ይህን ያውቁ ኖሯል?
ይህን ያውቁ ኖሯል?
አይሁዳውያን ሰንበትን ማክበር የሚጀምሩት ከምሽት አንስቶ የሆነው ለምንድን ነው?
ይሖዋ የስርየትን ቀን አስመልክቶ ለሕዝቡ እንዲህ የሚል ሕግ ሰጥቷቸው ነበር፦ “በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ። . . . ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ . . . ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።” (ዘሌዋውያን 23:28, 32) ይህ ትእዛዝ እያንዳንዱ ቀን የሚጀምረው ከመሸ ማለትም ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ሲሆን የሚያበቃው ደግሞ በቀጣዩ ቀን ፀሐይ ስትጠልቅ እንደሆነ ያሳያል። ስለሆነም አይሁዳውያን አንድ ቀን ብለው የሚጠሩት ከምሽት አንስቶ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ያለውን ጊዜ ነው።
ይህ ዓይነቱ የቀን አቆጣጠር አምላክ ከተጠቀመበት ጋር የሚመሳሰል ነው። ስለ መጀመሪያው የፍጥረት ቀን የሚናገረው ዘገባ “መሸ፤ ነጋም፤ የመጀመሪያ ቀን” በማለት ይገልጻል። የሚቀጥሉትም ቀናት የተቆጠሩት በተመሳሳይ መንገድ ሲሆን ‘ቀናቱ’ የሚጀምሩት ‘ምሽት’ ላይ ነበር።—ዘፍጥረት 1:5, 8, 13, 19, 23, 31
እንዲህ ያለ የቀን አቆጣጠር የሚጠቀሙት አይሁዳውያን ብቻ አልነበሩም። አቴናውያን፣ ኑሚዲያውያንና ፊንቄያውያን ተመሳሳይ የሆነ የቀን አቆጣጠር ነበራቸው። በሌላው በኩል ባቢሎናውያን አንድ ቀን ጀመረ የሚሉት ፀሐይ ስትወጣ ነው። ግብጻውያንና ሮማውያን ደግሞ አንድ ቀን ብለው የሚጠሩት፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ አገሮች እንደሚጠቀሙበት ከእኩለ ሌሊት አንስቶ እስከሚቀጥለው እኩለ ሌሊት ድረስ ያለውን ጊዜ ነው። አይሁዳውያን ግን አሁንም ድረስ ሰንበትን ማክበር የሚጀምሩት ከምሽት አንስቶ ሲሆን የሚቆየውም እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ነው።
“የሰንበት መንገድ” ሲባል ምን ማለት ነው?
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሲያርግ ከተመለከቱ በኋላ “የሰንበት መንገድ ያህል ይርቅ” ወደ ነበረው ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። (የሐዋርያት ሥራ 1:12) አንድ መንገደኛ በቀን 30 ኪሎ ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ሊጓዝ ይችላል። ይሁንና የደብረ ዘይት ተራራ ይገኝ የነበረው በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ነበር። ታዲያ “የሰንበት መንገድ” ሲባል ምን ማለት ነው?
ሰንበት፣ እስራኤላውያን ከመደበኛ ሥራቸው የሚያርፉበት ዕለት ነበር። በዚህ ቀን እሳት ማንደድ እንኳ የለባቸውም ነበር። (ዘፀአት 20:10፤ 35:2, 3) ይሖዋ “በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቆይ፤ ማንም [አይውጣ]” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (ዘፀአት 16:29) ይህ ሕግ፣ እስራኤላውያን ከተለመደው እንቅስቃሴያቸው እንዲያርፉና ለመንፈሳዊ ነገሮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል።
ወግ አጥባቂ የነበሩት ረቢዎች ይሖዋ በሰጠው ሕግ ውስጥ ከሰፈረው መመሪያ ውጪ፣ አንድ ሰው በሰንበት ቀን ለአምልኮም ይሁን ለሌላ ጉዳይ ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንዳለበት የሚወስን የማያፈናፍን ደንብ አውጥተው ነበር። ይህን አስመልክቶ ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለዚያስቲካል ሊትሬቸር እንደሚከተለው ብሏል፦ “የሰንበትን አከባበር አስመልክቶ በወጣው ጥብቅ ሕግ የተነሳ . . . በሰንበት ቀን፣ ማንኛውም እስራኤላዊ የሰንበት መንገድ ተብሎ ከሚጠራው የተወሰነ ርቀት በላይ መጓዝ እንደሌለበት የሚደነግግ ደንብ ወጥቶ ነበር።” ይህ ርቀት 2,000 ክንድ ማለትም በ900 ሜትርና በአንድ ኪሎ ሜትር መካከል ያለ ርቀት ነው።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሩሳሌም ከደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆና ስትታይ