በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥሩ አባት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ጥሩ አባት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ጥሩ አባት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

“አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።”—ቈላስይስ 3:21

ንድ አባት ልጆቹ እንዳይመረሩበት ምን ማድረግ ይችላል? አባት መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት መገንዘቡ እጅግ አስፈላጊ ነው። የአእምሮ ጤንነትን አስመልክቶ የሚናገር አንድ መጽሔት “አባትነት፣ በልጆች የስሜትና የአስተሳሰብ ብስለት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል ከባድ ኃላፊነት ነው” ብሏል።

የአባት ኃላፊነት ምንድን ነው? በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆችን መቅጣት የአባቶች ኃላፊነት እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ብዙ ጊዜ እናቶች ልጃቸው ሲያስቸግራቸው ‘ቆይ ብቻ! አባትህ ይምጣ’ ብለው መናገራቸው የተለመደ ነው። ልጆች ሥርዓታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ወላጆች ሚዛኑን የጠበቀ ተግሣጽ መስጠትና ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ጥብቅ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ጥሩ አባት መሆን ሲባል ከዚህ ያለፈ ነገር ይጠይቃል።

የሚያሳዝነው ግን ወላጆቻቸው ጥሩ አርዓያ የሆኗቸው ሁሉም አባቶች አይደሉም። አንዳንዶቹ ካለአባት ያደጉ ናቸው። በሌላው በኩል ደግሞ ኃይለኛና ከመጠን በላይ ጥብቅ የሆኑ አባቶች ያሳደጓቸው ሰዎች እነሱም ልጆቻቸውን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ይይዟቸው ይሆናል። አንድ አባት፣ እሱ ባደገበት መንገድ ልጆቹን ለማሳደግ ከመጣር ይልቅ የተሻለ ወላጅ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

ጥሩ አባት ለመሆን የሚረዳ ጠቃሚና አስተማማኝ ምክር የሚገኝበት አንድ ምንጭ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብን ሕይወት በተመለከተ ከሁሉ የተሻለ ምክር ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር በግምታዊ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ካለመሆኑም ሌላ መመሪያውን መከተላችን አይጎዳንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር፣ የመጽሐፉ ባለቤትና የቤተሰብ መሥራች የሆነውን የይሖዋ አምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቅ ነው። (ኤፌሶን 3:14, 15) አባት ከሆንክ መጽሐፍ ቅዱስ ለወላጆች የሚሰጠውን ምክር መመርመርህ ጠቃሚ ነው። *

ጥሩ አባት መሆንህ በልጆችህ አካላዊና ስሜታዊ ደኅንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊነታቸውም ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከአባቱ ጋር የሚቀራረብ ልጅ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት አይከብደውም። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ የሁላችንም አባት መሆኑን ይናገራል። (ኢሳይያስ 64:8) ልጆች ከአባታቸው የሚፈልጓቸው ስድስት ነገሮች ምን እንደሆኑ እስቲ እንመልከት። በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ አባቶች ልጆቻቸው የሚፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት የሚረዷቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች እንመረምራለን።

1 ልጆች የአባታቸውን ፍቅር ማግኘት ይፈልጋሉ

ይሖዋ ለአባቶች ግሩም ምሳሌ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የበኩር ልጁ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ምን እንደሚሰማው ሲገልጽ “አብ ወልድን ይወዳል” ይላል። (ዮሐንስ 3:35፤ ቈላስይስ 1:15) ይሖዋ ለልጁ ፍቅርና አድናቆት እንዳለው ደጋግሞ ገልጿል። ኢየሱስ ሲጠመቅ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” በማለት ይሖዋ ከሰማይ ተናግሯል። (ሉቃስ 3:22) ኢየሱስ አባቱ እንደሚወደው በፍጹም ተጠራጥሮ አያውቅም። ታዲያ አንድ ሰብዓዊ አባት ከአምላክ ምን ሊማር ይችላል?

