በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር”

“በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር”

በእምነታቸው ምሰሏቸው

“በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር”

ዮሴፍና ማርያም ራቅ ብላ ወደምትገኘው ወደ ቤተ ልሔም በመጓዝ ላይ ናቸው። ማርያም በአህያ ላይ ተቀምጣ ለሰዓታት ስትጓዝ የቆየች ሲሆን የተመቻት አትመስልም። ዮሴፍ ደግሞ በቀስታ ፊት ፊቷ ይሄዳል። ማርያም በማሕፀኗ ውስጥ ያለው ጽንስ ሲንቀሳቀስ ተሰማት።

በዚህ ወቅት ማርያም ‘የመውለጃ ጊዜዋ ተቃርቦ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 2:5) ምናልባት ባልና ሚስቱ ማሳዎችን እያቆራረጡ ሲሄዱ የሚያርሱ ወይም የሚዘሩ ገበሬዎች ማርያምን በማየት በእንዲህ ያለ ሁኔታ ላይ ያለች ሴት ለምን እንደምትጓዝ ሳይገርማቸው አይቀርም። ማርያም ከምትኖርበት ከናዝሬት ተነስታ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ወደ ቤተ ልሔም እንድትጓዝ ያነሳሳት ምን ነበር?

ታሪኩ የሚጀምረው ከጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ማለትም ይህች ወጣት አይሁዳዊት ከዚያ በፊት ተሰምቶ የማይታወቅ አንድ ኃላፊነት በተቀበለችበት ጊዜ ነበር። ማርያም የምትወልደው ወደፊት መሲሕ የሚሆነውን የአምላክን ልጅ ነበር። (ሉቃስ 1:35) የመውለጃዋ ጊዜ ሲቃረብ ይህን ጉዞ እንድታደርግ የሚያስገድድ ሁኔታ ተፈጠረ። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ማርያም እምነቷን የሚፈታተኑ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋታል። ማርያም መንፈሳዊ ጥንካሬዋን ይዛ እንድትቀጥል የረዳት ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ወደ ቤተ ልሔም የተደረገ ጉዞ

እንዲህ ያለውን ጉዞ ያደረጉት ዮሴፍና ማርያም ብቻ አልነበሩም። በወቅቱ አውግስጦስ ቄሳር ሁሉም ሰው ወደየራሱ ከተማ በመሄድ እንዲመዘገብ አዋጅ አውጥቶ ነበር። ታዲያ ዮሴፍ ለዚህ አዋጅ ምን ምላሽ ሰጠ? ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ።”—ሉቃስ 2:1-4

ቄሳር በዚህ ጊዜ ይህን አዋጅ ማውጣቱ የአጋጣሚ ጉዳይ አልነበረም። ከሰባት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የተነገረ አንድ ትንቢት መሲሑ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ይገልጻል። ከናዝሬት 11 ኪሎ ሜትር ብቻ ርቃ የምትገኝ ቤተ ልሔም የተባለች ከተማ የነበረች ቢሆንም ትንቢቱ መሲሑ የሚወለደው ‘በቤተ ልሔም ኤፍራታ’ መሆኑን ለይቶ ይጠቅሳል። (ሚክያስ 5:2) በዛሬው ጊዜ በናዝሬትና ከናዝሬት በስተ ደቡብ በምትገኘው በዚህች ትንሽ መንደር መካከል ኮረብታማ አካባቢዎችን አቋርጦ የሚያልፍ 150 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ አለ። ዮሴፍ እንዲሄድ የታዘዘው ደግሞ ወደዚህችኛዋ መንደር ነበር፤ ይህች ስፍራ የንጉሥ ዳዊት ዘሮች የትውልድ ከተማ ስትሆን ዮሴፍም ሆነ ሚስቱ ከዳዊት ወገን ነበሩ።

