በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአቍማዳ ውስጥ ያለ እንባ

በአቍማዳ ውስጥ ያለ እንባ

በአቍማዳ ውስጥ ያለ እንባ

ወጣቱ በሽሽት ላይ ያለ ስደተኛ ነው። በጭንቀት የተዋጠው ይህ ወጣት ዓይኑ እንባ አቅርሮ ይሖዋ አምላኩን “እንባዬን በዕቃህ [‘በአቊማዳህ፣’ የግርጌ ማስታወሻ] አጠራቅም” በማለት ደግነትና ርኅራኄ እንዲያሳየው ይማጸናል። (መዝሙር 56:8) ይህ ወጣት ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነው። ይሁንና ዳዊት እዚህ ላይ የጠቀሰው አቍማዳ ምንድን ነው? አምላክ እንባችንን በአቍማዳ የሚያጠራቅመውስ እንዴት ነው?

አቍማዳ፣ ለዳዊት እንግዳ ነገር አልነበረም። አቍማዳ ውኃ፣ ዘይት፣ ወይን ጠጅ ሌላው ቀርቶ ቅቤ ለመያዝ ያገለግል ነበር። እንደ ትዋሬግ ያሉ በሰሃራ በረሃ ውስጥ የሚኖሩ ዘላኖች አሁንም ድረስ ከፍየል ወይም ከበግ ቆዳ የተሠራ አቍማዳ ይጠቀማሉ። እንዲህ ያሉ አቍማዳዎች እንደ እንስሳው ቆዳ ትልቅነት ብዙ ሊትር ውኃ ሊይዙ ይችላሉ። አቍማዳ ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በረሃ ውስጥ ሳይቀር ውኃን እንደቀዘቀዘ ማቆየት ይችላል። በጥንት ጊዜ ሰዎች አቍማዳዎችን የሚጭኑት በአህያ ወይም በግመል ላይ ነበር። በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች በመስክ መኪና ፊት ላይ ታስሮ ልታይ ትችላለህ።

ዳዊት አቍማዳን አስመልክቶ ከተናገረው ልብ የሚነካ ሐሳብ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዓለም የሚቆጣጠረው ሰይጣን እንደሆነና በዛሬው ጊዜም “በታላቅ ቍጣ” እንደተሞላ ይናገራል። በመሆኑም በምድራችን ላይ አስጨናቂ ሁኔታዎች ይታያሉ። (ራእይ 12:12) በዚህም የተነሳ ብዙዎች በተለይም አምላክን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎች ልክ እንደ ዳዊት ስሜታዊ፣ አእምሯዊና አካላዊ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። አንተስ ያለህበት ሁኔታ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው? እነዚህ ታማኝ ሰዎች ‘እያለቀሱም’ ቢሆን ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ አቋማቸውን ሳያጎድፉ ለመኖር ጥረት ከማድረግ ፈጽሞ ወደኋላ አይሉም። (መዝሙር 126:6) እነዚህ ሰዎች፣ በሰማይ የሚኖረው አባታቸው እየደረሰባቸው ያለውን ችግር እንደሚያይ ብቻ ሳይሆን ችግሩ የሚያስከትልባቸውን የስሜት መረበሽም በሚገባ እንደሚረዳላቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። ርኅሩኅ የሆነው አምላክ የአገልጋዮቹን ሥቃይ በሚገባ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ ያፈሰሱትን እንባና ያሳለፉትን ችግር ፈጽሞ አይረሳም። በመሆኑም በምሳሌያዊ አነጋገር እንባቸውን በአቍማዳ ያጠራቅማል።