በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነቴ ያጋጠሙኝን አሳዛኝ ሁኔታዎች እንድቋቋም ረድቶኛል

እምነቴ ያጋጠሙኝን አሳዛኝ ሁኔታዎች እንድቋቋም ረድቶኛል

እምነቴ ያጋጠሙኝን አሳዛኝ ሁኔታዎች እንድቋቋም ረድቶኛል

ሶሌዳድ ካስቲዮ እንደተናገረችው

በሕይወቴ ውስጥ በብቸኝነት ልዋጥ እችል የነበረባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሩ። በ34 ዓመቴ ውድ ባለቤቴ በሞት ተለየኝ። ከስድስት ዓመት በኋላ አባቴ ሞተ። አባቴ ከሞተ ከስምንት ወራት በኋላ ደግሞ አንዱ ልጄ በማይድን በሽታ መያዙን አወቅኩ።

ስሜ ሶሌዳድ ሲሆን ትርጓሜውም “ብቸኝነት” ማለት ነው። ነገሩ እንግዳ ሊመስል ቢችልም በሕይወቴ ውስጥ ብቸኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም ማለት እችላለሁ። አሳዛኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙኝ ጊዜ ሁሉ ይሖዋ አምላክ አብሮኝ እንደሆነና ‘እንዳልፈራ እጄን ይዞ እንደሚረዳኝ’ ይሰማኛል። (ኢሳይያስ 41:13) የደረሱብኝን አሳዛኝ ሁኔታዎች መቋቋም የቻልኩትና እነዚህ ሁኔታዎች ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብ ያደረጉኝ እንዴት እንደሆነ እስቲ ላጫውታችሁ።

ደስታ የተሞላበት ሕይወት

የተወለድኩት ግንቦት 3, 1961 በባርሴሎና፣ ስፔን ውስጥ ሲሆን የወላጆቼ የሆሴ እና የሶሌዳድ ብቸኛ ልጅ ነበርኩ። ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ እናቴ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ተማረች። ከዚያ ቀደም ብሎ እናቴ ለነበሯት ሃማኖታዊ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ብትጥርም ከምትሄድበት ቤተ ክርስቲያን የሚያረካ መልስ አላገኘችም ነበር። አንድ ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን በመምጣት ለጥያቄዎቿ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ ሰጧት። መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ያቀረቡላትንም ግብዣ በደስታ ተቀበለች።

እናቴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር የሆነች ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ አባቴ የእሷን ምሳሌ ተከተለ። እናቴን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናት የነበረችው ኤልያና ለአምላክ ቃል ከፍተኛ ጉጉት እንዳለኝ ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባትም፤ ስለሆነም ትንሽ ልጅ ብሆንም እንኳ ለብቻዬ ባጠና የተሻለ እንደሚሆን ሐሳብ አቀረበች። ኤልያና ባደረገችልኝ እርዳታና እናቴ በሰጠችኝ ማበረታቻ በ13 ዓመቴ ለመጠመቅ ቻልኩ።

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ በተለይ አንድ ዓይነት ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገኝ ወደ ይሖዋ የመጸለይ ልማድ ነበረኝ። እውነቱን ለመናገር፣ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ሳለሁ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ችግሮች አላጋጠሙኝም ማለት ይቻላል። በጉባኤ ውስጥ ብዙ ጓደኞች የነበሩኝ ሲሆን ከወላጆቼም ጋር በጣም እቀራረብ ነበር። በ1982 እንደ እኔው ዓይነት መንፈሳዊ ግቦች የነበሩት ፌሊፔ የተባለ የይሖዋ ምሥክር አገባሁ።

