንቢቶች
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ዘላቂ ሰላምና ደስታ እንደሚያመጣ ይተነብያል። (ዳንኤል 2:44) አቡነ ዘበሰማያት ወይም አባታችን ሆይ በሚለው ጸሎት ላይ ኢየሱስ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው በሰፊው የሚታወቅ ትንቢት ላይ ከመንግሥቱ መምጣት ጋር የተያያዙ ክንውኖችን በዝርዝር ተናግሯል። እነዚህ ክንውኖች አንድ ላይ ተጣምረው የመጨረሻው ቀን ምልክት ሆነዋል፤ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎችም ይህን ምልክት በግልጽ ሊያስተውሉት ይችላሉ። የዚህ ምልክት ገጽታ ከሆኑት ከሚከተሉት ክንውኖች መካከል የትኞቹ ሲፈጸሙ ተመልክተሃል?
ዓለም አቀፍ ጦርነቶች። ኢየሱስ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) በ1914 ከተከሰተው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት ጊዜያት ጦርነቶች የሚደረጉት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነበር። አንደኛው የዓለም ጦርነት፣ የምድራችንን አብዛኛውን ክፍል ያካለለ ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ይበልጥ አውዳሚ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች መመረት የጀመሩበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በወቅቱ የተፈለሰፉት አዳዲስ አውሮፕላኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ቦምብ ለመጣል አገልግለዋል። የጦር መሣሪያዎች በገፍ መመረታቸው በጦርነት የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር ከዚያ ቀደም ፈጽሞ ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ እጅግ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል። በወቅቱ በውጊያ ከተሰለፉት 65 ሚሊዮን የሚያህሉ ወታደሮች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ሕይወታቸውን አጥተዋል አሊያም ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሰው ልጆች ወደ 20ኛው መቶ ዘመን ዘልቀው ሲገቡ ደግሞ በጦርነት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር የዚያኑ ያህል ጨምሮ ነበር። አንድ የታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት ከሆነ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሞቱት ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች “ቁጥር ይህ ነው ሊባል አይችልም።” ጦርነቶች አሁንም ድረስ ቀጥለዋል።
በየቦታው የሚከሰት ረሃብ። ኢየሱስ ‘በተለያየ ስፍራ ረሃብ እንደሚሆን’ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:7) በ2005 ሳይንስ የተባለው መጽሔት “በዓለም ላይ 854 ሚሊዮን (ከዓለም ሕዝብ 14 በመቶ) የሚሆኑ ሰዎች ዘላቂ ወይም ጊዜያዊ በሆነ የምግብ እጥረት ይሠቃያሉ” በማለት ገልጿል። በ2007 ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተገኘ አንድ ምንጭ፣ 33 አገሮች ሕዝቦቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል በቂ ምግብ እንደሌላቸው ሪፖርት አድርጓል። በዓለም ላይ የሚመረተው እህል እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ይህ ሁኔታ ሊከሰት የቻለው እንዴት ነው? አንዱ ምክንያት ሕዝቡን ለመመገብ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው መሬትና እህል ኤታኖል የተባለ ነዳጅ ለማምረት መዋሉ ነው። ዘ ዊትነስ የተባለው የደቡብ አፍሪካ ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ የመስክ መኪናን ለአንድ ጊዜ ያህል ብቻ ለመሙላት የሚያገለግል ኤታኖል ለማምረት የሚውለው እህል ለአንድ ሰው የዓመት ቀለብ ሊሆን ይችላል።” የምግብ ዋጋ መናር በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን ሳይቀር ከዕለት ጉርሳቸው አሊያም እንደ መድኃኒትና የቤት ማሞቂያ ከመሳሰሉት አስፈላጊ ነገሮች መካከል አንዱን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል።
