በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቻችሁን አስተምሩ

እንደ ዮሴፍ ወንድሞች ቅናት አድሮብህ ያውቃል?

እንደ ዮሴፍ ወንድሞች ቅናት አድሮብህ ያውቃል?

እስቲ በመጀመሪያ ቅናት ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት። ሰዎች አንድን ልጅ ጥሩ፣ ቆንጆ ወይም ጎበዝ እያሉ ሲያሞግሱት በመስማትህ በልጁ ላይ የጥላቻ ስሜት አድሮብህ ያውቃል? *— ከሆነ በልጁ ቀንተሃል ማለት ነው።

ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያበላልጡ ከሆነ በቤተሰብ ውስጥ ቅናት ሊፈጠር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በቅናት ምክንያት ከባድ ችግር ስለደረሰበት አንድ ቤተሰብ ይናገራል። በዚህ ቤተሰብ ውስጥ ቅናት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነና ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት።

ዮሴፍ የያዕቆብ 11ኛ ልጅ ሲሆን ወንድሞቹም ይቀኑበት ነበር። ለምን እንደሚቀኑበት ታውቃለህ?— አባታቸው ያዕቆብ ከሁሉም ልጆቹ አብልጦ ይወደው ስለነበር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ያዕቆብ ለዮሴፍ በኅብረ ቀለማት ያጌጠ ልብስ አሠርቶለት ነበር። ያዕቆብ፣ ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ ይወደው የነበረው “በስተርጅናው ስለ ወለደው” እንዲሁም ከሚወዳት ሚስቱ ከራሔል የወለደው የመጀመሪያ ልጅ ስለነበር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዮሴፍ ወንድሞች፣ አባታቸው ከእነርሱ አብልጦ እንደሚወደው ሲመለከቱ ዮሴፍን ጠሉት’ ይላል። አንድ ቀን ዮሴፍ፣ አባቱን ጨምሮ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለእሱ ሲሰግዱለት በሕልሙ እንደተመለከተ ለቤተሰቡ ነገራቸው። በዚህም ምክንያት ‘ወንድሞቹ እንደቀኑበትና’ አባቱም ሳይቀር እንደተቆጣው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 37:1-11

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የዮሴፍ ወንድሞች የቤተሰባቸውን በጎችና ፍየሎች ለማሰማራት ራቅ ወዳለ አካባቢ ሄዱ፤ በዚህ ወቅት ዮሴፍ የ17 ዓመት ልጅ ነበር። ያዕቆብም ልጆቹ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንዲያይ ዮሴፍን ላከው። አብዛኞቹ ወንድሞቹ የዮሴፍን መምጣት ሲመለከቱ ምን ሊያደርጉት እንዳሰቡ ታውቃለህ?— ሊገድሉት ፈልገው ነበር! ይሁንና ከመካከላቸው ሁለቱ ማለትም ሮቤልና ይሁዳ፣ ዮሴፍ እንዲሞት አልፈለጉም።

ይሁዳ፣ ወደ ግብጽ የሚሄዱ ነጋዴዎችን ሲመለከት ለወንድሞቹ ዮሴፍን “እንሽጠው” አላቸው። እነሱም በሐሳቡ በመስማማት ሸጡት። ከዚያም አንድ ፍየል አርደው የዮሴፍን ልብስ በደም ነከሩት። ልብሱንም ለአባታቸው ባሳዩት ጊዜ ያዕቆብ “ክፉ አውሬ በልቶታል፣ በእርግጥም ዮሴፍ ተቦጫጭቈአል” በማለት አለቀሰ።—ዘፍጥረት 37:12-36

ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ፣ በግብጹ ገዥ በፈርዖን ዘንድ ተወዳጅ ሆነ። ይህም የሆነው ዮሴፍ በአምላክ እርዳታ አማካኝነት ፈርዖን ያያቸውን ሁለት ሕልሞች መፍታት ስለቻለ ነው። ፈርዖን በመጀመሪያው ሕልሙ ላይ በቅድሚያ ሰባት ወፋፍራም ላሞች ከዚያም ሰባት ከሲታ ላሞች ተመለከተ። በሁለተኛው ሕልሙ ላይ ደግሞ በቅድሚያ ሰባት ያማሩ የእሸት ዛላዎች ከዚያም ሰባት የቀጨጩ የእሸት ዛላዎች ተመለከተ። ዮሴፍ ሁለቱም ሕልሞች፣ እጅግ የተትረፈረፈ ምርት የሚገኝባቸው ሰባት ዓመታት እንደሚመጡና ከዚያ በኋላ ግን ሰባት የረሃብ ዓመታት እንደሚከሰቱ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ተናገረ። ፈርዖን በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ጥጋብ በሚሆንባቸው ዘመናት ዮሴፍ ለድርቁ ጊዜ የሚሆን እህል እንዲያከማች ኃላፊነት ተሰጠው።

የረሃቡ ዘመን ሲመጣ፣ ዮሴፍ ከሚኖርበት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀው የሚገኙት የዮሴፍ ቤተሰቦች እህል አለቀባቸው። ያዕቆብ የዮሴፍን አሥር ታላላቅ ወንድሞች እህል እንዲያመጡ ወደ ግብጽ ላካቸው። በዚህ ጊዜ ወንድሞቹ ከዮሴፍ ጋር የተገናኙ ቢሆኑም ማን መሆኑን አላወቁም ነበር። ዮሴፍ ማንነቱን ሳይነግራቸው ወንድሞቹ ለእሱ ያላቸው አመለካከት ተለውጦ መሆኑን ለማወቅ ፈተናቸው። ከዚያም በእሱ ላይ መጥፎ ነገር በመፈጸማቸው እንደተጸጸቱ ተገነዘበ። በኋላም ዮሴፍ ማንነቱን ነገራቸው። በድጋሚ በመገናኘታቸው ምን ያህል ተደስተው ሊሆን እንደሚችል ገምት!—ዘፍጥረት ምዕራፍ 40 እስከ 45

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ስለ ቅናት ምን ያስተምርሃል?— ቅናት ብዙ ችግር ሊያስከትል ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው የገዛ ወንድሙን እንኳ እንዲጎዳ ሊያነሳሳው ይችላል! እስቲ የሐዋርያት ሥራ 5:17, 18⁠ን እና የሐዋርያት ሥራ 7:54-59⁠ን እናንብብና ቅናት፣ ሰዎች በኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ላይ ምን እንዲያደርጉ እንዳነሳሳቸው እንመልከት።— እነዚህን ጥቅሶች ስታነብ በሌሎች እንዳንቀና መጠንቀቅ ያለብን ለምን እንደሆነ ተገነዘብክ?—

ዮሴፍ 110 ዓመት የኖረ ሲሆን ልጆችንና የልጅ ልጆችን ለማየት በቅቷል። ዮሴፍ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ እንዲሁም ቅናትን እንዲያስወግዱ እንዳስተማራቸው እርግጠኞች ነን።—ዘፍጥረት 50:22, 23, 26

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።