በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አዳም ፍጹም ከነበረ እንዴት ኃጢአት ሊሠራ ቻለ?

አዳም ፍጹም ከነበረ እንዴት ኃጢአት ሊሠራ ቻለ?

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

አዳም ፍጹም ከነበረ እንዴት ኃጢአት ሊሠራ ቻለ?

አምላክ አዳምን የፈጠረው የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረው አድርጎ ስለነበር አዳም ኃጢአት ሊሠራ ይችል ነበር። ይህ ስጦታ ማለትም የመምረጥ ነፃነት ደግሞ አዳም ፍጹም እንደሆነ ከሚገልጸው እውነታ ጋር የሚጋጭ አይደለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ምሉዕ በሆነ ሁኔታ ፍጹም ነው ሊባል የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (ዘዳግም 32:3, 4፤ መዝሙር 18:30፤ ማርቆስ 10:18) ሌሎች ነገሮች ሁሉ ፍጹም የሚሆኑት በተወሰነ ደረጃ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቢላ ሥጋ ለመክተፍ ፍጹም ተስማሚ ነው ሊባል ይችላል፤ ይሁንና ይህን ቢላ ሾርባ ለመብላት ትጠቀምበታለህ? አንድ ነገር ፍጹም የሚሆነው ከተሠራበት ዓላማ አንጻር ብቻ ነው።

ታዲያ አምላክ አዳምን የፈጠረው ለምን ዓላማ ነበር? የመምረጥ ነፃነትና የማሰብ ችሎታ ያላቸውን የሰው ዘሮች በአዳም አማካኝነት ለማስገኘት ነበር። ለአምላክና ለመንገዶቹ ፍቅር ማዳበር የሚፈልጉ ሰዎች ሕጎቹን በመታዘዝ ይህን ፍላጎታቸውን ማሳየት ይችሉ ነበር። በመሆኑም ሰዎች አምላክን የሚታዘዙት በደመ ነፍስ ሳይሆን ወደውና ፈቅደው ነው። (ዘዳግም 10:12, 13፤ 30:19, 20) አዳም አምላክን ላለመታዘዝ መምረጥ የማይችል ቢሆን ኖሮ ያልተሟላ ማለትም ፍጽምና የጎደለው ይሆን ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዳም የመመረጥ ነፃነቱን እንዴት እንደተጠቀመበት ሲገልጽ “መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ” ጋር በተያያዘ አምላክ የሰጠውን ሕግ በመጣስ የሚስቱን የዓመጽ ጎዳና እንደተከተለ ይናገራል።—ዘፍጥረት 2:17፤ 3:1-6

ታዲያ ‘አምላክ፣ አዳምን ትክክልና ስህተት የሆነውን በመምረጥ ረገድ ጉድለት እንዲኖርበት አድርጎ ስለፈጠረው ጥበብ ያለበት ውሳኔ የማድረግ ወይም ፈተናዎችን የመቋቋም ችሎታ ሳይኖረው ቀርቷል’ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው? አዳም የዓመጽ ጎዳና ከመከተሉ በፊት ይሖዋ አምላክ፣ አዳምና ሔዋንን ጨምሮ በምድር ላይ የፈጠራቸውን ፍጥረታት በሙሉ “እጅግ መልካም” መሆናቸውን ተናግሮ ነበር። (ዘፍጥረት 1:31) በመሆኑም አዳም ኃጢአት ሲሠራ አምላክ በአዳም አፈጣጠር ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ማድረግ አላስፈለገውም፤ ከዚህ ይልቅ አዳምን ለፈጸመው ነገር ተጠያቂ አድርጎታል። (ዘፍጥረት 3:17-19) አዳም ለአምላክና ትክክል ለሆኑ ነገሮች ያለው ፍቅር ከምንም በላይ አምላክን እንዲታዘዝ ሊገፋፋው ይገባ ነበር።

ኢየሱስ ምድር በነበረበት ወቅት እንደ አዳም ፍጹም ሰው ነበር። ኢየሱስ፣ ከአዳም ዘሮች በተለየ መልኩ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ስለ ተጸነሰ በቀላሉ በፈተና እንዲሸነፍ የሚያደርግ የኃጢአት ዝንባሌ አልወረሰም። (ሉቃስ 1:30, 31፤ 2:21፤ 3:23, 38) ኢየሱስ ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም በፈቃደኝነት ለአባቱ ታማኝ ሆኖ ኖሯል። ይሁንና አዳም የመምረጥ ነፃነቱን ተጠቅሞ የይሖዋን መመሪያ ለመታዘዝ አሻፈረኝ ማለቱ ተጠያቂ አድርጎታል።

ይሁን እንጂ አዳም አምላክን ላለመታዘዝ የመረጠው ለምንድን ነው? ያለበትን ሁኔታ በተወሰነ መንገድ ማሻሻል እንደሚችል ተሰምቶት ይሆን? በፍጹም፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “የተታለለው አዳም አይደለም” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 2:14) አዳም ከተከለከለው ዛፍ የበላችውን የሚስቱን ፈቃድ ለመከተል መርጧል። ሚስቱን ለማስደሰት ያለው ምኞት ፈጣሪውን ለመታዘዝ ካለው ፍላጎት በልጦበታል። በእርግጥም አዳም የተከለከለውን ፍሬ ከመብላቱ በፊት፣ አለመታዘዙ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ሊነካበት እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ነበረበት። አዳም ለአምላክ ጥልቅና ጽኑ ፍቅር ስላልነበረው ለሚስቱ ተጽዕኖ በመንበርከክ በፈተናው ተሸንፏል።

አዳም ኃጢአት የሠራው ልጆች ከመውለዱ በፊት ስለነበር ዘሮቹ በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው ሆነዋል። ያም ሆኖ እኛም ልክ እንደ አዳም የመምረጥ ነፃነት አለን። እንግዲያው በይሖዋ ጥሩነት ላይ በአድናቆት እናሰላስል፤ እንዲሁም ልንታዘዘውና ልናመልከው ለሚገባው አምላክ ጥልቅ ፍቅር ይኑረን።—መዝሙር 63:6፤ ማቴዎስ 22:36, 37