ከባድ የመሬት መናወጦች። ኢየሱስ “ታላቅ የመሬት መናወጥ” እንደሚሆን ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) በዛሬው ጊዜ፣ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በመሬት መናወጥ ምክንያት ጉዳት እየደረሰባቸው እንዳለ የሚሰማህ ከሆነ አልተሳሳትክም። በ2007 ረጀንደር ቻዳ የተባሉ የምድርን ነውጥ የሚያጠኑ ሕንዳዊ፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሬት መንቀጥቀጥ በዓለም ዙሪያ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ማስተዋል ችለናል” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “ይህ ለምን እንደሆነ ግን ማንም አያውቅም” ብለዋል። ከዚህም በላይ ለመሬት መንቀጥቀጥ በተጋለጡ አካባቢዎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት ማደጉ በእነዚህ አደጋዎች የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው ከሆነ፣ በ2004 የሕንድ ውቅያኖስን የመታው የመሬት መንቀጥቀጥና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተነሳው ሱናሚ “ባለፉት 500 ዓመታት ውስጥ ከደረሱት የመሬት መናወጦች ሁሉ እጅግ አስከፊ ጉዳት የደረሰበት” ዓመት እንዲሆን አድርጎታል።
ፈውስ ያልተገኘላቸው በሽታዎች። ኢየሱስ ‘ቸነፈር እንደሚከሰት’ አስቀድሞ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ነባርም ሆኑ አዳዲስ በሽታዎች በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎችን እያጠቁ ሲሆን ለእነዚህ በሽታዎችም መድኃኒት ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የወባ በሽታ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ በመሄዱ በሽታውን ለማጥፋት ታስበው በተነደፉ ዓለም አቀፋዊ መርሐ ግብሮች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈልጓል። ከዚህም በተጨማሪ ሳንባ ነቀርሳን ጨምሮ ሌሎች ነባር በሽታዎች ኤድስን ከመሳሰሉ አዳዲስ በሽታዎች ጋር ተዳምረው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ይገኛሉ። የዓለም የጤና ድርጅት “አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በሳንባ ነቀርሳ ባክቴሪያ ተይዟል” በማለት ዘግቧል። ድርጅቱ አክሎም፣ የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በበርካታ አገሮች እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች መካከል አንዱ ኤች አይ ቪ መሆኑን ገልጿል። በእያንዳንዱ ሴኮንድ አንድ ሰው በሳንባ ነቀርሳ የሚያዝ ሲሆን በሽታው መድኃኒት የማይበግረው እየሆነም መጥቷል። በአውሮፓ የሚገኝ አንድ የሳንባ ነቀርሳ ሕመምተኛ “ምንም ዓይነት መድኃኒት ቢሰጠውም ከያዘው በሽታ መዳን እንዳልቻለ” ኒው ሳይንቲስት የተባለ መጽሔት በ2007 ዘግቧል።
ሥነ ምግባራዊ ውድቀትና ማኅበራዊ ቀውስ። ኢየሱስ ማቴዎስ 24:12) ኢየሱስ ከተናገረው ትንቢት በተጨማሪ ሐዋርያው ጳውሎስ ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ እሴቶች እያሽቆለቆሉ እንደሚሄዱ ጠቁሟል። ጳውሎስ፣ የአምላክ መንግሥት ይህን ሥርዓት ከማጥፋቱ በፊት ባለው ‘የመጨረሻ ዘመን’ ውስጥ ስለሚኖሩት አስጨናቂ ሁኔታዎች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉ፤ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ለዕርቅ የማይሸነፉ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በከንቱ በትዕቢት የተወጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉና። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው፤ ኀይሉን ግን ክደዋል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እንዲህ ያሉ መጥፎ ባሕርያትን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሲያሳዩ አልተመለከትክም?
“ክፋት ስለሚገን የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል። (ኢየሱስና ጳውሎስ አሁን ላለው የዓለም ሁኔታ ምክንያት የሆኑትን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በሙሉ አልዘረዘሩም። ይሁንና የተናገሯቸው ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ የምናያቸውን ክስተቶችና የሰዎችን ባሕርይ በትክክል የሚገልጹ ናቸው። ስለ ወደፊቱ ጊዜስ ምን ማለት ይቻላል? ስለ መሲሑ መምጣት በትክክል የተነበየው የኢሳይያስ መጽሐፍ የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ስለሚያመጣቸው በረከቶችም ይገልጻል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን በረከቶች እንመለከታለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
‘ሕዝብ በሕዝብ ላይ ይነሣል’
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ቸነፈር . . . ይሆናል”
[ምንጭ]
© WHO/P. Virot