ታዲያ ማርያም የዮሴፍን ውሳኔ ትደግፍ ይሆን? ጉዞው በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆንባት ምንም ጥርጥር የለውም። ወቅቱ የበጋው ወራት አብቅቶ ክረምት ሊገባ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ ቀለል ያለ ዝናብ መኖሩ የሚጠበቅ ነገር ነው። በተጨማሪም ቤተ ልሔም ከ760 ሜትር ከፍታ በላይ የምትገኝ ስለሆነች ዮሴፍ ‘ከገሊላ ተነስቶ ወደ ይሁዳ ወጣ’ መባሉ ትክክል ነው። ቤተ ልሔም እስኪደርሱ ድረስ አድካሚ የሆነውን አቀበት ለበርካታ ቀናት መጓዝ ነበረባቸው። በመንገድ ላይ ሲጓዙ ማርያም ሁኔታዋ ብዙ ጊዜ እንድታርፍ ስለሚያስገድዳት ጉዞው ከተለመደው ቀን በላይ ፈጅቶ ሊሆን ይችላል። ልትወልድ የተቃረበች አንዲት ወጣት ምጥ ሲጀምራት እሷን ለመርዳት ዝግጁ ከሆኑት ወዳጅ ዘመዶቿ ጋር ለመሆን መፈለጓ አይቀርም። በመሆኑም ማርያም ይህንን ጉዞ ለማድረግ መንፈሰ ጠንካራ መሆን አስፈልጓታል።

ሉቃስ፣ ዮሴፍ ‘ለመመዝገብ የተጓዘው ከማርያም ጋር እንደነበር’ ተናግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ‘በታጨችለት መሠረት [ዮሴፍ] ማርያምን እንዳገባት’ ገልጿል። (ሉቃስ 2:4, 5 NW) ማርያም ያገባች መሆኗ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ዮሴፍን በመንፈሳዊ ጉዳዮች ረገድ የቤተሰቡ ራስ አድርጋ በመመልከት አምላክ የሰጣትን ረዳት የመሆን ኃላፊነቷን ትወጣና ባሏ የሚያደርገውን ውሳኔ ትደግፍ ነበር። * እምነቷን ሊፈትን ይችል የነበረውን ይህን ሁኔታ ታዛዥነት በማሳየት በቀላሉ ልትወጣው ችላለች።

ማርያም፣ ዮሴፍን ለመታዘዝ ያነሳሳት ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? መሲሑ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ የሚናገረውንስ ትንቢት ታውቅ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ይህ ትንቢት፣ በሃይማኖት መሪዎች ሌላው ቀርቶ በሕዝቡ ዘንድ እንኳ በስፋት ይታወቅ ስለነበር ማርያም ስለ ሁኔታው ሳታውቅ አትቀርም። (ማቴዎስ 2:1-7፤ ዮሐንስ 7:40-42) ከዚህም በተጨማሪ ማርያም ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ ነበር። (ሉቃስ 1:46-55) ማርያም ለመሄድ የወሰነችው ይሖዋ ያስነገረውን ትንቢት በማወቋም ይሁን የባሏን ወይም የመንግሥትን ትእዛዝ ለማክበር በመፈለጓ አሊያም በሁሉም ምክንያቶች፣ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች። ይሖዋ፣ ትሑትና ታዛዥ የሆኑ ወንዶችንና ሴቶችን ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። ታዛዥነት ከፍ ተደርጎ በማይታይበት በዛሬው ጊዜ ማርያም በየትም ቦታ ለሚኖሩ ታማኝ ሰዎች መልካም አርዓያ ትሆናለች።

የክርስቶስ መወለድ

ማርያም የቤተ ልሔምን መንደር በሩቁ ስታይ እፎይታ ሳይሰማት አልቀረም። ማርያምና ዮሴፍ፣ በመከሩ ወራት መጨረሻ ላይ የሚለቀመውን የወይራ ፍሬ እየተመለከቱ አቀበቱን ሲወጡ የዚህችን ትንሽ መንደር ታሪክ ሳያስቡ አይቀሩም። ነቢዩ ሚክያስ እንደተናገረው ቤተ ልሔም ከሌሎች የይሁዳ ከተሞች እጅግ አነስተኛ ብትሆንም ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩት የቦዔዝ፣ የኑኃሚን እንዲሁም የዳዊት የትውልድ ከተማ ናት።

ዮሴፍና ማርያም እዚያ ሲደርሱ መንደሯ በሰው ተጥለቅልቃ ነበር። ሌሎች ሰዎች ለመመዝገብ ከእነሱ ቀደም ብለው ወደ ከተማዋ መጥተው ስለነበር ለማረፊያ የሚሆን ቦታ አልነበረም። * በመሆኑም በጋጣ ውስጥ ከማደር በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም። ዮሴፍ፣ ሚስቱ ከዚህ በፊት ተሰምቷት የማያውቅ ሥቃይ እየበረታባት ሲሄድ መመልከቱ ምን ያህል አስጨንቆት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ምንም በማያመቸው በዚህ ስፍራ ማርያም ምጥ ጀመራት!

በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ሴቶች ማርያም የነበረችበትን ሁኔታ መረዳት አይከብዳቸውም። ይህ ከመሆኑ ከ4,000 ዓመታት ገደማ በፊት ይሖዋ፣ ሰዎች በወረሱት ኃጢአት ምክንያት በሚወልዱበት ጊዜ እንደሚሠቃዩ ተናግሯል። (ዘፍጥረት 3:16) ማርያም እንዲህ ያለው ሥቃይ እንዳልደረሰባት የተገለጸ ነገር የለም። የሉቃስ ዘገባ፣ ማርያም ስላጋጠማት ሥቃይ ከመግለጽ ይልቅ “የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች” በማለት በአጭሩ ይናገራል። (ሉቃስ 2:7) ማርያም ከወለደቻቸው ቢያንስ ሰባት ልጆች መካከል “የበኵር” ልጇን ወለደች። (ማርቆስ 6:3) ይህ ልጅ ግን ከሌሎቹ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይህ ልጅ የማርያም የበኵር ልጅ ብቻ ሳይሆን ከይሖዋ “ፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር” የሆነ የአምላክ አንድያ ልጅ ነው!—ቈላስይስ 1:15

የሉቃስ ዘገባ በመቀጠል በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚታወቀውን ማርያም ያደረገችውን አንድ ክንውን ሲገልጽ ‘[ሕፃኑን] በጨርቅ ጠቅልላ በግርግም አስተኛችው’ በማለት ይናገራል። (ሉቃስ 2:7) የክርስቶስን ልደት አስመልክቶ የሚቀርቡ ድራማዎች፣ ሥዕሎችና ሌሎች ትዕይንቶች ይህን ክንውን ከመጠን በላይ ማራኪ በማድረግ ከእውነታው በራቀ መንገድ ሲያቀርቡት ይስተዋላል። ይሁን እንጂ በወቅቱ ምን እንደተከሰተ ተመልከት። ግርግም፣ ከብቶች የሚመገቡበት ገንዳ ነው። ዮሴፍና ማርያም ያረፉት በዛሬው ጊዜ እንደሚታየው ንጹሕ አየር እንደልብ በማይገኝበት ወይም ንጽሕና በሌለው ጋጣ ውስጥ ነበር። ማንም ወላጅ ቢሆን አማራጭ ካላጣ በስተቀር እንዲህ ባለው ስፍራ ላይ ልጅ መውለድ እንደማይፈልግ ግልጽ ነው። አብዛኞቹ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ማርያምና ዮሴፍ ለአምላክ ልጅ ይበልጥ የተሻለውን ለማድረግ የቻሉትን ሁሉ ጥረው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም!

ይሁን እንጂ ዮሴፍና ማርያም በገጠማቸው ሁኔታ ከመማረር ይልቅ ከሁሉ የተሻለውን ለማድረግ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ማርያም ሕፃኑን እንዲሞቀውና ጉዳት እንዳይደርስበት በጨርቅ ጠቅልላ በጥንቃቄ ግርግም ውስጥ በማስተኛት እንደተንከባከበችው ልብ በል። ማርያም ሁኔታው ከልክ በላይ እንዲያስጨንቃት ከመፍቀድ ይልቅ ለልጇ የቻለችውን ሁሉ አድርጋለች። ማርያምና ዮሴፍ ለልጃቸው ሊሰጡት የሚችሉት ከሁሉ የላቀ ነገር መንፈሳዊ እንክብካቤ ማድረግ መሆኑን ተገንዝበው ነበር። (ዘዳግም 6:6-8) በዛሬው ጊዜም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ለመንፈሳዊ ነገሮች ቦታ በማይሰጥ ዓለም ውስጥ ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ነገር ቅድሚያ ይሰጣሉ።

ሊጠይቋት ከመጡ ሰዎች ማበረታቻ አገኘች

ሰላማዊ የነበረው ሁኔታ ድንገት በሰዎች ጫጫታ ታወከ። ቤተሰቡን በተለይም ሕፃኑን ለማየት የጓጉት እረኞች ወደ ጋጣው እየተጣደፉ ገቡ። በአድናቆት የተዋጡት እነዚህ ሰዎች ፊታቸው በደስታ ያበራ ነበር። እረኞቹ መንጎቻቸውን ይጠብቁበት ከነበረው ስፍራ የመጡት በፍጥነት ነበር። * ከዚያም በመገረም ይመለከቷቸው ለነበሩት ባልና ሚስት ያጋጠማቸውን አስደናቂ ነገር ተረኩላቸው። እረኞቹ በሌሊት መንጎቻቸውን እየጠበቁ ሳሉ አንድ መልአክ ድንገት አጠገባቸው ቆመ። የይሖዋ ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ መልአኩ፣ ክርስቶስ ወይም መሲሕ በቤተ ልሔም መወለዱንና ሕፃኑም በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ እንደሚያገኙት ነገራቸው። ከዚያም አንድ አስደናቂ ነገር ተፈጸመ! ብዙ የመላእክት ሠራዊት ይሖዋን ሲያወድሱ ታዩ።