ልጃችንን ለይሖዋ ፍቅር እንዲኖረው አድርጎ ማሳደግ

ከአምስት ዓመት በኋላ ቆንጆ ልጅ የወለድን ሲሆን ስሙንም ሳኡል አልነው። እኔና ፌሊፔ ልጅ በማግኘታችን በጣም ተደሰትን። ሳኡል ጤናማ፣ አምላክን የሚወድ እንዲሁም ሚዛናዊ አመለካከት ያለው ልጅ ሆኖ እንደሚያድግ ተስፋ አድርገን ነበር። እኔና ፌሊፔ ለሳኡል ስለ ይሖዋ በማስተማር እንዲሁም ከእሱ ጋር አብረን ምግብ በመመገብ፣ ወደ መናፈሻ ቦታ በመሄድና የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወት ብዙ ጊዜ እናሳልፍ ነበር። ሳኡል፣ አባቱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች ለመንገር በሚሄድበት ጊዜ አብሮት መሆን ያስደስተው ነበር። ፌሊፔም፣ ሳኡል መጥሪያ በመደወል ለሰዎች ትራክት መስጠት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በማስተማር ገና በለጋ ዕድሜው በአገልግሎት ላይ እንዲካፈል ያደርገው ነበር።

ሳኡል ላሳየነው ፍቅርና ለሰጠነው ሥልጠና ጥሩ ምላሽ ይሰጥ ነበር። በስድስት ዓመቱ አዘውትሮ ከእኛ ጋር ይሰብክ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ማዳመጥ የሚወድ ከመሆኑም በላይ በቤተሰብ መልክ የምናደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ትምህርት ቤት የገባ ሲሆን ባገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ቀለል ያሉ ውሳኔዎችን ያደርግ ጀመር።

ይሁን እንጂ ሳኡል ሰባት ዓመት ሲሆነው በቤተሰባችን ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተከሰተ። ፌሊፔ በቫይረስ የሚመጣ የሳንባ ኢንፌክሽን ያዘው። ባለቤቴ መሥራት የተሳነው ከመሆኑም በላይ የአልጋ ቁራኛ ሆነ፤ ከዚያም ለ11 ወራት ያህል ከዚህ በሽታ ጋር ሲታገል ከቆየ በኋላ በ36 ዓመቱ አረፈ።

በዚያን ጊዜ ያሳለፍኳቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሳስብ አሁንም ድረስ አለቅሳለሁ። ባለቤቴ በሽታው ቀስ በቀስ እያሸነፈው ሲሄድ ዓይን ዓይኑን ከማየት በቀር ምንም ማድረግ አልቻልኩም። በውስጤ የነበረኝ ተስፋና ዕቅድ መና ሆኖ እንደቀረ ቢሰማኝም እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ፌሊፔን ለማጽናናት ጥሬያለሁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አነብለት የነበረ ሲሆን ይህም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በማንችልባቸው ጊዜያት ብርታት ይሰጠን ነበር። ባለቤቴ ሲሞት ግን የባዶነት ስሜት ተሰማኝ።

ያም ሆኖ የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም። መንፈሱን እንዲሰጠኝ አዘውትሬ እጠይቀው ነበር። ከፌሊፔ ጋር አስደሳች ጊዜያት እንዳሳልፍ ስላደረገኝና ፌሊፔን በትንሣኤ የማግኘት ተስፋ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። እኔና ባለቤቴ አብረን ያሳለፍናቸውን መልካም ጊዜያት በማስታወስ መጽናናት እንድችል እንዲሁም ልጃችንን ጥሩ ክርስቲያን አድርጌ ለማሳደግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠኝ አምላክን ጠየቅኩት። የደረሰብኝ ሐዘን ከፍተኛ ቢሆንም መጽናናት ችያለሁ።

ወላጆቼና የጉባኤያችን አባላት ይህ ነው የማይባል ድጋፍ አድርገውልኛል። ያም ሆኖ ቅድሚያውን ወስጄ ሳኡልን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትና እንዴት ይሖዋን ማገልገል እንዳለበት ማስተማር ነበረብኝ። የቀድሞ አሠሪዬ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ የቢሮ ሥራ እንድሠራ ግብዣ ቢያቀርብልኝም ከሳኡል ጋር ይበልጥ ጊዜ ማሳለፍ እንድችልና ከትምህርት ቤት ሲመለስ አብሬው እንድሆን ስል የጽዳት ሥራ ለመሥራት መረጥኩ።

“ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” የሚለው ጥቅስ ለሳኡል መንፈሳዊ ሥልጠና መስጠቴ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እንድገነዘብ አድርጎኛል። (ምሳሌ 22:6) ይህ ጥቅስ፣ ሳኡል የይሖዋን አስተሳሰብ እንዲማር ለመርዳት የቻልኩትን ሁሉ ከጣርኩ ይሖዋ ጥረቴን እንደሚባርክ እንዳስተውል ረድቶኛል። እርግጥ ነው፣ በኢኮኖሚ ረገድ አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ አስፈልጎኛል፤ ሆኖም ከልጄ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እፈልግ የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ ከማንኛውም ቁሳዊ ሃብት ጋር የሚወዳደር አልነበረም።

ሳኡል 14 ዓመት ሲሆነው አባቴ ሞተ። በተለይ ሳኡል የአያቱ ሞት አባቱን በማጣቱ ምክንያት የተሰማውን ሐዘን ስለቀሰቀሰበት ስሜቱ በጣም ተጎድቶ ነበር። አባቴ ይሖዋን በመውደድ ረገድ ግሩም ምሳሌ ነበር። ከአባቴ ሞት በኋላ ሳኡል በቤተሰባችን ውስጥ ያለው ወንድ እሱ ብቻ በመሆኑ ከዚህ በኋላ እናቱንም ሆነ ሴት አያቱን መንከባከብ እንዳለበት ተሰማው።

ከሉኪሚያ ጋር መታገል

አባቴ ከሞተ ከስምንት ወራት በኋላ ሳኡል ከፍተኛ የድካም ስሜት ይሰማው ስለነበር የቤተሰባችን ሐኪም በአካባቢያችን ወደሚገኘው ሆስፒታል እንድወስደው ሐሳብ አቀረበልኝ። ሐኪሞች ብዙ ምርመራ ካደረጉለት በኋላ ሳኡል ሉኪሚያ የተባለ በሽታ እንደያዘው ነገሩኝ። *

ሳኡል በሽታውን ለመቋቋምና ሐኪሞቹ የሚሰጡትን የኬሞቴራፒ ሕክምና ለመከታተል ሲል ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በተደጋጋሚ ጊዜያት ሆስፒታል መግባት አስፈልጎት ነበር። ለመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የተከታተለው ሕክምና ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ያህል እፎይታ አስገኝቶለት ነበር። ይሁን እንጂ ሳኡል፣ ካንሰሩ ስላገረሸበት ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የኬሞቴራፒ ሕክምና ተደረገለት፤ ይህ ደግሞ አቅሙን በጣም አዳከመው። ከዚህ በኋላ ሳኡል እፎይታ ያገኘው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ሲሆን ለሦስተኛ ጊዜ የኬሞቴራፒ ሕክምና ለማድረግ የሚያስችል አቅም አልነበረውም። ሳኡል ሕይወቱን ለይሖዋ የወሰነ ሲሆን ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር የመሆን ፍላጎትም ነበረው፤ ይሁን እንጂ በ17 ዓመቱ ሞተ።

ሐኪሞች የኬሞቴራፒ ሕክምና የሚያስከትለውን የጎንዮሽ ጉዳት ለመከላከል ደም እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ጊዜያት ሐሳብ አቅርበዋል። እርግጥ ነው፣ ደም መውሰድ በሽታውን አያድነውም። ሐኪሞቹ፣ ሳኡል የሉኪሚያ በሽታ እንደያዘው ሲነግሩን እኔም ሆንኩ ሳኡል ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የይሖዋን ሕግ መታዘዝ ስለምንፈልግ እንዲህ ያለውን ሕክምና እንደማንቀበል ግልጽ አደረግንላቸው። (የሐዋርያት ሥራ 15:19, 20) ሳኡል ደም የማይወስደው በራሱ ውሳኔ መሆኑን እኔ በማልኖርባቸው ጊዜያትም ለሐኪሞቹ ማስረዳት ነበረበት። (በገጽ 31 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

