በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጉብኝት ክፍት የሆነው በዓላማ ነው

ለጉብኝት ክፍት የሆነው በዓላማ ነው

ለጉብኝት ክፍት የሆነው በዓላማ ነው

በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ በምትገኘውና ቀድሞ ክሩገርስዶርፕ በመባል በምትታወቀው በሞካሌ ከተማ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ይገኛል። በዚህ ትልቅ ቅርንጫፍ ቢሮ በኩል የሚያልፉ ብዙ ሰዎች “እዚህ ውስጥ የሚሠራው ምንድን ነው?” ብለው ይጠይቃሉ። በዚህም ምክንያት በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሠሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮው በጥቅምት 12 እና 13, 2007 ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ዝግጅት አደረጉ። ይህን ያደረጉበት ዓላማ፣ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚናፈሰው ወሬ ውሸት መሆኑን ለማጋለጥና ቅርንጫፍ ቢሮው ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ምን እያከናወነ እንዳለ ለሕዝብ ለማሳየት ነበር።—ማቴዎስ 28:19, 20

በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያገለግሉት የይሖዋ ምሥክሮች በግቢው መግቢያ ላይ ሰዎች እንዲጎበኙ የሚጋብዙ ትልልቅ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ያስቀመጡ ሲሆን ለአካባቢው ነዋሪዎችም ልዩ የመጋበዣ ወረቀት አሰራጩ። ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር የሥራ ግንኙነት ያላቸው ሰዎችና ቤተሰቦቻቸውም ተጋብዘው ነበር። ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ከ500 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች ቅርንጫፍ ቢሮውን ጎበኙ።

የብዙዎቹን ጎብኚዎች ትኩረት የሳበው፣ በሰዓት 90,000 መጽሔቶችን ማተም የሚችለው ማን ሮላንድ ሊትማን የተባለው ማተሚያ ማሽን ነበር። በተጨማሪም የመጽሐፍ መጠረዣ ክፍሉ እንዲሁም በቀን ከ14,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝኑ ጽሑፎች የሚታሸጉበትና የሚላኩበት ሰፊው የጽሑፍ መላኪያ ክፍል ብዙዎችን አስደንቋቸዋል። በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ የሚሠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን ለማሳየት የሚረዱ ማራኪ መግለጫዎችን አዘጋጅተው ነበር። ከእነዚህ መካከል ከጉተንበርግ አንስቶ ዘመናዊ እስከሆነው ሊት-ኦፍሴት ማተሚያ ድረስ ያለውን የሕትመት መሣሪያዎች እድገት በአጭሩ የሚያስቃኘው መግለጫ ይገኝበታል። ከዚህም ባሻገር ቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢውን ለመንከባከብ ምን ያህል ጥረት እንደሚያደርግ የሚያሳይ መግለጫ ለእይታ ቀርቦ ነበር። ለምሳሌ፣ በማተሚያ ማሽኖች ላይ ከሚገኙት ማድረቂያዎች የሚወጡትን መርዛማ ጋዞችና ሽታዎች የሚያስወግድ እንዲሁም የወረቀት ብናኞችን የሚሰበስብ መሣሪያን የሚያሳይ መግለጫ ቀርቧል።

በአካባቢው የሚታተም አንድ ጋዜጣ ጉብኝቱን አስመልክቶ የጻፈውን አምድ የጀመረው፣ በቅርንጫፍ ቢሮው የሚኖሩት 700 ፈቃደኛ ሠራተኞች “ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮች” እንደሆኑ በመግለጽ ነበር። በተጨማሪም ማተሚያ ክፍሉ “እጅግ ንጹሕ እንደሆነና ሁሉም ነገር በተመደበለት ሰዓት መሠረት እንደሚከናወን” አትቷል። ቅርንጫፍ ቢሮውን ከጎበኙት መካከል የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወም የነበረ አንድ ሰው ይገኝበታል። ይህ ሰው ከግብኝቱ በኋላ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “እንኳን ደስ አላችሁ። በሁሉም ነገር የተሳካለት፣ እንዲህ ያለ ድርጅት ማየት የተለመደ ነገር አይደለም” ብሏል።

ብዙ ሰዎች ቅርንጫፍ ቢሮውን በመጎብኘታቸው የተሰማቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በ151 ቋንቋዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑና ማተሚያ ክፍሉ በደቡባዊና በመካከለኛው አፍሪካ ለሚገኙ 18 አገሮች ጽሑፎችን የሚያትም መሆኑ በርካታ ጎብኚዎችን አስደንቋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ሌሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎችም በሥራ ሰዓት ለጉብኝት ክፍት ናቸው። በአካባቢህ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ መቼ መጎብኘት እንደምትችል ለምን አትጠይቅም?

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጋበዣ ወረቀት

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጎብኚዎች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ሲገቡ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሞካሌ ከተማ የሚገኘው የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማን ሮላንድ ሊትማን ማተሚያ ማሽን

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ መጠረዣ ክፍል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጽሑፍ መላኪያ ክፍል