እነዚህ ትሑት ሰዎች በፍጥነት ወደ ቤተ ልሔም መሄዳቸው አያስገርምም። መልአኩ በነገራቸው መሠረት በግርግም የተኛውን አዲስ የተወለደ ሕፃን ለማየት ጓጉተው መሆን አለበት። ይህንን የምሥራች ሰምተው ዝም ከማለት ይልቅ “የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ።” (ሉቃስ 2:17, 18) በወቅቱ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እረኞችን ዝቅ አድርገው ይመለከቷቸው እንደነበር ጥርጥር የለውም። ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ትሑትና ታማኝ ሰዎች ከፍ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። ይሁንና የእረኞቹ መምጣት በማርያም ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?

ማርያም ገና መገላገሏ ስለነበር ደክሟት እንደሚሆን ግልጽ ነው፤ ያም ሆኖ እረኞቹ የተናገሩትን እያንዳንዱን ነገር በጥሞና አዳምጣለች። ከዚህም በተጨማሪ ‘ማርያም ይህንን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር።’ (ሉቃስ 2:19) በእርግጥም ይህች ወጣት ስለ ሁኔታዎቹ በጥልቅ ታስብ ነበር። መልአኩ የተናገረው ነገር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ታውቃለች። አምላኳ ይሖዋ፣ ልጇ ማን መሆኑን እንድታውቅና ምን ያህል ከፍ ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባው እንድትገነዘብ ፈልጎ ነበር። በመሆኑም ከማዳመጥ ያለፈ ነገር አድርጋለች። በቀጣዮቹ ወራትና ዓመታት በእነዚህ ቃላት ላይ ማሰላሰል እንድትችል ሁሉንም በልቧ መዝግባ ይዛለች። ማርያም በሕይወት ዘመኗ ሁሉ አስደናቂ እምነት እንዲኖራት የረዳት ቁልፍ ጉዳይ ይህ ነው።

አንተስ የማርያምን ምሳሌ ትከተላለህ? ይሖዋ በቃሉ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች እንዲሰፍሩልን አድርጓል። ያም ሆኖ ለእነዚህ እውነቶች ትኩረት የማንሰጥ ከሆነ ምንም ጥቅም አያስገኙልንም። መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አንድ የሥነ ጽሑፍ ሥራ ሳይሆን በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ መጽሐፍ አድርገን በመቀበል በየጊዜው የምናነብ ከሆነ ለእነዚህ እውነቶች ትኩረት እንደሰጠን ማሳየት እንችላለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከዚያም ልክ እንደ ማርያም እነዚህን መንፈሳዊ እውነቶች በልባችን ለመያዝና በጥልቀት ለመረዳት መጣር ይኖርብናል። የይሖዋን ምክር ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በአእምሯችን በመያዝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባነበብናቸው ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል።

በልቧ ልትይዛቸው የሚገቡ ተጨማሪ ነገሮች

ሕፃኑ ስምንት ቀን ሲሆነው ማርያምና ዮሴፍ በሙሴ ሕግ መሠረት ገረዙት፤ እንደታዘዙትም ስሙን ኢየሱስ አሉት። (ሉቃስ 1:31) በ40ኛውም ቀን ከቤተ ልሔም ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ወሰዱት፤ ከዚያም የሙሴ ሕግ፣ ድሆች ሁለት ዋነሶች ወይም እርግቦች እንዲያቀርቡ በሚያዘው መሠረት የመንጻት መሥዋዕት አቀረቡ። ማርያምና ዮሴፍ፣ አቅሙ እንዳላቸው እንደ ሌሎች ወላጆች ጠቦትና ዋኖስ ማቅረብ ባለመቻላቸው ኃፍረት ተሰምቷቸው ከነበረ ይህን ስሜታቸው ወደ ጎን ገሸሽ አድርገውት መሆን አለበት። እዚያ በነበሩበት ጊዜ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ግሩም ማበረታቻ አግኘተው እንደነበር ግልጽ ነው።—ሉቃስ 2:21-24