ልጆችህን እንደምትወዳቸው ከመንገር ወደኋላ አትበል። የአምስት ልጆች አባት የሆነው ኬልቨን እንዲህ ይላል፦ “ልጆቼን እንደምወዳቸው መናገር ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዳቸው ትኩረት በመስጠት ለእነሱ ያለኝን ፍቅር ለመግለጽ ሁልጊዜ ጥረት አደርግ ነበር። ሽንት ጨርቃቸውን እቀይርና ገላቸውንም አጥብ ነበር።” ከዚህም በተጨማሪ ልጆችህ የአንተን አድናቆት ማግኘት ይፈልጋሉ። በመሆኑም ከመጠን በላይ ነቃፊ ወይም በሆነ ባልሆነው የምትቆጣ አትሁን። ከዚህ ይልቅ ባገኘኸው አጋጣሚ ሁሉ አመስግናቸው። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሴት ልጆች ያሉት ዶኒዜቲ፣ “አንድ አባት ልጆቹን የሚያመሰግንበት አጋጣሚ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለበት” ብሏል። ልጆችህ፣ እንደምታደንቃቸው ማወቃቸው ለራሳቸው ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። ይህ ደግሞ ይበልጥ ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ይረዳቸዋል።

2 ልጆች ጥሩ ምሳሌ የሚሆናቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል

በዮሐንስ 5:19 ላይ ኢየሱስ የሚያደርገው “አብ ሲሠራ ያየውን ብቻ” እንደሆነ ተገልጿል። ኢየሱስ፣ አባቱ “ሲሠራ” የተመለከተውን በተግባር ላይ ያውል እንደነበር ልብ በል። ልጆችም በአብዛኛው የሚያደርጉት እንደዚሁ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አባት ሚስቱን በአክብሮት የሚይዛት ከሆነ ልጁም ሲያድግ ሴቶችን በአክብሮት ሊይዝ ይችላል። የአንድ አባት ምሳሌነት በወንዶች ልጆቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ሴቶች ልጆቹ ለወንዶች በሚኖራቸው አመለካከት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል።

ልጆችህ ይቅርታ መጠየቅ ይከብዳቸዋል? በዚህ ረገድም ምሳሌ መሆንህ አስፈላጊ ነው። ኬልቨን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቹ ውድ ካሜራ በሰበሩበት ጊዜ የሆነውን ነገር እስከ አሁን ድረስ ያስታውሳል። በዚህ ጊዜ በጣም በመናደዱ ጠረጴዛውን በቡጢ ሲመታው ለሁለት ተሰነጠቀ። ኬልቨን ባደረገው ነገር የተጸጸተ ሲሆን ንዴቱን መቆጣጠር ባለመቻሉም ባለቤቱንና ልጆቹን ይቅርታ ጠየቃቸው። ኬልቨን ይቅርታ መጠየቁ በልጆቹ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይሰማዋል፤ ምክንያቱም ልጆቹ ይቅርታ መጠየቅ አይከብዳቸውም።

3 ልጆች ደስታ የሰፈነበት የቤተሰብ ሕይወት ይፈልጋሉ

ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር መኖር እጅግ የሚያስደስተው መሆኑ ምንም አያስገርምም። ምሳሌ 8:30 በኢየሱስና በአባቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን እንደሚመስል እንድንረዳ ያስችለናል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “[በአባቴ ዘንድ] ዋና ባለሙያ ነበርሁ። ሁልጊዜ በፊቱ ሐሤት [አደርጋለሁ]።” በእርግጥም በይሖዋና በኢየሱስ መካከል በጣም የተቀራረበ ዝምድና አለ።

ልጆችህ ደስታ በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር ይፈልጋሉ። ጊዜ ወስደህ ከልጆችህ ጋር የምትጫወት ከሆነ ቤታችሁ ደስታ የሰፈነበት ይሆናል። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መጫወታቸው በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ያጠናክረዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ልጅ ያለው ፌሊክስ በዚህ ሐሳብ ይስማማል። እንዲህ ብሏል፦ “ከልጄ ጋር ለመዝናናት ጊዜ መመደቤ በመካከላችን ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አድርጓል። የተለያዩ ጨዋታዎችን እንጫወታለን፣ ከወዳጆቻችን ጋር አብረን ጊዜ እናሳልፋለን እንዲሁም አስደሳች ወደሆኑ ቦታዎች እንሄዳለን። ይህ ደግሞ የቤተሰባችንን ትስስር ይበልጥ አጠናክሮልናል።”