በመጨረሻም ሐኪሞቹ፣ ሳኡል የበሽታውን ባሕርይ በሚገባ በመገንዘቡ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ሐኪሞቹ ብዙውን ጊዜ ሐሳባችንን እንድንለውጥ ይገፋፉን የነበረ ቢሆንም አቋማችንን በማክበር ያለ ደም ሊያክሙት ተስማሙ። ሳኡል አቋሙን ለሐኪሞቹ ሲያስረዳ ስመለከት ኩራት ተሰማኝ። ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና እንደነበረው በግልጽ ይታይ ነበር።

ሳኡል ሉኪሚያ እንደያዘው ያወቅን ሰሞን በባርሴሎና አድርገነው በነበረው ትልቅ ስብሰባ ላይ ወደ ይሖዋ ቅረብ የሚል ርዕስ ያለው አዲስ መጽሐፍ ወጣ። ተወዳዳሪ የሌለው ይህ መጽሐፍ የሚደርሱብንን አስቸጋሪና አስጨናቂ ሁኔታዎች መቋቋም እንድንችል እንደ መልሕቅ ሆኖልናል። ሆስፒታል ውስጥ በቆየንባቸው ጊዜያት ከዚህ መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎችን አብረን እናነብ ነበር። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ማስታወሳችን ከዚያ በኋላ የደረሱብንን አስቸጋሪ ሁኔታዎች በጽናት ለመቋቋም ረድቶናል። በመጽሐፉ መቅድም ላይ የተጠቀሰው ኢሳይያስ 41:13⁠ን በሕይወታችን ውስጥ ልዩ ትኩረት የሰጠነው በዚህ ጊዜ ነበር። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ።”

የሳኡል እምነት የሌሎችን ልብ ነክቷል

በቫል ዴብሮን ሆስፒታል የሚገኙ ሐኪሞችና ነርሶች፣ ሳኡል በሳል አስተሳሰብና ብሩህ ተስፋ ያለው ልጅ መሆኑ ያስደንቃቸው ነበር። እሱን ይንከባከቡ የነበሩ ሐኪሞች በሙሉ በጣም ይወዱት ነበር። ከደም ካንሰር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚከታተለው ሐኪም በሉኪሚያ በሽታ የሚሠቃዩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክር ልጆችንም አክሞ ስለሚያውቅ ለይሖዋ ምሥክሮች አክብሮት ነበረው። ይህ ሐኪም፣ ሳኡል ሞትን ለመጋፈጥ የማይፈራ ብሎም ብሩህ አመለካከትና ለሚያምንባቸው ነገሮች ጥብቅ አቋም ያለው ልጅ እንደነበር ያስታውሳል። ነርሶቹ እስከ ዛሬ ድረስ ከተንከባከቧቸው በሽተኞች ሁሉ የተለየ መሆኑን ለሳኡል ገልጸውለታል። ሳኡል ሊሞት በተቃረበበት ጊዜም እንኳ ፈጽሞ ተማርሮ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ ተጫዋች እንደነበር ተናግረዋል።

አንዲት የሥነ ልቦና ባለሙያ፣ በሳኡል ዕድሜ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ልጆች ለሞት በሚያደርስ በሽታ ሲያዙ በሚሰማቸው ሥቃይና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተነሳ ብዙ ጊዜ ለሐኪሞችና ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ አስቸጋሪ ፀባይ ያላቸው ልጆች እንደሚሆኑ ነገረችኝ። ሆኖም እንዲህ ያለ ባሕርይ በሳኡል ላይ እንዳልተመለከተች ገለጸችልኝ። ሳኡል በጣም የተረጋጋና ብሩህ አመለካከት ያለው መሆኑ አስገርሟታል። ይህ ደግሞ እኔና ሳኡል ስለምናምንባቸው ነገሮች እንድንነግራት አጋጣሚ ሰጥቶናል።