ስምዖን የሚባል አንድ አረጋዊ ወደ እነሱ በመቅረብ ለማርያም በልቧ ልትይዘው የሚገባ ተጨማሪ ነገር ነገራት። ስምዖን፣ ከመሞቱ በፊት መሲሑን እንደሚያየው ቃል ተገብቶለት የነበረ ሲሆን የይሖዋ ቅዱስ መንፈስም ሕፃኑ ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት አዳኝ መሆኑን ጠቆመው። ከዚህም በተጨማሪ ስምዖን፣ ጽናት የሚጠይቅ ሥቃይ እንደሚደርስባት ማርያምን አስጠነቀቃት፤ እንዲያውም በሰይፍ እንደምትወጋ ያህል ከባድ ሥቃይ እንደሚሰማት ነገራት። (ሉቃስ 2:25-35) እነዚህ አስደንጋጭ ቃላት እንኳ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በኋላ የገጠማትን አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት እንድትቋቋም ሳይረዷት አልቀሩም። ከስምዖን በኋላ ደግሞ ሐና የተባለች ነቢይት ሕፃኑን ኢየሱስን በተመለከተችው ጊዜ የኢየሩሳሌምን መቤዠት ለሚጠባበቁ ሰዎች ሁሉ ስለ እሱ ተናገረች።—ሉቃስ 2:36-38

ዮሴፍና ማርያም ልጃቸውን ኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ማምጣታቸው በእርግጥም ተገቢ ነበር! ልጃቸው በሕይወት ዘመኑ በሙሉ በይሖዋ ቤተ መቅደስ በታማኝነት መገኘት የጀመረው በዚህ መንገድ ነበር። ማርያምና ዮሴፍ፣ በቤተ መቅደሱ በነበሩበት ጊዜም የይሖዋን አምልኮ ለመደገፍ የቻሉትን ሁሉ ያደረጉ ሲሆን መመሪያና ማበረታቻም አግኝተዋል። ማርያም ከቤተ መቅደሱ ስትመለስ እምነቷ ተጠናክሮ ብሎም ልቧ ለማሰላሰል በሚረዷትና ለሌሎች ልታካፍላቸው በምትችላቸው ጠቃሚ ነገሮች ተሞልቶ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ይህን ምሳሌ ሲከተሉ ማየት እጅግ ያስደስታል። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን አዘውትረው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዘዋቸው ይሄዳሉ። እንዲህ የሚያደርጉ ወላጆች ለእምነት አጋሮቻቸው የማበረታቻ ቃላትን በመናገር የይሖዋን አምልኮ ለመደገፍ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህ ወላጆች ከስብሰባዎች የሚመለሱት እምነታቸው ተጠናክሮ፣ ተደስተውና ልባቸው ለሌሎች በሚያካፍሉት ነገር ተሞልቶ ነው። አንተም በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንድትገኝ በአክብሮት ተጋብዘሃል። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የአንተም እምነት እንደ ማርያም ይበልጥ ይጠናከራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በዚህ ዘገባና ማርያም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ‘ተነሥታ እንደሄደች’ በሚገልጸው ታሪክ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። (ሉቃስ 1:39) ወደ ኤልሳቤጥ በሄደችበት ጊዜ ማርያም የታጨች ብትሆንም ከዮሴፍ ጋር ገና ስላልተጋቡ እሱን ሳታማክር ሄዳ ሊሆን ይችላል። ከተጋቡ በኋላ ግን ማርያምና ዮሴፍ አብረው የተጓዙ ቢሆንም እንኳ ጉዞውን አስመልክቶ ውሳኔ ያደርግ የነበረው ዮሴፍ እንደሆነ ተገልጿል።

^ አን.14 በወቅቱ የከተማዋ ሰዎች ለመንገደኞች የማረፊያ ቦታ ማዘጋጀታቸው የተለመደ ነበር።

^ አን.19 እረኞቹ በዚያ ሌሊት በጎቻቸውን በሜዳ ላይ ሲጠብቁ እንደነበር መገለጹ የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት ትክክል መሆኑን ያረጋግጣል። ክርስቶስ የተወለደው በጎች በረት ውስጥ በሚያድሩበት በታኅሣሥ ወር ላይ ሳይሆን በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ መሆን ይኖርበታል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስምዖን በትንቢት የተነገረለትን አዳኝ በማየቱ ተባርኳል