4 ልጆች መንፈሳዊ ነገሮችን መማር ያስፈልጋቸዋል

ኢየሱስ ከአባቱ ተምሯል፤ በመሆኑም “[ከአባቴ] የሰማሁትን ለዓለም እናገራለሁ” ለማለት ችሏል። (ዮሐንስ 8:26) አምላክ፣ ለልጆች ሥነ ምግባራዊ እሴቶችንም ሆነ መንፈሳዊ ነገሮችን የማስተማር ኃላፊነት የሰጠው ለአባት ነው። አባት መሆንህ ከሚያስከትልብህ ኃላፊነቶች አንዱ ትክክለኛ መመሪያዎችን በልጆችህ ልብ ውስጥ መትከል ነው። እንዲህ ያለው ሥልጠና መሰጠት ያለበት ደግሞ ከሕፃንነት ጀምሮ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ፌሊክስ፣ ልጁ ገና ሕፃን ሳለ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ * በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደሚገኙት ያሉ ማራኪና አስደሳች ታሪኮችን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ያነብለት ነበር። ልጁ እያደገ ሲሄድም ለዕድሜው የሚመጥኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ተጠቅሞ ያስተምረው ነበር።

“በቤተሰብ ደረጃ የምናደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስደሳች እንዲሆን ማድረግ ጥረት ይጠይቃል። ወላጆች ልጆቻቸውን አድርጉ እያሏቸው እነሱ ግን የማይፈጽሟቸውን ነገሮች ልጆች በቀላሉ ማስተዋል ይችላሉ። በመሆኑም ወላጆች መንፈሳዊ ነገሮችን እንደሚያደንቁ ማሳየታቸው አስፈላጊ ነው” በማለት ዶኒዜቲ ይናገራል። የሦስት ወንዶች ልጆች አባት የሆነው ካርሎስ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ለቤተሰቡ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አስመልክተን የምንወያይበት ሳምንታዊ ስብሰባ አለን። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በስብሰባው ላይ የምንወያይበትን ነጥብ መምረጥ ይችላል።” ኬልቨን፣ ልጆቹ የትም ይሁኑ የት እንዲሁም እየሠሩ ያሉት ነገር ምንም ይሁን ምን ስለ አምላክ ለማስተማር ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀምበታል። ኬልቨን የሰጠው አስተያየት፣ ሙሴ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሰናል፦ “ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዛት በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።”—ዘዳግም 6:6, 7

5 ልጆች ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል

ልጆች ሲያድጉ ስኬታማና ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ከተፈለገ ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ወላጆች ተግሣጽ መስጠት ሲባል ማስፈራራትንና ማንቋሸሽን ጨምሮ ልጆችን ርኅራኄ በጎደለው መንገድ መያዝ ማለት ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጡትን ተግሣጽ ከጭካኔ ድርጊት ጋር አያያይዘውም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋ እንደሚያደርገው ሁሉ ወላጆችም ለልጆቻቸው ፍቅራዊ ተግሣጽ መስጠት ይኖርባቸዋል። (ዕብራውያን 12:4-11) መጽሐፍ ቅዱስ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው” ይላል።—ኤፌሶን 6:4

አንዳንድ ጊዜ ልጆችን መቅጣት ያስፈልግ ይሆናል። ይሁንና አንድ ልጅ ለምን እንደተቀጣ ማወቅ አለበት። ወላጆች ተግሣጽ ሲሰጡ ልጁ እንደተጠላ ሆኖ እንዲሰማው ማድረግ የለባቸውም። መጽሐፍ ቅዱስ ልጅን ሊጎዳ የሚችል ጭካኔ የተሞላበት ድብደባን ያወግዛል። (ምሳሌ 16:32 የ1954 ትርጉም) ኬልቨን እንዲህ ብሏል፦ “ከባድ ጥፋት በመፈጸማቸው ምክንያት ለልጆቼ እርማት ስሰጣቸው የምቀጣቸው ስለምወዳቸው መሆኑን እንዲረዱ ሁልጊዜ እጥራለሁ።”