ሳኡል በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኝን አንድ የይሖዋ ምሥክር ያለበትን ችግር መቋቋም እንዲችል ረድቶት እንደነበረም ትዝ ይለኛል። ይህ የይሖዋ ምሥክር ለስድስት ዓመታት በመንፈስ ጭንቀት ሲሠቃይ የነበረ ሲሆን የሚሰጠውም ሕክምና ምንም መፍትሔ አላመጣለትም። ይህ የጉባኤያችን አባል ሳኡልን ለመንከባከብ በርካታ ጊዜያት ሆስፒታል አድሯል። ሳኡል ለበሽታው ያለው አመለካከት ልቡን በጥልቅ እንደነካው አጫውቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ ሳኡል የድካም ስሜት ቢኖርበትም ሊጠይቁት የመጡትን ሰዎች ሁሉ ለማበረታታት እንደሚጥር አስተውሎ ነበር። “የሳኡል ምሳሌነት ያለብኝን የመንፈስ ጭንቀት እንድቋቋም ረድቶኛል” በማለት ይህ የይሖዋ ምሥክር ተናግሯል።

ሳኦል ከሞተ ሦስት ዓመት ያለፈ ቢሆንም ሐዘኑ እስከ አሁን ድረስ አልወጣልኝም። ጠንካራ አይደለሁም፤ ሆኖም አምላክ “እጅግ ታላቅ ኀይል” ሰጥቶኛል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) አሳዛኝ ሁኔታዎችም እንኳ አዎንታዊ ጎን ሊኖራቸው እንደሚችል ተምሬያለሁ። የባለቤቴን፣ የአባቴንና የልጄን ሐዘን ለመቋቋም ጥረት ማድረጌ ራስ ወዳድ እንዳልሆን እንዲሁም የሌሎችን ሥቃይ ይበልጥ እንድረዳ አስችሎኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንድቀርብ አድርጎኛል። የሰማዩ አባቴ አሁንም ድረስ ከጎኔ ስለሆነና እጄን ይዞ ስለሚረዳኝ የወደፊቱ ጊዜ ምንም አያስፈራኝም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.19 ሳኡልን የያዘው ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የተባለ ነጭ የደም ሴሎችን የሚያጠቃ የደም ካንሰር ነው።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለምን እንደሆነ ጠይቀህ ታውቃለህ?

የይሖዋ ምሥክሮች ደም አይወስዱም ሲባል ሰምተህ ይሆናል። ደም የማይወስዱት ለምን እንደሆነ ጠይቀህ ታውቃለህ?

ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመሥርተው የሚወስዱትን ይህን አቋም ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉንም የሕክምና ዓይነት እንደማይቀበሉ አሊያም ለሕይወት አክብሮት እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። ይህ ፈጽሞ ከእውነታው የራቀ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው ከሁሉ የተሻለ ሕክምና ማግኘት ይፈልጋሉ። ይሁንና ደም መውሰድን የሚጠይቁ ሕክምናዎችን አይቀበሉም። ለምን?

አቋማቸው የተመሠረተው፣ አምላክ ለሰው ልጆች በሰጣቸው መሠረታዊ ሕግ ላይ ነው። ከኖኅ የጥፋት ውኃ በኋላ አምላክ ለኖኅና ለቤተሰቡ የእንስሳትን ሥጋ እንዲበሉ የፈቀደላቸው ቢሆንም እንኳ ደም እንዳይበሉ ከልክሏቸው ነበር። (ዘፍጥረት 9:3, 4) ሁሉም የሰው ዘሮች የመጡት ከኖኅ ስለሆነ ይህ ሕግ ለሁሉም ሰብዓዊ ፍጡር ይሠራል። ይህ ሕግ ፈጽሞ አልተሻረም። ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ ቆይቶም አምላክ ደም ቅዱስ መሆኑን እንዲሁም ሕይወትን እንደሚወክል በመግለጽ ለእስራኤላውያን ይህን ሕግ በድጋሚ ሰጥቷቸዋል። (ዘሌዋውያን 17:14) ከ1,500 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሐዋርያት፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች ‘ከደም እንዲርቁ’ አዘዋቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 15:29

የይሖዋ ምሥክሮች ደም የሚወስዱ ከሆነ ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን ሕግ አክብረዋል ለማለት ፈጽሞ አይቻልም። ስለሆነም ሌሎች አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋማቸውም ብዙውን ጊዜ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው መምረጣቸው ምንም አያስደንቅም።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ፌሊፔና ከልጃችን ሳኡል ጋር

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆቼ ሆሴ እና ሶሌዳድ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሳኡል ከመሞቱ ከአንድ ወር በፊት