6 ልጆች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል

ልጆችን ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎችና ከመጥፎ ጓደኞች መጠበቅ ያስፈልጋል። የሚያሳዝነው ግን ምንም የማያውቁትን ልጆች መጠቀሚያ የሚያደርጉ “ክፉዎች” በዚህ ዓለም ላይ አሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13) ልጆችህን ከጥቃት መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ምክር ይሰጣል፦ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል።” (ምሳሌ 22:3) ልጆችህ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉትን አደጋዎች ነቅተህ በመከታተል ከጥቃት ልትጠብቃቸው ትችላለህ። ልጆችህን ወደ አደጋ ሊመሯቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድመህ ማስተዋልና እነሱን ከአደጋ ለመጠበቅ የቻልከውን ሁሉ ማድረግ ይገባሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆችህ ኢንተርኔት እንዲጠቀሙ ከፈቀድክላቸው ለጥቃት በማያጋልጣቸው መንገድ መጠቀም የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያውቁ ማድረግ አለብህ። ኮምፒውተሩን ልጆችህ ሲጠቀሙ በቀላሉ ማየት በምትችልበት ቦታ ላይ ብታስቀምጠው የተሻለ ይሆናል።

አንድ አባት ልጆቹ በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች መቋቋም እንዲችሉ አስቀድሞ ሊያዘጋጃቸውና ሊያሠለጥናቸው ያስፈልጋል። አንድ ሰው አንተ በሌለህበት ልጆችህን በጾታ ሊያስነውራቸው ቢሞክር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ? * ልጆችህ፣ ሌሎች ሰዎች ሊነኳቸው የማይገቡ የሰውነት ክፍሎቻቸውን በተመለከተ ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን አጠቃቀም ለይተው ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። ኬልቨን እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች ሰዎች ሌላው ቀርቶ አስተማሪዎቻቸው እንኳ ለልጆቼ እንዲህ ያለውን ሥልጠና እንዲሰጧቸው ፈጽሞ አልፈቀድኩም። ልጆቼን ስለ ጾታና የጾታ ጥቃት ስለሚሰነዝሩ ሰዎች የማስተማሩ ኃላፊነት የራሴ እንደሆነ ይሰማኛል።” በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የኬልቨን ልጆች በጥሩ ሁኔታ አድገው ደስተኛ ቤተሰብ መሥርተዋል።

የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ጣር

አንድ አባት ለልጆቹ ከሚሰጣቸው ስጦታ ሁሉ የላቀው ከአምላክ ጋር ጠንካራ ዝምድና እንዲኖራቸው መርዳት ነው። በዚህ ረገድ አባቶች ምሳሌ መሆናቸው ወሳኝ ነው። ዶኒዜቲ እንዲህ ብሏል፦ “አባቶች እነሱ ራሳቸው ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ማሳየት አለባቸው። በተለይም አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ በአምላክ የሚታመኑ መሆናቸው በግልጽ መታየት ይኖርበታል። እንዲህ የሚያደርጉ ከሆነ በይሖዋ እንደሚታመኑ ያሳያሉ። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው በሚጸልዩበት ጊዜ አባትየው አምላክ ያደረገላቸውን መልካም ነገሮች ደጋግሞ መጥቀሱ ልጆች ከአምላክ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ያለውን ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል።”

ታዲያ ጥሩ አባት ለመሆን ቁልፉ ምንድን ነው? ልጆችህን እንዴት ማሳደግ እንዳለብህ ከማንም በተሻለ የሚያውቀውን የይሖዋ አምላክን ምክር ለማግኘት ጥረት አድርግ። ልጆችህን የአምላክ ቃል በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ካሠለጠንካቸው፣ “በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” የሚለው የምሳሌ 22:6 ጥቅስ እውን ሲሆን ማየት ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክሮች በዋነኝነት ያተኮሩት በአባቶች ላይ ቢሆንም አብዛኞቹ መመሪያዎች ለእናቶችም ይሠራሉ።

^ አን.18 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

^ አን.25 ልጆችን ከጾታ ጥቃት መጠበቅ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የጥቅምት 2007 ንቁ! መጽሔት ገጽ 3-11⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አባት ለልጆቹ ጥሩ ምሳሌ መሆን አለበት

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ አባት የልጆቹን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ይገባዋል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጆች ፍቅራዊ ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል